በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው’

‘ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው’

‘ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው’

“እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።” (መክብብ 12:13) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን በአምላክ መንፈስ መሪነት ወደዚህ ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ መደምደሚያ ላይ ደርሷል! ኢዮብም አምላክን መፍራት ያለውን ጥቅም በመረዳቱ “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 28:28

ይሖዋን የመፍራት ባሕርይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት መኮትኮት የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው? እውነተኛ አምላኪዎቹ እንደመሆናችን መጠን በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ አምላካዊ ፍርሃት ያለን መሆኑ በምን መንገዶች ይጠቅመናል? ምሳሌ ምዕራፍ 14 ከቁጥር 26 እስከ 35 ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል። a

‘የጽኑ አምባ’ ምንጭ

ሰሎሞን “እግዚአብሔርን የሚፈራ ጽኑ አምባ አለው፤ ልጆቹም መጠጊያ ይኖራቸዋል” በማለት ገልጿል። (ምሳሌ 14:26) አምላክን የሚፈራ ሰው ታማኝና ሁሉን ቻይ አምላክ በሆነው በይሖዋ ይታመናል። እንዲህ ያለው ሰው የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠበቁ ምንም አያስገርምም! ለእርሱ የወደፊት ሕይወቱ ረጅምና እርካታ የሞላበት ነው።

ይህ ዓለም ባወጣቸው ዕቅዶች፣ ባቋቋማቸው ድርጅቶች፣ በሚመራባቸው ፍልስፍናዎችና በሚያመርታቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ የሚመኩ ሰዎች ስለሚኖራቸው የወደፊት ዕጣ ምን ለማለት ይቻላል? የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምንም ዓይነት ተስፋ ቢያደርጉ አጭር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ታዲያ “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን” የምንወድበት ምን ምክንያት ይኖራል?—1 ዮሐንስ 2:15

አምላክን የሚፈሩ ወላጆች ልጆቻቸው ‘መጠጊያ እንዲኖራቸው’ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል? መዝሙራዊው “ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 34:11) ልጆች አምላክን እንዲፈሩ የወላጆቻቸውን ምሳሌነትና መመሪያ አግኝተው ካደጉ ወደፊት በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ይሆናሉ።—ምሳሌ 22:6

“እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሰውን ከሞት ወጥመድ ያድነዋል” በማለት ሰሎሞን አክሎ ተናግሯል። (ምሳሌ 14:27) እውነተኛው አምላክ ‘የሕያው ውሃ ምንጭ’ በመሆኑ ይሖዋን መፍራት “የሕይወት ምንጭ” ነው። (ኤርምያስ 2:13 የ1954 ትርጉም) ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ማግኘታችን የዘላለም ሕይወት ያስገኝልናል። (ዮሐንስ 17:3) አምላካዊ ፍርሃት ከሞት ወጥመድም ያድነናል። እንዴት? ምሳሌ 13:14 እንዲህ ይላል:- “የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።” ይሖዋን የምንፈራ፣ ሕጎቹን የምንታዘዝና ቃሉ መንገዳችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ ያለ እድሜያችን እንድንቀጭ ከሚያደርጉን መጥፎ ድርጊቶችና ስሜቶች አንጠበቅም?

“የንጉሥ ክብር”

ሰሎሞን በአብዛኛው የንግሥና ዘመኑ ይሖዋን የሚታዘዝና ፈሪሃ አምላክ ያለው ንጉሥ ነበር። ይህ ደግሞ አገዛዙ ጥሩ እንዲሆን ረድቶታል። የአንድን ንጉሥ አገዛዝ የተሳካ ነው የሚያሰኘው ምንድን ነው? ምሳሌ 14:28 “የሕዝብ ብዛት የንጉሥ ክብር ሲሆን፣ የዜጐች ማነስ ግን ለገዥ መጥፊያው ነው” በማለት መልሱን ይሰጣል። የአንድ ንጉሥ ስኬት የሚለካው በተገዢዎቹ ደኅንነት ነው። ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ በሥሩ መተዳደር ከመረጠ ይህ ንጉሥ ጥሩ ገዥ ነው ሊባል ይችላል። ሰሎሞን “ከባሕር [ከቀይ ባሕር] እስከ ባሕር [ሜዲትራንያን] ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ [ከኤፍራጥስ] እስከ ምድር ዳርቻ” ገዝቷል። (መዝሙር 72:6-8) ግዛቱ ታይቶ በማይታወቅ ሰላምና ብልጽግና ይታወቅ ነበር። (1 ነገሥት 4:24, 25) የሰሎሞን የግዛት ዘመን የተሳካ ነበር። በሌላ በኩል በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣት ለገዥ ውርደት ነው።

