በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

እንድርያስ የተባለ አንድ ወጣት አይሁዳዊ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲናገር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማ ምን ያህል እንደተደሰተ መገመት ትችላለህ! መጽሐፍ ቅዱስ እንድርያስ በፍጥነት ወደ ወንድሙ ሄዶ “መሲሑን [ወይም ክርስቶስን] አገኘነው” ብሎ ነገረው። (ዮሐንስ 1:41) በዕብራይስጡና በግሪክኛው ቋንቋ ብዙውን ጊዜ “መሲሕ” እና “ክርስቶስ” ተብለው የሚተረጎሙት ቃላት “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው። ኢየሱስ የተቀባ ወይም በአምላክ የተመረጠ ይኸውም ተስፋ የተሰጠበት መሪ ነበር። (ኢሳይያስ 55:4) መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑን በማስመልከት የተነገሩ ትንቢቶችን በመያዙ በዚያን ጊዜ የነበሩ አይሁዳውያን በጉጉት ይጠባበቁት ነበር።—ሉቃስ 3:15

ኢየሱስ በእርግጥ በአምላክ መመረጡን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ 30 ዓመት በሆነው ጊዜ ማለትም በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ምን እንደተከሰተ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ለመጠመቅ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሄደ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፣ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።” (ማቴዎስ 3:16, 17) ዮሐንስ እነዚህን የማረጋገጫ ቃላት ከሰማ በኋላ ኢየሱስ በአምላክ የተመረጠ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አድሮበት ይሆን? ይሖዋ አምላክ መንፈሱን በኢየሱስ ላይ በማፍሰስ ወደፊት የሚቋቋመው መንግሥቱ ንጉሥ በማድረግ ቀብቶታል ወይም ሾሞታል። ስለዚህ ኢየሱስ፣ የተቀባ ማለትም ክርስቶስ ሆኗል። ታዲያ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? የመጣውስ ከየት ነው?

“አመጣጡ ከጥንት” ነበር

የኢየሱስ ሕይወት በሦስት ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው ክፍል የጀመረው ምድር ላይ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ነው። ሚክያስ 5:2 መሲሑ “አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን የሆነ” ነው በማለት ይናገራል። ኢየሱስ ራሱም “እኔ ከላይ ነኝ” በማለት ከሰማይ እንደመጣ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:23) ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር ነበር።

ፍጡራን ሁሉ ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት አምላክ ብቻውን የኖረበት ዘመን ነበር። አምላክ መፍጠር የጀመረው ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት ነው። የመጀመሪያ ፍጥረቱ ማን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል ኢየሱስን “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” በማለት ይገልጸዋል። (ራእይ 3:14 የ1954 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ . . . ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” በማለት ይናገራል። (ቈላስይስ 1:15, 16) አዎን፣ አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ብቸኛ ፍጡር ኢየሱስ ነው። የአምላክ ‘አንድያ ልጅ’ የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው። (ዮሐንስ 3:16) የአምላክ የበኩር ልጅ “ቃል” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። (ዮሐንስ 1:14) ለምን? ምድር ላይ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በሰማይ የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግል ስለነበረ ነው።

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን” ሲፈጥር “ቃል” ከይሖዋ አምላክ ጋር ነበር። አምላክ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ” ያለው ለኢየሱስ ነበር። (ዮሐንስ 1:1፤ ዘፍጥረት 1:1, 26) የይሖዋ የበኩር ልጅ ከአባቱ ጎን በመሆን በትጋት ይሠራ ነበር። በምሳሌ 8:22-31 ላይ “ከጐኑ [ከፈጣሪ] ዋና ባለሙያ ነበርሁ። ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት እያደረግሁ፣ ዕለት ተዕለት በደስታ እሞላ ነበር” በማለት እንደተናገረ ተደርጎ ተገልጿል።

