በእርግጥ ዲያብሎስ መኖሩን ታምናለህ?
በእርግጥ ዲያብሎስ መኖሩን ታምናለህ?
ዲያብሎስ ሕያው አካል እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። አምላክ በሰዎች ዓይን እንደማይታይ ሁሉ ዲያብሎስም አይታይም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ይላል። (ዮሐንስ 4:24) ዲያብሎስ መንፈሳዊ ፍጡር ቢሆንም ከፈጣሪ በተለየ መልኩ መጀመሪያ አለው።
ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ ከረዥም ጊዜ በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጡራንን ወደ ሕልውና አምጥቷል። (ኢዮብ 38:4, 7) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መንፈሳዊ ፍጥረታት መላእክት ብሎ ይጠራቸዋል። (ዕብራውያን 1:13, 14) አምላክ ሁሉንም ፍጹም አድርጎ የፈጠራቸው ሲሆን ከመካከላቸው አንዱም ቢሆን ዲያብሎስ አልነበረም ወይም መጥፎ ባሕርይ አልነበረውም። ታዲያ ዲያብሎስ የመጣው ከየት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል ስለ ሌሎች ሆን ብሎ በተንኮል ውሸት የሚናገር “ስም አጥፊ” ማለት ሲሆን “ሰይጣን” ደግሞ “ተቃዋሚ” ማለት ነው። ቀደም ሲል ታማኝ የነበረ ሰው መስረቅ ሲጀምር ራሱን ሌባ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ፍጹም ከነበሩት የአምላክ መንፈሳውያን ልጆች መካከል አንዱ ተገቢ ያልሆነ ምኞቱን በተግባር ሲያውለው ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው እንዴት ወደ ኃጢአት ሊያመራ እንደሚችል ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15
ከዲያብሎስ ጋር በተያያዘም የተከሰተው ነገር ይህ ነበር። ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ጥንዶች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር፣ በአምላክ ላይ ለማመጽ ያሰበው መልአክ ሁኔታውን በትኩረት ይከታተል ነበር። ይሖዋ መላዋን ምድር እርሱን በሚያመልኩ ጻድቃን ሰዎች እንዲሞሏት ለአዳምና ለሔዋን የሰጠውንም ትእዛዝ ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ይህ መልአክ ክብርና ትልቅ ቦታ ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ተመለከተ። በሰዎች የመመለክ መብት ያለው አምላክ ብቻ ቢሆንም፣ ስግብግብነት ይህን መብት ለማግኘት እንዲቋምጥ አደረገው። ይህ መንፈሳዊ የአምላክ ልጅ ይህንን የተሳሳተ ምኞት ከአእምሮው በማውጣት ፋንታ ውሸት ወደ መናገር ብሎም ወደ ማመጽ እስኪያደርሰው ድረስ በውስጡ እንዲያድግ ፈቀደለት። እስቲ ምን እንዳደረገ እንመልከት።
ዘፍጥረት 3:1-5) ሰይጣን ይህን ሲል አምላክ፣ ለአዳምና ለሔዋን እውነቱን አልነገራቸውም፤ እንደውም ሔዋን የዛፉን ፍሬ ብትበላ መልካምና ክፉውን የመወሰን ሥልጣን ስለሚኖራት እንደ አምላክ መሆን ትችላለች ማለቱ ነበር። ይህ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ውሸት ነበር። መልአኩ ይህንን በመናገሩ ስም አጥፊና የአምላክ ተቃዋሚ ሆነ። በዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን የአምላክ ጠላት ‘የጥንቱ እባብ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን’ በማለት ይጠራዋል።—ራእይ 12:9
ዓመጸኛው መልአክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ ተጠቀመ። እባቡ ሔዋንን “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” አላት። ሔዋንም የአምላክን ትእዛዝና ሳይታዘዙ ከቀሩ ምን እንደሚደርስባቸው ስትነግረው እባቡ እንዲህ አላት:- “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” (“ንቁ”
ዲያብሎስ ለሔዋን የነገራት ውሸት ልክ እንዳቀደው ተሳካለት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ።” (ዘፍጥረት 3:6) ሔዋን ሰይጣንን አምና በአምላክ ላይ ያመጸች ከመሆኗም በላይ አዳም የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ለማድረግ ችላለች። በዚህ መልኩ ዲያብሎስ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በአምላክ ላይ በማሳመጽ ረገድ ተሳክቶለታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ በማይታይ ሁኔታ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ዓላማው ምንድን ነው? ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ ዞር እንዲሉና እርሱን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው። (ማቴዎስ 4:8, 9) መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል” የሚለውን ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገቢ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:8
