የራስን ጥቅም መሠዋት የይሖዋን በረከት ያስገኛል
“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው”
የራስን ጥቅም መሠዋት የይሖዋን በረከት ያስገኛል
ጥቅጥቅ ባለው የካሜሩን ደን ውስጥ አንድ ሰው በብስክሌት እየተጓዘ ነው። ሌሎችን ለማበረታታት ሲል በጎርፍ በተጥለቀለቁ መንገዶች ላይና በጭቃ ውስጥ ብስክሌቱን እያሽከረከረ ለሰዓታት የሚጓዘው ይህ ሰው የተለያዩ አደጋዎች ያጋጥሙታል። በዚምባብዌ የሚገኙ ሌሎች ደግሞ ገለልተኛ በሆነ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ለማስተማር ብለው በጣም የሞሉ ወንዞችን በመሻገር አሥራ አምስት ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛሉ። በዚህ ወቅት ልብስና ጫማቸው በውኃ እንዳይርስ አውልቀው በጭንቅላታቸው ላይ አስተካክለው በማስቀመጥ ወንዙን ይሻገራሉ። በሌላ ቦታ ደግሞ አንዲት ሴት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናት ነርስ ጊዜ የሚኖራት ንጋት አካባቢ ብቻ ስለሆነ እርሷን ለመርዳት ስትል ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ ከእንቅልፏ ትነሳለች።
ይህን መሰሉን ጥረት የሚያደርጉትን እነዚህን ሰዎች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች የሚያስተምሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸው ነው። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሲባል የዘወትርና ልዩ አቅኚዎችን፣ ሚስዮናውያንን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቴላውያንን ያጠቃልላል። እነርሱም ባላቸው የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ተለይተው ይታወቃሉ። a
ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ” ሲል የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ይሁን እንጂ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?
እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በይሖዋ አገልግሎት ራሳቸውን ያስጠመዱበትን ምክንያት ሲጠየቁ ለአምላክና ለሰው ልጆች ካላቸው ፍቅር የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ። (ማቴዎስ 22:37-39) አዎን፣ ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ለተግባር የሚያነሳሳቸው ፍቅር ካልሆነ ዋጋ ስለሌለው እንዲህ ብለው መመለሳቸው የተገባ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:1-3
የራስን ጥቅም በመሠዋት ማገልገል
ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሁሉም ክርስቲያኖች ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ያስተላለፈውን ጥሪ ይቀበላሉ። (ማቴዎስ 16:24) ራስን መካድ ማለት የይሖዋ አምላክና የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት ለመሆን እንዲሁም በእነርሱ ለመመራት ራስን በፈቃደኝነት ማቅረብ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ብዙዎች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ እንዲያገለግሉ አነሳስቷቸዋል።
ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በሳኦ ፖሎ፣ ብራዚል የሚኖሩትን የ56 ዓመቷን ዡልያን እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። “አንድ ቻይናዊ ወንድም ስልክ ደውሎ ቻይንኛ ለመማር ፈቃደኛ እንደሆንኩ ጠየቀኝ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ። “ዕድሜዬ ስለገፋ አዲስ ቋንቋ መማር እችላለሁ ብዬ አላስብም ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህን ከባድ ሥራ ለመቀበል ተስማማሁ። በአሁኑ ጊዜ በቻይንኛ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን ለሌሎች ማካፈል ችያለሁ።”
በፔሩ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በቅርብ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዘወትር አቅኚዎች ለማንም ወዳልተመደቡ የአገልግሎት ክልሎች በመሄድ ድፍረትና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አሳይተዋል። መሠረተ ልማት ወዳልተዘረጋባቸው እንዲሁም ሥራ የማግኘት ዕድል አናሳ ወደሆነባቸው ራቅ ወዳሉ ከተሞች ጭምር ሄደዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በተመደቡበት ቦታ ለመቆየት ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አገልግሎታቸው በየቦታው እድገት እንዲገኝ አስችሏል። እነዚህ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉ የዘወትር አቅኚዎች ባከናወኑት ሥራ ምክንያት አዳዲስ ቡድኖች መቋቋማቸውን ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሪፖርት አድርገዋል።”
አንዳንድ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። (ሮሜ 16:3,4) አፍሪካ ውስጥ በአንድ በጦርነት በሚታመስ አካባቢ የሚያገለግል የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “እኔና ባለቤቴ የዓማጽያኑን ክልልና መንግሥት የሚቆጣጠራቸውን ክልሎች የሚለየው የመጨረሻው ኬላ ላይ ከመድረሳችን በፊት አራት የዓማጽያኑ መኮንኖችና ጠባቂዎቻቸው ያዙን። ከዚያም ማንነታችንን ለማወቅ ስለፈለጉ የመታወቂያ ካርዳችንን እንድናሳያቸው ጠየቁን። መታወቂያችንን ሲመለከቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከሚገኙት አካባቢዎች የመጣን መሆናችንን በማወቃቸው ተጠራጠሩን። እንዲያውም ሰላይ ነህ ብለው ጉድጓድ ውስጥ ሊጥሉኝ ወሰኑ። እኔ ግን ስለማንነታችን በግልጽ ስለነገርኳቸው እንድንሄድ ፈቀዱልን።” ይህ ወንድምና ባለቤቱ የራሳቸውን ጥቅም በመሠዋት ባደረጉላቸው ጉብኝት ጉባኤዎቹ ምንኛ አመስጋኞች ናቸው!
ምንም እንኳ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እነዚህን የመሰሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ ነው። (ኢሳይያስ 6:8) እነዚህ ትጉህ ሠራተኞች ይሖዋን ለማገልገል ያገኙትን ልዩ መብት ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በተመሳሳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎችም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በማሳየት ይሖዋን እያወደሱ ይገኛሉ። ይሖዋም በምላሹ እየባረካቸው ነው። (ምሳሌ 10:22) እነዚህ ጠንካራ ሠራተኞች የይሖዋ በረከትና እርዳታ እንደማይለያቸው በመተማመን እንደ መዝሙራዊው “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” ይላሉ።—መዝሙር 121:2 NW
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ኅዳር/ታኅሣሥ የሚለውን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል።”—መዝሙር 110:3
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ይሖዋ ለእርሱ ያደሩ አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል
“ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።”—1 ቆሮንቶስ 15:58
“እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም።”—ዕብራውያን 6:10