በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሆሴዕ ትንቢት ከአምላክ ጋር እንድንሄድ ይረዳናል

የሆሴዕ ትንቢት ከአምላክ ጋር እንድንሄድ ይረዳናል

የሆሴዕ ትንቢት ከአምላክ ጋር እንድንሄድ ይረዳናል

“እግዚአብሔርን ይከተላሉ።”—ሆሴዕ 11:10

1. የሆሴዕ መጽሐፍ ምን ምሳሌያዊ ድራማ ይዟል?

 አስደናቂ ገጸ ባሕርያት የሚካፈሉበትና ትኩረት የሚስብ ታሪክ ያለው ድራማ ያስደስትሃል? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሆሴዕ መጽሐፍ ምሳሌያዊ ድራማ ይዟል። a ድራማው የአምላክ ነቢይ በነበረው በሆሴዕ የቤተሰብ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ይሖዋ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከጥንቷ እስራኤል ጋር ስለመሠረተው ምሳሌያዊ ጋብቻም ያወሳል።

2. ስለ ሆሴዕ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

2 የዚህ ድራማ መቼት በሆሴዕ ምዕራፍ 1 ላይ ይገኛል። ሆሴዕ አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ግዛት ውስጥ ይኖር የነበረ ይመስላል፤ ይህ መንግሥት ከአሥሩ ነገዶች መካከል ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በኤፍሬም ነገድ ስምም ይጠራል። ሆሴዕ ትንቢት የተናገረው በመጨረሻዎቹ ሰባት የእስራኤል ነገሥታት እንዲሁም ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ በተባሉት የይሁዳ ነገሥታት የግዛት ዘመን ነበር። (ሆሴዕ 1:1) በመሆኑም ሆሴዕ ቢያንስ ለ59 ዓመታት በነቢይነት አገልግሏል። በስሙ የተጠራው መጽሐፍ ተጽፎ ያበቃው በ745 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ ነው፤ ያም ቢሆን ግን ብዙዎች “እግዚአብሔርን ይከተላሉ” ተብሎ በተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተመላለሱ ባሉበት በዛሬው ጊዜም መጽሐፉ ጠቃሚ ነው።—ሆሴዕ 11:10

የመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት ምን ይመስላል?

3, 4. ሆሴዕ ምዕራፍ 1 እስከ 5 ምን እንደያዘ በአጭሩ ግለጽ።

3 ከሆሴዕ 1 እስከ 5 ያሉትን ምዕራፎች በአጭሩ መመልከታችን በአምላክ ላይ እምነት በማሳደርና ከእርሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ከይሖዋ ጋር ለመሄድ ያደረግነውን ውሳኔ ያጠናክርልናል። የእስራኤል ነዋሪዎች መንፈሳዊ ምንዝር በመፈጸማቸው ጥፋተኞች ሆነው ቢገኙም ንስሐ ከገቡ አምላክ ምሕረት ያደርግላቸዋል። ሆሴዕ ከሚስቱ ከጎሜር ጋር የነበረው ግንኙነት ለዚህ ምሳሌ ተደርጎ ተገልጿል። ጎሜር ለሆሴዕ አንድ ልጅ ከወለደችለት በኋላ በምንዝር ሁለት ልጆች ሳትወልድ አልቀረችም። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ንስሐ ለገቡ እስራኤላውያን ምሕረት ለማሳየት ፈቃደኛ እንደነበረ ሁሉ ሆሴዕም ሚስቱን እንደገና ወስዷታል።—ሆሴዕ 1:1 እስከ 3:5

4 በእስራኤል ውስጥ እውነት፣ ፍቅርና እውቀት ስለጠፋ ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የሚያቀርበው ክስ ነበረው። አምላክ ጣዖት አምላኪዋን እስራኤልንም ሆነ ዓመጸኛ የሆነውን የይሁዳ መንግሥት ይቀጣል። ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች ‘መከራ’ ሲደርስባቸው ይሖዋን ይፈልጉታል።—ሆሴዕ 4:1 እስከ 5:15

ድራማው ጀመረ

5, 6. (ሀ) በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ምንዝር ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር? (ለ) ለጥንቷ እስራኤል የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ለእኛ ምን ትምህርት ይዟል?

