በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ!

በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ!

በእምነት እንጂ በማየት አትመላለሱ!

“በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም።”—2 ቆሮንቶስ 5:6, 7 የ1954 ትርጉም

1. ሐዋርያው ጳውሎስ በእምነት እንጂ በማየት እንዳልተመላለሰ የሚጠቁመው ምንድን ነው?

 ወቅቱ 55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ ሳውል በመባል የሚታወቅ አንድ ሰው ክርስትናን ከተቀበለ ወደ 20 ዓመታት ገደማ አልፈዋል። በዚህ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ይህ ሰው የዓመታት ማለፍ በአምላክ ላይ ያለውን እምነት አልቀነሰበትም ወይም አላዳከመበትም። በሰማይ ያሉትን ነገሮች በሰብዓዊ ዓይኑ መመልከት ባይችልም እንኳ እምነቱ ጠንካራ ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ላላቸው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 5:6, 7 የ1954 ትርጉም

2, 3. (ሀ) በእምነት እንደምንመላለስ የምናሳየው እንዴት ነው? (ለ) በማየት መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው?

2 በእምነት መመላለስ አምላክ ሕይወታችንን ሊመራልን እንደሚችል ሙሉ በሙሉ ማመንን ይጠይቃል። ይሖዋ ለእኛ ከሁሉ ይበልጥ የሚጠቅመንን እንደሚያውቅ ፍጹም እምነት ሊኖረን ይገባል። (መዝሙር 119:66) በሕይወታችን ውስጥ ውሳኔዎች ስናደርግና በተግባር ስናውላቸው ‘የማናየውንም ነገር’ ግምት ውስጥ እናስገባለን። (ዕብራውያን 11:1) ይህም ቃል የተገባልንን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ይጨምራል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በሌላ በኩል ግን በማየት መመላለስ ሲባል ሕይወታችንን የምንመራው በምናያቸውና በምንሰማቸው ነገሮች ላይ ብቻ ተመሥርተን ይሆናል ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ የአምላክን ፈቃድ ጨርሶ ችላ እንድንል ሊያደርገን ስለሚችል አደገኛ ነው።—መዝሙር 81:12፤ መክብብ 11:9

3 ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ‘የታናሹ መንጋ’ አባላትም ሆንን በምድር ላይ የሚኖሩት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል፣ ሁላችንም በእምነት እንጂ በማየት እንዳንመላለስ የተሰጠውን ምክር ልብ ልንለው ይገባል። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐንስ 10:16) በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠውን ይህንን ምክር መከተላችን ‘ለጥቂት ጊዜ በኃጢአት በሚገኝ ደስታና’ በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ተሸንፈን እንዳንወድቅ እንዲሁም የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ቅርብ መሆኑን እንዳንዘነጋ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ከዚህም በተጨማሪ በማየት መመላለስ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች እንመለከታለን።—ዕብራውያን 11:25

“ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ” መራቅ

4. ሙሴ ምን ምርጫ አደረገ? ለምንስ?

4 የእንበረም ልጅ የነበረው ሙሴ ምን ዓይነት ሕይወት ሊኖረው ይችል እንደነበረ አስብ። በጥንቷ ግብፅ በንጉሡ ልጆች መካከል ያደገው ሙሴ በቀላሉ ሥልጣን፣ ብልጽግናና ተደማጭነት የማግኘት አጋጣሚ ነበረው። ሙሴ እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር:- ‘ታዋቂ የሆነውን የግብፃውያንን ጥበብ የተማርኩ ከመሆኑም በላይ በንግግሬም ሆነ በተግባሬ ብርቱ ሰው ነኝ። ከንጉሣዊው ቤተሰብ ጋር ያለኝን ዝምድና ካጠበቅሁ በሥልጣኔ ተጠቅሜ በጭቆና ቀንበር ሥር ያሉትን ዕብራውያን ወንድሞቼን መርዳት እችላለሁ።’ (የሐዋርያት ሥራ 7:22) ሆኖም ሙሴ ከዚህ በተቃራኒ “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ።” እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? ሙሴ በግብፅ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ነገር ሁሉ እርግፍ አድርጎ እንዲተው ያነሳሳው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ “የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብፅን ለቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በሐሳቡ ጸና” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ዕብራውያን 11:24-27) ሙሴ ይሖዋ የጽድቅ አቋማቸውን ለሚጠብቁ ሰዎች በሚሰጠው የተረጋገጠ ሽልማት ላይ እምነት ማሳደሩ ከኃጢአትና ኃጢአት ከሚያስገኘው ጊዜያዊ ደስታ እንዲርቅ ረድቶታል።

5. የሙሴ ምሳሌ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

5 እኛም ብንሆን ብዙውን ጊዜ እንደሚከተሉት ባሉ ከባድ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለማድረግ እንገደዳለን:- ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የማይስማሙ አንዳንድ ድርጊቶቼንና ልማዶቼን መተው ይኖርብኝ ይሆን? ቁሳዊ ጥቅም የሚያስገኝልኝ ቢመስልም ለመንፈሳዊ እድገቴ እንቅፋት ሊሆን የሚችል ሥራ ብጀምር ያወጣል?’ የሙሴ ምሳሌ፣ ይህ ዓለም የሚያንጸባርቀውን የቅርቡን ብቻ የመመልከት ዝንባሌ እንደምንከተል የሚያሳይ ውሳኔ ከማድረግ እንድንቆጠብ ያበረታታናል። ከዚህ በተቃራኒ “የማይታየው” ይሖዋ አምላክ ባለው ጥልቅ ጥበብ ላይ እምነት እናሳድር። እኛም እንደ ሙሴ ይህ ዓለም ሊያቀርብልን ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይልቅ የይሖዋን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንመልከት።

6, 7. (ሀ) ዔሳው በማየት ለመመላለስ እንደመረጠ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ከዔሳው ታሪክ ምን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እናገኛለን?

6 ሙሴን የእምነት አባት ከነበረው ከይስሐቅ ልጅ ከዔሳው ጋር እስቲ አወዳድረው። ዔሳው ቅጽበታዊ እርካታ ማግኘትን መርጦ ነበር። (ዘፍጥረት 25:30-34) ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት የጎደለው ዔሳው “ለአንድ ጊዜ መብል ሲል” የብኩርና መብቱን አሳልፎ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 12:16) ብኩርናውን ለመሸጥ ያደረገው ውሳኔ ከይሖዋ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደሚነካ ወይም በዘሮቹ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አላሰበም። ዔሳው መንፈሳዊ አመለካከት አልነበረውም። ውድ የሆኑትን የአምላክ ተስፋዎች አቅልሎ ተመለከታቸው። ዔሳው በእምነት ሳይሆን በማየት ተመላልሷል።

7 ዔሳው በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ክርስቲያኖች የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ቀላልም ሆነ ከባድ ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የምንፈልገውን ነገር አሁኑኑ ማግኘት እንዳለብን የሚገልጸው የሰይጣን ዓለም ፕሮፖጋንዳ እንዳያታልለን መጠንቀቅ አለብን። እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘የማደርጋቸው ውሳኔዎች የዔሳው ዓይነት ዝንባሌ እንዳለኝ ያሳያሉ? አሁን የምፈልገውን ነገር ለማግኘት ጥረት ማድረጌ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ሁለተኛውን ቦታ እንድሰጥ ያስገድደኛል? የማደርጋቸው ምርጫዎች ከአምላክ ጋር ያለኝን ወዳጅነትና ወደፊት የማገኘውን ሽልማት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው? ለሌሎች ምን ዓይነት አርዓያ እየሆንኩ ነው?’ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት እንዳለን የሚያሳዩ ከሆኑ ይሖዋ ይባርከናል።—ምሳሌ 10:22

ከፍቅረ ንዋይ ወጥመድ መሸሽ

8. የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር? ይህስ የእኛን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሿ እስያ በምትገኘው በሎዶቅያ ላለው ጉባኤ መልእክት አስተላልፎ ነበር። መልእክቱ ፍቅረ ንዋይን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። የሎዶቅያ ክርስቲያኖች በቁሳዊ ሁኔታ ሀብታሞች ቢሆኑም በመንፈሳዊ ግን ድሆች ነበሩ። በእምነት መመላለሳቸውን ከመቀጠል ይልቅ ቁሳዊ ንብረት መንፈሳዊ እይታቸውን እንዲጋርድባቸው ፈቅደዋል። (ራእይ 3:14-18) ፍቅረ ንዋይ ዛሬም ተመሳሳይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እምነታችንን የሚያዳክም ከመሆኑም በላይ የሕይወትን ‘ሩጫ በጽናት መሮጣችንን’ እንድናቆም ያደርገናል። (ዕብራውያን 12:1) ጠንቃቆች ካልሆንን ‘የምድራዊ ሕይወት ተድላ’ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን በማዳፈን ‘አንቆ’ ሊያስቀራቸው ይችላል።—ሉቃስ 8:14

9. በምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ የምንደሰትና የምንረካ መሆናችን ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

9 መንፈሳዊ ጥበቃ ለማግኘት ቁልፉ፣ በዚህ ዓለም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀምና ራሳችንን በቁሳዊ ነገሮች ለማበልጸግ ከመጣር ይልቅ ባለን የመርካትን ዝንባሌ ማዳበር ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:31፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) በማየት ሳይሆን በእምነት የምንመላለስ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ባለው መንፈሳዊ ገነት እንደሰታለን። ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ስንመገብ “ከልብ በመነጨ ደስታ” ለመዘመር አንገፋፋም? (ኢሳይያስ 65:13, 14) ከዚህም በላይ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ከሚያፈሩ ሰዎች ጋር ባለን ወዳጅነት እንደሰታለን። (ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ በመንፈሳዊ መንገድ በሚያቀርብልን ነገሮች መርካታችንና መንፈሳችን መታደሱ በጣም አስፈላጊ ነው!

10. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ጥሩ ነው?

10 ራሳችንን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቃችን ይጠቅመናል:- ‘በሕይወቴ ውስጥ ለቁሳዊ ነገሮች ምን ያህል ቦታ እሰጣለሁ? ያለኝን ቁሳዊ ንብረት የምጠቀምበት የተንደላቀቀ ሕይወት ለመምራት ነው ወይስ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት? ከፍተኛ እርካታ የሚያስገኝልኝ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው ወይስ ቅዳሜና እሁድን ከክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች ርቆ ማሳለፍ? ብዙውን ጊዜ ቅዳሜና እሁድን ለመስክ አገልግሎትና ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ከማዋል ይልቅ ለመዝናናት ፕሮግራም አወጣለሁ?’ በእምነት መመላለስ ሲባል በይሖዋ ተስፋዎች ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ ሥራዎች ራሳችንን ማስጠመድ ማለት ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:58

መጨረሻውን አቅርቦ መመልከት

11. በእምነት መመላለስ መጨረሻውን አቅርበን እንድንመለከት የሚረዳን እንዴት ነው?

11 በእምነት መመላለስ መጨረሻው ሩቅ ነው ወይም ጨርሶ አይመጣም የሚለውን ሥጋዊ አመለካከት እንድናስወግድ ይረዳናል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች አቅልለው ከሚመለከቱ ዘባቾች በተቃራኒ እኛ፣ የአምላክ ቃል በዘመናችን እንደሚሆን የተናገረው ትንቢት በዓለም ላይ እየተከናወኑ ባሉት ነገሮች እንዴት እየተፈጸመ እንዳለ እናስተውላለን። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ለአብነት ያህል፣ የሰዎችን አመለካከትና ባሕርይ ጠቅለል አድርገን ስንመለከት የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ለመሆኑ ማስረጃ አይሆነንም? (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ዛሬ በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ነገሮች ስንቃኝ ታሪክ ራሱን እየደገመ እንዳለ አድርገን ከማሰብ ይልቅ የክርስቶስ ‘መምጣትና የዓለም መጨረሻ ምልክት’ እየታየ መሆኑን በእምነት ዓይናችን እናስተውላለን።—ማቴዎስ 24:1-14

12. በሉቃስ 21:20, 21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

12 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተፈጸመና ከዘመናችን ጋር የሚመሳሰል አንድ ክስተት እንመልከት። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ እያለ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር:- “ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ፣ ጥፋቷ መቃረቡን ዕወቁ። በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማ ያሉትም ከዚያ ይውጡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮም ሠራዊት በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን ሲከብባት ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። ሆኖም የሮም ሠራዊት በድንገት ከተማዋን ለቅቆ ሲሄድ ክርስቲያኖች እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የጠቆማቸው ከመሆኑም በላይ ‘ወደ ተራሮች መሸሽ’ የሚችሉበት አጋጣሚ ከፈተላቸው። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮማውያን ሠራዊት እንደገና ተመልሶ በመምጣት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ከመሰንዘርም አልፎ ቤተ መቅደሷን ደመሰሰው። ጆሴፈስ በዚያ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያን እንደተገደሉና 97,000 የሚያህሉ ደግሞ በግዞት እንደተወሰዱ ዘግቧል። በዚያን ወቅት የነበረው የአይሁድ ሥርዓት መለኮታዊ ፍርድ ተፈጽሞበታል። በእምነት የተመላለሱትና የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ የሰሙት ግን ከጥፋቱ ተርፈዋል።

13, 14. (ሀ) ወደፊት ምን ሁኔታዎች ይፈጸማሉ? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ በንቃት መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?

13 በዘመናችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር በቅርቡ ይፈጸማል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች መለኮታዊው ፍርድ ሲፈጸም የሚያበረክቱት ድርሻ ይኖራል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የሮም ሠራዊት፣ በሮም ውስጥ ሰላም የማስፈን (የፓክስ ሮማና) ተልእኮ እንደነበረው ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሰላም ለማስጠበቅ ታስቦ የተዘጋጀ አካል ነው። የሮም ወታደሮች በወቅቱ በነበረው ዓለም ላይ አንጻራዊ ደኅንነት እንዲኖር ጥረት ቢያደርጉም ኢየሩሳሌምን ባድማ ያደረጓት እነርሱ ነበሩ። ዛሬም በተመሳሳይ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ኃይሎች ሃይማኖትን እንደ ችግር ቆስቋሽ አካል አድርገው በመቁጠር ዘመናዊቷን ኢየሩሳሌም ማለትም ሕዝበ ክርስትናን እንዲሁም ቀሪውን የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ለማውደም እርምጃ እንደሚወስዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይገልጻል። (ራእይ 17:12-17) አዎን፣ ዓለም አቀፉ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በጥፋት አፋፍ ላይ ነው።

14 የሐሰት ሃይማኖት መጥፋት የታላቁን መከራ መጀመር ይጠቁማል። ታላቁ መከራ ሊደመደም ሲል የዚህ ክፉ ሥርዓት ቀሪ ክፍሎች ድምጥማጣቸው ይጠፋል። (ማቴዎስ 24:29, 30፤ ራእይ 16:14, 16) በእምነት መመላለሳችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ በንቃት እንድንከታተል ይረዳናል። አምላክ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ለማስፈን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንም ሆነ ማንኛውንም ሰብዓዊ አካል ይጠቀማል በሚለው አመለካከት አንታለልም። እንግዲያው አኗኗራችን “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው” ብለን እንደምናምን የሚያሳይ መሆን አይኖርበትም?—ሶፎንያስ 1:14

በማየት መመላለስ ምን አደጋ አለው?

15. የእስራኤል ብሔር የአምላክን በረከት ቢያይም በምን ዓይነት ወጥመድ ወድቋል?

15 የጥንቶቹ እስራኤላውያን ታሪክ፣ በማየት መመላለስ እምነታችንን እንዲያዳክመው መፍቀድ ምን አደጋ እንደሚያስከትል ያሳያል። እስራኤላውያን የግብፅን የሐሰት አማልክት ያዋረዷቸውን አሥር መቅሰፍቶች ከመመልከታቸውም በላይ ድንቅ በሆነ መንገድ ቀይ ባሕርን ቢሻገሩም የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ የወርቅ ጥጃ ሠርተው አመለኩ። “ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ [በመቆየቱ]” መጠበቅ ሰለቻቸው። (ዘፀአት 32:1-4) ትዕግሥት ማጣታቸው በሰብዓዊ ዓይናቸው ሊያዩ የሚችሉትን ጣዖት ወደማምለክ መርቷቸዋል። በማየት መመላለሳቸው ይሖዋን ስላስቆጣው “ሦስት ሺህ ያህል” ሰዎች ተገደሉ። (ዘፀአት 32:25-29) በዛሬው ጊዜም አንድ የአምላክ አገልጋይ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳጣና አምላክ ቃሉን ለመፈጸም ባለው ችሎታ ላይ ጥርጣሬ እንዳደረበት የሚያሳይ ውሳኔ ቢያደርግ እንዴት አሳዛኝ ይሆናል!

16. እስራኤላውያን የሚያዩት ነገር ተጽዕኖ ያሳደረባቸው እንዴት ነበር?

16 እስራኤላውያን የሚያዩትን ነገር መከተላቸው በሌሎች መንገዶችም መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። በማየት መመላለሳቸው ጠላቶቻቸውን በመፍራት እንዲርበደበዱ አደረጋቸው። (ዘኍልቍ 13:28, 32፤ ዘዳግም 1:28) ከዚህም በላይ መለኮታዊ ምንጭ ያለውን የሙሴን ሥልጣን ወደ መገዳደርና ኑሯቸውን ወደ ማማረር መርቷቸዋል። እምነት የለሽ መሆናቸው ተስፋይቱን ምድር ከመውረስ ይልቅ አጋንንት በሚቆጣጠሯት በግብፅ የነበራቸውን ሕይወት እንዲመርጡ አድርጓቸዋል። (ዘኍልቍ 14:1-4፤ መዝሙር 106:24) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ለማይታየው ንጉሣቸው ምን ያህል አክብሮት እንደጎደላቸው ሲመለከት እንዴት አዝኖ ይሆን!

