በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕቢተኛ ልብ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ

ትዕቢተኛ ልብ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ

ትዕቢተኛ ልብ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ

“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል።”—ያዕቆብ 4:6

1. ተገቢ የሆነ የኩራት ስሜት እንዲያድርብን ሊያደርግ የሚችል ምሳሌ ጥቀስ።

 ኩራት እንዲሰማህ ያደረገህ በሕይወትህ ውስጥ የምታስታውሰው አጋጣሚ አለ? አብዛኞቻችን እንዲህ እንዲሰማን የሚያደርግ አስደሳች ነገር ገጥሞን ያውቃል። በተወሰነ መጠን ኩራት ቢሰማን ስሕተት አይደለም። ለአብነት ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት ሴት ልጃቸው ጥሩ ባሕርይ እንዳላትና ጎበዝ ተማሪ እንደሆነች የሚገልጽ የትምህርት ቤት ሪፖርት ሲመለከቱ ፊታቸው ላይ የእርካታ ስሜት ይነበብ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ባልደረቦቹ፣ በእነርሱ እርዳታ በተቋቋመ አዲስ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙት ወንድሞች ስደት ቢደርስባቸውም በታማኝነት በመጽናታቸው ኩራት ተሰምቷቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 1:1, 6፤ 2:19, 20፤ 2 ተሰሎንቄ 1:1, 4

2. አብዛኛውን ጊዜ የኩራት ስሜት መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ከላይ ያሉት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ኩራት አንድ ነገር በማድረጋችን ወይም በማግኘታችን የተነሳ የሚሰማንን ደስታ ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ኩራት ስለ ራስ ተገቢ ያልሆነ አመለካከት ማዳበርን ወይም ባለን ችሎታ፣ መልክ፣ ሀብት አሊያም ሥልጣን የተነሳ ከሌሎች እንደምንበልጥ አድርጎ ማሰብን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ኩራት በትዕቢትና በእብሪተኝነት ዝንባሌ ይገለጻል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ያለው የኩራት መንፈስ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ እንደሚኖርብን ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ከመጀመሪያው አባታችን ከአዳም የወረስነው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ስላለን ነው። (ዘፍጥረት 8:21) በዚህም የተነሳ ልባችን ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ኩራት እንዲያድርብን በማድረግ በቀላሉ ሊያስተን ይችላል። ለምሳሌ ክርስቲያኖች በዘራቸው፣ በሀብታቸው፣ በትምህርት ደረጃቸው፣ በተፈጥሮ ችሎታዎቻቸው ወይም በሥራቸው ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ በማሰብ የመኩራት ዝንባሌ እንዳይኖራቸው ሊጠነቀቁ ይገባል። እንደዚህ ባሉት ነገሮች መኩራት ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ይሖዋን ያሳዝነዋል።—ኤርምያስ 9:23፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 4:7፤ ገላትያ 5:26፤ 6:3, 4

3. ትዕቢት ምንድን ነው? ኢየሱስ ስለዚህ ባሕርይ ምን ብሏል?

3 ተገቢ ያልሆነን ኩራት እንድናስወግድ የሚያነሳሳን ሌላም ምክንያት አለ። እንዲህ ያለው የኩራት ስሜት በልባችን ውስጥ እንዲያድግ ከፈቀድንለት ከጊዜ በኋላ በጣም መጥፎ የሆነውን የኩራት ዓይነት ይኸውም የትዕቢትን ባሕርይ እናዳብራለን። ትዕቢት ምንድን ነው? ትዕቢተኛ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ ከመመልከትም አልፎ ከእርሱ ያነሱ እንደሆኑ የሚያስባቸውን ሰዎች ይንቃቸዋል። (ሉቃስ 18:9፤ ዮሐንስ 7:47-49) ኢየሱስ፣ “ከሰው ልብ” ከሚወጡትና ‘ሰውን ከሚያረክሱት’ መጥፎ ባሕርያት መካከል አንዱ “ትዕቢት” እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 7:20-23) ክርስቲያኖች ትዕቢተኛ ልብ እንዳይኖራቸው መጠንቀቃቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ መገንዘብ ይችላሉ።

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትዕቢተኛ ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጹ ምሳሌዎች መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

