ስሜታችንን ለመቆጣጠር የሚረዱ ነገሮች
ስሜታችንን ለመቆጣጠር የሚረዱ ነገሮች
አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ስሜት አስተሳሰብህን ይቆጣጠረዋል? በቀላሉ የምትናደድበት፣ የምትቆጣበት ወይም የምትበሳጭበት ጊዜ አለ? የኑሮ ጭንቀት ሕይወትህን ይቆጣጠረዋል? እንግዲያውስ ምን ሊረዳህ ይችላል?
እንዲህ ያሉ ስሜቶች ልናስወግዳቸው የማንችላቸው የሕይወት ክፍል ናቸው። በአግባቡ ከተያዙ ሕይወትን ይበልጥ አስደሳች ያደርጉልናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 7:7) ዓመጽና አደጋ በሞላበት ዓለም ውስጥ እየኖረ በአካባቢው የሚፈጸመው ነገር ስሜቱን የማይረብሸው ማን አለ? ይሁን እንጂ ቅዱስ ጽሑፉ “ለሰው . . . በሥራው ከመደሰት የተሻለ ነገር እንደሌለው አየሁ” በማለትም ይናገራል። (መክብብ 3:22) ስለዚህ ሕይወታችንን ይበልጥ በደስታ የተሞላ ለማድረግ ገንቢ የሆኑ ስሜቶችን በመኮትኮት መደሰት መቻል ይኖርብናል። ጠቃሚ የሆኑ ስሜቶችን ማዳበር፣ መጥፎ የሆኑትን ደግሞ መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?
ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ ስሜቶች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ይረዳል። ለምሳሌ ያህል፣ ከአቅማችን በላይ የሆነ ችግር ገጥሞን በምንጨነቅበት ወቅት አእምሯችን እዚያ ላይ እንዲያተኩር ከመፍቀድ ይልቅ የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ወይም አካባቢያችንን መለወጥ አይሻልም? በእግር መንሸራሸር፣ ለስላሳ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም ለተቸገረ ሰው መልካም ነገር መሥራት የተወሰነ እረፍት ከመስጠቱም በተጨማሪ ደስታ ያስገኝልናል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
አፍራሽ የሆነ አስተሳሰብን ማስወገድ የሚቻልበት ዋናው መንገድ በፈጣሪ ላይ እምነት መጣል ነው። አፍራሽ የሆነው አስተሳሰብ ካስቸገረን ‘የሚያስጨንቀንን ሁሉ’ ለአምላክ በጸሎት መንገር ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ . . የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጣል። (መዝሙር 34:18, 19) አምላክ ‘ረዳትና አዳኝ’ እንደሚሆነን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? (መዝሙር 40:17) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና አምላክ ለአገልጋዮቹ ደህንነት እንደሚያስብ በሚያሳዩ እውነተኛ ምሳሌዎች ላይ በማሰላሰል እምነታችንን ማሳደግ እንችላለን።