በዚህ ረገድ ስለ ታላቁ ሰሎሞን ማለትም መሲሐዊ ንጉሥ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምን ማለት ይቻላል? በዘመናችን ያሉትን ተገዢዎቹን ብቻ እንኳ እናስብ። ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላኛው ድረስ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አምላክን የሚፈሩ ወንዶችና ሴቶች በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ለመኖር መርጠዋል። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ላይ እምነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በእውነተኛ አምልኮ አንድ ሆነው ሕያው የሆነውን አምላክ በማምለክ ላይ ይገኛሉ። (ዮሐንስ 14:1) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ከሞት ይነሳሉ። ገነት የሆነችው ምድር ንጉሡ ላደረገላቸው ነገር አድናቆት ባሳዩ ጻድቅና ደስተኛ በሆኑ ሰዎች ትሞላለች። ይህ ደግሞ የክርስቶስ አገዛዝ ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ይሆናል! እንግዲያውስ የመንግሥቱን ተስፋ ከፍ አድርገን እንያዝ።

መንፈሳዊና አካላዊ ጥቅሞች

ለአምላክ ያለን አክብሮታዊ ፍርሃት የልብ ሰላምና የተረጋጋ መንፈስ ይሰጠናል። ይህ ሊሆን የቻለው ጥበብ ካላት በርካታ ገጽታዎች መካከል የማመዛዘን ችሎታና ማስተዋል ስለሚገኙ ነው። ምሳሌ 14:29 “ታጋሽ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤ ግልፍተኛ ሰው ግን ቂልነትን ይገልጣል” ይላል። ማስተዋል፣ በቁጣ መገንፈል መንፈሳዊነታችንን እንደሚጎዳ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳንወርስ’ ከሚያደርጉን ሥራዎች መካከል “ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቊጣ፣ ራስ ወዳድነት” ተጠቅሰዋል። (ገላትያ 5:19-21) የሚያስቆጣ ነገር ቢያጋጥመን እንኳ ተቆጥተን እንዳንቆይ ምክር ተሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ትዕግሥት ማጣት ደግሞ በኋላ የሚጸጽተንን ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድንናገርና እንድናደርግ ሊገፋፋን ይችላል።

የእስራኤል ንጉሥ ቁጣ ስለሚያስከትለው አካላዊ ጉዳት ሲናገር “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል፤ ቅናት ግን ዐጥንትን ያነቅዛል” ብሏል። (ምሳሌ 14:30) ቁጣና ንዴት ከሚያስከትሏቸው እክሎች መካከል በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚፈጠር ችግር፣ የጉበት በሽታ፣ የደም ግፊትና የቆሽት ሕመም ይገኙበታል። በተጨማሪም የጨጓራ ቁስለት፣ ሽፍታ፣ አስም፣ የቆዳ በሽታና የምግብ አለመፈጨት የመሳሰሉትን ችግሮች እንደሚያባብሱ ወይም እንደሚያመጡ ሐኪሞች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል።” (ምሳሌ 14:30) እንግዲያው “ሰላም የሚገኝበትን እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት” ማድረጋችን ጥበብ ነው።—ሮሜ 14:19

አምላክን መፍራት ከአድልዎ እንድንርቅ ይረዳናል

ሰሎሞን “ድኾቸን የሚያስጨንቅ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤ ለተቸገሩ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል” ብሏል። (ምሳሌ 14:31) አምላክን የሚፈራ ሰው የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ አንድ እርሱም ይሖዋ መሆኑን ይገነዘባል። በእኛ አምሳል የተፈጠረን ድሃ የሆነን ሰው የምንይዝበት መንገድ ለፈጣሪ ያለንን አመለካከት ያሳያል። አምላክን ለማክበር ከፈለግን ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት አድልዎ የሚታይበት መሆን የለበትም። አንድ ድሃ ክርስቲያን ያለ አድልዎ መንፈሳዊ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለድሃውም ሆነ ለሀብታሙ እኩል ማዳረስ ይኖርብናል።