4 ትዕቢተኛ ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመርህ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳይጠናወትህ ለመከላከል ይረዳሃል። እነዚህን ታሪኮች መመልከትህ ተገቢ ያልሆነ የኩራት ስሜት በውስጥህ መኖር አለመኖሩን ለመለየት ያስችልሃል፤ ከዚህም በላይ ይህ ባሕርይ ከጊዜ በኋላ በልብህ ውስጥ እያደገ የመሄድ አዝማሚያ ካለውም ለማወቅ ይረዳሃል። ይህም ትዕቢተኛ ልብ እንዲኖርህ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ወይም ስሜቶችን ለማስወገድ ይረዳሃል። እንዲህ በማድረግህም፣ አምላክ “በትዕቢታቸው የሚደሰቱትን፣ ከዚህች ከተማ አስወግዳለሁና፤ ከእንግዲህ ወዲያ፣ በቅዱስ ተራራዬ ላይ አትታበዩብኝም” በማለት በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ከጉዳት ትጠበቃለህ።—ሶፎንያስ 3:11

አምላክ በትዕቢተኞች ላይ እርምጃ ይወስዳል

5, 6. ፈርዖን ትዕቢተኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከተለ?

5 ይሖዋ እንደ ፈርዖን ባሉ ኃያል መሪዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ በማየት ስለ ትዕቢት ምን አመለካከት እንዳለው ማወቅ ትችላለህ። ፈርዖን ትዕቢተኛ ልብ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ፈርዖን፣ እርሱ ራሱ ሊመለክ የሚገባው አምላክ እንደሆነ ስለሚያስብ እስራኤላውያን ባሪያዎቹን ይንቃቸው ነበር። እስራኤላውያን ለይሖዋ ‘በዓል ለማድረግ’ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄዱ እንዲፈቅድላቸው ሲጠየቅ ምን ምላሽ እንደሰጠ ተመልከት። በትዕቢት ልቡ ያበጠው ፈርዖን “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር ማነው?” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።—ዘፀአት 5:1, 2

6 ይሖዋ በፈርዖን ላይ ስድስት መቅሰፍቶች ካመጣበት በኋላ ሙሴን በመላክ “እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን?” በማለት ጠየቀው። (ዘፀአት 9:17 የ1954 ትርጉም) ከዚያም ሙሴ ሰባተኛ መቅሰፍት ይኸውም ምድሪቷን የሚያጠፋ የበረዶ ማዕበል እንደሚመጣበት ነገረው። ፈርዖን አሥረኛው መቅሰፍት ከደረሰበትና እስራኤላውያንን እንዲሄዱ ከለቀቃቸውም በኋላ፣ እንደገና ሐሳቡን ቀይሮ ሕዝቡን ማሳደዱን ተያያዘው። በመጨረሻም ፈርዖንና ሠራዊቱ ቀይ ባሕር ውስጥ ገብተው መውጣት አቃታቸው። ባሕሩ በላያቸው ላይ ሲደረመስባቸው ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አስበው! የፈርዖን ትዕቢት ምን አስከተለ? ምርጥ የሆኑት ወታደሮቹ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብፅን እየተዋጋላቸው ነው” በማለት ተናግረዋል።—ዘፀአት 14:25

7. የባቢሎን ነገሥታት ትዕቢተኞች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

7 ሌሎች ትዕቢተኛ መሪዎችም በይሖዋ እጅ ውርደት ተከናንበዋል። የአሦር ንጉሥ የነበረው ሰናክሬም ከእነዚህ መካከል የሚጠቀስ ነው። (ኢሳይያስ 36:1-4, 20፤ 37:36-38) ከጊዜ በኋላ አሦር በባቢሎናውያን እጅ ወደቀች። ሆኖም ትዕቢተኛ የነበሩ ሁለት የባቢሎን ነገሥታትም እንዲሁ ውርደት ደርሶባቸዋል። ንጉሥ ቤልሻዛር ባደረገው ግብዣ ላይ ከመኳንንቶቹ ጋር ሆኖ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ በተወሰዱ ዕቃዎች ወይን ጠጅ እየጠጣ የባቢሎንን አማልክት ያወደሰበትን ጊዜ አስታውስ። በድንገት የሰው እጅ ጣቶች ታዩና በግድግዳው ላይ አንድ መልእክት ጻፉ። ነቢዩ ዳንኤል ምስጢራዊውን ጽሑፍ እንዲያብራራ ሲጠየቅ ቤልሻዛርን እንዲህ አለው:- “ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትን . . . ሰጠው። . . . ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸና . . . ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ። . . . ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም።” (ዳንኤል 5:3, 18, 20, 22) በዚያች ሌሊት የሜዶ ፋርስ ሠራዊት ባቢሎንን ድል ያደረገ ሲሆን ቤልሻዛርም ተገደለ።—ዳንኤል 5:30, 31

