ይሖዋ በፍጹም አይተውህም
ይሖዋ በፍጹም አይተውህም
በይሁዳ የሚኖሩት ክርስቲያኖች የሚደርስባቸውን ኃይለኛ ተቃውሞ እንዲሁም በአካባቢያቸው የነበሩት በፍቅረ ንዋይ ላይ ያተኮረ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሚያሳድሩባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም አስፈልጓቸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ ይሖዋ የተናገረውን “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” የሚለውን ሐሳብ በመጥቀስ እነዚህን ክርስቲያኖች አበረታቷቸዋል። (ዕብራውያን 13:5፤ ዘዳግም 31:6) ይህ ተስፋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን እንዳጠናከራቸው አያጠራጥርም።
ይኸው ተስፋ ያለንበት “የሚያስጨንቅ ጊዜ” የሚያመጣቸውን ጭንቀቶች እንድንቋቋም ይረዳናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በይሖዋ ከታመንንና በእርሱ እንደምንታመን በሚያሳይ መንገድ ከተመላለስን በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ሳይቀር ብርታት እናገኛለን። ይሖዋ ይህንን ቃሉን እንዴት እንደሚፈጽመው ለማየት መተዳደሪያ ሥራቸውን በድንገት ያጡ ሰዎችን ምሳሌ እንመልከት።
ያልተጠበቀ ሁኔታ ሲፈጠር
በዓለም ዙሪያ የሥራ አጦች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። ሥራ አጥነት “በጣም ከባድ ከሆኑት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንዱ” እንደሆነ አንድ የፖላንድ መጽሔት ገልጿል። የበለጸጉ አገሮችም ከዚህ ችግር አላመለጡም። ለምሳሌ፣ በኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ድርጅት አባላት መካከል እንኳ በ2004 የሥራ አጦች ቁጥር “ከ32 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህም በ1930ዎቹ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ከነበረው ቁጥር ይበልጣል።” በፖላንድ የሚገኘው ማዕከላዊ የስታትስቲክስ ቢሮ በታኅሣሥ 2003 ላይ ሦስት ሚሊዮን የሚያህሉ ሥራ አጦችን የመዘገበ ሲሆን “ይህም ማለት መሥራት በሚችልበት ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ሕዝብ 18 በመቶ የሚሆነው ሥራ አጥ ነው ማለት ነው።” በ2002 ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን መካከል 47.8 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጦች መሆናቸውን አንድ ምንጭ ገልጿል።
በድንገት ሥራ አጥ መሆንና ያልተጠበቀ የሥራ ቅነሳ የይሖዋ አገልጋዮችን ጨምሮ ብዙዎችን ሥጋት ላይ ጥሏል። “ጊዜና ዕድል [“አጋጣሚ፣” NW]” የሚያስከትሉት ችግር በማንኛውም ሰው ላይ ሊደርስ ይችላል። (መክብብ 9:11) ምናልባት እኛም እንደ መዝሙራዊው “የልቤ መከራ በዝቶአል” እንል ይሆናል። (መዝሙር 25:17) እንደዚህ የመሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችል ይሆን? ያጋጠመህ ችግር ስሜትህንና መንፈሳዊነትህን ሊነካ እንዲሁም በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሊጎዳህ ይችላል። ከሥራ ብትባረር ወደ ቀድሞው ሁኔታህ መመለስ ትችል ይሆን?
ስሜታዊ ውጥረትን መቋቋም
ያኑሽ ቪትዚንስኪ የተባሉ የሥነ ልቦና ጠበብት በባህሉ መሠረት ወንዶች የቤተሰቡ አስተዳዳሪ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ “ሥራ ማጣት ይበልጥ የሚጎዳው እነሱን ነው” ብለዋል። ግለሰቡ ከሥራ በመባረሩ ምክንያት “ከፍተኛ የስሜት ውጥረት ሊያጋጥመው ይችላል።” ከሥራ የተባረረ አንድ አባት ለራሱ ያለው ግምት ሊቀንስና “ከቤተሰቡ ጋር መጋጨት” ሊጀምር ይችላል።
ሁለት ልጆች ያሉት አዳም የተባለ አንድ ክርስቲያን አባት ሥራውን ባጣበት ወቅት ምን እንደተሰማው ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በቀላሉ የምረበሽ ሰው ሆንኩ፤ ሁሉ ነገር ያበሳጨኝ ጀመር። በዚያን ወቅት ባለቤቴም ሳይታሰብ ከሥራ ተቀንሳ ስለነበር በሕልሜ የማየው ሁሉ ስለ ሥራ እንዲሁም ለልጆቼና ለባለቤቴ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ ስለምችልበት መንገድ ነበር።” አንዲት ሴት ልጅ ያለቻቸው ሪሻርድና ማሪኦላ የተባሉ ባልና ሚስት የገቢያቸውን ምንጭ ባጡበት ወቅት ውዝፍ የባንክ ዕዳ ነበረባቸው። ሚስትየዋ እንዲህ ትላለች:- “ሁልጊዜ እጨነቅ ነበር፤ መበደራችን ትክክል እንዳልነበረ ሳስብ ሕሊናዬ ይወቅሰኝ ነበር። የእኔ ጥፋት እንደሆነ አስብ ነበር።” እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በቀላሉ ንዴት፣ ጭንቀት ወይም ምሬት ሊሰማን እንዲሁም ስሜታችንን መቆጣጠር ሊያቅተን ይችላል። ታዲያ መጥፎ ስሜቶችን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ገንቢ አመለካከት መያዝ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ውጤታማ ምክር ይሰጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ወደ ይሖዋ በጸሎት በምንቀርብበት ጊዜ “የእግዚአብሔር ሰላም” ይኖረናል፤ ይህም ሲባል በእርሱ ላይ እምነት ስላለን አእምሯችን ይረጋጋል ማለት ነው። የአዳም ሚስት የሆነችው ኢሬና እንዲህ ትላለች:- “በጸሎታችን ላይ ስላለንበት ሁኔታና አኗኗራችንን ከዚህ የበለጠ ለማቅለል ምን እንደምናደርግ ለይሖዋ ነገርነው። በትንሽ በትልቁ ይጨነቅ የነበረው ባለቤቴ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚገኝ ማሰብ ጀመረ።”
