በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ የተዉት ምሳሌ አበርትቶኛል

ወላጆቼ የተዉት ምሳሌ አበርትቶኛል

የሕይወት ታሪክ

ወላጆቼ የተዉት ምሳሌ አበርትቶኛል

ያኔዝ ሪኬል እንደተናገረው

ወቅቱ 1958 ሲሆን እኔና ባለቤቴ ስታንካ ወደ ኦስትሪያ ለመሰደድ ዩጎዝላቪያን ከኦስትሪያ በሚያዋስኑት የካረቫንከን ሰንሰለታማ ተራሮች አናት ላይ እየተጓዝን ነበር። በዩጎዝላቭ ድንበር የሚገኙት የታጠቁ ወታደሮች ማንም ሰው ጠረፍ አቋርጦ እንዳያልፍ በተጠንቀቅ ይጠብቁ ስለነበር ይህን ማድረጋችን አደገኛ ነበር። ጉዟችንን ስንቀጥል ድንገት ጭው ያለ ገደል አጋጠመን። እኔም ሆንኩ ስታንካ በኦስትሪያ በኩል ያለውን የተራሮች ገጽታ ከዚህ በፊት አይተነው አናውቅም። ድንጋያማና ጠጠራማ ወደሆነው ለመውረድ የሚያመች ቦታ ላይ እስክንደርስ ድረስ በምሥራቅ አቅጣጫ ጉዟችንን ቀጠልን። ምን እንደሚገጥመን ባናውቅም ይዘነው የነበረውን የዝናብ ልብስ እላያችን ላይ አስረን በእንፉቅቅ መውረድ ጀመርን።

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንደገባንና ወላጆቼ የተዉት የታማኝነት ምሳሌ በአስቸጋሪ ወቅቶችም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ እንድቀጥል እንዴት እንደረዳኝ ልንገራችሁ።

ተወልጄ ያደግሁት አሁን በማዕከላዊው አውሮፓ በምትገኘው ትንሽ አገር በስሎቬንያ ነው። አገሪቷ በአውሮፓ ሰንሰለታማ ተራሮች መካከል የምትገኝ ሲሆን በስተ ሰሜን ኦስትሪያ፣ በስተ ምዕራብ ጣሊያን፣ በስተ ደቡብ ክሮኤሺያ እንዲሁም በስተ ምሥራቅ ሃንጋሪ ያዋስኗታል። ይሁን እንጂ ወላጆቼ ፍራንትስና ሮዛሊያ ሪኬል በተወለዱበት ጊዜ ስሎቬንያ የኦስትሮ-ሃንጋሪ ግዛት ነበረች። በአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ ደግሞ ስሎቬንያ የሰርቦች፣ የክሮአቶችና የስሎቬኖች መንግሥት የሚባል አዲስ ግዛት ክፍል ሆነች። በ1929 የአገሪቷ ስም ወደ ዩጎዝላቪያ ተቀየረ፤ ቀጥተኛ ፍቺው “ደቡብ ስላቪያ” ማለት ነው። በዚሁ ዓመት ጥር 9 ላይ ውብና ማራኪ ከሆነው ብሌድ ሐይቅ አቅራቢያ በምትገኘው ፖድሆም መንደር ዳርቻ ተወለድኩ።

እናቴ ያደገችው አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ከአጎቶቿ አንዱ ቄስ ሲሆን ሶስት አክስቶቿ ደግሞ መነኮሳት ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ የማግኘት፣ የማንበብና ሐሳቡንም የመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። አባቴ ግን ለሃይማኖት ጥሩ አመለካከት አልነበረውም። ከ1914 እስከ 1918 በነበረው ታላቅ ጦርነት ላይ ሃይማኖት የተጫወተው ሚና በጣም አናዶታል።