8. ይሖዋ ትዕቢተኛ በነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች ላይ ምን እርምጃ ወስዷል?

8 የይሖዋን ሕዝቦች ይጠሉ ከነበሩ ሌሎች ትዕቢተኛ ሰዎች መካከል የግዙፉን ፍልስጥኤማዊ የጎልያድን፣ የፋርሱን ጠቅላይ ሚኒስትር የሐማን እንዲሁም የይሁዳ ገዢ የነበረውን የንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳን ሁኔታ ተመልከት። እነዚህ ሦስት ሰዎች ትዕቢተኞች ስለነበሩ በአምላክ እጅ ተዋርደው ሞተዋል። (1 ሳሙኤል 17:42-51፤ አስቴር 3:5, 6፤ 7:10፤ የሐዋርያት ሥራ 12:1-3, 21-23) ይሖዋ በእነዚህ ትዕቢተኛ ሰዎች ላይ የወሰደው እርምጃ “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” የሚለውን ሐቅ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ምሳሌ 16:18) በእርግጥም ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚቃወም’ ምንም ጥርጥር የለውም።—ያዕቆብ 4:6

9. የጢሮስ ነገሥታት ከሃዲዎች የሆኑት እንዴት ነው?

9 ትዕቢተኛ ከነበሩት የግብፅ፣ የአሦርና የባቢሎን ገዥዎች በተቃራኒ የጢሮስ ንጉሥ በአንድ ወቅት የአምላክን ሕዝቦች ረድቷቸዋል። በንጉሥ ዳዊትና በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን፣ የጢሮስ ንጉሥ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የእጅ ሞያተኞችን እንዲሁም ቤተ መንግሥቱንና የአምላክን ቤተ መቅደስ ለመገንባት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ልኮላቸዋል። (2 ሳሙኤል 5:11፤ 2 ዜና መዋዕል 2:11-16) የሚያሳዝነው ግን ከጊዜ በኋላ የጢሮስ ነገሥታት የይሖዋን ሕዝቦች ለማጥቃት ተነሱ። እንዲህ ያደረጉት ለምን ነበር?—መዝሙር 83:3-7፤ ኢዩኤል 3:4-6፤ አሞጽ 1:9, 10

“ልብህ ታበየ”

10, 11. (ሀ) ከጢሮስ ነገሥታት ጋር የተነጻጸረው ማን ነው? (ለ) የጢሮስ ነገሥታት ለእስራኤላውያን የነበራቸው አመለካከት እንዲቀየር ያደረገው ምንድን ነው?

10 ይሖዋ ሕዝቅኤል የተባለውን ነቢይ በመንፈሱ በማነሳሳት የጢሮስን ነገሥታት እንዲያጋልጣቸውና እንዲያወግዛቸው አድርጓል። “ስለ ጢሮስ ንጉሥ” የተነገረው ይህ መልእክት፣ የጢሮስን ነገሥታት ብቻ ሳይሆን “በእውነት አልጸናም” የተባለለትን የመጀመሪያውን ከሃዲ የሰይጣንን ሁኔታ በትክክል የሚገልጹ ሐሳቦችም ይዟል። (ሕዝቅኤል 28:12፤ ዮሐንስ 8:44) በአንድ ወቅት ሰይጣን በሰማይ የሚገኙትን የይሖዋን ልጆች ባቀፈው ድርጅት ውስጥ የሚያገለግል ታማኝ መንፈሳዊ ፍጡር ነበር። ይሖዋ አምላክ በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት ባስነገረው መልእክት ላይ የጢሮስ ነገሥታትም ሆኑ ሰይጣን ከሃዲ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን መሠረታዊ ምክንያት ጠቁሟል:-

