ወላጆች—ልጆቻችሁ ወደፊት ምን እንዲሆኑ ትፈልጋላችሁ?
ወላጆች—ልጆቻችሁ ወደፊት ምን እንዲሆኑ ትፈልጋላችሁ?
“ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ . . . የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ።”—መዝሙር 148:12, 13
1. ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ የሚያስጨንቋቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
ስለ ልጁ የወደፊት ሕይወት የማይጨነቅ የትኛው ወላጅ ነው? ሕጻኑ ከተወለደ ጀምሮ፣ እንዲያውም ከመወለዱ በፊት አንስቶ ወላጆቹ ስለ ደህንነቱ ይጨነቃሉ። ጤናማ ልጅ ይወለዳል? የተስተካከለ እድገት ይኖረው ይሆን? የልጁ ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ሌሎችም የሚያስጨንቁ ነገሮች ብቅ ይላሉ። በጥቅሉ ሲታይ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኙት መልካም የሆኑ ነገሮችን ብቻ ነው።—1 ሳሙኤል 1:11, 27, 28፤ መዝሙር 127:3-5
2. በዛሬው ጊዜ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው ሲያድጉ ጥሩ ኑሮ እንዲኖራቸው አጥብቀው የሚፈልጉት ለምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ለማቅረብ እየተቸገሩ ነው። በርካታ ወላጆች በሕይወት ዘመናቸው ጦርነት፣ የፖለቲካ ነውጥ፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ አካላዊና ስሜታዊ ቀውስ እንዲሁም እነዚህን የመሰሉ ከባድ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። እነርሱ ያጋጠማቸው ችግር በልጆቻቸው ላይ እንዲደርስ እንደማይፈልጉ የተረጋገጠ ነው። በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ወላጆች የወዳጆቻቸውና የዘመዶቻቸው ልጆች በአንድ ሙያ ሲካኑና የተሳካ የሚመስል ኑሮ ሲመሩ ይመለከቱ ይሆናል። ስለዚህ የእነርሱም ልጆች ሲያድጉ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ማለትም የተደላደለና ስጋት የሌለበት ሕይወት እንዲመሩ አቅማቸው የፈቀደውን ማንኛውንም ነገር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።—መክብብ 3:13
ጥሩ ሕይወት መምረጥ
3. ክርስቲያኖች ምን ምርጫ አድርገዋል?
3 ክርስቲያኖች የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናቸው መጠን ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመወሰን መርጠዋል። “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ከልባቸው ይታዘዛሉ። (ሉቃስ 9:23፤ 14:27) አዎን፣ ክርስቲያናዊ ሕይወት የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጨምራል። እንዲህ ሲባል ግን የክርስትና ሕይወት የድህነትና የጉስቁልና ኑሮ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም በተቃራኒው ይህ ዓይነቱ ሕይወት መስጠትንም ስለሚጨምር ጥሩ የሆነ ማለትም አስደሳችና አርኪ አኗኗር ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ” NW] ነው” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
4. ኢየሱስ ተከታዮቹ ምን እንዲፈልጉ አጥብቆ አሳሰባቸው?
4 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይኖሩ ነበር። መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት የሚገባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ጨቋኝ የሆነው የሮማውያን አገዛዝና በዘመኑ የነበሩ የይስሙላ ሃይማኖተኞች ከባድ ቀንበር ጭነውባቸው ነበር። (ማቴዎስ 23:2-4) እንዲህም ሆኖ ስለ ኢየሱስ የሰሙ በርካታ ሰዎች የግል ፍላጎታቸውን፣ አልፎ ተርፎም መተዳደሪያቸውን በደስታ እርግፍ አድርገው ትተው የእርሱ ተከታዮች ሆነዋል። (ማቴዎስ 4:18-22፤ 9:9፤ ቈላስይስ 4:14) እነዚህ ደቀ መዛሙርት የወደፊት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ይሆን? ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ በል:- “ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” (ማቴዎስ 19:29) ኢየሱስ፣ የሰማዩ አባት ተከታዮቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንደሚያውቅ አረጋግጦላቸዋል። ስለዚህ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው።—ማቴዎስ 6:31-33
5. አንዳንድ ወላጆች አምላክ አገልጋዮቹን እንደሚንከባከብ ኢየሱስ ስለሰጠው ዋስትና ምን ይሰማቸዋል?
