በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት ታስተውላለህ?

የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት ታስተውላለህ?

የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት ታስተውላለህ?

በጠና እንዲታመምም ሆነ ድንገተኛ አደጋ እንዲደርስበት የሚፈልግ ሰው የለም። እነዚህ ሁኔታዎች እንዳይደርሱበት የሚፈልግ ጥበበኛ ሰው፣ ችግሩ ሊከሰት መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በንቃት በማጤን ከሁኔታው ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ልናስተውለው የሚገባ አንድ ለየት ያለ ምልክት እንዳለ ገልጿል። ይህ ምልክት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሲሆን አንተንና ቤተሰብህን ጨምሮ መላውን የሰው ዘር ይነካል።

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክፋትን አስወግዶ ምድርን ገነት ስለሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ተናገረ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መንግሥቱ የሚመጣበትን ጊዜ ለማወቅ ስለጓጉ “የመምጣትህና [“የመገኘትህና፣” NW] የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።—ማቴዎስ 24:3

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በሰማይ መሲሐዊ ንግሥናውን ተቀብሎ የሰው ልጆችን መግዛት እስከሚጀምርበት ወቅት ድረስ በርካታ ዘመናት እንደሚያልፉ ያውቅ ነበር። የሰው ልጆች ንግሥናውን በዓይናቸው ሊያዩ ስለማይችሉ ተከታዮቹ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ ‘መገኘቱን’ እንዲሁም “የዓለም መጨረሻ” መድረሱን ለማስተዋል የሚረዳቸውን ምልክት ነግሯቸዋል። ይህ ምልክት የተለያዩ ክስተቶችን ያቀፈ ሲሆን እነዚህ ክስተቶች በአንድነት ሲጣመሩ የኢየሱስን መገኘት ያመለክታሉ።

የወንጌል ጸሐፊዎች የሆኑት ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ኢየሱስ የሰጠውን መልስ በጥንቃቄ አስፍረዋል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21) ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ከምልክቱ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ሰጥተዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ራእይ 6:1-8፤ 11:18) ኢየሱስ ስለጠቀሰው ምልክት በዝርዝር እናብራራ ብንል ቦታ አይበቃንም። ይሁንና ቀጥለን አምስት ጉልህ ክንውኖችን እንመለከታለን። ይህም ትርጉም ያለውና ጠቃሚ ሆኖ እንደምታገኘው እርግጠኞች ነን።—በገጽ 6 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

“አዲስ ምዕራፍ ከፋች”

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” (ማቴዎስ 24:7) በጀርመን የሚታተመው ደር ሽፒገል የተባለው መጽሔት ከ1914 በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ ሰዎች “የወደፊቱ ጊዜ የበለጠ ነጻነት፣ እድገትና ብልጽግና የሚገኝበት ወርቃማ ዘመን እንደሚሆን ይሰማቸው ነበር” ብሏል። በኋላ ላይ ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ። “ነሐሴ 1914 ጀምሮ ኅዳር 1918 ያበቃው ጦርነት አስገራሚ ክስተት ነበር። ጦርነቱ አሮጌውን ከአዲሱ የለየ የታሪክ ምዕራፍ ነበር” ሲል ጂኦ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። በዚህ አረመኔያዊ ጦርነት ከአምስት አህጉራት የተወጣጡ ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወታደሮች ተካፍለዋል። በየቀኑ በአማካይ 6,000 የሚያህሉ ወታደሮች ተገድለዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ትውልዶችና የፖለቲካ ሥርዓቶች የኖሩ የታሪክ ምሑራን “ከ1914 እስከ 1918 ያሉት ዓመታት አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሆኑ” ይናገራሉ።