እውነትን መማር

ጦርነቱ ካለፈ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የእናቴ ዘመድ ያኔዝ ብራዬትስ እና ሚስቱ አንችካ ብራዬትስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኑ። ያን ጊዜ የሚኖሩት በኦስትሪያ ነበር። አንችካ ከ1936 ጀምሮ በየጊዜው እየመጣች እናቴን ትጠይቃት ነበር። ለእናቴ መጽሐፍ ቅዱስ እና በስሎቬንያ ቋንቋ የተዘጋጁ የተለያዩ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሰጠቻት፤ እናቴም መጽሐፍ ቅዱሱን ወዲያውኑ ማንበብ ጀመረች። በ1938 ኦስትሪያ በሂትለር እጅ ስለወደቀች ያኔዝ እና አንችካ ወደ ስሎቬንያ ተመለሱ። ጨዋና ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ያላቸው አስተዋይ ባልና ሚስት እንደነበሩ አስታውሳለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች አንስተው ከእናቴ ጋር ለበርካታ ጊዜ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ይህ ደግሞ ሕይወቷን ለይሖዋ እንድትወስን አነሳስቷታል። ከዚያም በዚያው ዓመት ማለትም በ1938 ተጠመቀች።

እናቴ የገናን በዓል እንደማክበርና ደም የተጨመረበት ቋሊማ እንደመመገብ ያሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌላቸው ልማዶችን ከመፈጸም ስትቆጠብ በተለይ ደግሞ ቤታችን ውስጥ የነበሩትን ሥዕሎች በሙሉ ሰብስባ ስታቃጥል የአካባቢው ሰዎች የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነች። ብዙም ሳይቆይ ተቃውሞ ተነሳ። መነኩሴዎቹ አክስቶቿ ወደ ማርያምና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድትመለስ ለማሳመን ደብዳቤ እየጻፉ ብዙ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። እናቴ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን አንስታ የጻፈችላቸው ቢሆንም ምንም መልስ ሳታገኝ ቀርታለች። አያቴም በእጅጉ ይቃወማት ነበር። ይህን የሚያደርገው ግን በዘመዶቻችንና በመንደሩ ሰው ግፊት ተሸንፎ እንጂ ክፉ ሰው ስለሆነ አልነበረም። እናቴ የነበሯትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ብዙ ጊዜ ያቃጥልባት ነበር፤ ይሁንና መጽሐፍ ቅዱሷን ነክቶባት አያውቅም። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድትመለስ ተንበርክኮ ለምኗት ነበር። በቢላዋ እስከ ማስፈራራት የደረሰበት ጊዜም ነበር። የሆነ ሆኖ አባቴ ከአሁን በኋላ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ፈጽሞ መታገስ እንደማይችል ለአያቴ ነገረው።

አባቴ፣ እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብና የፈለገችውን ለማመን የራሷን ምርጫ የማድረግ መብቷን ያከብርላት ነበር። እርሱም በ1946 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። እናቴ ተቃውሞ ቢደርስባትም ስለ እውነት በድፍረት መቆም እንድትችል ይሖዋ እንዴት እንዳበረታትና ላሳየችውም እምነት እንዴት እንደባረካት መመልከቴ እኔ ራሴ ከአምላክ ጋር ያለኝን ዝምድና እንዳጠናክር አነሳስቶኛል። በተጨማሪም እናቴ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ጮክ ብላ ሁልጊዜ ታነብልኝ የነበረ መሆኑ በጣም ጠቅሞኛል።

እናቴና ማሪያ ሪፔ የተባለችው እህቷ ረዘም ያለ ውይይት ያደርጉ ነበር፤ በመጨረሻም እኔና አክስቴ ማሪያ ሐምሌ 1942 አጋማሽ ላይ አብረን ተጠመቅን። አንድ ወንድም መጥቶ አጠር ያለ ንግግር ከሰጠ በኋላ ቤታችን በነበረ አንድ ትልቅ የእንጨት ገንዳ ውስጥ ተጠመቅን።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ ተወሰድኩ

በ1942 ይኸውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመንና ጣሊያን ስሎቬንያን ወርረው ከሃንጋሪ ጋር ለሦስት ተከፋፈሏት። ቤተሰቦቼ ፎልክስበንት ከተባለው የናዚዎች ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። እኔም በትምህርት ቤት “ሃይል ሂትለር” ለማለት ፈቃደኛ አልነበርኩም። ጉዳዩ በአካባቢው ባለ ሥልጣናት ጆሮ ደረሰ፤ ይህን ያደረገው አስተማሪዬ ሳይሆን አይቀርም።

