በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና “ነቅታችሁ ጠብቁ”!

የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና “ነቅታችሁ ጠብቁ”!

የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና “ነቅታችሁ ጠብቁ”!

በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች የተመሠረቱት በ2004/05 በዓለም ዙሪያ ተደርገው በነበሩት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በወጣው ነቅተህ ጠብቅ! የተባለ ብሮሹር ላይ ነው።

“ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማቴዎስ 24:42

1, 2. ኢየሱስ የሚመጣበትን ጊዜ ከምን ጋር አመሳስሎታል?

 በሰፈራችሁ ውስጥ አንድ ሌባ ለመዝረፍ እያደባ መሆኑን ብታውቅ ምን ታደርጋለህ? የምትወዳቸውን ሰዎችና ውድ የሆኑ ንብረቶችህን ነቅተህ እንደምትጠብቅ እሙን ነው። ሌባ መቼ እንደሚመጣ የሚገልጽ ደብዳቤ ስለማይልክ በንቃት ትጠብቃለህ። እንዲያውም ሌባ የሚመጣው ድምፁን ሳያሰማና ሳይታሰብ ነው።

2 ኢየሱስ ሌባን በተደጋጋሚ ጊዜያት ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። (ሉቃስ 10:30፤ ዮሐንስ 10:10) ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን እንዲሁም ፍርድ ከመፈጸሙ በፊት የሚከሰቱትን ሁኔታዎች አስመልክቶ እንደሚከተለው በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር።” (ማቴዎስ 24:42, 43) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሚመጣበትን ሁኔታ ሳይጠበቅ ከሚከሰተው የሌባ አመጣጥ ጋር አመሳስሎታል።

3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መምጣቱ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ሰምቶ እርምጃ መውሰድ ምንን ይጨምራል? (ለ) ምን የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

3 ኢየሱስ የሚመጣበት ቀን በትክክል ስለማይታወቅ የተጠቀሰው ምሳሌ ተስማሚ ነበር። ይህን ትንቢት ከመናገሩ ጥቂት ቀደም ብሎ “ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:36) ስለዚህ ያዳምጡት የነበሩትን ሰዎች “ዝግጁ ሁኑ” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 24:44) ኢየሱስ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ የሚመጣው መቼም ይሁን መቼ፣ እርሱ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች በሥርዓት በመመላለስ ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ።

4 ኢየሱስ ማስጠንቀቂያ የሰጠው በዓለም ላሉ ሰዎች ብቻ ነው ወይንስ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ‘ነቅተው መጠበቅ’ አለባቸው? ‘ነቅቶ የመጠበቁ’ ጉዳይ አስቸኳይ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ምንን ይጨምራል? እንደሚሉት ያሉ አንዳንድ አስፈላጊ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ለማን ነው?

5. “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለው ማስጠንቀቂያ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ እንደሚሠራ እንዴት እናውቃለን?

5 የጌታ መምጣት መጪውን ጥፋት በተመለከተ እየተሰጠ ላለው ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ ላሉ የዓለም ሰዎች እንደ ሌባ አመጣጥ ድንገተኛ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ጴጥሮስ 3:3-7) ለእውነተኛ ክርስቲያኖችስ እንዲህ ይሆንባቸዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ “ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ የጌታም ቀን እንዲሁ እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 5:2) ‘የጌታ ቀን እንደሚመጣ’ ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለንም። ይሁንና ይህ ነቅተን የመጠበቃችንን አስፈላጊነት ይቀንሰዋል? ኢየሱስ “የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና” ሲል የተናገረው ለደቀ መዛሙርቱ እንደሆነ ልብ በል። (ማቴዎስ 24:44) ቀደም ሲልም ደቀ መዛሙርቱ ሳያቋርጡ መንግሥቱን እንዲፈልጉ አጥብቆ ባሳሰባቸው ጊዜ “ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር። (ሉቃስ 12:31, 40) ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል ማስጠንቀቂያ በሰጠበት ወቅት ተከታዮቹን በአእምሮው ይዞ እንደነበር ግልጽ አይደለም?

6. ‘ነቅተን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?