ጠቢቡ ንጉሥ አምላክን መፍራት ያለውን ሌላ ጥቅም ሲናገር:- “ክፉ ሰው በክፋቱ ይወድቃል፤ ጻድቅ ግን ፍጹም አቋሙን መጠበቁ መጠጊያ ይሆነዋል” ብሏል። (ምሳሌ 14:32 NW) ክፉ ሰው የሚወድቀው እንዴት ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚሉት ክፉ ሰው ጉዳት ሲደርስበት የማንሰራራት አጋጣሚ አይኖረውም። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን የሚፈራ ሰው መከራ ሲደርስበት ፍጹም አቋሙን በመጠበቁ መጠጊያ ያገኛል። እንዲሁም ሞት እንኳ ቢመጣ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት በመጣል ልክ እንደ ኢዮብ “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም” ብሎ ይወስናል።—ኢዮብ 27:5 የ1954 ትርጉም

ጽኑ አቋማችንን ለመጠበቅ አምላካዊ ፍርሃትና ጥበብ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ሆኖም ጥበብን ከየት ማግኘት ይቻላል? ምሳሌ 14:33 “ጥበብ በአስተዋዮች ልብ ታድራለች፤ በተላሎች መካከል ራሷን ትገልጣለች” በማለት መልስ ይሰጣል። አዎን፣ ጥበብ የምትገኘው በአስተዋይ ሰው ልብ ውስጥ ነው። ታዲያ በተላሎች መካከል ራሷን የምትገልጠው እንዴት ነው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚለው “ተላላ ሰው ጥበብ ያለው ቢሆንም ጠቢብ መስሎ ለመታየት ካለው ጉጉት የተነሳ በሚጠቀምበት ወቅት ያበላሸዋል።”

“ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች”

የእስራኤል ንጉሥ፣ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በብሔር ደረጃ አምላክን መፍራት ያለውን ውጤት አስመልክቶ ሲናገር “ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኀጢአት ግን ለየትኛውም ሕዝብ ውርደት ነው” ብሏል። (ምሳሌ 14:34) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በእስራኤል ብሔር ላይ በትክክል ታይቷል! እስራኤላውያን የአምላክን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች የሙጥኝ ብለው መጠበቃቸው በዙሪያቸው ከሚገኙት ብሔራት በሙሉ ላቅ ብለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ለአምላክ በተደጋጋሚ ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ለውርደት ተዳርገዋል፤ በመጨረሻም የይሖዋን ሞገስ አጥተዋል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ዛሬ ባሉት የአምላክ ሕዝቦችም ላይ ይሠራል። የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች አጥብቆ ስለሚከተል ከዓለም የተለየ ነው። ሆኖም ይህ ከፍ ያለ ደረጃ ተጠብቆ እንዲቆይ በግለሰብ ደረጃ አኗኗራችን ንጹሕ ሊሆን ይገባል። ኃጢአት መሥራት ውርደት የሚያስከትልብን ከመሆኑም በላይ ጉባኤውንና ይሖዋን ያስነቅፋል።

ሰሎሞን አንድን ንጉሥ ደስ የሚያሰኘውን ነገር ሲናገር “ጠቢብ አገልጋይ ንጉሥን ደስ ያሰኛል፤ አሳፋሪ አገልጋይ ግን ቊጣውን በራሱ ላይ ያመጣል” ብሏል። (ምሳሌ 14:35) በተጨማሪም ምሳሌ 16:13 “ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤ እውነት የሚናገረውን ሰው ይወዱታል” ይላል። አዎን፣ መሪያችንና ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን በማንጸባረቅና በማስተዋል ስንመላለስ እንዲሁም አንደበታችንን ለመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ ስንጠቀምበት ይደሰታል። እንግዲያውስ እውነተኛውን አምላክ መፍራት የሚያስገኘውን በረከት ካገኘን በዚህ ሥራ ራሳችንን እናስጠምድ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ⁠ምሳሌ 14:1-25 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-29⁠ንና የሐምሌ 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-20⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላካዊ ፍርሃትን መማር ይቻላል