5 አምላክ ሆሴዕን “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” የሚል መመሪያ ሰጠው። (ሆሴዕ 1:2) ምንዝር በእስራኤል ውስጥ ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የአመንዝራነት መንፈስ [አሥሩን ነገድ ባቀፈው መንግሥት ሥር ያሉትን ሰዎች] ያስታቸዋል፤ ለአምላካቸውም ታማኝ አልሆኑም። . . . ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማዊ፣ ምራቶቻችሁም አመንዝራ ይሆናሉ። . . . ወንዶች ከጋለሞቶች ጋር ይሴስናሉ፤ ከቤተ ጣዖት ዘማውያን ጋር ይሠዋሉና።”—ሆሴዕ 4:12-14

6 በእስራኤል ውስጥ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ምንዝር በጣም ተስፋፍቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እስራኤላውያኑን ‘ይቀጣቸዋል።’ (ሆሴዕ 1:4፤ 4:9) ይሖዋ ዛሬም የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙና ንጹሕ ባልሆነ አምልኮ የሚካፈሉ ሰዎችን ስለሚቀጣ ይህ ማስጠንቀቂያ ለእኛም ትምህርት ይዟል። ሆኖም ከአምላክ ጋር የሚሄዱ ሰዎች ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡለት ከመሆኑም በላይ “ማንም አመንዝራ . . . በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት” እንደሌለው ይገነዘባሉ።—ኤፌሶን 5:5፤ ያዕቆብ 1:27

7. ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የመሠረተው ጋብቻ የምን ምሳሌ ነው?

7 ሆሴዕ ጎሜርን ሲያገባት ድንግል ሳትሆን አትቀርም፤ ‘ወንድ ልጅ በወለደችለት’ ጊዜም ታማኝ ሚስት ነበረች። (ሆሴዕ 1:3) በተመሳሳይም በምሳሌያዊው ድራማ ላይ እንደሚታየው አምላክ በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስራኤላውያንን ከግብፃውያን ባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ተጋብቷል፤ ይህም ንጹሕ የጋብቻ ጥምረት ለመመሥረት እንደሚደረግ ውል ነበር። እስራኤል በዚህ ቃል ኪዳን ስትስማማ ‘ለባሏ፣’ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቃል ገብታለች። (ኢሳይያስ 54:5) አዎን፣ ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የመሠረተው ንጹሕ ጋብቻ እስራኤል ከአምላክ ጋር ለፈጸመችው ምሳሌያዊ ጋብቻ ተምሳሌት ነው። ሆኖም ሁኔታዎቹ ተለወጡ!

8. አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት የተቋቋመው እንዴት ነው? በዚህ መንግሥት ሥር ስለሚከናወነው አምልኮስ ምን ማለት ይቻላል?

8 የሆሴዕ ሚስት “እንደ ገና ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች።” ጎሜር ይህቺን ሴት ልጅና በኋላ ላይ የተወለደውን ወንድ ልጅ የፀነሰቻቸው በምንዝር ሳይሆን አይቀርም። (ሆሴዕ 1:6, 8) ጎሜር እስራኤልን ስለምትወክል ‘እስራኤል ምንዝር የፈጸመችው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በ997 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከእስራኤል ነገዶች አሥሩ በደቡባዊው ክፍል ከሚገኙት የይሁዳና የብንያም ነገዶች ተገነጠሉ። በስተ ሰሜን የነበረው የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ሕዝቡ ይሖዋን ለማምለክ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደሱ እንዳይሄድ ለማገድ ሲል በእስራኤል የጥጃ አምልኮ አስጀመረ። የጾታ ብልግና የሚፈጸምባቸውን መረን የለቀቁ ግብዣዎች ያካተተው በኣል የተባለው የሐሰት አምላክ አምልኮ በእስራኤል ተስፋፋ።

9. በሆሴዕ 1:6 ላይ በተነገረው ትንቢት መሠረት እስራኤል ምን ደረሰባት?