11 “በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ፣ በዔድን ነበርህ፤ እያንዳንዱ የከበረ ድንጋይ አስጊጦህ ነበር፤ . . . ጠባቂ ኪሩብ ሆነህ ተቀብተህ ነበር፤ . . . ከተፈጠርህበት ቀን ጀምሮ፣ ክፋት እስከ ተገኘብህ ድረስ፣ በመንገድህ ነቀፌታ አልነበረብህም። ንግድህ ስለ ደረጀ፣ በዐመፅ ተሞላህ፣ ኀጢአትም ሠራህ፤ . . . ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፤ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አስወጣሁህ። በውበትህ ምክንያት፣ ልብህ ታበየ፤ ከክብርህ ታላቅነት የተነሣም፣ ጥበብህን አረከስህ።” (ሕዝቅኤል 28:13-17) በእርግጥም የጢሮስ ነገሥታት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ዓመጽ እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸው ትዕቢት ነበር። የንግድ ማዕከል የነበረችው ጢሮስ እጅግ ከመበልጸጓም በላይ ማራኪ የሆኑ ምርቶቿ ስመ ጥር አድርገዋት ነበር። (ኢሳይያስ 23:8, 9) የጢሮስ ነገሥታት በጣም እብሪተኞች ከመሆናቸው የተነሳ የአምላክን ሕዝቦች መጨቆን ጀመሩ።

12. ሰይጣን የክህደትን ጎዳና ወደመከተል የመራው ምንድን ነው? አሁንም ምን ማድረጉን አልተወም?

12 በተመሳሳይም፣ በኋላ ሰይጣን የሆነው መንፈሳዊ ፍጡር በአንድ ወቅት አምላክ የሰጠውን ማንኛውንም ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ነበረው። ሆኖም አመስጋኝ ከመሆን ይልቅ “በትዕቢት ተነፍቶ” የአምላክን አመራር መናቅ ጀመረ። (1 ጢሞቴዎስ 3:6) ስለ ራሱ ከሚገባው በላይ ማሰቡ አዳምና ሔዋን እርሱን እንዲያመልኩት ወደ መመኘት መራው። ይህ ክፉ ምኞት በውስጡ በመፀነሱ ኃጢአት ተወለደ። (ያዕቆብ 1:14, 15) ሰይጣን አምላክ ከከለከለው ብቸኛው ዛፍ ፍሬ እንድትበላ ሔዋንን አሳታት። ከዚያም በሔዋን በመጠቀም አዳም የተከለከለውን ፍሬ እንዲበላ አደረገው። (ዘፍጥረት 3:1-6) በዚህ መንገድ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አምላክ በእነርሱ ላይ የነበረውን የመግዛት መብት ለመቀበል አሻፈረን አሉ፤ በሌላ አባባል የሰይጣን አምላኪዎች ሆኑ። የሰይጣን ትዕቢት ግን ለከት አልነበረውም። ኢየሱስ ክርስቶስን ጨምሮ በሰማይም ሆነ በምድር የሚኖሩትን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ በማታለል የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት እንዳይቀበሉ ለማድረግና እርሱን እንዲያመልኩት ለመገፋፋት ሲሞክር ቆይቷል።—ማቴዎስ 4:8-10፤ ራእይ 12:3, 4, 9

13. ትዕቢት ምን አስከትሏል?

13 ከዚህ መመልከት እንደምትችለው የትዕቢት ምንጭ ሰይጣን ሲሆን ዛሬ በዓለም ላይ የምንመለከተው ኃጢአት፣ ሥቃይና መከራ እንዲሁም ሙስና ዋና መንስኤ ደግሞ ትዕቢት ነው። “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ተገቢ ያልሆነ የኩራትና የትዕቢት ዝንባሌን ለማስፋፋት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ስለሚያውቅ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ጦርነት አውጆአል። ዓላማው እነርሱን ከአምላክ ማራቅና ራሳቸውን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞችና ትዕቢተኞች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን” እንደዚህ ያለው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ በሰፊው እንደሚታይ አስቀድሞ ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2፤ ራእይ 12:12, 17

14. ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጡራኖቹ ጋር ላለው ግንኙነት መሠረት የሚሆነው ሕግ የትኛው ነው?