6 ‘ነቅተን መጠበቅ’ እና ‘ተዘጋጅተን መጠበቅ’ የሚገባን ለምንድን ነው? ኢየሱስ “ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:40, 41) ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁት ሰዎች የአምላክን ትእዛዝ የማያከብረው ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ ‘ይወሰዳሉ’ ወይም ይድናሉ። የራሳቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ የቆዩ ሌሎች ደግሞ ‘ይቀራሉ’ ወይም ይጠፋሉ። ከእነዚህ መካከል በአንድ ወቅት እውነትን ቢማሩም እንኳ ነቅተው ያልጠበቁ ሰዎች ይገኙ ይሆናል።

7. የመጨረሻውን ቀን አለማወቃችን ምን አጋጣሚ ይሰጠናል?

7 ይህ አሮጌ ሥርዓት የሚጠፋበትን ትክክለኛ ቀን ለይተን አለማወቃችን አምላክን የምናገለግለው በቅን ልቦና ተነሳስተን መሆኑን ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጠናል። እንዴት? መጨረሻው ገና ሊመስል ይችላል። የሚያሳዝነው እንዲህ የሚሰማቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ለይሖዋ አገልግሎት የነበራቸው ቅንዓት ቀዝቅዟል። ይሁን እንጂ ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰንነው ራሳችንን ምንም ሳንቆጥብ በፈቃደኝነት እርሱን ለማገልገል ነው። ይሖዋን የሚያውቁ ሰዎች በመጨረሻው ሰዓት ላይ ቅንዓት ለማሳየት መሯሯጥ አምላክን እንደማያስደስተው ይገነዘባሉ። እርሱ ልብን ያያል።—1 ሳሙኤል 16:7

8. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነቅተን እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

8 ይሖዋን ከልብ ስለምንወደው የእርሱን ፈቃድ መፈጸም ትልቅ ደስታ ይሰጠናል። (መዝሙር 40:8፤ ማቴዎስ 26:39) እንዲሁም ለዘላለም ልናገለግለው እንፈልጋለን። ይህ ተስፋ እኛ ካሰብነው ጊዜ መዘግየቱ ዋጋማነቱን አይቀንሰውም። ነቅተን የምንጠብቅበት ዋነኛው ምክንያት የይሖዋ ቀን ከዓላማው አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚያስገኘውን ውጤት ለማየት ስለምንጓጓ ነው። ይሖዋን ለማስደሰት ያለን ልባዊ ፍላጎት በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ እንድናደርግና በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን እንድናስቀድም ይገፋፋናል። (ማቴዎስ 6:33፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ነቅቶ መጠበቅ በምናደርገው ውሳኔና በዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እስቲ እንመልከት።

ሕይወትህ ወዴት እያመራ ነው?

9. በዓለም የሚገኙ ሰዎች በዘመናችን እየተከሰቱ ያሉትን ነገሮች ትርጉም በአስቸኳይ መረዳት ያለባቸው ለምንድን ነው?

9 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ከባድ ችግሮችና አስደንጋጭ ሁኔታዎች የዕለት ተዕለት ክስተቶች እየሆኑ እንደመጡ ይገነዘባሉ። እንዲሁም ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ አያስደስታቸው ይሆናል። ይሁንና በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች ምን እንደሚያመለክቱ ያውቃሉ? የምንኖረው “የዓለም መጨረሻ” ላይ እንደሆነ ተገንዝበዋል? (ማቴዎስ 24:3) ራስ ወዳድነትና ዓመጽ፣ አልፎ ተርፎም አምላክ የለሽነት መስፋፋቱ “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁም ምልክት መሆኑን አስተውለዋል? (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሰዎች በአስቸኳይ እነዚህን ቁምነገሮች ማወቅና ሕይወታቸው ወዴት እያመራ እንዳለ መገንዘብ ይገባቸዋል።

10. ነቅተን እየጠበቅን መሆናችንን እርግጠኞች ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? በየዕለቱ ከሥራችን፣ ከጤናችን፣ ከቤተሰባችንና ከአምልኳችን ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እናውቃለን፤ የሚለውንም በሥራ ላይ ለማዋል እንጣጣራለን። ስለዚህ ራሳችንን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘የኑሮ ጭንቀት ሕይወቴን በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲመራው ፈቅጃለሁ? የዓለም ፍልስፍናና አስተሳሰብ በማደርገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ፈቅጃለሁ?’ (ሉቃስ 21:34-36፤ ቆላስይስ 2:8) በፍጹም ልባችን በይሖዋ እንደምንታመንና በራሳችን ማስተዋል እንደማንደገፍ ማሳየታችንን መቀጠል ያስፈልገናል። (ምሳሌ 3:5) በዚህ መንገድ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን የዘላለም ሕይወት አጥብቀን መያዝ እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19