ይሖዋ አምላክና አንድያ ልጁ አብረው ጎን ለጎን በመሥራታቸው እርስ በርሳቸው ምን ያህል የጠበቀ ትውውቅ ሊኖራቸው እንደሚችል ግልጽ ነው! ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖሩ በአምላክ ልጅ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ መገመት አያዳግትም። ይህ ታዛዥ ልጅ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ሊሆን ችሏል። በእርግጥም በቈላስይስ 1:15 መሠረት ኢየሱስ “የማይታየው አምላክ አምሳል ነው” መባሉ የተገባ ነው። ስለ ኢየሱስ የምናገኘው እውቀት መንፈሳዊ ፍላጎታችንንም ሆነ አምላክን ለማወቅ ያለንን የተፈጥሮ ዝንባሌ ለማሟላት አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ኢየሱስ ምድር ሳለ ያደረገው ነገር በሙሉ ይሖዋ ይጠብቅበት የነበረውን ነው። ስለዚህ ኢየሱስን ማወቅ ስለ ይሖዋ ያለንን እውቀት ማሳደግ ማለት ነው። (ዮሐንስ 8:28፤ 14:8-10) ታዲያ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው እንዴት ነው?

ሰው ሆኖ ምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት

የኢየሱስ ሕልውና ሁለተኛ ክፍል የጀመረው አምላክ ልጁን ወደ ምድር በላከው ጊዜ ነው። ይሖዋ ኢየሱስ በሰማይ የነበረውን ሕይወት ማርያም ወደተባለች ታማኝ አይሁዳዊት ድንግል ማሕፀን በማዛወር ተአምር ሠርቷል። ኢየሱስ ሰብዓዊ አባት ስላልነበረው ምንም ዓይነት የፍጽምና ጉድለት አልወረሰም። ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም ኃይል በማርያም ላይ ‘በመጸለል’ በተአምራዊ ሁኔታ እንድታረግዝ አድርጓታል። (ሉቃስ 1:34, 35) በዚህ ምክንያት ማርያም ፍጹም የሆነ ልጅ መውለድ ችላለች። ኢየሱስ የአናጢው የዮሴፍ የማደጎ ልጅ ሆኖ በኑሮው ዝቅተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ አደገ፤ የዚህ ቤተሰብ ልጆች በርካታ ሲሆኑ እርሱ የበኩር ልጅ ነበር።—ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:22, 23፤ ማርቆስ 6:3

ስለ ኢየሱስ የልጅነት ጊዜ የሚታወቀው ነገር ጥቂት ቢሆንም በአንድ ወቅት የተከሰተው ግን ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ነው። ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ዓመታዊ ጉዞ ባደረጉበት ጊዜ ይዘውት ሄዱ። በኢየሩሳሌም እያለ በቤተ መቅደሱ ውስጥ “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው” ረዘም ያለ ጊዜ ያሳለፈ ከመሆኑም በላይ “የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር።” አዎን፣ ወጣቱ ኢየሱስ የሚያመራምሩና መንፈሳዊ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን አስገራሚ መልሶች ይሰጥ ነበር። (ሉቃስ 2:41-50) ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ከተማ ሲሆን የአናጢነትን ሙያ ከአሳዳጊ አባቱ ከዮሴፍ ተማረ።—ማቴዎስ 13:55

ኢየሱስ 30 ዓመት እስኪሆነው ድረስ በናዝሬት ኖረ። ከዚያም ለመጠመቅ ወደ ዮሐንስ ሄደ። ኢየሱስም እንደተጠመቀ በከፍተኛ ቅንዓት አገልግሎቱን ማከናወን ጀመረ። ለሦስት ዓመት ተኩል በትውልድ አገሩ በሙሉ ተዘዋውሮ ስለ አምላክ መንግሥት አውጇል። ኢየሱስ ከአምላክ እንደተላከ ተጨባጭ ማስረጃ አሳይቷል። እንዴት? ከሰው ችሎታ በላይ የሆኑ ብዙ ተአምራትን በማከናወን ነው።—ማቴዎስ 4:17፤ ሉቃስ 19:37, 38

ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ የመራራትና የአዛኝነት ስሜት ነበረው። በተለይ ለሰዎች በነበረው አመለካከትና በሚያደርግላቸው ነገሮች ርኅራኄ እንዳለው በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስ ደግና በቀላሉ የሚቀረብ ስለነበር ሰዎች ወደ እርሱ ይሳቡ ነበር። ልጆች እንኳን ሳይቀሩ አጠገቡ ሲሆኑ ደስ ይላቸው ነበር። (ማርቆስ 10:13-16) ምንም እንኳን በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ሴቶችን በንቀት ይመለከቱ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ግን ያከብራቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:9, 27) ድሆችና የተጨቆኑ ሰዎች ‘ለነፍሳቸው ዕረፍት እንዲያገኙ’ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) የማስተማር ዘዴው በጣም ግልጽ፣ ቀላልና ለሁኔታው ተስማሚ ነበር። የኢየሱስ ትምህርቶች አድማጮቹ ስለ እውነተኛው አምላክ፣ ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንደነበረው የሚያንጸባርቁ ነበሩ።—ዮሐንስ 17:6-8

ኢየሱስ ተአምር ለማድረግ የሚያስችለውን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በመጠቀም በርኅራኄ ስሜት ተነሳስቶ በሽተኞችንና ሕመምተኞችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 15:30, 31) ለምሳሌ፣ አንድ በለምጽ የተያዘ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። ኢየሱስ ምን አደረገ? እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። የታመመውም ሰው ተፈወሰ!—ማቴዎስ 8:2-4

ኢየሱስን ለማዳመጥ የተሰበሰቡት ሰዎች ያለምግብ ለሦስት ቀናት የቆዩበትን አጋጣሚ ደግሞ እንመልከት። ለሕዝቡ በጣም ስላዘነ በተአምራዊ ሁኔታ “ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አራት ሺህ ወንዶች[ን]” መግቧል። (ማቴዎስ 15:32-38) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ወዳጆቹን ለማዳን ማዕበሉን ጸጥ አድርጓል። (ማርቆስ 4:37-39) የሞቱትንም ሰዎች አስነስቷል ማለትም እንደገና መኖር እንዲችሉ ወደ ሕይወት መልሷቸዋል። a (ሉቃስ 7:22፤ ዮሐንስ 11:43, 44) ኢየሱስ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች በሙሉ ለወደፊቱ ተስፋ እንዲኖራቸው ፍጹም ሕይወቱን እንኳ ቤዛ አድርጎ በፈቃደኝነት ሰጥቷል። ኢየሱስ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል!

ኢየሱስ አሁን ያለው የት ነው?

ኢየሱስ 33 ዓመት ተኩል ሲሆነው በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ተገደለ። b ሆኖም ሞት የሕይወቱ መጨረሻ አልሆነም። ከሦስት ቀን በኋላ ይሖዋ ልጁን መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት እንዲነሳ ባደረገው ጊዜ ሦስተኛው የሕይወቱ ክፍል ጀመረ። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖሩ ለነበሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ታይቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:3-8) ከዚያም በኋላ በሰማይ ‘በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ’ ንጉሣዊ ሥልጣኑን የሚቀበልበትን ጊዜ ሲጠባበቅ ቆይቷል። (ዕብራውያን 10:12, 13) ንጉሣዊ ሥልጣኑን የሚቀበልበት ጊዜ ሲደርስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስን በዓይነ ሕሊናችን እንዴት ልንመለከተው ይገባል? የምናስበው ሊሞት ተቃርቦ እንደሚያጣጥር ሰው አድርገን ነው? ወይስ ሊመለክ እንደሚገባው አካል? ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ሰውም ሆነ ሁሉን ቻይ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እየገዛ ያለ ኃያል ንጉሥ ነው። በቅርቡ ደግሞ በመከራ በተሞላችው ምድራችን ላይ መግዛት ይጀምራል።

ራእይ 19:11-16 ኢየሱስ ክርስቶስን በጽድቅ ለመፍረድ ለጦርነት እንደሚገሰግስ፣ በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ንጉሥ አድርጎ በምሳሌያዊ ሁኔታ ገልጾታል። “ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ” ይዟል። አዎን፣ ኢየሱስ ክፉዎችን ለማጥፋት ታላቅ ኃይሉን ይጠቀማል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስና አባቱ እነዚህን ሰዎች አርማጌዶን ተብሎ ከሚጠራው ‘ሁሉን የሚችል አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በሕይወት ጠብቀው በማሳለፍ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋሉ።—ራእይ 7:9, 14፤ 16:14, 16፤ 21:3, 4