በባቡር ተጭነን ባቫሪያ ውስጥ ሁትንባክ በምትባል መንደር አቅራቢያ ወደሚገኝ በግዳጅ የጉልበት ሥራ ይሠራበት ወደነበረ ካምፕ ተወሰድን። አባቴ እዚያ አካባቢ ካለ ዳቦ ጋጋሪ ጋር እየሠራሁ ከቤተሰቡ ጋር እንድኖር ዝግጅት አደረገ። የኋላ ኋላ በጣም የረዳኝን የዳቦ ጋጋሪነት ሙያ የተማርኩት በዚህ ጊዜ ነበር። ከጊዜ በኋላ መላው ቤተሰቤ (አክስቴ ማሪያንና ቤተሰቧን ጨምሮ) ወደ ጉንዘንሃውዘን ካምፕ ተወሰዱ።

ጦርነቱ እንዳከተመ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር በመሆን ወላጆቼ ወዳሉበት ቦታ ለመሄድ ዝግጅት አደረግሁ። እንደ ነገ ልሄድ ዛሬ ምሽት ላይ አባቴ ሳይታሰብ እኔ ጋር መጣ። ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ስላልነበሩ ከእነርሱ ጋር ሄጄ ቢሆን ኖሮ ምን ሊገጥመኝ እንደሚችል መገመት ይከብዳል። ይሖዋ በወላጆቼ አማካኝነት ጥበቃና ሥልጠና እንዳገኝ ማድረጉ ፍቅራዊ እንክብካቤው እንዳልተለየኝ አስገንዝቦኛል። እኔና አባቴ ከቤተሰቦቻችን ጋር ለመገናኘት ለሦስት ቀናት ጉዞ አደረግን። በሰኔ 1945 ሁላችንም ወደ ቤታችን ገባን።

ከጦርነቱ በኋላ በፕሬዚዳንት ዮሴፕ ብሮዝ ቲቶ የሚመሩት ኮሚኒስቶች ዩጎዝላቪያን ማስተዳደር ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ችግር መፍትሔ ሳያገኝ ቀረ።

በ1948 ከኦስትሪያ የመጣ አንድ ወንድም ቤታችን ተጋብዞ ነበር። ፖሊሶች ይህን ወንድም በሄደበት እየተከታተሉ እርሱ ገብቶ የጠየቃቸውን ወንድሞች በሙሉ ያስሩ ነበር። አባቴም ወንድምን ቤቱ ስላስተናገደውና ለፖሊስ ሪፖርት ስላላደረገ ለሁለት ዓመት ታሰረ። ይህ ወቅት ለእናቴ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም አባቴ ከአጠገቧ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን እኔም ሆንኩ ታናሽ ወንድሜ በገለልተኝነት አቋማችን ሳቢያ በቅርቡ ችግር እንደሚገጥመን ገብቷት ነበር።

መቄዶንያ ውስጥ ታሰርኩ

በኅዳር ወር 1949 ለወታደራዊ አገልግሎት እንድመለመል መጥሪያ ደረሰኝ። ወታደር ሆኖ ለማገልገል ሕሊናዬ እንደማይፈቅድልኝ ለማስረዳት ሄድኩ። ባለ ሥልጣናቱ ሊሰሙኝ እንኳ ፈቃደኞች አልነበሩም፤ እንዲያውም ከምልምል ወታደሮች ጋር በባቡር አድርገው የዩጎዝላቪያ ጠረፍ ወደሆነችው ወደ መቄዶንያ ላኩኝ።

ከቤተሰቦቼም ሆነ ከእምነት ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ለሦስት ዓመት ያህል ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበረኝ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ጽሑፍ አልነበረኝም። ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። መጽናት የቻልኩት በይሖዋ ላይ እንዲሁም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወው ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ነበር። ወላጆቼ የተዉልኝ ምሳሌም ብርታት ሰጥቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ ብርታት ለማግኘት በተደጋጋሚ መጸለዬ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል።