11-13. (ሀ) በኖኅ ዘመን (ለ) በሎጥ ዘመን ከተከሰተው ነገር ምን እንማራለን?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ነቅተን እንድንጠብቅ ሊረዱን የሚችሉ በርካታ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ይዟል። እስቲ በኖኅ ዘመን ምን እንደተከሰተ እንመልከት። አምላክ እርምጃ ከመውሰዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ አድርጓል። ሆኖም ከኖኅና ከቤተሰቡ በስተቀር ለማስጠንቀቂያው ትኩረት የሰጠ ሰው አልነበረም። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኢየሱስ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:37-39) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የዚህ ዓለም ሐሳብ ሌላው ቀርቶ የተለመዱ የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴዎች፣ አምላክ ቅድሚያ እንድንሰጣቸው ላሳሰበን መንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ እያሳጡን ከሆነ ያለንበትን ሁኔታ ቆም ብለን መመርመር ይኖርብናል።—ሮሜ 14:17

12 ስለ ሎጥ ዘመንም እናስብ። ሎጥና ቤተሰቡ ይኖሩባት የነበረችው የሰዶም ከተማ በቁሳዊ ሀብት የበለጸገች ብትሆንም በሥነ ምግባር የረከሰች ነበረች። ይሖዋ ከተማይቱን ለማጥፋት መላእክቱን ላከ። መላእክቱ ሎጥና ቤተሰቡ ከሰዶም እንዲሸሹና ወደኋላ ዞረው እንዳይመለከቱ አሳሰቧቸው። ሎጥና ቤተሰቡ መላእክቱ እያደፋፈሯቸው ከተማይቱን ለቅቀው ወጡ። ሆኖም የሎጥ ሚስት በሰዶም ስለነበረው ቤቷ ማሰቧን እንዳላቆመች ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። የተሰጣትን ትእዛዝ ጥሳ ወደኋላ ዞራ በመመልከቷ ሕይወቷን አጥታለች። (ዘፍጥረት 19:15-26) ኢየሱስ “የሎጥን ሚስት አስታውሱ” በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። ይህን ማስጠንቀቂያ እየሠራንበት ነው?—ሉቃስ 17:32

13 መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ሰምተው እርምጃ የወሰዱ ሰዎች ከጥፋት ተርፈዋል። የኖኅና የቤተሰቡ እንዲሁም የሎጥና የልጆቹ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ነው። (2 ጴጥሮስ 2:9) በእነዚያ ጊዜያት ተሰጥተው ስለነበሩት ማስጠንቀቂያዎች ማሰላሰላችን ጽድቅ ወዳድ የነበሩ ሰዎች መዳን እንዳገኙ ስለሚያስገነዝበን እንጽናናለን። ይህም አምላክ “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—2 ጴጥሮስ 3:13

“የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል”!

14, 15. (ሀ) የፍርዱ “ሰዓት” ምንን ያጠቃልላል? (ለ) ‘እግዚአብሔርን መፍራትና ክብር መስጠት’ ምን ይጨምራል?

14 ነቅተን ስንኖር ምን መጠበቅ እንችላለን? የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ዓላማ እንዴት ደረጃ በደረጃ እንደሚፈጸም ይናገራል። ተዘጋጅተን መጠበቅ የምንፈልግ ከሆነ የተጻፈውን ነገር በሥራ ላይ ማዋል እጅግ አስፈላጊ ነው። ትንቢቱ ክርስቶስ በሰማይ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት በ1914 በጀመረው “በጌታ ቀን” ውስጥ የሚፈጸሙ ክንውኖችን ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። (ራእይ 1:10) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ፣ ‘የሚሰብከው የዘላለም ወንጌል’ የተሰጠው አንድ መልአክ በሰማይ መካከል እየበረረ እንዳለ ተገልጾልናል። ይህ መልአክ በታላቅ ድምፅ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል” ሲል ተናግሯል። (ራእይ 14:6, 7) የፍርዱ “ሰዓት” የተባለው አጭር ጊዜ ሲሆን ፍርዱ የሚታወጅበትንና የሚፈጸምበትን ጊዜ እንደሚያጠቃልል በትንቢቱ ላይ ቁልጭ ተደርጎ ተገልጿል። አሁን በዚያ ወቅት ላይ እንገኛለን።

