በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምልክቶችን ማስተዋል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!

ምልክቶችን ማስተዋል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!

ምልክቶችን ማስተዋል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!

“መጀመሪያ ላይ ልጃችን አንድሪያስን የያዘው ቀላል ራስ ምታት መስሎኝ ነበር። ሆኖም የምግብ ፍላጎቱን ከማጣቱም በላይ ኃይለኛ ትኩሳት ጀመረው። ራስ ምታቱ እየተባባሰ ሲሄድ ስጋት አደረብኝ። ባለቤቴ እቤት እንደመጣ ወደ ሐኪም ወሰድነው። ሐኪሙም የበሽታውን ምልክቶች ከመረመረ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል እንድንወስደው ነገረን። ችግሩ ራስ ምታት ብቻ አልነበረም። አንድሪያስን የያዘው የማጅራት ገትር በሽታ ነበር። ከዚያም እንድሪያስ ሕክምና ተደረገለትና ብዙም ሳይቆይ ተሻለው።”—በጀርመን የምትኖር ጌርትሩት የተባለች እናት

ጌርትሩት ያጋጠማት ሁኔታ ለብዙ ወላጆች እንግዳ ነገር ላይሆን ይችላል። ወላጆች ልጃቸው ታምሞ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶችን ያስተውላሉ። ሁሉም ዓይነት ሕመም አደገኛ ነው ባይባልም እንኳ ወላጆች ልጃቸው መታመሙን የሚያሳዩትን ምልክቶች ችላ ብለው ቢያልፉ አሳዛኝ ውጤት ሊገጥማቸው ይችላል። ምልክቶቹን አስተውሎ ተስማሚ እርምጃ መውሰድ በሁኔታዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ይህ በእርግጥም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ምልክቶችን አጢኖ ተስማሚ እርምጃ መውሰድ ጤና ነክ ባልሆኑ ጉዳዮችም ላይ ይሠራል። በታኅሣሥ 2004 በሕንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ አገሮች ላይ የደረሰው የሱናሚ አደጋ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። በወቅቱ እንደ አውስትራሊያና ሃዋይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ መንግሥታዊ ድርጅቶች በሰሜናዊ ሱማትራ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚከሰትና ይህም ሌሎች አደጋዎች ሊያስከትል እንደሚችል አስቀድመው ተረድተው ነበር። ይሁንና ለአደጋው በተጋለጡ አካባቢዎች የሚኖሩት ሰዎች ማስጠንቀቂያውን እንዲሰሙም ሆነ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም ከ220,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑ ምልክቶች

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አድማጮቹ ምልክቶችን አስተውለው ተስማሚ እርምጃ እንዲወስዱ አስተምሯቸው ነበር። እጅግ ታላቅ ጠቀሜታ ስላላቸው ጉዳዮችም ተናግሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ እንደሚከተለው ይላል:- “ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው ሊፈትኑት በመሻት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ ‘ምሽት ላይ፣ “ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል” ትላላችሁ፤ ንጋት ላይም፣ “ሰማዩ ቀልቶአል፣ ከብዶአልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል” ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም።’”—ማቴዎስ 16:1-3

ኢየሱስ “የዘመኑን ምልክት” በመጥቀስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን አድማጮቹ ያሉበት ጊዜ ምን ያህል አጣዳፊ መሆኑን መገንዘብ እንደነበረባቸው ጠቁሟል። ምክንያቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአይሁድ ሥርዓት ላይ ሁሉንም የሚነካ ድንገተኛ ጥፋት ሊደርስ ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ መገኘቱን የሚጠቁም ሌላ ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። በዚህ ወቅት የተናገራቸው ነገሮች በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ እጅግ ታላቅ ትርጉም አላቸው።