5 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ያውቃል፤ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ለሚያስቀድሙ በተለይም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለሚካፈሉ እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጦላቸዋል። (ሚልክያስ 3:6, 16፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) ይሁን እንጂ አንዳንድ ወላጆች በዚህ ረገድ ልባቸው የተከፈለ ነው። በአንድ በኩል ልጆቻቸው በይሖዋ አገልግሎት እድገት አድርገው፣ ምናልባትም ከተወሰነ ወቅት በኋላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ ለማየት ይመኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በዛሬው ጊዜ የሚታየውን የኢኮኖሚና የሥራ ሁኔታ ሲያስቡ፣ ወጣቶች ጥሩ ሥራ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ብቃት ለማሟላት ወይም ደግሞ ያሰቡት ሳይሳካ ቢቀር እንኳ የኋላ ኋላ መውደቂያ እንዳያጡ መጀመሪያ ትንሽ ቢማሩ ጥሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ወላጆች እንዲህ ሲሉ ልጆቻቸው ከፍተኛ ትምህርት መከታተል እንዳለባቸው መናገራቸው ነው።
ለወደፊቱ ጊዜ ማዘጋጀት
6. በዚህ ርዕስ ውስጥ “ከፍተኛ ትምህርት” የሚለው ሐረግ ምንን ያመለክታል?
6 የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ ከአገር አገር ይለያያል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ለ12 ዓመት መደበኛ ትምህርት ይሰጣል። ከዚያ በኋላ ተማሪዎቹ እንደ ሕክምና፣ ሕግ፣ ምሕንድስናና እንደነዚህ ባሉ ሌሎች ሙያዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ለማግኘት ቀጥሎ ደግሞ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ለመከታተል በዩኒቨርሲቲ አሊያም በኮሌጅ ተጨማሪ አራት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለመማር ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ርዕስ ውሰጥ “ከፍተኛ ትምህርት” እየተባለ የተጠቀሰው እንዲህ ያለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአጭር ጊዜ ሥልጠና በመስጠት በአንድ ዓይነት ሙያ ወይም አገልግሎት በሰርተፊኬት አሊያም በዲፕሎማ የሚያስመርቁ የቴክኒክና የሙያ ትምህርት ቤቶች አሉ።
7. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለምን ዓይነት ግፊቶች የተጋለጡ ናቸው?
7 በአሁኑ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትኩረት የሚሰጡት ተማሪዎቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት ለማዘጋጀቱ ጉዳይ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ሥራ የሚያስገኙ ትምህርቶችን ከመስጠት ይልቅ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናዎችን በጥሩ ውጤት ለማለፍ የሚያስችሏቸውን የቀለም ትምህርቶች በማስተማሩ ላይ ያተኩራሉ። በዛሬው ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተስፋ የሚጣልበትና ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመያዝ ያበቃል ተብሎ የሚታመንበት ዲግሪ ለማግኘት ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው እንዲማሩ ከአስተማሪዎች፣ ከአማካሪዎችና አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች ከፍተኛ ግፊት ይደረግባቸዋል።
8. ክርስቲያን ወላጆች ምን ምርጫዎች ተደቅነውባቸዋል?
8 ታዲያ ክርስቲያን ወላጆች ምን ማድረግ አለባቸው? እርግጥ ነው፣ ልጆቻቸው በትምህርት በኩል እንዲሳካላቸውና ወደፊት ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ሙያ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 22:29) ይሁንና ቁሳዊ ሃብት ለማካበትና ስኬት ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ ይኖርባቸዋል? ወላጆች በቃልም ሆነ በተግባር ልጆቻቸው ምን ዓይነት ግብ እንዲኖራቸው ያበረታቷቸዋል? አንዳንድ ወላጆች ወደፊት ልጆቻቸውን ከፍተኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው ተቋማት ለማስተማር እንዲችሉ ከወዲሁ ገንዘብ ለማጠራቀም ጠንክረው ይሠራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ለዚሁ ዓላማ ሲሉ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። እንዲህ ያለው ውሳኔ የሚያስከፍለው ዋጋ በብርና በሳንቲም ብቻ የሚሰላ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ምን ኪሳራ ያስከትላል?—ሉቃስ 14:28-33
ከፍተኛ ትምህርት መከታተል የሚያስከትለው ኪሳራ
9. በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ስለሚጠይቀው ወጪ ምን ለማለት ይቻላል?