ከጊዜ በኋላ ስኮፕዬ አቅራቢያ ኢድሪዞቮ ውስጥ ወደሚገኘው ወኅኒ ቤት ተላክሁ። በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ያሉት እስረኞች በተለያየ ዓይነት ሥራና ሙያ ላይ ተሠማርተው ነበር። መጀመሪያ ላይ የተሰጠኝ ሥራ ጽዳትና ተላላኪነት ነበር። የደኅንነት ፖሊስ የነበረ አንድ እስረኛ ያስቸግረኝ የነበረ ቢሆንም ከዘብ ጠባቂዎቹና ከእስረኞቹ አልፎ ተርፎም ከወኅኒ ቤቱ ፋብሪካ ኃላፊዎች ጋር ጥሩ የሥራ ግንኙነት ነበረኝ።

ከዚያ በኋላ ወኅኒ ቤቱ ዳቦ ጋጋሪ እንደሚፈልግ ተረዳሁ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ኃላፊው ለስም ጥሪ ወደተሰለፍንበት መጣና ፊት ለፊቴ ቆሞ “ዳቦ ጋጋሪ ነህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “አዎን ጌታዬ” ብዬ መለስኩለት። እርሱም “ነገ ጠዋት ዳቦ ቤት ሪፖርት አድርግ” አለኝ። እዚያ መሥራት ከጀመርኩ በኋላ ያመናጭቀኝ የነበረው እስረኛ ብዙውን ጊዜ በዳቦ ቤት በኩል ያልፍ የነበረ ቢሆንም ምንም ሊያደርግ አልቻለም። እዚያም ከየካቲት እስከ ሐምሌ 1950 ድረስ ሠራሁ።

ከዚያም ከመቄዶንያ በስተ ደቡብ ፕሬስፓ ሐይቅ አቅራቢያ ወደሚገኘው ቮልኮዴሪ ወደተባለ የጦር ሰፈር እንድዛወር ተደረገ። በቅርብ ባለው በኦቴሾቮ ከተማ ለቤተሰቦቼ ደብዳቤ መጻፍ ችዬ ነበር። ከሌሎች እስረኞች ጋር ሆኜ በመንገድ ሥራ ላይ ተመድቤ እሠራ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የምውለው ሥራው ቀለል በሚልበት ዳቦ ቤት ውስጥ ነበር። በዚህ ሁኔታ የተወሰነ ጊዜ ከሠራሁ በኋላ በኅዳር 1952 ተፈታሁ።

እስር ቤት እያለሁ በፖድሆም አንድ ጉባኤ ተቋቁሞ ነበር። ጉባኤው መጀመሪያ ላይ ይካሄድ የነበረው ስፖድንዬ ጎርዬ ከተማ በሚገኝ አንድ ትንሽ ሆቴል ውስጥ ነበር። በኋላ ላይ አባቴ ከቤታችን አንዱን ክፍል መሰብሰቢያ እንዲሆን ፈቀደ። ከመቄዶንያ ስመለስ አብሬያቸው መሰብሰብ ስለቻልኩ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። ከዚህም በላይ እስር ቤት ከመግባቴ በፊት ተዋውቄያት ከነበረችው ከስታንካ ጋር ያለኝን ግንኙነት ይበልጥ አጠናከርኩ። ከዚያም ሚያዝያ 24, 1954 ተጋባን። ይሁን እንጂ ብዙም እፎይ ሳልል መከራው እንደገና ተመልሶ መጣ።

ማሪቦር ውስጥ ታሰርኩ

በመስከረም ወር 1954 ሌላ መጥሪያ ወረቀት ደረሰኝ። በዚህ ጊዜ በምሥራቅ ስሎቬንያ ጠረፍ ላይ በምትገኘው በማሪቦር ከሦስት ዓመት ተኩል በላይ እንድታሰር ተበየነብኝ። አጋጣሚውን ሳገኝ የተወሰነ ወረቀትና እርሳሶችን ገዛሁ። ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከመጠበቂያ ግንብ እንዲሁም ከሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ውስጥ ማስታወስ የቻልኳቸውን ጥቅሶችና ሐሳቦች ሁሉ መጻፍ ጀመርኩ። የጻፍኩትን ማስታወሻ አነብብ የነበረ ሲሆን ሌላም ሐሳብ ትዝ ሲለኝ በደብተሬ ላይ እጽፍ ነበር። መጨረሻ ላይ ማስታወሻ ደብተሬ ሞላ፤ እንዲህ ማድረጌ አእምሮዬ በእውነት ላይ እንዲያተኩርና በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኜ እንድቀጥል ረድቶኛል። እውነትን በድፍረት ለሌሎች እንዳካፍል ያስቻሉኝ ጸሎትና ማሰላሰልም በመንፈሳዊ ብርቱ እንድሆን ይህ ነው የማይባል እርዳታ አበርክተውልኛል።

በዚህ ወቅት በወር አንዴ ደብዳቤ እንድቀበልና ለ15 ደቂቃ ያህል ጠያቂ እንዲያየኝ ተፈቅዶልኝ ነበር። ስታንካ እስር ቤት በጠዋት ለመድረስ ሌሊቱን በሙሉ በባቡር ትጓዝ ነበር፤ ከዚያም እኔን ጠይቃ በዛው ቀን ወደ ቤት ትመለሳለች። ስታንካ በየጊዜው እየመጣች ትጠይቀኝ የነበረ መሆኑ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንድችል አንድ ነገር አቀድኩ። ስታንካ ልትጠይቀኝ ስትመጣ እኔ እርሷና አንድ ጠባቂ በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጥ የነበረ ሲሆን ሁለታችን ፊት ለፊት እንሆናለን። አንድ ቀን ጠባቂው ለአፍታ ዞር ሲልልኝ በሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ በቦርሳዋ መጽሐፍ ቅዱስ ይዛልኝ እንድትመጣ የሚናገር ደብዳቤ ቦርሳዋ ውስጥ ከተትኩ።

ስታንካና ወላጆቼ እንዲህ ማድረጉ በጣም አደገኛ እንደሆነ ስለተሰማቸው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ገነጣጥለው የተወሰኑ ገጾችን በዳቦዎች ውስጥ እያደረጉ ይልኩልኝ ጀመር። በዚህ ዓይነት መንገድ የምፈልገውን መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ። በተመሳሳይም ስታንካ በእጇ የገለበጠቻቸው የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ይደርሱኝ ነበር። ጽሑፎችን ከየት እንደማገኛቸው ማንም ሰው እንዳያውቅ ለማድረግ ስል ወዲያውኑ በራሴ እጅ ጽሑፍ እገለብጠውና እርሷ የምታመጣልኝን ቅጂ አስወግደው ነበር።

ዘወትር ከመስበኬ የተነሳ አብረውኝ የነበሩት እስረኞች ችግር ውስጥ መውደቄ እንደማይቀር ይነግሩኝ ነበር። በአንድ ወቅት ላይ ከአንድ እስረኛ ጋር አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እያደረግን ነበር። ከዚያም በሩ በቁልፍ ሲከፈትና አንድ ጠባቂ ወደ ውስጥ ሲገባ ሰማን። ወዲያውኑም በቃ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን መታሰሬ ነው ብዬ አሰብኩ። ይሁን እንጂ ጠባቂው የመጣው ይህን አስቦ አልነበረም። ውይይታችንን ስላዳመጠ እርሱም ለመሳተፍ ፈልጎ ነበር። ላነሳቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ በማግኘቱ ደስ እያለው መዝጊያውን ከውጪ ዘግቶ ሄደ።

ከእስር በምፈታበት በመጨረሻው ወር ላይ የእስረኞች ተሃድሶ ኃላፊው ለእውነት ብዬ የወሰድኩትን ቁርጥ አቋም እንደሚያደንቅ ነገረኝ። ይህ ደግሞ የይሖዋን ስም ለማስታወቅ ላደረግኩት ከፍተኛ ጥረት ወሮታ እንደሆነ ተሰማኝ። ግንቦት 1958 ከወኅኒ ቤት ወጣሁ።