15 ይህ የፍርድ ሰዓት ከማብቃቱ በፊት አሁኑኑ ‘እግዚአብሔርን እንድንፈራና ክብር እንድንሰጠው’ ተመክረናል። ይህ ምንን ይጨምራል? ትክክለኛ አምላካዊ ፍርሃት ከክፉ ነገር እንድንርቅ ሊያነሳሳን ይገባል። (ምሳሌ 8:13) አምላክን የምናከብር ከሆነ የሚሰጠንን ምክርና መመሪያ በጥሞና እንሰማለን። በሌሎች ነገሮች ከልክ በላይ ተጠምደን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ የማንበቡን ጉዳይ ችላ አንልም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ የተሰጠንን ምክር አቅልለን አንመለከትም። (ዕብራውያን 10:24, 25) የአምላክን መሲሐዊት መንግሥት ምሥራች የማወጅ መብታችንን ከፍ አድርገን የምንመለከተው ከመሆኑም በላይ ይህንን ሥራ በቅንዓት እናከናውናለን። ሁልጊዜ በሙሉ ልባችን በይሖዋ እንታመናለን። (መዝሙር 62:8) ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ እንደሆነ ስለምንገነዘብ በሕይወታችን ላይ ሥልጣን እንዳለው አምነን በመቀበል በፈቃደኝነት እንገዛለታለን። እንዲህ በመሰሉ መንገዶች ሁሉ ከልብ አምላክን ትፈራዋለህ? ክብርንስ ትሰጠዋለህ?

16. ታላቂቱ ባቢሎንን በተመለከተ በራእይ 14:8 ላይ የተገለጸው ፍርድ ፍጻሜውን አግኝቷል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

16 የራእይ መጽሐፍ 14ኛ ምዕራፍ በፍርዱ ሰዓት የሚከናወኑ ተጨማሪ ክስተቶችን ይዘረዝራል። በመጀመሪያ፣ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን ታላቂቱ ባቢሎንን በተመለከተ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ሌላም ሁለተኛ መልአክ . . . ‘ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!’ እያለ ተከተለው።” (ራእይ 14:8) አዎን፣ ከአምላክ አመለካከት አንጻር ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃለች። ቅቡዓን የይሖዋ አገልጋዮች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሕዝቦችንና ብሔራትን ባሪያ አድርገው ከኖሩት ባቢሎናዊ የሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች በ1919 ነፃ ወጥተዋል። (ራእይ 17:1, 15) ከዚያ ጊዜ አንስቶ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ራሳቸውን ማቅረብ ችለዋል። እንዲሁም የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሰበክ ቆይቷል።—ማቴዎስ 24:14

17. ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ምን ማድረግን ይጨምራል?

17 ይሁን እንጂ አምላክ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የበየነው ፍርድ በዚህ ብቻ አያበቃም። በቅርቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትጠፋለች። (ራእይ 18:21) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች “በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ . . . ከእርሷ [ከታላቂቱ ባቢሎን] ውጡ” ሲል ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠቱ ተገቢ ነው። (ራእይ 18:4, 5) ከታላቂቱ ባቢሎን የምንወጣው እንዴት ነው? ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር የነበረንን ማንኛውንም ግንኙነት ከማቋረጥ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጨምራል። በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ በርካታ በዓላትና ልማዶች፣ ዓለም ለጾታ ያለው ልቅ አመለካከት፣ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ የመጣው በመዝናኛ መልክ የሚቀርቡ መናፍስታዊ ድርጊቶችና ሌሎችም ነገሮች የባቢሎን ተጽዕኖ አለባቸው። በድርጊታችንም ሆነ በልባችን ምኞት ከታላቂቱ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ እንደተለየን ማሳየታችን ነቅተን ለመኖር የግድ አስፈላጊ ነው።

18. ንቁ ክርስቲያኖች በራእይ 14:9, 10 ላይ በተጠቀሰው መሠረት ምን እንዳያደርጉ ይጠነቀቃሉ?