14 ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣን ትዕቢት ያስከተለውን መጥፎ ውጤት በድፍረት አጋልጧል። ኢየሱስ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ጠላቶቹ በተገኙበት ቢያንስ ሦስት ጊዜ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል” በማለት ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ላለው ግንኙነት መሠረት የሚሆነውን ሕግ ገልጿል።—ሉቃስ 14:11፤ 18:14፤ ማቴዎስ 23:12

ትዕቢተኛ ልብ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ

15, 16. አጋር እንድትታበይ ያደረጋት ምን ነበር?

15 ከላይ እንደ ምሳሌ የተገለጹት ትዕቢተኛ ሰዎች ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው መሆናቸውን አስተውለህ ይሆናል። ይህ ሲባል ተራ የሆኑ ሰዎች የትዕቢት ዝንባሌ ሊጠናወታቸው አይችልም ማለት ነው? አይደለም። በአብርሃም ቤተሰብ ውስጥ የተፈጸመውን አንድ ክንውን ተመልከት። አብርሃም ወራሽ የሚሆነው ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ሚስቱ ሣራ ደግሞ ልጅ መውለድ የምትችልበት ዕድሜ አልፏል። በወቅቱ የአብርሃም ዓይነት ሁኔታ የገጠመው ሰው ሁለተኛ ሚስት አግብቶ ልጆች መውለዱ የተለመደ ነገር ነበር። አምላክ መጀመሪያ ላይ ለጋብቻ ያወጣውን ሥርዓት ለእውነተኛ አገልጋዮቹ እንደገና የሚያስተላልፍበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ እንዲህ ያለውን ጥምረት ይፈቅድ ነበር።—ማቴዎስ 19:3-9

16 የአብርሃም ሚስት ሣራ፣ ግብፃዊት ከሆነችው አገልጋይዋ ወራሽ ሊሆን የሚችል ልጅ እንዲወልድ ለባሏ ሐሳብ ያቀረበችለት ሲሆን አብርሃምም በጉዳዩ ተስማማ። አጋር የአብርሃም ሁለተኛ ሚስት በመሆን ፀነሰችለት። አጋር እንዲህ ያለ ክብር በማግኘቷ አመስጋኝ ልትሆን ይገባት ነበር፤ እርሷ ግን ልቧ እንዲታበይ ፈቀደች። መጽሐፍ ቅዱስ “አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች” ይላል። ይህ አመለካከቷ በአብርሃም ቤተሰብ ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር በማድረጉ ሣራ አጋርን አባረረቻት። ሆኖም ችግሩ መፍትሔ ነበረው። የአምላክ መልአክ አጋርን “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእርሷም ተገዥላት” የሚል ምክር ለገሳት። (ዘፍጥረት 16:4, 9) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው አጋር ይህንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ለሣራ የነበራትን አመለካከት በማስተካከሏ ከእርሷ ታላቅ ሕዝብ ሊገኝ ችሏል።

17, 18. ማንኛችንም ብንሆን የትዕቢት ዝንባሌ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

17 የአጋር ታሪክ አንድ ሰው ሁኔታው ሲሻሻል ሊታበይ እንደሚችል ያሳያል። ይህ ዘገባ አምላክን በማገልገል ረገድ ጥሩ ልብ የነበረው ክርስቲያንም እንኳ ሀብት ወይም ሥልጣን ሲያገኝ ሊታበይ እንደሚችል ትምህርት ይሰጠናል። ባገኘው ስኬት፣ በማስተዋሉ ወይም በችሎታው ሌሎች ሲያደንቁትም እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ሊያዳብር ይችላል። በእርግጥም አንድ ክርስቲያን በተለይ ደግሞ ሁኔታዎች ሲሳኩለት አሊያም የበለጠ ኃላፊነት ሲያገኝ ልቡ እንዳይታበይ መጠንቀቅ አለበት።