9 ስለ ኪሳራ ስናስብ በአብዛኛው ወደ አእምሯችን የሚመጣው የገንዘብ ክፍያ ነው። በአንዳንድ አገሮች ለከፍተኛ ትምህርት የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍነው መንግሥት ሲሆን የሚፈለገውን ብቃት የሚያሟሉ ተማሪዎችም መክፈል አይጠበቅባቸውም። ይሁንና በብዙ ቦታዎች ከፍተኛ ትምህርት ለመማር በጣም ብዙ ወጪ ማውጣት የሚያስፈልግ ሲሆን ዋጋውም በየጊዜው ይጨምራል። ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ ይላል:- “ከፍተኛ ትምህርት ጥሩ አጋጣሚ የሚከፍት በር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። አሁን አሁን ግን በሃብታሞችና ብዙም ሃብታም ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት መገለጫ ሆኗል።” በሌላ አነጋገር ጥራት ያለው ከፍተኛ ትምህርት፣ ልጆቻቸው ልክ እንደ እነርሱ ሃብታምና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው እንዲሆኑ የሚፈልጉ ሰዎች ንብረት ሆኗል። ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ ያለውን ግብ መምረጥ አለባቸው?—ፊልጵስዩስ 3:7, 8፤ ያዕቆብ 4:4
10. ከፍተኛ ትምህርት ይህን ሥርዓት ከማሳደግ ጋር በቅርብ የተቆራኘው እንዴት ነው?
10 በነፃ ከፍተኛ ትምህርት መማር በሚቻልባቸው አገሮችም እንኳን ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስውር ግዴታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ የአንድ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር መንግሥት “ሆን ብሎ ጎበዝ ተማሪዎችን የመጨረሻው ትልቅ ደረጃ ላይ ለማድረስ፣ የፒራሚድ ቅርጽ ያለው የትምህርት መዋቅር” እንደሚከተል ዘግቧል። “የመጨረሻው ትልቅ ደረጃ” ላይ መድረስ ሲባል በእንግሊዝ አገር በሚገኙት ኦክስፎርድና ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙት አይቪ ሊግ የሚባሉ ምርጥ ትምህርት ቤቶችና በሌሎች የዓለማችን ታላላቅ ተቋማት ውስጥ መግባት ማለት ነው። መንግሥት እንዲህ ያለውን የረጅም ጊዜ ፕሮግራም ያወጣው ለምንድን ነው? “የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ነው” በማለት ዘገባው ይናገራል። ተማሪው ትምህርቱን የሚማረው በነፃ ሊሆን ቢችልም ይህንን ሥርዓት ለማሳደግ መላ ሕይወቱን ይከፍላል። ዓለም ይህን የመሰለውን አኗኗር በከፍተኛ ጉጉት ቢከታተልም ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው እንዲህ ያለውን ነገር ሊመኙላቸው ይገባል?—ዮሐንስ 15:19፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
11. አልኮል ከልክ በላይ መጠጣትንና የሥነ ምግባር ብልግናን የመሳሰሉ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ የተለመዱ ተግባራትን በሚመለከት ዘገባዎች ምን ይላሉ?