ኢየሱስ ሰላም በሰፈነበት ግዛቱ ለመላው የሰው ልጆች ጥቅም የሚያስገኙ ተአምራትን ያደርጋል! (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1-10) ማንኛውንም ዓይነት በሽታ ይፈውሳል እንዲሁም ሞትን ያጠፋል። ይሖዋ ኢየሱስን በመጠቀም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይዘረጋላቸዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) በኢየሱስ መንግሥት ግዛት ውስጥ የምናገኘው ሕይወት ምን ያህል አስደናቂ እንደሚሆን ለመገመት ያዳግታል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት መቅሰማችንና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይበልጥ መተዋወቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት የታወቁ ነበሩ። የኢየሱስ ጠላቶች እንኳን ሳይቀሩ ‘ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እንዳደረገ’ አምነዋል።—ዮሐንስ 11:47, 48

b ኢየሱስ የሞተው በእንጨት ላይ ነው ወይስ በመስቀል ለሚለው ጥያቄ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለ መጽሐፍ ገጽ 87-89 ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

በርካታ ሃይማኖተኛ ሰዎች ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ሥላሴ ነው ይላሉ። በዚህ ትምህርት መሠረት “አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው፣ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው፤ ሆኖም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይደሉም።” ሦስቱም “ዘላለማዊና እኩል” ናቸው ተብሎ ይታሰባል። (ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ) እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል ነው?

ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11) እርሱ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የሌለው ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። (መዝሙር 90:2) በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ መጀመሪያ አለው። (ቈላስይስ 1:15, 16) ኢየሱስ፣ አምላክ አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ ‘አብ ከእኔ ይበልጣል’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም ኢየሱስ እርሱም ሆነ መላእክት የማያውቋቸው ሆኖም አምላክ ብቻ የሚያውቃቸው አንዳንድ ነገሮች እንደነበሩ ገልጿል።—ማርቆስ 13:32

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ወደ አባቱ ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:42) ኢየሱስ ከእርሱ በላይ ለሆነ አካል ካልሆነ በቀር ለማን ሊጸልይ ይችላል? በተጨማሪም ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው አምላክ እንጂ ራሱ አልነበረም። (የሐዋርያት ሥራ 2:32) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ምድር ከመጣ በኋላ ከአባቱ ጋር እኩል እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላስ? አንደኛ ቆሮንቶስ 11:3 “የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ይላል። በዚህም ምክንያት ልጁ ሁልጊዜ ለአምላክ ይገዛል ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:28) ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ሳይሆን የአምላክ ልጅ እንደሆነ ያሳያሉ።

የሥላሴ ሦስተኛ ክፍል ነው የሚባለው መንፈስ ቅዱስ ደግሞ አካል አይደለም። መዝሙራዊው ወደ አምላክ ሲጸልይ “መንፈስህን ስትልክ፣ እነርሱ ይፈጠራሉ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 104:30) ይህ መንፈስ አምላክ ራሱ ሳይሆን እርሱ የፈለገውን ሁሉ ለመሥራት የሚልከው ወይም የሚጠቀምበት ኃይል ነው። አምላክ መንፈሱን ተጠቅሞ ግዑዙን ሰማይ፣ ምድርንና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ፈጥሯል። (ዘፍጥረት 1:2፤ መዝሙር 33:6) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉትን ሰዎች ለማነሳሳት የተጠቀመው በዚህ መንፈስ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) ስለዚህ ሥላሴ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለው ትምህርት አይደለም። c መጽሐፍ ቅዱስ “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው” በማለት ይናገራል።—ዘዳግም 6:4 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

c ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ የአምላክ ቅቡዕ ሆኗል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ኃይሉን በሙሉ አምላክ ለሰጠው ሥራ አውሏል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ኃያል ንጉሥ ነው