9 ጎሜር በምንዝር እንደወለደቻት የሚታሰበውን ሁለተኛ ልጅዋን ከተገላገለች በኋላ አምላክ ለሆሴዕ እንዲህ አለው:- “ይቅር እላቸው ዘንድ ለእስራኤል ቤት ከእንግዲህ ስለማልራራላቸው፣ ስሟን ሎሩሃማ [“ምሕረት ያልተደረገላት” ማለት ነው] ብለህ ጥራት።” (ሆሴዕ 1:6) ይሖዋ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት አሦራውያን እስራኤላውያንን ማርከው እንዲወስዷቸው አድርጓል። ሆኖም አምላክ ለሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት ምሕረት በማሳየት አድኗቸዋል፤ ይህን ያደረገው ግን በቀስት፣ በሰይፍ፣ በጦርነት ወይም በፈረሶችና በፈረሰኞች አልነበረም። (ሆሴዕ 1:7) በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ መልአክ በይሁዳ ዋና ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ስጋት ፈጥረው የነበሩትን 185,000 አሦራውያን ወታደሮች በአንድ ሌሊት ገደለ።—2 ነገሥት 19:35

ይሖዋ በእስራኤል ላይ የመሠረተው ክስ

10. ጎሜር በአመንዝራነት የፈጸመችው ድርጊት ለምን ነገር ምሳሌ ነው?

10 ጎሜር ሆሴዕን ትታ ከሌላ ወንድ ጋር መኖር በመጀመሯ “አመንዝራ ሴት” ሆነች። ይህም የእስራኤል መንግሥት ጣዖት አምላኪ ከሆኑ ብሔራት ጋር ፖለቲካዊ ስምምነት መፍጠሯንና በእነርሱ መታመን መጀመሯን ያመለክታል። እስራኤል ላገኘችው ቁሳዊ ብልፅግና ይሖዋን ከማመስገን ይልቅ ብልፅግናዋን ከእነዚህ ብሔራት አማልክት እንዳገኘችው ትናገር ነበር፤ ከዚህም በላይ በሐሰት አምልኮ በመካፈል ከአምላክ ጋር የነበራትን የጋብቻ ቃል ኪዳን አፈረሰች። ይሖዋ በመንፈሳዊ አመንዝራ በሆነችው ብሔር ላይ ክስ መመሥረቱ ምንም አያስገርምም!—ሆሴዕ 1:2፤ 2:2, 12, 13

11. ይሖዋ እስራኤልና ይሁዳ በግዞት እንዲወሰዱ በፈቀደበት ወቅት የሕጉ ቃል ኪዳን ተሰረዘ?

11 እስራኤል ባሏን ስለተወች ምን ቅጣት ደረሰባት? አምላክ ወደ ባቢሎን “ምድረ በዳ” እንድትሄድ አደረገ፤ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስራኤላውያንን በግዞት ወስዷቸው የነበረውን አሦርን ድል ያደረገው የባቢሎን መንግሥት እንዲማርካት ፈቀደ። (ሆሴዕ 2:14) ይሖዋ አሥሩን ነገድ ያቀፈው መንግሥት እንዲወድቅ ባደረገበት ወቅት፣ መጀመሪያ ላይ ከ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ጋር የገባውን የጋብቻ ቃል ኪዳን አልሰረዘም። ሌላው ቀርቶ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፏትና የይሁዳን ሕዝብ በግዞት እንዲወስዱ በፈቀደበት ወቅትም እንኳ በሙሴ ሕግ አማካኝነት ከ12ቱ ነገዶች ጋር ያደረገውን ምሳሌያዊ የጋብቻ ስምምነት አላፈረሰም። ይህ ዝምድና የተቋረጠው የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስ ክርስቶስን አንቀበልም ብለው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባስገደሉት ጊዜ ነበር።—ቈላስይስ 2:14

ይሖዋ ለእስራኤል የሰጠው ማስጠንቀቂያ

12, 13. በሆሴዕ 2:6-8 ላይ ተመዝግቦ የምናገኘው ሐሳብ ፍሬ ነገር ምንድን ነው? በእስራኤልስ ላይ ምን ፍጻሜ ነበረው?