11 ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በተቋማቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ነው። ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ዕፅ የሚወሰድባቸው፣ አልኮል አለልክ የሚጠጣባቸው፣ የጾታ ብልግናና የማጭበርበር ተግባር የሚፈጸምባቸው፣ የአንድ ቡድን አባል ለመሆን የሚፈልጉ ተማሪዎች መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚገደዱባቸውና ሌሎች መጥፎ ባሕርያት የሚታዩባቸው ቦታዎች እንደሆኑ የታወቀ ነው። እስቲ አልኮል አለመጠን ስለ መጠጣት እንመልከት። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት የመስከር ዓላማ ይዞ ከመጠን በላይ ስለመጠጣት ሲዘግብ “[በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች] መካከል ወደ 44 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ቢያንስ ቢያንስ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ከልክ በላይ ይጠጣሉ” ብሏል። ይህ ችግር በአውስትራሊያ፣ በብሪታንያ፣ በሩስያና በሌሎችም ቦታዎች በሚገኙ ወጣቶች ላይ በስፋት ይታያል። የጾታ ብልግናን በተመለከተ ደግሞ እናንሳ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስለ አንድ ጊዜ ጾታዊ ቅርርብ ሲናገሩ ይሰማሉ፤ እንደ ኒውስዊክ ዘገባ ከሆነ ይህ ነገር “ተራ ትውውቅ ባላቸውና ከዚያ በኋላ የመነጋገር እቅድ እንኳን በሌላቸው ወጣቶች መካከል ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጠር ጾታዊ ቅርርብን የሚያመለክት ሲሆን ከመሳሳም አንስቶ የጾታ ግንኙነት እስከ መፈጸም ያሉትን ድርጊቶች ሊያካትት ይችላል።” ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች እንዲህ ባለው ድርጊት ይካፈላሉ። ጥናት የሚያካሂዱ አንዲት ሴት “እንደማንኛውም የኮሌጅ ተማሪ ከሆንክ በዚህ ድርጊት ትካፈላለህ” ብለዋል።—1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:9, 10
12. የኮሌጅ ተማሪዎች ምን ጫናዎች አሉባቸው?
12 በተቋማቱ ውስጥ ካለው መጥፎ ሁኔታ በተጨማሪ የቤት ሥራና ፈተናዎች የሚፈጥሩት ጫና አለ። ተማሪዎች ፈተናዎችን ለማለፍ ማጥናትና የቤት ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የተረጋገጠ ነው። እንዲሁም አንዳንዶቹ እየተማሩም የትርፍ ሰዓት ሥራ መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማከናወን ጊዜያቸውንና ኃይላቸውን ያሟጥጥባቸዋል። ታዲያ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ምን ያህል ጊዜና ጉልበት ይተርፋቸዋል? ጫና ሲበዛባቸው የቱን ኃላፊነታቸውን ይተዋሉ? የመንግሥቱን ፍላጎቶች ያስቀድማሉ ወይስ ወደ ጎን ገሸሽ ያደርጋሉ? (ማቴዎስ 6:33) መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ” በማለት ክርስቲያኖችን ያስጠነቅቃል። (ኤፌሶን 5:15, 16) አንዳንድ የኮሌጅ ተማሪዎች በትምህርታቸው ምክንያት ጊዜያቸውና ጉልበታቸው በመሟጠጡ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጋጩ ድርጊቶች በመካፈላቸው ሳቢያ ከእምነት መውጣታቸው በጣም ያሳዝናል!
13. ክርስቲያን ወላጆች ሊያስቡባቸው የሚገቡት የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
13 የሥነ ምግባር ብልግና፣ መጥፎ ጠባይና ሌሎች ጫናዎች የሚበዙት በኮሌጅ ወይም በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ብቻ እንዳልሆነ እሙን ነው። ቢሆንም በዓለም የሚገኙ በርካታ ወጣቶች እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተለመዱና ተቀባይነት ያላቸው እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ክርስቲያን ወላጆች ያለውን ሁኔታ እያወቁት ለአራት ዓመት፣ ምናልባትም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ልጆቻቸውን እንዲህ ላለው ነገር ማጋለጥ አለባቸው? (ምሳሌ 22:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22) ወጣቶች ከፍተኛ ትምህርት በመማር የሚያገኙት የትኛውም ጥቅም ያን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባውን ጉዳይ በተመለከተ በኮሌጅ ወይም በዩኒቨርሲቲ ምን የሚያገኙት ትምህርት አለ? a (ፊልጵስዩስ 1:10፤ 1 ተሰሎንቄ 5:21) ወላጆች ስለ እነዚህ ጥያቄዎችና ልጆችን ለትምህርት ወደ ሌላ ከተማ ወይም አገር መላክ ስላለው አደጋ በቁም ነገር በጸሎት ሊያስቡበት ይገባል።
ምን አማራጮች አሉ?
14, 15. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች ካላቸው አመለካከት በተቃራኒ ምን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ይዟል? (ለ) ወጣቶች ራሳቸውን ምን እያሉ መጠየቅ ይችላሉ?
