ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተመላለሰ ተመላለሱ
ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተመላለሰ ተመላለሱ
“ማንም [በአምላክ] እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።”—1 ዮሐንስ 2:6
1, 2. ኢየሱስን በትኩረት መመልከት ምን ማድረግን ያካትታል?
ሐዋርያው ጳውሎስ “በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። የእምነታችን ጀማሪና [“ራስና፣” የ1954 ትርጉም] ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት” በማለት ጽፎ ነበር። (ዕብራውያን 12:1, 2) በታማኝነት ጎዳና ለመመላለስ ኢየሱስ ክርስቶስን በትኩረት መመልከት ያስፈልገናል።
2 በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “እንመልከት” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቃል “ባልተከፋፈለ ሐሳብ በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ፣” “አንድን ነገር ለመመልከት ሲባል የእይታ አቅጣጫን መቀየር፣” “በትኩረት መመልከት” የሚል ትርጉም አለው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ግሪካዊው ሯጭ ትኩረቱን ከውድድሩና ከመጨረሻው መሥመር ወደ ተመልካቹ ባዞረበት ቅጽበት ፍጥነቱ ይቀንሳል። ከአንድ ክርስቲያን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።” ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮች ለመንፈሳዊ እድገታችን እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስን በትኩረት ልንመለከተው ይገባል። ሆኖም የእምነታችንን ራስ የምንመለከተው ምን ለማግኘት ነው? “ራስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መሪ፣ በሁሉም ነገር ቅድሚያውን በመውሰድ አርዓያ የሚሆን” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስን በትኩረት መመልከት የእርሱን ምሳሌ መከተልን ይጠይቃል።
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተመላለስ መመላለስ በእኛ በኩል ምን ይጠይቅብናል? (ለ) ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም [በአምላክ] እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:6) ኢየሱስ የአባቱን ትእዛዛት እንደጠበቀ እኛም የኢየሱስን ትእዛዛት በመጠበቅ በአምላክ መኖር እንችላለን።—ዮሐንስ 15:10
4 እንግዲያው ኢየሱስ እንደተመላለሰው ለመመላለስ እርሱን እንደ ዋና መሪያችን በትኩረት በመመልከት ፍለጋውን በቅርብ መከተል ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ ልንወያይባቸው የሚገቡት አስፈላጊ ጥያቄዎች:- ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ የሚመራን እንዴት ነው? እርሱ የተመላለሰበትን መንገድ መኮረጃችን ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይገባል? ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን አርዓያ መከተል ምን ጥቅሞች አሉት? የሚሉት ናቸው።
ኢየሱስ ተከታዮቹን የሚመራው እንዴት ነው?
5. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ ምን ቃል ገብቶላቸዋል?
5 ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ በመገለጥ አንድ አስፈላጊ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር። “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው። መሪያቸው ኢየሱስ ይህን ኃላፊነት ሲወጡ አብሯቸው እንደሚሆንም እንዲህ በማለት ቃል ገብቶላቸዋል:- “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ በደረሰበት በዚህ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተከታዮቹ ጋር የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
6, 7. ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚመራን እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ “አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 14:26) በኢየሱስ ስም የተላከው መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይመራናል እንዲሁም ያበረታታናል። መንፈሳዊ ማስተዋል የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር” መገንዘብ እንድንችል እርዳታ ያደርግልናል። (1 ቆሮንቶስ 2:10) ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱስ፣ “የመንፈስ ፍሬ” የሆኑትን እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን አምላካዊ ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል።—ገላትያ 5:22, 23
7 ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናጠናና የተማርነውን ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር የይሖዋ መንፈስ እንደ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ እውቀት፣ ፍትሕ እንዲሁም የመለየት ችሎታ ያሉትን ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል። (ምሳሌ 2:1-11) መንፈስ ቅዱስ የሚያጋጥመንን ፈተናና ችግር ተቋቁመን መጽናት እንድንችልም ይደግፈናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ክርስቲያኖች ‘ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳቸውን እንዲያነጹና ቅድስናቸውን ፍጹም እንዲያደርጉት’ ተመክረዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ የአምላክን የቅድስና ወይም የንጽሕና መሥፈርት ማሟላት ይቻለናል? ኢየሱስ በዚህ ዘመን እኛን ለመምራት የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ይሖዋ አምላክም በዚህ መንፈስ እንዲጠቀም ሥልጣን ሰጥቶታል።—ማቴዎስ 28:18