12 አምላክ እስራኤል ‘ዘማዊነትን እንድታስወግድ’ ቢመክራትም እርሷ ግን ውሽሞቿን ተከትላ ለመሄድ ፈለገች። (ሆሴዕ 2:2, 5) ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾህ እዘጋለሁ፤ መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ አጥራለሁ። ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም። ከዚያም እንዲህ ትላለች፤ ‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤ የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’ እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣ ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን [ወይም “የበኣል ምስል የሠሩበትን፣” NW የግርጌ ማስታወሻ]፣ ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣ እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም።”—ሆሴዕ 2:6-8

13 እስራኤል ‘ውሽሞቼ’ ያለቻቸውን ብሔራት እርዳታ ብትሻም አንዳቸውም ቢሆኑ ሊረዷት አልቻሉም። ዙሪያዋን ጥቅጥቅ ባለ ጥሻ የታጠረች ያህል ተከብባ ስለነበር ምንም እርዳታ ሊያደርጉላት አልቻሉም። ከሦስት ዓመታት የአሦራውያን ከበባ በኋላ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ዋና ከተማዋ ሰማርያ ወደቀች፤ አሥሩን ብሔር ያቀፈው መንግሥት ከዚያ በኋላ እንደገና ማንሠራራት አልቻለም። በምርኮ ከተወሰዱት እስራኤላውያን መካከል አባቶቻቸው ይሖዋን ያገለግሉ በነበሩበት ወቅት ሁኔታዎች ምን ያህል የተሻሉ እንደነበሩ የተገነዘቡት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው። እነዚህ ቀሪዎች የበኣል አምልኮን በመተው ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን የቃል ኪዳን ዝምድና ለማደስ ይፈልጋሉ።

የድራማው ሌላ ገጽታ

14. ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የነበረውን ትዳር እንደገና ያደሰው ለምንድን ነው?

14 በሆሴዕ ትዳርና እስራኤል ከይሖዋ ጋር በነበራት ዝምድና መካከል ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሚከተለውን ጥቅስ እንመልከት:- “እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ ‘እርሷ በሌላ ሰው የምትወደድ አመንዝራ ብትሆንም፣ አሁንም ሂድና ሚስትህን ውደዳት።’” (ሆሴዕ 3:1) ሆሴዕ ጎሜርን አብራው ትኖር ከነበረው ሰው እንደገና በመግዛት የታዘዘውን ፈጸመ። ከዚያም “ከእኔ ጋር ብዙ ቀን ተቀመጪ፤ አታመንዝሪ ወይም ሌላ ሰው አትውደጂ” በማለት ሚስቱን አጥብቆ መከራት። (ሆሴዕ 3:2, 3) ጎሜር ምክሩን ስለሰማች ሆሴዕም ከእርሷ ጋር በትዳር አብሮ ቀጠለ። ይህ ሁኔታ አምላክ ከእስራኤልና ከይሁዳ ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ የሚሠራው እንዴት ነው?

15, 16. (ሀ) እርማት የተቀበለው የአምላክ ብሔር ምሕረት ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረበት? (ለ) ሆሴዕ 2:18 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

15 ከእስራኤልና ከይሁዳ በግዞት የተወሰዱት ምርኮኞች በባቢሎን እያሉ አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት ‘በፍቅር ቃል አነጋገራቸው።’ ሕዝቡ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ንስሐ መግባትና ጎሜር ወደ ባሏ እንደተመለሰች ሁሉ እነርሱም ወደ ባላቸው መመለስ ነበረባቸው። ከዚያም ይሖዋ እንደ ሚስቱ የሚቆጥራትን የታረመችውን ብሔር ከባቢሎን “ምድረ በዳ” አውጥቶ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ይመልሳታል። (ሆሴዕ 2:14, 15) ይሖዋ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይህንን ቃሉን ፈጽሟል።