አንደኛው የዓለም ጦርነት፣ የማይቀለበሱ ማኅበረሰባዊ ለውጦች አስከትሏል፤ የሰው ልጆችንም ወደዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት አሸጋግሯቸዋል። ቀሪው የ20ኛው መቶ ዘመን፣ ጦርነትና ወታደራዊ ግጭት እንዲሁም ሽብርተኝነት የተስፋፋበት በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል። በምንኖርበት ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ላይም ቢሆን ሁኔታዎች አልተሻሻሉም። ጦርነትን ጨምሮ ሌሎች የምልክቱ ገጽታዎች በመታየት ላይ ናቸው።

ረሃብ፣ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ

“ራብ . . . ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:7) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ረሃብ አውሮፓን አጥቅቶ የነበረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሰው ዘር በምግብ እጥረት ሲሰቃይ ኖሯል። የታሪክ ምሑር የሆኑት አለን ቡለክ እንደጻፉት፣ በ1933 በሩሲያና በዩክሬን “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ረሃብተኞች በየገጠሩ ይንከራተቱ ነበር . . . በየመንገዱ ዳር አስከሬን ወድቆ ይታይ ነበር።” ቲዎዶር ሃሮልድ ኋይት የተባሉ ጋዜጠኛ በ1943 የቻይና ግዛት በሆነችው በሄናን ውስጥ ስለተከሰተው ረሃብ እንደሚከተለው ሲሉ ያዩትን ዘግበዋል:- “በረሃብ ጊዜ የማይበላ ነገር የለም ማለት ይቻላል፤ ሁሉም ነገር ይታኘካል፣ ይበላል፣ ሰውነት ደግሞ ወደ ኃይል ይቀይረዋል። ይሁንና አንድ ሰው እሞታለሁ የሚል ፍርሃት ካላደረበት በስተቀር ቀደም ሲል የማይበላውን ነገር ለመብላት አያስብም።” ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ረሃብ የተለመደ ክስተት እየሆነ መምጣቱ ያሳዝናል። ምድር ለሁሉም የሚበቃ እህል የምታበቅል ቢሆንም፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ግምት መሠረት በመላው ዓለም 840 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በምግብ እጥረት ሳቢያ ይሰቃያሉ።

“ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል።” (ሉቃስ 21:11) “በ1918 የተከሰተው የኅዳር በሽታ ከ20 እስከ 50 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይገመታል፤ ይህ ደግሞ ብላክ ዴዝ በተባለው ቸነፈር ወይም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በላይ ነው” ሲል ዙዶይቼ ፃይቱንግ ዘግቧል። ከዚህ ጊዜ አንስቶ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች እንደ ወባ፣ ፈንጣጣ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የልጅነት ልምሻና ኮሌራ በመሳሰሉ በሽታዎች ተጠቅተዋል። የኤድስ ስርጭት አለመገታቱ ዓለማችንን ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏታል። የሕክምናው ዘርፍ አስደናቂ እድገት ያስመዘገበ ቢሆንም እንኳ ለበሽታ መፍትሔ አለመበጀቱ ብዙዎቻችንን ግራ ያጋባ ጉዳይ ሆኗል። የሰው ልጆች እስካሁን ሊፈቱት ያልቻሉት ይህ እንቆቅልሽ በዓይነቱ ልዩ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር በግልጽ ያሳያል።

“የመሬት መንቀጥቀጥ።” (ማቴዎስ 24:7) ባለፉት 100 ዓመታት በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከ1914 ጀምሮ ሕንጻን የማፍረስና መሬትን የመሰንጠቅ ኃይል ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች በየዓመቱ በአማካይ 18 ጊዜ መድረሳቸውን አንድ ምንጭ ገልጿል። አንድን ሕንጻ ሙሉ ለሙሉ የማውደም ኃይል ያላቸው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጦች ደግሞ በዓመት አንዴ ተከስተዋል። ቴክኖሎጂ ቢመጥቅም፣ ፈጣን የሕዝብ እድገት ያላቸው ብዙ ከተሞች የሚገኙት የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያጠቃው አካባቢ መሆኑ በዚህ ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል።

የምሥራች!