ወደ ኦስትሪያ፣ ከዚያም ወደ አውስትራሊያ ተሰደድን

እናቴ ለተወሰነ ጊዜ ከታመመች በኋላ በነሐሴ ወር 1958 በሞት አንቀላፋች። ከዚያም በመስከረም ወር 1958 ሦስተኛው የመጥሪያ ወረቀት ደረሰኝ። በዚያን ቀን ምሽት እኔና ስታንካ ቀደም ሲል የጠቀስኩትን ድንበር አቋሯጭ የሆነውን አስገራሚ ጉዞ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረግን። አንዳንድ ዕቃዎችን በሚታዘሉ ሁለት ቦርሳዎች ውስጥ ከከተትን በኋላ ለማንም ሳንነግር በመስኮት በኩል ወጥተን ሄድን፤ ከዚያም ከስቶል ተራራ በስተ ምዕራብ ወዳለው የኦስትሪያ ድንበር አቀናን። እፎይታ ማግኘት ስለፈለግን ይሖዋ መንገዱን ያዘጋጀልን ይመስለኛል።

የኦስትሪያ ባለ ሥልጣኖች ለሳልዝበርግ ቅርብ ወደሆነው የስደተኞች ካምፕ ወሰዱን። እዚያ በቆየንባቸው ስድስት ወራት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የአገሩ ተወላጅ ከሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንውል ስለነበር በካምፕ ውስጥ ያሳለፍነው ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። በካምፑ የሚገኙ ሌሎች ሰዎች በፍጥነት ጓደኞች ማፍራታችን አስደንቋቸዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኘነው በዚህ ወቅት ነበር። ከቤት ወደ ቤትም በነጻነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበክነው በዚሁ ጊዜ ነበር። የምንሄድበት ጊዜ ሲደርስ ከውድ ወዳጆቻችን መለየቱ በጣም ከበደን።

የኦስትሪያ ባለ ሥልጣኖች ወደ አውስትራሊያ እንድንሄድ ግብዣ አቀረቡልን። የዚህን ያህል ርቀን እንሄዳለን ብለን አስበንም አልመንም አናውቅም ነበር። ወደ ጀኖአ፣ ጣሊያን በባቡር ከተጓዝን በኋላ ወደ አውስትራሊያ በሚሄድ መርከብ ተሳፈርን። መጨረሻ ላይ በኒው ሳውዝ ዌልስ፣ ዎሎንጎንግ ከተማ መኖር ጀመርን። እዚህም መጋቢት 30, 1965 ልጃችን ፊሊፕ ተወለደ።

በአውስትራሊያ መኖራችን ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ለፈለሱ ሰዎች መስበክንና ሌሎች ብዙ የአገልግሎት መስኮች ከፍቶልናል። አምላክን በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆነን ማገልገል መቻላችንን ጨምሮ ይሖዋ ለሰጠን በረከቶች ሁሉ አመስጋኞች ነን። ፊሊፕ እና ባለቤቱ ሱዚ በአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የማገልገል መብት ያገኙ ሲሆን በስሎቬንያ ቅርንጫፍ ቢሮም ለሁለት ዓመት ያህል አገልግለዋል።

እኔና ባለቤቴ እርጅናና የጤና ችግር ያለብን ቢሆንም ለይሖዋ የምንሰጠውን አገልግሎት በመቀጠላችን ደስተኞች ነን። ወላጆቼ ለተዉልኝ የታማኝነት ምሳሌ አመስጋኝ ነኝ! ብርታት ያስገኘልኝ ከመሆኑም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ” በማለት የተናገረውን በሥራ እንዳውል ረድቶኛል።—ሮሜ 12:12

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቼ በ1920ዎቹ መገባደጃ ላይ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እናቴ (በስተ ቀኝ ያለችው)፣ እውነትን ካስተማረቻት ዘመዷ ከአንችካ ጋር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከስታንካ ጋር የተጋባን ሰሞን

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ቤታችን የነበረው ጉባኤ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ፣ ከልጃችን ከፊሊፕና ከባለቤቱ ከሱዚ ጋር