16 አምላክ እንደሚከተለው በማለት የገባውን ቃልም ፈጽሟል:- “በዚያን ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፣ በምድርም ላይ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረት ጋር፣ ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ሁሉም በሰላም እንዲኖሩ፣ ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን፣ ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።” (ሆሴዕ 2:18) ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ቀሪዎች አራዊትን ሳይፈሩ ተረጋግተውና ተማምነው መኖር ችለዋል። ይህ ትንቢት በ1919 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ነጻ በወጡበት ወቅትም ተፈጽሟል። በአሁኑ ጊዜ፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ካላቸው ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይኖራሉ። በእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል የአውሬነት ባሕርያት አይታዩም።—ራእይ 14:8፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ ገላትያ 6:16

ከትምህርቱ ጥቅም ማግኘት

17-19. (ሀ) በእነዚህ አንቀጾች ላይ የትኞቹን የይሖዋ ባሕርያት እንድንኮርጅ ተበረታተናል? (ለ) የይሖዋ ምሕረትና ርኅራኄ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

17 አምላክ መሐሪና ርኅሩኅ ነው፤ እኛም እነዚህን ባሕርያት ልናዳብር ይገባል። የሆሴዕ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ከሚሰጡን ትምህርቶች አንዱ ይህ ነው። (ሆሴዕ 1:6, 7፤ 2:23) አምላክ ንስሐ ለገቡት እስራኤላውያን ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከሚከተለው ምሳሌ ጋር የሚስማማ ነው:- “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።” (ምሳሌ 28:13) “እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላትም ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን የሚያጽናኑ ናቸው።—መዝሙር 51:17

18 የሆሴዕ ትንቢት አምላካችን ርኅሩኅና መሐሪ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። አንዳንዶች ከጽድቅ ጎዳናዎቹ ዘወር ቢሉም እንኳ ንስሐ ገብተው መመለስ ይችላሉ። እንዲህ ካደረጉ ደግሞ ይሖዋ በደስታ ይቀበላቸዋል። በምሳሌያዊ መንገድ እንደ ሚስቱ ተደርገው ከተገለጹት ከእስራኤል ብሔር አባላት አንዳንዶቹ ንስሐ ሲገቡ ምሕረት አሳይቷቸዋል። ትእዛዛቱን በመጣስ ‘የእስራኤልን ቅዱስ ቢያስቆጡትም እንኳ እርሱ ግን መሓሪ እንደ መሆኑ መጠን ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን አሰበ።’ (መዝሙር 78:38-41) እንዲህ ያለው ምሕረት ርኅሩኅ ከሆነው አምላካችን ከይሖዋ ጋር መሄዳችንን እንድንቀጥል ሊገፋፋን ይገባል።

19 በእስራኤል ውስጥ እንደ መግደል፣ መስረቅና ማመንዘር የመሳሰሉት ኃጢአቶች ተስፋፍተው የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ሕዝቡን ‘በፍቅር ቃል አነጋግሯቸዋል።’ (ሆሴዕ 2:14፤ 4:2) ይሖዋ ባሳየው ምሕረትና ርኅራኄ ላይ ስናሰላስል ልባችን ሊነካ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ሊጠናከር ይገባል። እንግዲያው እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን እንጠይቅ:- ‘ከሌሎች ጋር ባለኝ ግንኙነት የይሖዋን ምሕረትና ርኅራኄ ይበልጥ መኮረጅ የምችለው እንዴት ነው? አንድ የእምነት ባልንጀራዬ ቢያስቀይመኝና ይቅርታ ቢጠይቀኝ ልክ እንደ አምላክ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነኝ?’—መዝሙር 86:5

20. አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች መተማመን እንደምንችል የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

20 አምላክ እውነተኛ ተስፋ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ “የአኮርንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሆሴዕ 2:15) ጥንት የነበረችውና በሚስት የተመሰለችው የይሖዋ ድርጅት ‘የአኮር ሸለቆ’ ወደሚገኝበት የትውልድ አገሯ እንደምትመለስ እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ተሰጥቷት ነበር። በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይህ ተስፋ መፈጸሙ ይሖዋ ከፊታችን ባስቀመጠልን የተረጋገጠ ተስፋ ለመደሰት በቂ ምክንያት ይሆነናል።

21. እውቀት ከአምላክ ጋር እንድንሄድ በመርዳት ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

21 ከአምላክ ጋር መመላለሳችንን ለመቀጠል ስለ እርሱ እውቀት መሰብሰብና የተማርነውን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። በእስራኤል ውስጥ ይሖዋን ማወቅ ጨርሶ ጠፍቶ ነበር። (ሆሴዕ 4:1, 6) አንዳንዶች ግን መለኮታዊውን ትምህርት ከፍ አድርገው ይመለከቱትና ከተማሩት ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖሩ ስለነበር በእጅጉ ተባርከዋል። ሆሴዕ እንዲህ ካደረጉት ሰዎች አንዱ ነው። በኤልያስ ዘመን የነበሩትና ጉልበታቸውን ለበዓል ያላንበረከኩት 7,000 እስራኤላውያንም እንዲሁ አድርገዋል። (1 ነገሥት 19:18፤ ሮሜ 11:1-4) እኛም ከአምላክ ለምናገኘው መመሪያ ያለን አድናቆት ከእርሱ ጋር መሄዳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—መዝሙር 119:66፤ ኢሳይያስ 30:20, 21

22. ስለ ክህደት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

22 ይሖዋ በሕዝቡ መካከል አመራር የሚሰጡት ወንዶች ክህደትን እንዲያስወግዱ ይጠብቅባቸዋል። ሆኖም ሆሴዕ 5:1 በእስራኤል ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እናንተ ካህናት፤ ይህን ስሙ! እናንት እስራኤላውያን፤ አስተውሉ! የንጉሥ ቤት ሆይ፤ ስሙ! ይህ ፍርድ በእናንተ ላይ ነው፤ በምጽጳ ወጥመድ፣ በታቦርም ላይ የተዘረጋ መረብ ሆናችኋልና።” ከሃዲ የሆኑት መሪዎች እስራኤላውያንን በጣዖት አምልኮ እንዲካፈሉ በማነሳሳት ወጥመድና መረብ ሆነውባቸው ነበር። የታቦር ተራራና ምጽጳ የተባለው ቦታ እንዲህ ያለው የሐሰት አምልኮ ማዕከል ሳይሆኑ አይቀሩም።

23. ሆሴዕ ምዕራፍ 1 እስከ 5ን በማጥናትህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

23 እስካሁን ባደረግነው ጥናት የሆሴዕ ትንቢት ይሖዋ መሐሪ፣ ተስፋ የሚሰጥ፣ መመሪያዎቹን ተግባራዊ የሚያደርጉትን የሚባርክ እንዲሁም ክህደትን የሚጠላ አምላክ እንደሆነ አሳይቶናል። እንግዲያው ቀደም ባሉት ዘመናት እንደነበሩት ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም ይሖዋን እንፈልግ፤ እንዲሁም ሁልጊዜ እርሱን ለማስደሰት እንጣር። (ሆሴዕ 5:15) እንዲህ ብናደርግ መልካም የሆነውን የምናጭድ ከመሆኑም በላይ በታማኝነት ከአምላክ ጋር የሚሄዱ ሁሉ የሚያገኙትን ተወዳዳሪ የሌለው ደስታና ሰላም እናገኛለን።—መዝሙር 100:2፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በገላትያ 4:21-26 ላይም ምሳሌያዊ ድራማ ተጠቅሷል። ይህንን ድራማ በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 693, 694 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የመሠረተው ጋብቻ የምን ምሳሌ ነበር?

• ይሖዋ በእስራኤል ላይ ክስ የመሠረተው ለምንድን ነው?

በሆሴዕ ምዕራፍ 1 እስከ 5 ላይ ከሚገኘው ትምህርት ልብህን የነካው የትኛው ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሆሴዕ ሚስት ማንን እንደምትወክል ታውቃለህ?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት የሰማርያ ነዋሪዎች በአሦራውያን ተማርከዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደስተኛ የሆነው ሕዝብ ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