የመጨረሻው ዘመን ምልክት አብዛኞቹ ገጽታዎች አስጨናቂ ቢሆኑም እንኳ ኢየሱስ የምሥራች ጨምሮ ተናግሯል።

“ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ የጀመረው የመንግሥቱን ወንጌል የመስበኩ ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ታላቅ ፍጻሜውን ያገኛል። በእርግጥም ይህ ሥራ አሁን በመከናወን ላይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ይሰብካሉ፤ እንዲሁም የተማሩትን በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ያስተምራሉ። በአሁኑ ጊዜ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ወንጌሉን በመስበክ ላይ ይገኛሉ።

ኢየሱስ በዓለም ላይ በሚከሰቱ አስጨናቂ ሁኔታዎች የተነሳ ሕይወት መኖሩን ያቆማል እንዳላለ ልብ በል። ከዚህም በላይ በመላው ዓለም የምልክቱ አንድ ክፍል ብቻ እንደሚታይ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኙ ሰዎች ሊለዩት የሚችሉ በርካታ ክስተቶችን ያቀፈ ምልክት እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል።

በአንድ ክንውን ወይም ክስተት ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውን ጥምር ክንውን ታስተውላለህ? በምድር ላይ የሚከሰቱት ነገሮች በአንተም ሆነ በቤተሰብህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ‘ታዲያ እነዚህን ሁኔታዎች ያስተዋሉት ሰዎች ለምን ጥቂት ሆኑ?’ በማለት እንጠይቅ ይሆናል።

የግል ፍላጎት ሲቀድም

“መዋኘት ክልክል ነው፣” “አደገኛ፣” “በዝግታ ይንዱ።” እነዚህን የመሰሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ዘወትር የምናይ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ትኩረት አይሰጣቸውም። ለምን? ብዙውን ጊዜ ጥቅማችንን ማስቀደም ስለሚቀናን ነው። ለምሳሌ ያህል ሕጉ ከሚፈቅደው የፍጥነት መጠን በላይ ማሽከርከር እንዳለብን ይሰማን ወይም በተከለከለ ሥፍራ የመዋኘት ከፍተኛ ጉጉት ያድርብን ይሆናል። ይሁንና የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ችላ ማለት ጥበብ አይደለም።

ለአብነት ያህል በኦስትሪያ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን እንዲሁም በስዊዘርላንድ በሚገኙት የአልፓይን ተራሮች ለመዝናናት የሚሄዱ ቱሪስቶች የበረዶ ናዳ አደጋ በሚያጋጥምባቸው ሥፍራዎች እንዳይንሸራተቱ የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለታቸው ሕይወታቸውን የሚያጡበት ጊዜ አለ። እንደ ዙዶይቼ ፃይቱንግ ገለጻ እነዚህን መሰል ማስጠንቀቂያዎች ችላ የሚሉ ብዙዎቹ ቱሪስቶች “በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ እስካላለፍክ ድረስ ምኑን ተደሰትከው” የሚል ፈሊጥ አላቸው። ይሁንና ማስጠንቀቂያዎችን ችላ ማለት አሳዛኝ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።

ሰዎች ኢየሱስ ለገለጻቸው ምልክቶች ደንታ ቢስ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? ምናልባት ስግብግብነት አሳውሯቸው፣ ግዴለሽነት አጥቅቷቸው፣ ውሳኔ ላይ መድረስ አቅቷቸው፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቀሴ ፋታ ነስቷቸው ወይም ክብሬን አጣለሁ የሚል ሥጋት አሸንፏቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁኔታዎች የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት ችላ እንድትል አድርገውህ ይሆን? ምልክቱን አስተውሎ ተስማሚውን እርምጃ መውሰድ ጥበብ አይሆንም?

ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ሰዎች የኢየሱስን መገኘት የሚያሳውቀውን ምልክት ማስተዋልና ተስማሚውን እርምጃ መውሰድ ችለዋል። በጀርመን የሚኖር ክሪስቲያን የተባለ አንድ ወጣት ባለ ትዳር “ዘመኑ ተስፋ አስቆራጭ ነው። የምንኖረው ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ መሆኑ አያጠራጥርም” ሲል ጽፏል። እሱና ባለቤቱ ስለ መሲሐዊው መንግሥት ለሌሎች በመንገር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። በዚሁ አገር የሚኖረው ፍራንክ ከባለቤቱ ጋር በመሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች በመናገር ሌሎችን ያበረታታል። ፍራንክ “በዘመናችን ያሉ በርካታ ሰዎች በዓለም ላይ ባሉት ሁኔታዎች የተነሳ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይጨነቃሉ። በመሆኑም በምድር ላይ ስለምትቋቋመው ገነት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በመናገር ሰዎችን ለማጽናናት እንጥራለን” ሲል ተናግሯል። ክሪስቲያንና ፍራንክ የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች በመስበክ፣ የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመው ምልክት አንዱ ገጽታ እንዲፈጸም የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።—ማቴዎስ 24:14

የመጨረሻዎቹ ቀናት ወደ ታላቅ ፍጻሜያቸው ሲደርሱ ኢየሱስ ይህን አሮጌ ሥርዓትና ደጋፊዎቹን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። ከዚያም መሲሐዊው መንግሥት ምድርን ማስተዳደር ይጀምራል፤ እንዲሁም በትንቢት እንደተነገረው ምድርን ወደ ገነትነት ይለውጣል። የሰው ልጆች ከሕመምና ከሞት ነፃ ይሆናሉ፤ ሙታንም ዳግመኛ በምድር ላይ ለመኖር ከሞት ይነሣሉ። የዘመኑን ምልክት የሚያስተውሉ ሁሉ እነዚህ አስደሳች ተስፋዎች ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። አንድ ሰው ስለ ምልክቱ ይበልጥ መማሩና የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ለማለፍ ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቁ ጥበብ ያለበት እርምጃ አይደለም? በእርግጥም ይህ ሁሉም ሰው ሊወስደው የሚገባ አፋጣኝ እርምጃ ነው።—ዮሐንስ 17:3

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኙ ሰዎች ሊለዩት የሚችሉ በርካታ ክስተቶችን ያቀፈ ምልክት እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውን ጥምር ክንውን ታስተውላለህ?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የመጨረሻዎቹ ቀናት መለያ ምልክቶች

ታይቶ የማይታወቅ ጦርነት።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:4

ረሃብ።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:5, 6, 8

ቸነፈር።—ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8

የዓመጽ መብዛት።—ማቴዎስ 24:12

የመሬት መንቀጥቀጥ።—ማቴዎስ 24:7

የጊዜው አስጨናቂ መሆን።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

የገንዘብ ፍቅር።—2 ጢሞቴዎስ 3:2

ለወላጆች አለመታዘዝ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2

የፍቅር መጥፋት።—2 ጢሞቴዎስ 3:3

ከአምላክ ይልቅ ተድላን መውደድ።—2 ጢሞቴዎስ 3:4

ራስን አለመግዛት።—2 ጢሞቴዎስ 3:3

መልካም የሆነውን አለመውደድ።—2 ጢሞቴዎስ 3:3

ያንዣበበውን አደጋ አለማስተዋል።—ማቴዎስ 24:39

በመጨረሻው ዘመን ላይ የምንገኝ መሆኑን የማያምኑ ዘባቾች መነሳት።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4

የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ መሰበክ።—ማቴዎስ 24:14

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የአንደኛው የዓለም ጦርነት ወታደሮች:- ዘ ዎርልድ ዎር —ኤ ፒክቶሪያል ሂስትሪ ከተባለው መጽሐፍ፣ 1919፤ ድሃ ቤተሰብ:- AP Photo/Aijaz Rahi; የልጅነት ልምሻ ተጠቂ:- © WHO/P. Virot