8, 9. ክርስቶስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት አመራር የሚሰጠው እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን ለመምራት የሚጠቀምበትን ሌላ መንገድ ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ ስለ መገለጡና ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ በተናገረበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ባለቤቱ በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ [“ታማኝና ልባም ባሪያ፣” የ1954 ትርጉም] እንግዲህ ማነው? ባለቤቱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የተጣለበትን ዐደራ እየፈጸመ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።”—ማቴዎስ 24:3, 45-47
9 “ባለቤቱ” ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን “ባሪያ” የተባለው ደግሞ በምድር ላይ የሚገኙትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ያመለክታል። የባሪያው ክፍል በምድር ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ንብረቶች እንዲንከባከብ እንዲሁም መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እንዲያቀርብ ዐደራ ተጥሎበታል። ከጠቅላላው “ታማኝና ልባም ባሪያ” የተውጣጡ ብቃት ያላቸው ጥቂት ሽማግሌዎች የበላይ አካል በመሆን የባሪያውን ክፍል ወክለው ያገለግላሉ። እነዚህ የበላይ አካል አባላት በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የአምላክን መንግሥት የመስበክና መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ የማቅረብ ኃላፊነት ይመራሉ። በዚህ መንገድ ክርስቶስ በመንፈስ በተቀባው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም በበላይ አካሉ በኩል ጉባኤውን ይመራል።
10. ለሽማግሌዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?
10 ክርስቶስ ጉባኤውን ለመምራት “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” [NW] ተብለው በተጠሩት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾችም ይጠቀማል። እነዚህን ሽማግሌዎች የሰጠን “የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት” ነው። (ኤፌሶን 4:8, 11, 12) ዕብራውያን 13:7 ስለ እነዚህ የበላይ ተመልካቾች ሲናገር “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው” ይላል። ሽማግሌዎች ጉባኤውን ይመራሉ። የበላይ ተመልካቾች ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚመስሉ እምነታቸውን ልንኮርጅ ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ሽማግሌዎችን በመስጠት ለተደረገልን ዝግጅት ያለንን አድናቆት ለእነዚህ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” በመታዘዝና በመገዛት ማሳየት እንችላለን።—ዕብራውያን 13:17
11. ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ተከታዮቹን የሚመራው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለስ ምን ነገሮችን ያካትታል?
11 በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ፣ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም በጉባኤ ሽማግሌዎች አማካኝነት ተከታዮቹን ይመራቸዋል። ኢየሱስ እንደተመላለሰው ለመመላለስ አመራር የሚሰጥበትን መንገድ መገንዘብና ለዚያም ተገዢዎች መሆን ይኖርብናል። ከዚህም በላይ የእርሱን አርዓያ ልንኮርጅ ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ፍጹም የሆነውን የኢየሱስን አርዓያ መከተላችን ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይገባል?
በሥልጣን አጠቃቀማችሁ ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ
12. በጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች በተለይ የትኛውን የክርስቶስ ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል?
12 ኢየሱስ ማንም ያላገኘውን ከፍተኛ ሥልጣን አባቱ የሰጠው ቢሆንም ይህን ሥልጣን የሚጠቀምበት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ነው። ሁሉም የጉባኤው አባላት በተለይም የበላይ ተመልካቾች “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW] በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል። (ፊልጵስዩስ 4:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ በሥልጣን አጠቃቀማቸው ረገድ የክርስቶስን ፈለግ መከተላቸው ተገቢ ነው።
13, 14. ሽማግሌዎች፣ ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ በሚያበረታቱበት ጊዜ የክርስቶስን አርዓያ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። ከሚችሉት በላይ እንዲያደርጉ አልጠበቀባቸውም። (ዮሐንስ 16:12) ኢየሱስ ተከታዮቹን ሳያስጨንቃቸው የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ‘እንዲጣጣሩ’ አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 13:24) ይህንንም ያደረገው እርሱ ቅድሚያውን ወስዶ በመሥራትና ልባቸው እንዲያነሳሳቸው አጋጣሚ በመስጠት ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ሌሎች የጥፋተኝነት ስሜት አድሮባቸው አምላክን እንዲያገለግሉ ለማድረግ በማስፈራሪያ አይጠቀሙም። ከዚህ በተቃራኒ ሰዎች ለይሖዋና ለኢየሱስ እንዲሁም ለሌሎች ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው አምላክን እንዲያገለግሉ ያበረታታሉ።—ማቴዎስ 22:37-39
14 ኢየሱስ በሥልጣኑ አላግባብ በመጠቀም የሰዎችን ሕይወት ለመቆጣጠር አልሞከረም። ሊደረስባቸው የማይችሉ መሥፈርቶች ወይም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሕግጋት አላወጣም። የተጠቀመበት ዘዴ በሙሴ ሕግ የታቀፉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰዎች እንዲያስተውሉ መርዳትና ልባቸው ተነክቶ ለተግባር እንዲነሳሱ ማድረግ ነበር። (ማቴዎስ 5:27, 28) ሽማግሌዎች የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በመከተል በግብታዊነት ሕግ ከማውጣት ወይም እኛ ያልነው ካልተፈጸመ ብለው ድርቅ ከማለት ይቆጠባሉ። በአለባበስና በአጋጌጥ ወይም በመዝናኛ ረገድ ሽማግሌዎች በሚክያስ 6:8፤ በ1 ቆሮንቶስ 10:31-33 እንዲሁም በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 ላይ የሚገኙትን አምላካዊ መመሪያዎች በመጠቀም የሰዎችን ልብ ለመንካት ይጥራሉ።
ርኅሩኅና ይቅር ባዮች ሁኑ
15. ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ድክመት እንዴት ተመለከተው?
15 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሲሳሳቱና ሲያጠፉ በወሰደው እርምጃም ምሳሌ ይሆነናል። ሰው ሆኖ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የተከናወኑ ሁለት ክስተቶችን እንመልከት። ጌቴሴማኒ ከደረሱ በኋላ ኢየሱስ፣ “ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ” ሄደና ‘ነቅተው እንዲጠብቁ’ ነገራቸው። ከዚያ “ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ . . . ጸለየ።” ተመልሶ ሲመጣ “ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው።” ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ምን አደረገ? “መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አላቸው። (ማርቆስ 14:32-38) ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን በቁጣ ከመውቀስ ይልቅ ርኅራኄ አሳይቷቸዋል! በዚያው ምሽት ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ካደው። (ማርቆስ 14:66-72) ከዚያ በኋላ ሲገናኙ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ምን አድርጎለታል? ዘገባው “ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም [ለጴጥሮስ] ታይቷል” ይላል። (ሉቃስ 24:34) በሌላ ቦታም መጽሐፍ ቅዱስ “ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:5) ኢየሱስ ጴጥሮስን ከመቀየም ይልቅ ይህን ንስሐ የገባውን ሐዋርያ ይቅር ብሎታል እንዲሁም አበረታቶታል። ቆየት ብሎም ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶታል።—የሐዋርያት ሥራ 2:14፤ 8:14-17፤ 10:44, 45
16. የእምነት ባልንጀሮቻችን ሲያስቀይሙን ወይም ሲበድሉን ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
16 የእምነት ባልንጀሮቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ሲያስቀይሙን ወይም ሲበድሉን እኛም እንደ ኢየሱስ ርኅሩኆችና ይቅር ባዮች መሆን አይገባንም? ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:8, 9) አንድ ግለሰብ የኢየሱስን ምሳሌ ከመከተል ይልቅ ርኅራኄና ምሕረት ሳያሳየን ቢቀርስ? በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስን ለመምሰል የመጣርና እርሱ ቢሆን ኖሮ የሚወስደው ዓይነት እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለብን።—1 ዮሐንስ 3:16
መንግሥቱን አስቀድሙ
17. ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛ ቦታ እንደሰጠው የሚያሳየው ምንድን ነው?
17 ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለስ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የያዘው የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራ ነበር። ኢየሱስ በሰማርያ፣ በሲካር ከተማ አቅራቢያ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ሲመሠክር ከቆየ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 4:34) የአባቱን ፈቃድ ማድረግ የምግብን ያህል ሰውነት የሚገነባ፣ የሚያረካና መንፈስን የሚያድስ ሆኖለት ነበር። ታዲያ እኛስ ኢየሱስን በመምሰል የአምላክን ፈቃድ ብናስቀድም ሕይወታችን ትርጉም ያለውና አርኪ አይሆንልንም?
18. ልጆች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ ማበረታታት ምን በረከት ያስገኛል?
18 ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ ሲያበረታቷቸው እነርሱም ሆኑ የአብራካቸው ክፋዮች ብዙ በረከት ያገኛሉ። መንትያ ልጆች ያሉት አንድ አባት ልጆቹን አቅኚ እንዲሆኑ ከትንሽነታቸው ጀምሮ ያበረታታቸው ነበር። መንትዮቹም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። አባታቸው እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዳቸው ምን ያህል እንዳስደሰተው ሲገልጽ “ልጆቻችን አላሳፈሩንም። ‘ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው’ ብለን በአመስጋኝነት መናገር እንችላለን” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 127:3) ልጆችስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈላቸው የሚጠቀሙት እንዴት ነው? አምስት ልጆች ያሏት አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “አቅኚነት፣ ልጆቼ በሙሉ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው፣ የግል ጥናት ልማዳቸውን እንዲያሻሽሉና ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀምን እንዲማሩ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን እንዲለምዱ ረድቷቸዋል። ሁሉም በርከት ያሉ ማስተካከያዎች ለማድረግ ቢገደዱም አንዳቸውም ቢሆኑ በመረጡት ጎዳና አይጸጸቱም።”
19. ወጣቶች ጥበበኞች በመሆን ለወደፊቱ ጊዜ ምን ግብ ማውጣት ይኖርባቸዋል?
19 እናንት ወጣቶች፣ የወደፊት እቅዳችሁ ምንድን ነው? በአንድ መስክ የተዋጣላችሁ ባለሞያ ለመሆን እየጣራችሁ ነው? ወይስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ግብ አላችሁ? ጳውሎስ እንዲህ ሲል መክሮናል:- “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ። የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ።”—ኤፌሶን 5:15-17
ታማኞች ሁኑ
20, 21. ኢየሱስ ታማኝ የነበረው በምን መንገድ ነው? እኛስ የእርሱን የታማኝነት ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
20 ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለስ የእርሱን የታማኝነት ምሳሌ መኮረጅንም ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ምን ያህል ታማኝ እንደነበረ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።” ኢየሱስ ለአምላክ ፈቃድ በመገዛት የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥነት በታማኝነት ደግፏል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቃይቶ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል። እኛም ‘ያን አስተሳሰብ’ በመያዝ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን በታማኝነት ማቅረብ ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 2:5-8 የ1954 ትርጉም
21 ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ታማኝ እንደነበረም አሳይቷል። ደካሞችና ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም “እስከ መጨረሻው” ወዷቸዋል። (ዮሐንስ 13:1፣ የግርጌ ማስታወሻ) እኛም በተመሳሳይ ወንድሞቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው የሚፈጽሙትን ስሕተት በመመልከት ነቃፊዎች መሆን አይገባንም።
የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ ተከተሉ
22, 23. የኢየሱስን ፈለግ መከተል ምን ጥቅሞች አሉት?
22 ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ፍጹም አርዓያ የተወልንን የመሪያችንን ፈለግ ሙሉ በሙሉ መከተል እንደማንችል የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ግን ፍለጋውን በቅርብ ለመከተል ጥረት ማድረግ እንችላለን። ለዚህም ክርስቶስ አመራር የሚሰጥበትን መንገድ መረዳትና ለሥልጣኑ መገዛት እንዲሁም የተወልንን ምሳሌ በጥብቅ መከተል ይኖርብናል።
23 ክርስቶስን መምሰል ብዙ በረከቶች ያስገኛል። የራሳችንን ፈቃድ ከማድረግ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ስለምንፈጽም ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለውና አርኪ ይሆናል። (ዮሐንስ 5:30፤ 6:38) ንጹሕ ሕሊና አለን። አኗኗራችን ለሌሎች አርዓያ ይሆናል። ኢየሱስ ሸክማቸው የከበዳቸውና የደከማቸው ሁሉ ወደ እርሱ በመምጣት ለነፍሳቸው እረፍት እንዲያገኙ ጋብዟቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) የኢየሱስን ምሳሌ ስንከተል እኛም የሌሎችን መንፈስ የምናድስ እንሆናለን። እንግዲያው ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለሳችንን እንቀጥል።
ታስታውሳለህ?
• ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ተከታዮቹን የሚመራው እንዴት ነው?
• ሽማግሌዎች ከአምላክ የተሰጣቸውን ሥልጣን በሚጠቀሙበት መንገድ ረገድ የክርስቶስን አመራር መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
• ሰዎች ሲበድሉን ወይም ቅር ሲያሰኙን በምንወስደው እርምጃ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
• ወጣቶች የመንግሥቱን ጉዳዮች ማስቀደም የሚችሉት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች የክርስቶስን አመራር እንድንከተል ይረዱናል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች፣ አስደሳች ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖራችሁ ምን ግብ አውጥታችኋል?