14 በዛሬው ጊዜ ወጣቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ብቸኛ አማራጭ ዩኒቨርሲቲ መማራቸው ነው የሚለው አመለካከት ሰፊ ተቀባይነት አለው። ይሁንና ክርስቲያኖች በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አስተሳሰብ ከመከተል ይልቅ ቀጥሎ የተጠቀሰውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በተግባር ላይ ያውላሉ:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ይሖዋ በዚህ በመጨረሻው ዘመን መገባደጃ ላይ ለወጣቶችም ሆነ በዕድሜ ለገፉ ሕዝቦቹ ያለው ፈቃድ ምንድን ነው? ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም [“ሙሉ በሙሉ ፈጽም፣” NW]” በማለት አሳስቦታል። እነዚህ ቃላት ዛሬ ባለነው ሁሉ ላይ እንደሚሠሩ እሙን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:5
15 ለቁሳዊ ሀብት ትልቅ ግምት በሚሰጠው ዓለም መንፈስ ከመማረክ ይልቅ ሁላችንም ‘በሁኔታዎች ሁሉ የረጋን’ ማለትም መንፈሳዊ አቋማችንን የምንጠብቅ መሆን አለብን። ወጣት ከሆንክ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- “ብቁ የአምላክ ቃል አገልጋይ በመሆን ‘አገልግሎቴን ለመፈጸም’ አቅሜ የፈቀደውን ጥረት አደርጋለሁ? አገልግሎቴን ‘ሙሉ በሙሉ’ ለመፈጸም ምን እቅድ አውጥቻለሁ? የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሥራዬ የማድረግ አሳብ አለኝ?” በተለይ ‘ታላቅ ነገር መሻት’ ብሩህ የወደፊት ተስፋ እንደሚያስገኝላቸው በማሰብ የስስት ፍላጎታቸውን የሚያሳድዱ ወጣቶችን የምትመለከት ከሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ከባድ ሊሆኑብህ ይችላሉ። (ኤርምያስ 45:5) ስለዚህ ጥበበኛ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በቤታቸው ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲኖር በማድረግና ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ያሳድጓቸዋል።—ምሳሌ 22:6፤ መክብብ 12:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
16. ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉት እንዴት ነው?
16 በርካታ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ያሳለፈች እናት ያለችውና ሁለት ታናናሽ ወንድሞች ያሉት አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “እማማ ጓደኞቻችን እነማን እንደሆኑ በቅርብ ትከታተል ነበር። የትምህርት ቤት ጓደኞች አልነበሩንም፤ የምንቀራረበው በጉባኤ ውስጥ ካሉ መንፈሳዊ ልጆች ጋር ብቻ ነበር። እንዲሁም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ማለትም ሚስዮናውያንን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ ቤቴላውያንንና አቅኚዎችን ዘወትር ቤታችን በመጋበዝ እንድንቀራረብ ታደርግ ነበር። ተሞክሯቸውን ማዳመጣችንና ደስታቸውን መመልከታችን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመግባት ፍላጎት ልባችን ውስጥ እንዲተከል ረድቶናል።” በአሁኑ ጊዜ ሦስቱም ልጆች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ መሆኑ ያስደስታል! አንደኛው በቤቴል ውስጥ ያገለግላል፣ ሌላው ደግሞ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተካፈለ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ አቅኚ ነው።
17. ወላጆች ወጣት ልጆቻቸው የሚመርጧቸውን የትምህርት ዓይነቶችና ሥልጠናዎች በተመለከተ እንዴት መመሪያ ሊሰጧቸው ይችላሉ? (በገጽ 29 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት)
17 ወላጆች በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲሰፍን ከማድረግ በተጨማሪ ልጆቻቸው የሚመርጧቸውን የትምህርት ዓይነቶችና የሙያ ሥልጠናዎች በተመለከተ ከወዲሁ አስፈላጊውን መመሪያ መስጠት አለባቸው። አሁን በቤቴል በማገልገል ላይ የሚገኝ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “እናቴና አባቴ ከመጋባታቸው በፊትም ሆነ ከተጋቡ በኋላ አቅኚዎች ሆነው ያገለግሉ የነበረ ሲሆን መላው ቤተሰብ የአቅኚነት መንፈስ እንዲኖረው የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር። የምንማራቸውን ትምህርቶች ስንመርጥም ሆነ የወደፊት ሕይወታችንን የሚነካ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ የጥቂት ሰዓት ሥራ የሚያስገኝና አቅኚዎች ሆነን የማገልገል አጋጣሚ የሚከፍት ምርጫ እንድናደርግ ያበረታቱን ነበር።” ወላጆችም ሆኑ ልጆች ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት የሚያዘጋጁ የቀለም ትምህርቶችን ከመምረጥ ይልቅ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ ለማገልገል ስለሚያመቹ ሥልጠናዎች ማሰብ ይኖርባቸዋል። b
18. ወጣቶች ምን ዓይነት ሥራዎች ስለ መሥራት ሊያስቡ ይችላሉ?