ሥራህን በድንገት አጥተህ ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ላይ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ የማድረግ አጋጣሚ አለህ:- “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። . . . ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።” (ማቴዎስ 6:25, 33) ሪሻርድና ማሪኦላ ይህንን ምክር በተግባር ማዋላቸው ስሜታቸውን ለማረጋጋት አስችሏቸዋል። ማሪኦላ “ባለቤቴ ሁልጊዜ ያጽናናኛል፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደማይጥለን አጠንክሮ ይነግረኝ ነበር” ብላለች። ባለቤቷም አክሎ “አብረን የምናቀርበው የማያቋርጥ ጸሎት ወደ አምላክ ለመቅረብና እርስ በርሳችንም ለመቀራረብ አስችሎናል፤ ይህ ደግሞ የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ሰጥቶናል” በማለት ተናግሯል።
የአምላክ ቅዱስ መንፈስም ችግሮቻችንን ለመቋቋም ይረዳናል። ይህ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናፈራ የሚረዳን ሲሆን ይህ ባሕርይ እንድንረጋጋ ያስችለናል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህን ማድረጉ ቀላል ባይሆንም ኢየሱስ “የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ” በማለት ቃል ስለገባ የማይቻል ነገር አይደለም።—ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15
መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ችላ አትበል
ከሥራ ሳይታሰብ መፈናቀል በጣም ሚዛናዊ ለሆነ ክርስቲያን እንኳ መጀመሪያ ላይ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ቢችልም መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን ችላ ማለት የለብንም። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ በ40 ዓመቱ በመኳንንት መካከል የነበረውን ቦታ ባጣ ጊዜ ሕይወቱ ተለውጦ ግብጻውያን ይንቁት በነበረው የእረኝነት ሥራ ተሰማራ። (ዘፍጥረት 46:34) ሙሴ ራሱን ካጋጠመው ለውጥ ጋር ማስማማት ነበረበት። በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ውስጥ ይሖዋ በፊቱ ላለው አዲስ ሥራ እንዲያዘጋጀውና እንዲቀርጸው ፈቅዷል። (ዘፀአት 2:11-22፤ የሐዋርያት ሥራ 7:29, 30፤ ዕብራውያን 11:24-26) ሙሴ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ሥልጠና ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። እንግዲያው አስቸጋሪ ሁኔታዎች መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ እንድንል እንዲያደርጉን አንፍቀድ!
በድንገት ሥራ ማጣት የስሜት ቀውስ ሊያስከትል ቢችልም ይህ ከይሖዋ አምላክና ከሕዝቦቹ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። ቀደም ሲል የጠቀስነው አዳም የተሰማው እንደዚህ ነበር። እንዲህ ይላል:- “እኔና ባለቤቴ ሥራችንን ስናጣ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የመቅረትም ሆነ በወንጌላዊነቱ ሥራ የምናደርገውን ተሳትፎ የመቀነስ ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሯችን አልመጣም። እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዛችን ስለነገ ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ጠብቆናል።” ሪሻርድም ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ስብሰባዎቻችንና አገልግሎታችን ባይኖሩ ኖሮ በጭንቀት ተውጠን ችግሮቻችንን መቋቋም አንችልም ነበር። ከሌሎች ጋር የምናደርጋቸው መንፈሳዊ ጭውውቶች ትኩረታችንን በራሳችን ፊልጵስዩስ 2:4
ችግሮች ላይ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንድናስብ ስለሚያደርጉን ያበረታቱናል።”—ስለ ሥራ ብቻ እያሰቡ ከመጨነቅ ይልቅ ያለህን ትርፍ ጊዜ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች፣ ለግል ጥናት፣ የጉባኤ ሥራዎችን ለማከናወን ወይም አገልግሎትህን ለማስፋት ተጠቀምበት። ያለሥራ ከመቀመጥ ይልቅ “የጌታ ሥራ . . . የሚበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ ለአንተም ሆነ የምትሰብከውን የመንግሥቱን መልእክት ለሚሰሙ ቅን ሰዎች ደስታ ያስገኝላችኋል።—1 ቆሮንቶስ 15:58 የ1954 ትርጉም
ቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ማሟላት
እርግጥ ነው፣ መንፈሳዊ ምግብ የተራበን ሆድ አያጠግብም። የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወስ ይኖርብናል:- “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) አዳም “በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞች የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች በፈቃደኝነት ቢለግሱንም፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ሥራ የመፈለግ ግዴታ አለብን” ሲል በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋና ሕዝቦቹ በሚሰጡን ድጋፍ መታመን ብንችልም ሥራ ለመፈለግ ቅድሚያውን መውሰድ ያለብን እኛ መሆናችንን ግን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም።
ምን ማድረግ ትችላለህ? አዳም እንዲህ ብሏል:- “እጅህን አጣጥፈህ አምላክ ተአምር እንዲሠራ አትጠብቅ። ሥራ በምትፈልግበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ለመናገር አታቅማማ። ቀጣሪዎች ብዙ ጊዜ ለዚህ ትልቅ ቦታ ይሰጡታል።” ሪሻርድ ደግሞ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “የምታውቀውን ማንኛውንም ሰው ክፍት የሥራ ቦታ ያውቅ እንደሆነ ጠይቅ፤ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ድረስ እየሄድክ መጠየቅህን አታቋርጥ፤ ‘የልጅ ሞግዚት ይፈለጋል’ ወይም ‘ጊዜያዊ ሥራ—ሣር አጨዳ’ እንደሚሉት ያሉ ማስታወቂያዎችን ተከታተል። ያለማሰለስ ሥራ መፈለግህን ቀጥል! ሥራው ዝቅተኛ የሚባል ወይም የማትፈልገው ዓይነት ቢሆንም እንኳ ከመጠን በላይ መራጭ አትሁን።”
አዎን፣ ‘ጌታ ረዳትህ ነው።’ እርሱ ራሱ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል። (ዕብራውያን 13:5, 6) ከመጠን በላይ መጨነቅ አይኖርብህም። መዝሙራዊው ዳዊት “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 37:5) ‘መንገዳችንን ለይሖዋ በዐደራ መስጠት’ ሲባል በእርሱ መታመንና በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ ቢሆን በእርሱ መንገድ ነገሮችን ማከናወን ማለት ነው።
አዳምና ኢሬና፣ መስኮትና ደረጃ በማጽዳት እንዲሁም በቁጠባ በመኖር ራሳቸውን ማስተዳደር ችለዋል። ወደ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ሁልጊዜ ይሄዳሉ። ኢሬና “ልክ ስንቸገር እርዳታ እናገኛለን” ብላለች። ባለቤቷም እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል:- “በጸሎታችን የጠቀስናቸው ነገሮች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ እንዳልነበሩ ከተሞክሮ ተገንዝበናል። ይህ ደግሞ በራሳችን ማስተዋል ከመመራት ይልቅ በይሖዋ ጥበብ ላይ መታመንን አስተምሮናል። አምላክ የሚሰጠንን መፍትሔ በትዕግሥት መጠበቅ የተሻለ ነው።”—ያዕቆብ 1:4
ሪሻርድና ማሪኦላ ጊዜያዊ ሥራ የሚሠሩ ቢሆንም ተጨማሪ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ክልል ሄደው ያገለግሉም ነበር። ሪሻርድ እንዲህ ይላል:- “የምንበላው ነገር ልክ ሲያልቅብን ሥራ እናገኛለን። ከቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቻችን ጋር የሚጋጩ በጣም ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኙ ሥራዎች ብናገኝም ሳንቀበል ቀርተናል። ይሖዋን መጠባበቅ መርጠን ነበር።” ይሖዋ ነገሮችን እንደሚያሳካ እምነት በማሳደራቸው በርካሽ ዋጋ የሚከራይ ቤት ያገኙ ሲሆን ሪሻርድም ከጊዜ በኋላ ሥራ ማግኘት ችሏል።
መተዳደሪያ ማጣት በጣም የሚያስጨንቅ ቢሆንም ሁኔታውን ይሖዋ እንደማይተውህ የገባውን ቃል ሲፈጽም ለመመልከት እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ለምን አትመለከተውም? ይሖዋ ይንከባከብሃል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 41:10) ሥራ ማጣትን ጨምሮ ምንም ዓይነት ያልታሰበ ሁኔታ ቢያጋጥምህ እንዲያሽመደምድህ አትፍቀድ። የምትችለውን ሁሉ ካደረግክ በኋላ የቀረውን በይሖዋ እጅ ተወው። ይሖዋን “ዝም ብሎ” መጠበቅ የተሻለ ነው። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26) እንዲህ ካደረግህ የተትረፈረፈ በረከት ታገኛለህ።—ኤርምያስ 17:7
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጊዜውን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠቀምበት
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቆጣቢ መሆንን ተማር፤ እንዲሁም ሥራ በምታፈላልግበት ጊዜ ከልክ በላይ መራጭ አትሁን