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዲያብሎስ ሐቀኝነት የጎደለው እንዲሁም አደገኛ የሆነ እውን መንፈሳዊ አካል መሆኑን በግልጽ ይናገራል! ንቁ ለመሆን በመጀመሪያ ልንወስደው የሚገባው አስፈላጊ እርምጃ ዲያብሎስ በእርግጥ መኖሩን አምኖ መቀበል ነው። ሆኖም ራሳችንን ለመግዛትና ነቅተን ለመኖር ሌላም የሚያስፈልገን ነገር አለ። ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምበትን ዘዴና “ዕቅድ” ጠንቅቀን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ታዲያ ወጥመዶቹ ምንድን ናቸው? በሰይጣን ወጥመዶች እንዳንወድቅ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ዲያብሎስ በሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ፍላጎት ይጠቀማል
ዲያብሎስ የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ሁኔታቸውን ሲያጤን ቆይቷል። የሰውን ልጅ አፈጣጠር ይኸውም ፍላጎቱን እንዲሁም ትኩረቱን የሚስቡትንና የሚመኛቸውን ነገሮች ያውቃል። ሰይጣን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳላቸው በሚገባ የሚያውቅ በመሆኑ ዓላማውን ለማሳካት ይህንን እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። እንዴት? የሰው ልጆች ሃይማኖታዊ ውሸቶችን እንዲመገቡ በማድረግ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ብዙ ሃይማኖቶች ስለ አምላክ የሚያስተምሩት ነገር እርስ በርሱ የሚጋጭና ግራ የሚያጋባ ነው። ይህ ትምህርት የማንን ዓላማ የሚያራምድ ይመስልሃል? እርስ በርስ የሚጋጩ ትምህርቶች ሁሉ እውነት ሊሆኑ አይችሉም። እንግዲያው አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል ሲል ያመነጫቸውና የሚጠቀምባቸው ናቸው ቢባል ትክክል አይሆንም? እንዲያውም ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰዎችን አእምሮ ያሳወረ “የዚህ ዓለም አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል።—2 ቆሮንቶስ 4:4
መለኮታዊው እውነት ከሃይማኖታዊ ማታለያዎች ይጠብቃል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት በጥንት ዘመን አንድ ወታደር ወገቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ለመከላከል ከሚታጠቀው ቀበቶ ጋር አመሳስሎታል። (ኤፌሶን 6:14) የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት የምትማርና በዚህ እውነት ወገብህን የታጠቅክ ያህል ከተማርከው ነገር ጋር ተስማምተህ የምትኖር ከሆነ የአምላክ ቃል በሃይማኖታዊ ውሸቶችና ስህተቶች እንዳትታለል ይጠብቅሃል።
የሰው ልጅ መንፈሳዊ ፍላጎት ያለው መሆኑ የማያውቀውን ነገር ለመመርመር እንዲጥር አነሳስቶታል። ይህም ለሌላው የሰይጣን የማታለያ ዘዴ አጋልጦታል። ሰይጣን ሰዎች ያልተለመዱና ምስጢራዊ የሆኑ ነገሮችን ለማወቅ ያላቸውን ፍላጎት በመጠቀም በመናፍስታዊ ሥራዎች አማካኝነት ብዙዎችን በቁጥጥሩ ሥር አድርጓል። አንድ የእንስሳ አዳኝ በወጥመድ ላይ ምግብ እንደሚያስቀምጥ ሁሉ ሰይጣንም እንደ ጥንቆላ፣ ኮከብ ቆጠራ፣ ሂፕኖቲዝም፣ ድግምት፣ የእጅ አሻራ ማንበብና አስማት የመሳሰሉትን ነገሮች በመጠቀም በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ለማጥመድ ይሞክራል።—ዘሌዋውያን 19:31፤ መዝሙር 119:110
በመናፍስታዊ ድርጊት እንዳትጠመድ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ዘዳግም 18:10-12 እንዲህ ይላል:- “በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቊል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነውና፣ ከእነዚህ አ[ስ]ጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል።”
ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን ቅዱሳን ጽሑፎች ግልጽ የሆነ ምክር ይሰጡናል። ምናልባት በመናፍስታዊ ድርጊቶች ትካፈል የነበረ ቢሆንና አሁን ለማቆም ብትፈልግ ምን ማድረግ ትችላለህ? በጥንቷ ኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጌታን ቃል’ በተቀበሉ ጊዜ “ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ” ይላል። ያቃጠሉት 50,000 ብር ያህል የሚያወጡ ውድ መጻሕፍትን ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20) ሆኖም የኤፌሶን ክርስቲያኖች ጽሑፎቹን ከማቃጠል ወደኋላ አላሉም።
ሰይጣን ሰብዓዊ ድክመቶችን በመጠቀም ለማጥመድ ይሞክራል
ፍጹም የነበረው መልአክ ክብር ለማግኘት ባደረበት ምኞት በመሸነፉ ምክንያት ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ። በሔዋንም ውስጥ ኩራት እንዲሁም እንደ አምላክ የመሆን የራስ ወዳድነት ምኞት አሳደረባት። በዛሬው ጊዜ ሰይጣን በብዙዎች ውስጥ የኩራት መንፈስ በማሳደር በቁጥጥሩ ሥር አድርጓቸዋል። ለምሳሌ አንዳንዶች የራሳቸውን ዘር፣ ጎሳ ወይም ዜግነት ከሌላው እንደሚበልጥ አድርገው ያስባሉ። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትምህርት ምን ያህል ተቃራኒ ነው! (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን [እንደፈጠረ]” በግልጽ ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 17:26
ሰይጣን በሰዎች ውስጥ የሚያሳድረውን የኩራት መንፈስ ለመከላከል የሚቻልበት ውጤታማው መንገድ ትሕትናን ማዳበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ” ሲል ይመክረናል። (ሮሜ 12:3) እንዲሁም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል። (ያዕቆብ ) የሰይጣንን ጥረት በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳህ አንዱ መንገድ በሕይወትህ ውስጥ ትሕትናን እንዲሁም አምላክ የሚደሰትባቸውን ሌሎች ባሕርያት ማሳየት ነው። 4:6
ዲያብሎስ በሰብዓዊ ድክመቶቻችን የሚጠቀምበት ሌላው መንገድ ተገቢ ባልሆኑ የሥጋ ምኞቶች እንድንሸነፍ በማድረግ ነው። የይሖዋ አምላክ ዓላማ ሰዎች በደስታ እንዲኖሩ ነው። ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ፍላጎቶቻችንን ማርካት እውነተኛ ደስታ ያስገኛል። ሆኖም ሰይጣን፣ ሰዎች ምኞቶቻቸውን ሥነ ምግባር በጎደለው ሁኔታ እንዲያረኩ ይፈትናቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አእምሮን ንጹሕና በጎ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ከሁሉ የተሻለ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:8) ይህ ደግሞ አስተሳሰብህንና ስሜትህን እንድትቆጣጠር ይረዳሃል።
ዲያብሎስን መቃወማችሁን ቀጥሉ
ዲያብሎስን በመቃወም ረገድ ሊሳካልህ የሚችል ይመስልሃል? አዎን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ያረጋግጥልናል። (ያዕቆብ 4:7) የአምላክን እውቀት እየተማርክም ቢሆን ሰይጣንን በምትቃወምበት ጊዜ ወዲያው ተስፋ ቆርጦ በአንተ ላይ ፈተና ማምጣቱን አይተውም። እንዲያውም ዲያብሎስ “ሌላ አመቺ ጊዜ” ፈልጎ እንደገና ይሞክራል። (ሉቃስ 4:13) ሆኖም ዲያብሎስን በፍጹም መፍራት አይኖርብህም። እርሱን መቃወምህን ከቀጠልክ ከእውነተኛው አምላክ ሊያርቅህ አይችልም።
ሆኖም ዲያብሎስን ለመቃወም ስለ ማንነቱም ሆነ ሰዎችን ስለሚያስትበት መንገድ እንዲሁም የማታለያ ዘዴዎቹን ለመቋቋም መውሰድ ስለሚኖሩብን እርምጃዎች ማወቅ ያስፈልጋል። የትክክለኛ እውቀት ብቸኛው ምንጭ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት ለማጥናትና ከእነሱ የተማርኸውን በሕይወትህ ለመተግበር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ያለ ክፍያ በሚመችህ ጊዜ እንዲህ ያለ ጥናት እንድታደርግ ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ለመጻፍ ዛሬ ነገ አትበል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትጀምር ሰይጣን ተቃውሞ ወይም ስደት በማምጣት ከአምላክ ቃል እውነትን እንዳትማር ሊያደርግህ እንደሚፈልግ መገንዘብ አለብህ። ወዳጅ ዘመዶችህ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትህ ሊናደዱ ይችላሉ። ይህንን የሚያደርጉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አስደናቂ እውነቶች ካለማወቃቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ባንተ ላይ ያሾፉ ይሆናል። ሆኖም በእነዚህ ሁኔታዎች መሸነፉ አምላክን በእርግጥ የሚያስደስተው ይመስልሃል? ሰይጣን ስለ እውነተኛው አምላክ መማርህን እንድታቆም ለማድረግ ተስፋ ሊያስቆርጥህ ይፈልጋል። ሰይጣን እንዲያሸንፍህ አትፍቀድለት! (ማቴዎስ 10:34-39) ለሰይጣን ምንም የማድረግ ግዴታ የለብህም። ሕይወትህን የሰጠህ ይሖዋ ነው። ስለዚህ ዲያብሎስን በመቃወም ‘የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት’ ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን።—ምሳሌ 27:11
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች መናፍስታዊ መጽሐፎቻቸውን አቃጥለዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን