በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ አምልኮ እየጎረፉ ነው
“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው”
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ አምልኮ እየጎረፉ ነው
ስለ ዘመናችን የተነገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ላቅ ወዳለው የይሖዋ አምልኮ እንደሚተምሙ ይገልጻሉ። ለምሳሌ፣ ይሖዋ አምላክ በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት የሚከተለውን ተንብዮአል:- “ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” (ሐጌ 2:7) “በዘመኑ ፍጻሜ” ማለትም አሁን ባለንበት ወቅት ብሔራትና ሕዝቦች ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ አምልኮ እንደሚያቀርቡ ኢሳይያስም ሆነ ሚክያስ ተንብየው ነበር።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ ሚክያስ 4:1-4
እነዚህ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ይሆን? እስቲ የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ230 ከሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች የተውጣጡ ከ3,110,000 በላይ የሚሆኑ አዳዲሶች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ 10 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ስድስቱ የተጠመቁት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ነው። በ2004 በአማካይ በየሁለት ደቂቃው አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ወስኖ በመጠመቅ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆኗል! a
በአንደኛው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ‘ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች አምነው ወደ ጌታ እየተመለሱ ነው።’ እርግጥ፣ በቁጥር መጨመር ብቻ የይሖዋን በረከት የሚያሳይ ማስረጃ ባይሆንም ‘የይሖዋ እጅ’ ከሕዝቡ ጋር እንደሆነ ያረጋግጣል። (የሐዋርያት ሥራ 11:21) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ አምልኮ እንዲመጡ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ይህ እድገት በግለሰብ ደረጃ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው?
ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ወደ ይሖዋ ይሳባሉ
ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44) “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ የሚስባቸው ይሖዋ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) የአምላክ መንፈስ ሰዎች ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። (ማቴዎስ 5:3) አንዳንዶች ሕሊናቸውን የሚረብሽ ነገር ሲያጋጥማቸው፣ ተስፋ ማጣት ሲያስጨንቃቸው፣ ወይም ካጋጠማቸው ችግር መውጫ ቀዳዳው ሲጠፋባቸው ወደ አምላክ ዘወር በማለት እርሱ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ለመማር ይነሳሳሉ።—ማርቆስ 7:26-30፤ ሉቃስ 19:2-10
በርካታ ሰዎች ግራ ለሚያጋቧቸው ጥያቄዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሚቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራም አማካኝነት መልስ በማግኘታቸው ወደ ይሖዋ አምልኮ ሊሳቡ ችለዋል።
በጣሊያን የሚኖር ዳቪዴ የተባለ ዕፅ አዘዋዋሪ “አምላክ ካለ፣ የሰው ልጆች ግፍ የሚፈጸምባቸው ለምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ ያሳስበው ነበር። ለሃይማኖታዊ ነገሮች እምብዛም ፍላጎት አልነበረውም፤ ስለዚህ ይህን ጥያቄ ከሌሎች ጋር ለመከራከር ይጠቀምበት ነበር። “ለጥያቄዬ ትክክለኛና አሳማኝ መልስ አገኛለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር” ሲል ተናግሯል። “ሆኖም ያናገረኝ የይሖዋ ምሥክር በጣም ትዕግሥተኛ ከመሆኑም በላይ ለሚናገረው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ያሳየኝ ነበር። ውይይቱ በእኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።” ዛሬ ዳቪዴ ሕይወቱን አስተካክሎ ይሖዋን እያገለገለ ነው።
ሌሎች ደግሞ ከይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ጋር ሊተባበሩ የቻሉት ሕይወታቸው ዓላማ ያለው እንዲሆን ይፈልጉ ስለነበረ ነው። በዛግሬብ፣ ክሮኤሽያ የምትኖር አንዲት የሥነ አእምሮ ሐኪም ለራሷ ስሜታዊ ችግሮች ሕክምና ለማግኘት ወደ አንድ ታዋቂ የሥራ ባልደረባዋ ሄደች። በጣም የሚገርመው ዶክተሩ በዛግሬብ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስልክ ቁጥርና የአንድ የሚያውቀውን የይሖዋ ምሥክር ስም ሰጣት። ከዚያም እንዲህ አላት:- “እነዚህ ሰዎች ሊረዱሽ የሚችሉ ይመስለኛል። ወደ ቤተ ክርስቲያን ብልክሽ በዚያ የምታገኚው በድን የሆነ ምስል ብቻ ነው፣ የሚያናግርሽም ሰው አይኖርም፣ ሁሉም ነገር [በመንፈሳዊ] ጨለማ የተዋጠ ነው። ቤተ ክርስቲያን መሄድሽ የሚረዳሽ መስሎ አይታየኝም። ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ልኬያለሁ፤ አንቺም ቢሆን ወደ እነርሱ መሄድሽ ጥሩ ይመስለኛል።” ከዚያም ፈቃደኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ወዲያውኑ ሄደው ያነጋገሯት ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩላት። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይህች የሥነ አእምሮ ሐኪም የአምላክን ዓላማ ማወቋ ሕይወቷ ትርጉም እንዲኖረው እንደረዳት በደስታ ገልጻለች።—ብዙዎች አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እውነተኛ ማጽናኛ ሊሰጣቸው የቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ እንደሆነ ተገንዝበዋል። በግሪክ አገር አንድ የሰባት ዓመት ልጅ ትምህርት ቤት ውስጥ ከጣሪያ ላይ ወድቆ ሞተ። ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች እናቱን አገኟትና የትንሣኤን ተስፋ በመንገር ለማጽናናት ሞከሩ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ወዲያውኑ ሴትየዋ ማልቀስ ጀመረች። እህቶችም “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልጊ ከሆነ መቼ እንምጣ?” ብለው ጠየቋት። እሷም “አሁኑኑ” ብላ መለሰችላቸው። ሴትየዋ ወደ ቤቷ ከወሰደቻቸው በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። ዛሬ ቤተሰቦቿ በሙሉ ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አንተስ የበኩልህን ድርሻ እያበረከትክ ነው?
እነዚህ ተሞክሮዎች በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ያለውን ሥራ የሚጠቁሙ ናቸው። ይሖዋ ከየብሔራቱ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎችን ወደ እውነተኛው አምልኮ እየሰበሰበና እያስተማረ ነው። ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡት የዚህ ቡድን አባላት በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ በቅርቡ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈው ጽድቅ ወደሚሰፍንበት አዲስ ዓለም በሕይወት የመዝለቅ አስደሳች ተስፋ አላቸው።—2 ጴጥሮስ 3:13
ይሖዋ ሥራውን ስለባረከው ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ በተሳካ ሁኔታ ወደሚያበቃበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። (ኢሳይያስ 55:10, 11፤ ማቴዎስ 24:3, 14) በዚህ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በቅንዓት እየተካፈልክ ነው? ከሆነ መለኮታዊ ድጋፍ እንደምታገኝ እርግጠኛ ሆነህ “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” በማለት የመዝሙራዊውን አባባል ማስተጋባት ትችላለህ።—መዝሙር 121:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ መስከረም/ጥቅምት የሚለውን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም።”—ዮሐንስ 6:44
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከዚህ እድገት በስተጀርባ ያለው ማነው?
“እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ።”—መዝሙር 127:1
“ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም።” —1 ቆሮንቶስ 3:6, 7