በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን የጦር መሣሪያ መያዝ በሚጠይቅ ሥራ ላይ ቢሰማራ ንጹሕ ሕሊና ሊኖረው ይችላል?

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ የቤተሰባቸውን ቁሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ የጣለባቸውን ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከቱታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በግልጽ ከሚጋጩ የሥራ ዓይነቶች መቆጠብ ይገባቸዋል። ይህም ከቁማርና ደምን አላግባብ ከመጠቀም ጋር ግንኙነት ያላቸውን እንዲሁም የሲጋራ ውጤቶችን መጠቀምን የሚያበረታቱ ሥራዎችን ያካትታል። (ኢሳይያስ 65:11፤ የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ቈላስይስ 3:5) ሌሎች የሥራ ዓይነቶች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ የተወገዙ ባይሆኑም የግለሰቡን ወይም የሌሎችን ሕሊና ሊያቆሽሹ ይችላሉ።

ጠመንጃ ወይም ሌላ ዓይነት የጦር መሣሪያ መያዝ በሚጠይቅ ሰብዓዊ ሥራ ላይ መሰማራትም ሆነ አለመሰማራት ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። ሆኖም የጦር መሣሪያን መያዝ የሚጠይቅ ሥራ አንድን ግለሰብ መሣሪያውን በሌሎች ላይ እንዲጠቀምና የደም ባለዕዳ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም አንድ ክርስቲያን ድንገተኛ ሁኔታ ባጋጠመው ቁጥር የያዘውን መሣሪያ መጠቀም አለመጠቀምን በተመለከተ ቅጽበታዊ ውሳኔ ለማድረግ የሚገደድበት ሁኔታ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በመገንዘብ ጉዳዩን ከወዲሁ በጸሎት ሊያስብበት ይገባል። ከዚህም በላይ አንድ ግለሰብ መሣሪያ ከያዘ እርሱን አስቀድሞ ለማጥቃት ወይም አጸፋውን ለመመለስ ሲባል ሊተኮስበትና በዚህም ሳቢያ የመቁሰል ወይም የሞት አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።

አንድ ሰው የሚያደርገው ውሳኔ ሌሎችን መንካቱ አይቀርም። ለአብነት ያህል፣ የአንድ ክርስቲያን ተቀዳሚ ኃላፊነት ስለ አምላክ መንግሥት የምሥራች ለሌሎች መስበክ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ታዲያ አንድ ክርስቲያን መሣሪያ መታጠቅ የሚጠይቀውን ሥራ መተዳደሪያው አድርጎ ሌሎች ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ’ እንዴት ሊያስተምር ይችላል? (ሮሜ 12:18) ስለ ልጆች ወይም ስለ ሌሎች የቤተሰቡ አባላትስ ምን ለማለት ይቻላል? ቤት ውስጥ ሽጉጥ ማስቀመጥ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጠው ይሆን? አንድ ሰው በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም ለሌሎች መሰናክል ቢሆንስ?—ሮሜ 14:21

በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች “ጨካኞች” እንዲሁም “መልካም የሆነውን የማይወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) አንድ ሰው ይህን እያወቀ እንዲህ ዓይነት ከሰዎች ጋር ሊያጋጨው በሚችል መሣሪያ መታጠቅን በሚጠይቅ ሥራ ላይ ቢሰማራ ‘አንዳች ነቀፋ የለበትም’ ሊባል ይችላል? (1 ጢሞቴዎስ 3:10) በጭራሽ። ከዚህ የተነሳ አስፈላጊው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር በደግነት ከተለገሰው በኋላ መሣሪያ መያዙን ከቀጠለ ጉባኤው እንዲህ ዓይነቱን ሰው “የማይነቀፍ” እንደሆነ አድርጎ አይመለከተውም። (1 ጢሞቴዎስ 3:2፤ ቲቶ 1:5, 6) ስለሆነም እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ በጉባኤ ውስጥ ልዩ መብት ለማግኘት አይበቃም።

ኢየሱስ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን እስካስቀደሙ ድረስ ለመሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ከልክ በላይ መጨነቅ እንደማያስፈልጋቸው ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾላቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:25, 33) በእርግጥም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እስከታመንን ድረስ ‘እርሱ ደግፎ ይይዘናል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።’—መዝሙር 55:22