በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ሰው ዓመጽ የሞላባቸውን የኮምፒውተር ጨዋታዎች መጫወቱ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ይነካበታል?

“እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች [“አጥብቆ ይጠላቸዋል፣” የ1980 ትርጉም]” በማለት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ጽፏል። (መዝሙር 11:5) “መጥላት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው “ጠላት ተደርጎ የሚፈረጅን ሰው” ነው። ስለዚህ ዓመጽን የሚወድ ማንኛውም ሰው ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል። እንግዲያው፣ አንዳንድ የኮምፒውተር ጨዋታዎችን መጫወቴ ለዓመጽ ፍቅር እንድኮተኩት ያደርገኝ ይሆን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

ዓመጽ የሞላባቸው የኮምፒውተር ጨዋታዎች የጦር መሣሪያ መጠቀምን ያበረታታሉ። በአብዛኛው ተጫዋቹን የውጊያ ስልት ያስተምራሉ። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “የአሜሪካ ጦር ኃይል የኮምፒውተር ጨዋታዎችን እንደ አንድ የማሠልጠኛ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ይሁን እንጂ የጦር ኃይሉ የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ጨዋታዎች በተራው ሕዝብ እጅ የሚገኙ ናቸው።”

እውነት ነው፣ የዓመጽ ድርጊቶች የሞሉባቸውን የኮምፒውተር ጨዋታዎች የሚጫወቱ ሰዎች በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ አይደለም። ሆኖም የመዝናኛ ምርጫቸው ስለ ልባቸው ዝንባሌ ምን የሚያሳየው ነገር አለ? (ማቴዎስ 5:21, 22፤ ሉቃስ 6:45) በአካል የማያገኛቸውን ሰዎች በመውጋት፣ በጥይት በመምታት፣ የአካል ጉዳተኛ በማድረግና በመግደል ስለሚደሰት ሰው ምን ብለህ መደምደም ትችላለህ? ይህ ሰው በየሳምንቱ በእንደዚህ ዓይነት የውሸት ዓመጽ እየተዝናና ብዙ ሰዓት በማሳለፉ ነገሩ ሱስ ቢሆንበትስ? የብልግና ሥዕሎችን የሚመለከት አንድ ሰው ሥነ ምግባር ለጎደለው ድርጊት መጥፎ ምኞት እያሳደረ እንደሆነ ሁሉ ይህም ሰው ለዓመጽ ፍቅር እያዳበረ እንደሆነ መገመት አያዳግትም።—ማቴዎስ 5:27-29

ዓመጽ ወዳድ የሆነን ሰው ይሖዋ ምን ያህል ይጠላዋል? ዳዊት ‘አጥብቆ ይጠላዋል’ ሲል ገልጿል። በኖኅ ዘመን ይሖዋ ዓመጽን ለሚወዱ ሰዎች ያለውን ከባድ ጥላቻ አሳይቷል። ይሖዋ ለኖኅ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በእርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 6:13) እውነተኛው አምላክ ሰዎች ዓመጸኛ በመሆናቸው ጠቅላላውን የሰው ዘር ዓለም አጠፋ። ኖኅንና ቤተሰቡን ማለትም ዓመጻን ያልወደዱትን ስምንት ሰዎች ብቻ አተረፈ።—2 ጴጥሮስ 2:5

የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ።” ለዓመጽ ፍቅር ማሳደርን ከመማር ይልቅ “ጦርነትን ከእንግዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:4) የአምላክ ጠላት ከመሆን ይልቅ ወዳጁ ሆነን ለመቀጠል ከፈለግን ‘ከክፉ መራቅና መልካምን ማድረግ’ እንዲሁም ‘ሰላምን መፈለግና መከተል’ ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 3:11

የዓመጽ ድርጊት የሞላባቸውን የቪዲዮ ጨዋታዎች የመጫወት ልማድ ቢኖረንስ? ይሖዋ የሚጠላቸውን ድርጊቶች በመተው እርሱን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። በእርግጥም መንፈሳዊነታችንን የሚጎዳውን ይህን ድርጊት ማቆም እንድንችል አምላክ በቅዱስ መንፈሱ እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። እንደ ሰላም፣ ደግነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉት ባሕርያት በሕይወታችን ላይ አምላካዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ከፈቀድን ይህን ድርጊት ማቆም እንችላለን።—ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23