18 ትዕቢትን እንድናስወግድ ሊያነሳሳን የሚገባው ከሁሉ የላቀው ምክንያት አምላክ ለዚህ ባሕርይ ያለው አመለካከት ነው። ቃሉ “ትዕቢተኛ ዐይን፣ እብሪተኛ ልብ፣ የክፉዎችም መብራት ኀጢአት ናቸው” ይላል። (ምሳሌ 21:4) መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ “በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑ” ክርስቲያኖችን “እንዳይታበዩ” የሚያስጠነቅቅ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:17፤ ዘዳግም 8:11-17) ሀብታም ያልሆኑ ክርስቲያኖችም ‘ምቀኝነትን’ ማስወገድ አለባቸው፤ እንዲሁም ሀብታም ድሃ ሳይል ማንኛውም ሰው የትዕቢት ዝንባሌ ሊጠናወተው እንደሚችል ማስታወስ ይኖርባቸዋል።—ማርቆስ 7:21-23፤ ያዕቆብ 4:5

19. ዖዝያን መልካም ስሙን ያበላሸው እንዴት ነው?

19 ትዕቢት ከሌሎች መጥፎ ባሕርያት ጋር ተዳምሮ ከይሖዋ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽብን ይችላል። ለምሳሌ ንጉሥ ዖዝያን መግዛት እንደጀመረ አካባቢ የነበረውን አመለካከት እንይ። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እርሱም . . . በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። . . . እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።” (2 ዜና መዋዕል 26:4, 5) የሚያሳዝነው ግን ንጉሥ ዖዝያን “ዕብሪቱ ለውድቀት [እንዲዳርገው]” በመፍቀዱ የነበረው መልካም ስም ተበላሸ። በትዕቢት በመነሳት ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። ካህናቱ ይህን የእብሪት ኃጢአት ከመፈጸም እንዲታቀብ ሲያስጠነቅቁት “ዖዝያን ተቈጣ።” በዚህም የተነሳ ይሖዋ በለምጽ መታው፤ የአምላክን ሞገስ እንዳጣ ወደ መቃብሩ ወረደ።—2 ዜና መዋዕል 26:16-21

20. (ሀ) የንጉሥ ሕዝቅያስ መልካም ስም አደጋ ላይ የወደቀው እንዴት ነበር? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

20 ይህንን ታሪክ ከንጉሥ ሕዝቅያስ ምሳሌ ጋር ማወዳደር ትችላለህ። ይህ ንጉሥ በአንድ ወቅት ‘ልቡ በመታበዩ’ የነበረው መልካም ስም ሊጎድፍ ነበር። የሚያስደስተው ግን ‘ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን በማዋረዱ’ የአምላክን ሞገስ እንደገና ማግኘት ችሏል። (2 ዜና መዋዕል 32:25, 26) ሕዝቅያስ የትዕቢት ዝንባሌውን ያስተካከለው በትሕትና መሆኑን ልብ በል። አዎን፣ ትሕትና የትዕቢት ተቃራኒ ነው። እንግዲያው በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ክርስቲያናዊ ትሕትናን እንዴት ማዳበር እንደምንችል እንዲሁም ይህ ባሕርይ እንዳይጠፋብን ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።

21. ትሑት ክርስቲያኖች የትኛውን ጊዜ በጉጉት መጠበቅ ይችላሉ?

21 ትዕቢት የሚያስከትላቸውን መጥፎ ውጤቶች ፈጽሞ አንዘንጋ። ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ስለሚቃወም’ ተገቢ ያልሆነ የኩራት ዝንባሌን ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ትሑት ክርስቲያኖች ለመሆን ጥረት ካደረግን ትዕቢተኞችና ሥራዎቻቸው ከምድር ገጽ ላይ ተጠራርገው ከሚጠፉበት ከታላቁ የአምላክ ቀን እንደምንተርፍ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በዚያን ጊዜ “የሰው እብሪት ይዋረዳል፤ የሰውም ኵራት ይወድቃል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል።”—ኢሳይያስ 2:17

ለማሰላሰል የሚረዱ ነጥቦች

• ትዕቢተኛን ሰው እንዴት ትገልጸዋለህ?

• የትዕቢት ምንጭ ማን ነው?

• አንድ ሰው እንዲታበይ ሊያደርገው የሚችለው ምንድን ነው?

• ትዕቢተኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፈርዖን ትዕቢት ውርደት አስከትሎበታል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጋር የነበረችበት ሁኔታ መሻሻሉ እንድትታበይ አድርጓታል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቅያስ ትሑት በመሆን የይሖዋን ሞገስ እንደገና ማግኘት ችሏል