17. በሳሙኤል ዘመን እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያ ችላ እንዲሉ ያደረጋቸው ምን ነበር?

17 የይሖዋ ምርጥ ሕዝብ የነበረው የእስራኤል ብሔር በነቢዩ ሳሙኤል ዘመንም በማየት መመላለስ በሚያመጣው ወጥመድ እንደገና ወድቋል። እስራኤላውያን የሚያዩት ንጉሥ እንደሚፈልጉ ገለጹ። ይሖዋ ንጉሣቸው እንደሆነ በተጨባጭ ያሳያቸው ቢሆንም በዚህ ረክተው በእምነት መመላለስ አልቻሉም። (1 ሳሙኤል 8:4-9) ያደረጉት ምርጫ ራሳቸውን የሚጎዳ ቢሆንም እንኳ እንከን የለሽ የሆነውን የይሖዋን መመሪያ ትተው በዙሪያቸው እንደነበሩት ብሔራት ለመሆን ወሰኑ።—1 ሳሙኤል 8:19, 20

18. በማየት መመላለስ ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

18 በዚህ ዘመን የምንገኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከእርሱ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ቀደም ባሉት ዘመናት ከተፈጸሙት ክንውኖች ትምህርት ለመቅሰምና የተማርነውንም ተግባራዊ ለማድረግ እንፈልጋለን። (ሮሜ 15:4) እስራኤላውያን በማየት በተመላለሱበት ወቅት አምላክ በሙሴ አማካኝነት እየመራቸው እንዳለ ዘንግተው ነበር። እኛም ካልተጠነቀቅን ይሖዋ አምላክና ታላቁ ሙሴ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤን እየመሩ እንዳሉ ልንዘነጋ እንችላለን። (ራእይ 1:12-16) የይሖዋን ድርጅት ምድራዊ ክፍል በሰብዓዊ አመለካከት የማየት አዝማሚያ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ አለብን። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካዳበርን አጉረምራሚዎች ልንሆንና ይሖዋ ለወከላቸው ሰዎችም ሆነ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት ልናጣ እንችላለን።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም

በእምነት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

19, 20. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ለምንስ?

19 መጽሐፍ ቅዱስ “ተጋድሎአችን ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር ነው” ይላል። (ኤፌሶን 6:12) ዋነኛው ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን ዓላማውም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጥፋት ነው። አምላክን ለማገልገል ካደረግነው ውሳኔ ወደኋላ እንድንል ለማድረግ ማንኛውንም ማታለያ ይጠቀማል። (1 ጴጥሮስ 5:8) በሰይጣን ሥርዓት ውጫዊ ገጽታ ከመታለል ምን ሊጠብቀን ይችላል? በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ ጥበቃ ይሆንልናል! ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነትና ትምክህት ማሳደራችን “ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ እምነታችን [እንዳይጠፋ]” ይረዳናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) እንግዲያው በይሖዋ በረከቶች ሙሉ በሙሉ በመተማመን በእምነት መመላለሳችንን እንቀጥል። እንዲሁም በቅርቡ ከሚመጣው ሁሉ ለማምለጥ እንድንችል መጸለያችንን አናቋርጥ።—ሉቃስ 21:36

20 በማየት ሳይሆን በእምነት በመመላለስ ረገድ ፈለጉን ልንከተለው የሚገባ የላቀ ምሳሌ አለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:21) የሚቀጥለው ርዕስ እንደ ክርስቶስ መመላለስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

ታስታውሳለህ?

• በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስን በተመለከተ ከሙሴና ከዔሳው ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ፍቅረ ንዋይን ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

• በእምነት መመላለስ መጨረሻው ሩቅ እንደሆነ አድርጎ የማሰብን ዝንባሌ እንድናስወግድ የሚረዳን እንዴት ነው?

• በማየት መመላለስ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴ በእምነት ተመላልሷል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ መዝናኛ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳትካፈል እንቅፋት ይሆንብሃል?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ ቃል ትኩረት መስጠትህ ጥበቃ የሚሆንልህ እንዴት ነው?