18 ራእይ 14:9, 10 ስለ “ፍርዱ ሰዓት” ሌላ ገጽታ ይናገራል። አንድ ሌላ መልአክ “ማንም ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ፣ ምልክቱንም በግምባሩ ወይም በእጁ ላይ የሚቀበል ቢኖር፣ እርሱ ደግሞ . . . የእግዚአብሔርን ቊጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል” በማለት ተናገረ። ለምን? ‘አውሬውና ምስሉ’ የይሖዋን ሉዓላዊነት የማይቀበለውን የሰው ልጅ አገዛዝ ይወክላሉ። ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉ ሰዎች ተጽዕኖ አሸንፏቸው በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት ምልክቱን እንዳይቀበሉ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት በሰማይ እንደተቋቋመና ይህ መንግሥት ሰብዓዊ አገዛዞችን በሙሉ በማጥፋት ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ያውቃሉ።—ዳንኤል 2:44

የጥድፊያ ስሜታችሁ እንዳይጠፋ ተጠንቀቁ

19, 20. (ሀ) ወደ መጨረሻው ዘመን ማብቂያ በቀረብን መጠን ሰይጣን ምን ለማድረግ እንደሚሞክር እርግጠኛ መሆን እንችላለን? (ለ) ምን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን?

19 ወደ መጨረሻው ዘመን ማብቂያ በቀረብን መጠን ተጽዕኖውና ፈተናው እያየለ ይሄዳል። በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ እስከኖርን ድረስ ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት የጤና ማጣት፣ የዕድሜ መግፋት፣ ወዳጅ ዘመዶቻችንን በሞት ማጣት፣ ጎጂ ስሜቶች፣ የአምላክን ቃል በምንሰብክበት ጊዜ የሚያጋጥመን የግዴለሽነት ዝንባሌ እና ሌሎችም ብዙ ነገሮች ተጽዕኖ ያደርጉብናል። ሰይጣን እኛን ተስፋ አስቆርጦ ምሥራቹን መስበካችንን እንድናቆም ወይም ደግሞ በአምላክ የአቋም ደረጃዎች መመራታችንን እንድናቋርጥ ለማድረግ እነዚህን ተጽዕኖዎች መጠቀም እንደሚፈልግ በጭራሽ አትዘንጋ። (ኤፌሶን 6:11-13) ያለነው የጥድፊያ ስሜታችንን በምናጠፋበት ወቅት ላይ አይደለም!

20 ኢየሱስ ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርጉ ብዙ ተጽዕኖዎች እንደሚደርሱብን ስለተገነዘበ “ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:42) ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን ነቅተን መኖራችንን እንቀጥል። እውነት ውስጥ ስንመላለስ ቅንዓታችን እንዲቀዘቅዝ ወይም ከነጭራሹ እውነትን እንድንተው ሊያደርጉን የሚችሉትን የሰይጣን ዘዴዎች እንከላከል። በበለጠ ቅንዓት የአምላክን መንግሥት የምሥራች ለመስበክ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለውን የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመታዘዝ የጥድፊያ ስሜታችንን ጠብቀን እናቆይ። እንዲህ ማድረጋችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣለት ከመሆኑም በላይ እርሱ ዘላለማዊ በረከት ከሚያወርሳቸው ሰዎች ተርታ እንድንሰለፍ ያደርገናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ ‘ነቅቶ ስለመጠበቅ’ የሰጠው ማስጠንቀቂያ በክርስቲያኖችም ላይ እንደሚሠራ እንዴት እናውቃለን?

• ‘ነቅተን እንድንጠብቅ’ የሚረዱን የትኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎች ናቸው?

• የፍርዱ ሰዓት ምንድን ነው? ከማለቁስ በፊት እንድናደርጋቸው በጥብቅ የተነገሩን ነገሮች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ፣ የሚመጣበትን ጊዜ ከሌባ አመጣጥ ጋር አመሳስሎታል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታላቂቱ ባቢሎን መጥፊያ ቀርቧል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከምንጊዜውም በበለጠ ቅንዓት ለመስበክ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