18 በበርካታ አገሮች ውስጥ በጣም የሚፈለጉት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሳይሆኑ የእጅ ሙያተኞችና አገልግሎት ሰጪዎች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ እንደዘገበው “በሚቀጥሉት አሥርተ ዓመታት ከሠራተኛው ኃይል ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በአራት ዓመት ትምህርት የሚገኝ ዲግሪ እንዲኖረው አይጠበቅበትም፤ ከዚያ ይልቅ ከኮሌጆች የሚገኝ ዲፕሎማ ወይም አንድ ዓይነት የሙያ ሰርተፊኬት በቂ ይሆናል።” እነዚህን የመሰሉ በርካታ ተቋማት ለቢሮ ሥራ የሚጠቅሙ ሙያዎችን፣ የመኪና ጥገና፣ የኮምፒውተር ጥገና፣ የቧንቧ ሥራ፣ የፀጉር ሥራና ሌሎችም በርካታ የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ። እነዚህ ሙያዎች ተፈላጊነት አላቸው? እንዴታ! አንዳንዶች የሚያልሙትን ያህል የሚማርኩ አይሁኑ እንጂ ገቢ ያስገኛሉ፤ እንዲሁም ይሖዋን ማገልገልን ዋነኛ ሥራቸው ላደረጉ ሰዎች የሥራ ሰዓታቸውን ለመምረጥና ምን ያህል እንደሚሠሩ ለመወሰን ነፃነት ይሰጧቸዋል።—2 ተሰሎንቄ 3:8
19. በእርግጥ አስደሳችና አርኪ ሕይወት የሚያስገኘው ምንድን ነው?
19 መጽሐፍ ቅዱስ “ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ . . . ስሙ ብቻውን ከፍ ያለ ነውና፣ ክብሩም ከምድርና ከሰማይ በላይ ነውና፣ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ” በማለት ያሳስባል። (መዝሙር 148:12, 13) ዓለም ከሚሰጠው ሥልጣንና የድካም ዋጋ ይልቅ ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ማገልገል አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንደሚያስገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ዋስትና በጭራሽ አትዘንጉ።—ምሳሌ 10:22
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት ይልቅ ለቲኦክራሲያዊ ትምህርት የላቀ ዋጋ የሰጡ ሰዎችን ተሞክሮ በሚከተሉት ጽሑፎች ላይ ማግኘት ትችላለህ። መጠበቂያ ግንብ:- ግንቦት 1, 1982 ከገጽ 3-6 እና ሚያዝያ 15, 1979 ከገጽ 5-10፤ ንቁ! መጽሔቶች:- ሰኔ 8, 1978 ገጽ 15 እና ነሐሴ 8, 1974 ከገጽ 3-7 (ሁሉም የሚገኙት በእንግሊዝኛ ነው።)
b በጥቅምት 8, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 4-6 ላይ የሚገኘውን “አስተማማኝ ሕይወት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት” የሚለውን ርዕስና በግንቦት 8, 1989 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 12-14 ላይ የወጣውን “ምን ዓይነት የሥራ መስክ መምረጥ ይሻለኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ክርስቲያኖች አስተማማኝ የወደፊት ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉት በምን ላይ ነው?
• ወላጆች የልጆቻቸውን የወደፊት ሕይወት በተመለከተ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?
• ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ያለው ትርፍና ኪሳራ በሚሰላበት ጊዜ የትኛው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል?
• ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን ማገልገልን ሥራቸው እንዲያደርጉት መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከፍተኛ ትምህርት ጠቀሜታው ምን ያህል ነው?
ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ብዙ ሰዎች ጥሩ ክፍያና አስተማማኝ ሥራ የሚያስገኝላቸውን ዲግሪ ለመያዝ ይፈልጋሉ። ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ያወጣቸው ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኮሌጅ ከሚገቡት መካከል በስድስት ዓመት ውስጥ ዲግሪ የሚይዘው ከአራቱ አንዱ ብቻ መሆኑን ማወቁ ያሳዝናል። የተመረቁትስ ቢሆኑ ዲግሪያቸው ጥሩ ሥራ ለማግኘት ዋስትና ይሆናቸዋል? በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ምን እንደሚያሳዩ ተመልከት።
“ሃርቫርድም ሆነ ዱክ [ዩኒቨርሲቲ] መማር ጥሩ ሥራና ከፍተኛ ክፍያ በቶሎ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም። . . . ኩባንያዎች ስለሚቀጥሯቸው ወጣት ምሩቃን ብዙም አያውቁም። ውብ የሆነው ዲፕሎማ (አይቪ ሊግ የሚሰጠው ዲግሪ) ይማርክ ይሆናል። በኋላ ግን አንድን ሰው በቀጣሪው ዘንድ ተፈላጊ የሚያደርገው ችሎታው ነው።”—ኒውስ ዊክ፣ ኅዳር 1, 1999
“በአሁኑ ወቅት አንድ ሥራ ካለፉት ጊዜያት የበለጠ ሙያ የሚጠይቅ ቢሆንም . . . ሥራውን ለመሥራት የሚያስፈልጉት ሥልጠናዎች የሚሰጡት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፤ እነርሱም አንድ ሰው ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ የሚማራቸው የሂሳብ፣ የማንበብና የመጻፍ ችሎታዎች . . . እንጂ በኮሌጅ ደረጃ የሚገኙ ሙያዎች አይደሉም። . . . ተማሪዎች ጥሩ ሥራ ለማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሯቸውን ሙያዎች ጠንቅቀው ማወቅ ይገባቸዋል እንጂ ኮሌጅ መግባት አያስፈልጋቸውም።”—አሜሪካን ኤጁኬተር፣ ጸደይ 2004
“ብዙ ኮሌጆች ተማሪዎቻቸው ከተመረቁ በኋላ በሥራው ዓለም ለሚያጋጥማቸው ተጨባጭ ሁኔታ በተገቢው መንገድ አያዘጋጅዋቸውም። የሙያ ትምህርት ቤቶች . . . ያላቸው ተፈላጊነት በፍጥነት እየጨመረ ነው። የተማሪዎቻቸው ቁጥር ከ1996 እስከ 2000 ባለው ጊዜ ውስጥ 48 በመቶ ጨምሯል። . . . በአንጻሩ ግን ለመማር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትና ብዙ ጊዜ የሚፈጁት የኮሌጅ ዲፕሎማዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተፈላጊነታቸው ቀንሷል።”—ታይም፣ ጥር 24, 2005
“የዩናይትድ ስቴትስ የሠራተኛ ጉዳይ አስተዳደር አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በ2005 ቢያንስ ቢያንስ ከሦስት የኮሌጅ ምሩቃን መካከል አንዱ ከዲግሪው ጋር የሚመጣጠን ሥራ ማግኘቱ አጠራጣሪ እንደሚሆን ያለውን ስጋት ገልጿል።”—ዘ ፊውቸሪስት፣ ሐምሌ/ነሐሴ 2000
ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ አስተማሪዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሐሳቦች በመነሳት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት መማር ስላለው ጠቀሜታ ጥርጣሬ እየገባቸው ነው። “ሰዎችን እያስተማርን ያለነው የተሳሳተ ግብ ይዘን ነው” በማለት ፊውቸሪስት ዘግቧል። በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን እንደሚል ተመልከት:- “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”—ኢሳይያስ 48:17, 18
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግል ፍላጎቶቻቸውን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ኢየሱስን ተከትለዋል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በጎ ተጽዕኖ በሚያሳድር መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እንዲያድጉ ያደርጋሉ