በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳካ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ትምህርት ነው?

የተሳካ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ትምህርት ነው?

የተሳካ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ትምህርት ነው?

ከባድ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውህ የማትወጣበት ማጥ ውስጥ የገባህ ያህል ተሰምቶህ ያውቃል? ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱን ወይም ሌላውን ለመፍታት ስትጥር ደግሞ ሌላ ስህተት ብትሠራ ምን ያህል ሥቃይ ሊገጥምህ እንደሚችል አስብ! በማንኛውም ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔዎችን በማድረግ ሁሉንም ዓይነት ችግሮች በተሳካ መንገድ የመፍታት ችሎታ ኖሮት የተወለደ ሰው የለም። ይህ ደግሞ የትምህርትን አስፈላጊነት ያጎላል። ይሁን እንጂ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ትምህርት ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ብዙዎች፣ በዕድሜ የገፉም ሆኑ ወጣቶች የቀለም ትምህርት ያለውን ጥቅም ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። አንዳንድ ምሁራን “የኮሌጅ ዲግሪ ከሌለህ ደህና ሥራ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው” ብለው እስከመናገር ደርሰዋል። ሆኖም ቁሳዊ ስኬት የሰው ልጅ ፍላጎቶችን በሙሉ ማሟላት አይችልም። ለምሳሌ ከፍተኛ ትምህርት ጥሩ ወላጅ፣ የትዳር ጓደኛ አሊያም ጥሩ ወዳጅ እንድትሆን ያደርጋል? እንዲያውም በትምህርት ደረጃቸው የብዙዎችን አድናቆት ያተረፉ ሰዎች መጥፎ ባሕርይ ሊኖራቸውና የቤተሰብ ሕይወታቸው ሊበላሽ የሚችል ከመሆኑም ሌላ ሕይወታቸውን እስከማጥፋት የደረሱም አሉ።

ሌሎች ደግሞ መመሪያ ለማግኘት ሲሉ ፊታቸውን ወደ ሃይማኖት ዞር ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ስለማያገኙ ተስፋ ይቆርጣሉ። ለምሳሌ በሜክሲኮ የምትኖረው ኤሚልያ a እንዲህ ትላለች:- “ከ15 ዓመት በፊት እኔና ባለቤቴ አብረን መኖር እንደማንችል ተሰምቶኝ ነበር። ነጋ ጠባ እንጨቃጨቃለን። መጠጥ እንዲያቆም ማድረግ አልቻልኩም። ትንንሽ ልጆቻችንን ለብቻቸው ጥዬ እርሱን ፍለጋ የወጣሁባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። በወቅቱ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ይደርስብኝ ነበር። ምናልባት መፍትሔ ባገኝ ብዬ በተደጋጋሚ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄጃለሁ። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ የሚጠቀስ ቢሆንም የእኔን ችግር በተመለከተ የተሰጠ ምክር ግን ሰምቼ አላውቅም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ቀርቦ የነገረኝም የለም። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ተቀምጬ የተወሰኑ ጸሎቶችን ደግሜ መሄዱ እርካታ አላስገኘልኝም።” ሌሎች ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቻቸው ምሳሌ ሆነው ባለመገኘታቸው ስሜታቸው በጣም ይጐዳል። በመጨረሻም ሕይወትን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል ትምህርት ወይም ሥልጠና ከሃይማኖት ማግኘት እንደማይችሉ ተሰምቷቸው ብዙዎች በሃይማኖት ላይ የነበራቸውን እምነት ያጣሉ።

ስለዚህ ‘ሕይወቴን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለመምራት መማር ያለብኝ ምን ዓይነት ትምህርት ነው?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። እውነተኛ ክርስትና ለዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ መልስ ይሰጣል? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተቀይሯል።