በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የይሖዋ መንገድ ቅን ነው’

‘የይሖዋ መንገድ ቅን ነው’

‘የይሖዋ መንገድ ቅን ነው’

“የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነውና፤ ጻድቃን ይሄዱበታል።”—ሆሴዕ 14:9

1, 2. ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት የጀመረው እንዴት ነበር? ሆኖም ሕዝቡ ምን ሆኑ?

 ይሖዋ በሙሴ ዘመን እስራኤላውያንን በብሔር መልክ ሲያደራጃቸው አጀማመራቸው ቀና ነበር። ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሁኔታቸው በጣም ስለተበላሸ አምላክ እጅግ በደለኞች ሆነው አግኝቷቸዋል። ይህም ከምዕራፍ 10 እስከ 14 ባለው የሆሴዕ ትንቢት ላይ በግልጽ ሰፍሯል።

2 የእስራኤላውያን ልብ ግብዝ ሆኗል። በአሥሩ ነገድ መንግሥት ሥር ያለው ሕዝብ ‘ክፋትን በመዝራት’ ኃጢአትን አጭዷል። (ሆሴዕ 10:1, 13) ይሖዋ “እስራኤል ገና ሕፃን ሳለ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት” ብሏል። (ሆሴዕ 11:1) አምላክ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ቢያወጣቸውም የእነርሱ ምላሽ ግን ውሸትና ተንኰል ነበር። (ሆሴዕ 11:12) በዚህም ምክንያት ይሖዋ “ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ፍቅርንና ፍትሕን ጠብቅ” የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል።—ሆሴዕ 12:6

3. ዓመጸኛዋ ሰማርያ ምን ሊደርስባት ነው? እስራኤላውያን ምሕረት ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ዓመጸኛዋ ሰማርያና ንጉሥዋ አስከፊ ጥፋት ይደርስባቸዋል። (ሆሴዕ 13:11, 16) ሆኖም የሆሴዕ ትንቢት የመጨረሻ ምዕራፍ የሚጀምረው “እስራኤል ሆይ፤ . . . ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ” በሚለው ልመና ነው። እስራኤላውያን ይቅርታ ከጠየቁ አምላክ የምሕረት እጁን ይዘረጋላቸዋል። እርግጥ “የእግዚአብሔር መንገድ ቅን” መሆኑን መቀበልና በመንገዱ መሄድ ይኖርባቸዋል።—ሆሴዕ 14:1-6, 9

4. በሆሴዕ ትንቢት ውስጥ የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን?

4 ከዚህ ቀጥሎ በምንመረምረው የሆሴዕ ትንቢት ውስጥ ከአምላክ ጋር ለመሄድ የሚረዱ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመለከታለን:- (1) ይሖዋ ከግብዝነት የራቀ አምልኮ እንድናቀርብለት ይጠብቅብናል፤ (2) አምላክ ለሕዝቦቹ ጽኑ ፍቅሩን ያሳያቸዋል፤ (3) ምንጊዜም ቢሆን በይሖዋ መታመን አለብን፤ (4) የይሖዋ መንገዶች ሁልጊዜ ቀና ናቸው እንዲሁም (5) ኃጢአተኞች ወደ ይሖዋ መመለስ ይችላሉ።

ይሖዋ ግብዝነት የሌለበት አምልኮ እንድናቀርብለት ይፈልጋል

5. ይሖዋ ምን ዓይነት አገልግሎት እንድናቀርብለት ይጠብቅብናል?

5 ይሖዋ ንጹሕና ግብዝነት የሌለበት ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብለት ይጠብቅብናል። እስራኤል ግን ፍሬ እንደማይሰጥ “የተንዠረገገ ወይን” ሆኖ ነበር። የብሔሩ ነዋሪዎች ለሐሰት አምልኮ የሚገለገሉባቸውን ‘ብዙ መሠዊያዎች’ ሠርተዋል። እንዲያውም እነዚህ ከሃዲዎች ዐምዶችን (ለርኩስ አምልኮ የሚገለገሉባቸው ረዣዥም ሐውልቶች ሊሆኑ ይችላሉ) አቁመዋል። ይሖዋ እነዚህን መሠዊያዎችና ዐምዶች ለማፈራረስ ወስኗል።—ሆሴዕ 10:1, 2

6. ከአምላክ ጋር ለመሄድ የትኛውን ባሕርይ ማስወገድ ይኖርብናል?

6 ግብዝነት በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ቦታ የለውም። እስራኤላውያን ግን ‘ልባቸው አታላይ ሆኖ’ ነበር! ለይሖዋ የተወሰነ ብሔር አባላት በመሆን በአንድ ወቅት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን የገቡ ቢሆንም ግብዞች ሆነው ተገኙ። እኛ ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን? ራሳችንን ለአምላክ ከወሰንን ግብዞች መሆን አይገባንም። ምሳሌ 3:32 “እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል” በማለት ያስጠነቅቃል። ከአምላክ ጋር መሄድ እንድንችል “ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ [“ግብዝነት ከሌለበት እምነት የሚወጣ፣” የ1954 ትርጉም] ፍቅር” ማሳየት ይኖርብናል።—1 ጢሞቴዎስ 1:5

አምላክ ለሕዝቦቹ ጽኑ ፍቅሩን ያሳያቸዋል

7, 8. (ሀ) አምላክ ጽኑ ፍቅሩን የሚያሳየን ምን ካደረግን ነው? (ለ) ከባድ ኃጢአት ከሠራን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 ይሖዋን ከግብዝነት በራቀና ቀና በሆነ መንገድ ካመለክነው ፍቅራዊ ደግነቱን ወይም ጽኑ ፍቅሩን ያሳየናል። ዓመጸኞቹ እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ነበር:- “ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና።”—ሆሴዕ 10:12

8 እስራኤላውያን ተጸጽተው ይሖዋን ቢፈልጉ ምን ነበረበት! ይህን ቢያደርጉ በደስታ “ጽድቅን” ያስተምራቸው ነበር። ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ይሖዋ ይቅር እንዲለን በመጸለይና የጉባኤ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያደርጉልን በመጠየቅ ይሖዋን እንፈልግ። (ያዕቆብ 5:13-16) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል” ስለሚል የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር ለማግኘት ጥረት ልናደርግ ይገባል። (ገላትያ 6:8) ‘በመንፈስ ብንዘራ’ አምላክ ታማኝ ወይም ጽኑ ፍቅሩን ያሳየናል።

9, 10. ሆሴዕ 11:1-4 በእስራኤላውያን ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ሕዝቦቹን የሚይዘው በፍቅር እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በሆሴዕ 11:1-4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል:- “እስራኤል ገና ሕፃን ሳለ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት። . . . ለበኣል አማልክት ሠዉ፤ ለምስሎችም ዐጠኑ። ኤፍሬምን [እስራኤልን] እጁን ይዤ፣ እንዲራመድ ያስተማርሁት እኔ ነበርሁ፤ ነገር ግን የፈወስኋቸው እኔ እንደ ሆንሁ፣ እነርሱ አላስተዋሉም። በሰው የርኅራኄ ገመድ፣ በፍቅርም ሰንሰለት ሳብኋቸው፤ ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ አነሣሁላቸው፤ ዝቅ ብዬም መገብኋቸው።”

10 እዚህ ላይ እስራኤል በትንሽ ልጅ ተመስሏል። ይሖዋ እስራኤላውያንን በእጁ ይዞ በመምራት በእግራቸው መሄድ እንዲችሉ በፍቅር አስተምሯቸዋል። ‘በፍቅር ሰንሰለት’ ሲስባቸው ቆይቷል። እንዴት ያለ ልብ የሚነካ ሥዕላዊ አገላለጽ ነው! ልጃችሁ መራመድ እንዲችል ‘ዳዴ’ እያላችሁ ስታለማምዱት ይታያችሁ። እጃችሁን ትዘረጉለት ይሆናል። እንዲያውም ሕፃኑ እንዳይወድቅ የሚረዳው ገመድ ታዘጋጁለት ይሆናል። ይሖዋ ለእናንተ ያለው ፍቅርም የዚህን ያህል ጥልቅ ነው። ‘በፍቅር ሰንሰለት’ ሊመራችሁ ይወዳል።

11. አምላክ ‘ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ ያነሣላቸው’ በምን መንገድ ነው?

11 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ሲገልጽ “ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ አነሣሁላቸው፤ ዝቅ ብዬም መገብኋቸው” ብሏል። አንድ ከብት ሲመገብ እንዳይቸገር ቀንበሩ እንደሚነሳለት ሁሉ አምላክ ቀንበራቸውን አቅልሎላቸው ነበር። የጠላቶቻቸው ጨቋኝ ቀንበር የሚጫንባቸው ለይሖዋ በመገዛት የሚሸከሙትን ቀንበር ከሰበሩ ብቻ ነው። (ዘዳግም 28:45, 48፤ ኤርምያስ 28:14) እኛም በዋነኛው ጠላታችን በሰይጣን መዳፍ ውስጥ ላለመግባትና እርሱ በሚጭንብን የጭቆና ቀንበር ላለመሠቃየት እንጠንቀቅ። ከዚህ ይልቅ ከአፍቃሪው አምላካችን ጋር በታማኝነት መሄዳችንን እንቀጥል።

ዘወትር በይሖዋ ታመኑ

12. በሆሴዕ 12:6 መሠረት ከአምላክ ጋር መሄዳችንን መቀጠል እንድንችል ምን ያስፈልገናል?

12 ከአምላክ ጋር መሄዳችንን ለመቀጠል ዘወትር በእርሱ መታመን አለብን። እስራኤላውያን “ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ፍቅርንና ፍትሕን ጠብቅ፤ ዘወትርም በአምላክህ ታመን” ተብለው ነበር። (ሆሴዕ 12:6) ከዳተኞቹ እስራኤላውያን ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት፣ ፍትሕ በማድረግና ‘ዘወትር በአምላክ በመታመን’ ንስሐ ገብተው ወደ ይሖዋ መመለሳቸውን ማሳየት ይችሉ ነበር። ከአምላክ ጋር በታማኝነት ስንሄድ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ረጅም ቢሆን አሁንም ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት፣ ፍትሕ ማድረግና በአምላክ መታመን ቁርጥ ውሳኔያችን ሊሆን ይገባል።—መዝሙር 27:14

13, 14. ጳውሎስ ሆሴዕ 13:14ን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ይህስ በይሖዋ ለመታመን ምን ምክንያት ይሰጠናል?

13 ሆሴዕ ለእስራኤላውያን የተናገረው ትንቢት በአምላክ ለመታመን የሚያበቃቸውን ምክንያት ይጠቅሳል። ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ?” (ሆሴዕ 13:14) ይሖዋ በዚያን ጊዜ እስራኤላውያንን ቃል በቃል ከሞት የመታደግ ዓላማ የነበረው ባይሆንም በመጨረሻ ግን ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ በዚህም ሞት ተቀዳጅቶት የነበረውን የይስሙላ ድል ይሽርበታል።

14 ጳውሎስ ለቅቡዓን የእምነት ባልደረቦቹ በላከው ደብዳቤ ላይ ከሆሴዕ ትንቢት ጠቅሶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ ‘ሞት በድል ተዋጠ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ ‘ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?’ የሞት መንደፊያ ኀጢአት ነው፤ የኀጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” (1 ቆሮንቶስ 15:54-57) ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሞት እንደሚነሱ የሚያጽናና ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ይህ በይሖዋ ለመታመን የሚያበቃ አስደሳች ምክንያት ነው! ይሁን እንጂ ከትንሣኤ ተስፋ በተጨማሪ ከአምላክ ጋር እንድንሄድ የሚያበረታታን ጠንካራ ምክንያት አለ።

የይሖዋ መንገድ ምንጊዜም ቅን ነው

15, 16. ስለ ሰማርያ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር? ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?

15 ‘የይሖዋ መንገድ ቅን እንደሆነ’ ያለን እምነት ከአምላክ ጋር መሄዳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። የሰማርያ ነዋሪዎች በአምላክ የጽድቅ መንገድ አልተመላለሱም። ስለሆነም ኃጢአት በመፈጸማቸውና በይሖዋ ባለመታመናቸው የሚገባቸውን ብድራት መቀበል ይኖርባቸዋል። “የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤ በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ሆሴዕ 13:16) ሰማርያን ድል ያደረጓት አሦራውያን እንዲህ ያለውን ጭካኔ ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ ሰዎች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ያረጋግጣሉ።

16 ሰማርያ የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ሰማርያ የሚለው ስም የዚህን መንግሥት መላ ግዛት ሊያመለክት ይችላል። (1 ነገሥት 21:1) አሦራዊው ንጉሥ ሰልምናሶር አምስተኛ በ742 ከክርስቶስ ልደት በፊት የሰማርያን ከተማ ከበበ። በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰማርያ ድል ስትሆን በከተማይቱ ይኖሩ ከነበሩት ታላላቅ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ መስጴጦምያና ወደ ሜዶን በግዞት ተወሰዱ። ሰማርያን ድል አድርጎ የያዘው ሰልምናሶር አምስተኛ ይሁን ወራሹ ዳግማዊ ሳርጎን በእርግጠኝነት አይታወቅም። (2 ነገሥት 17:1-6, 22, 23፤ 18:9-12) ይሁን እንጂ የሳርጎን መዝገብ 27,290 እስራኤላውያን በላይኛው ኤፍራጥስና በሜዶን ወደሚገኙ ቦታዎች እንደተጋዙ ያመለክታል።

17. የአምላክን መሥፈርቶች ከማቃለል ይልቅ ምን ማድረግ አለብን?

17 የሰማርያ ነዋሪዎች በይሖዋ የጽድቅ መንገድ ለመሄድ አሻፈረን ማለታቸው ከባድ መዘዝ አስከትሎባቸዋል። ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እኛም የጽድቅ መሥፈርቶቹን በንቀት በመመልከት ኃጢአት የመሥራት ልማድ ካለን አሳዛኝ ውጤት ይደርስብናል። እንዲህ ያለውን የክፋት መንገድ ከመከተል እንራቅ! ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ተግባራዊ እናድርግ:- “ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።”—1 ጴጥሮስ 4:15, 16

18. አምላክን ‘ማመስገን’ የምንችለው እንዴት ነው?

18 በራሳችን አስተሳሰብ እየተመራን የመሰለንን ከማድረግ ይልቅ በአምላክ ቀና መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ‘እናመሰግናለን።’ ቃየን ኃጢአት እያደባበት እንደሆነ ይሖዋ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከመስማት ይልቅ በራሱ መንገድ በመሄዱ ሕይወት አጠፋ። (ዘፍጥረት 4:1-8) በለዓም የሞዓብ ንጉሥ የሰጠውን ዋጋ ቢቀበልም እስራኤልን ለመርገም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀረ። (ዘኍልቍ 24:10) ሌዋዊው ቆሬና ሌሎች እስራኤላውያን በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ በማመጻቸው አምላክ አጠፋቸው። (ዘኍልቍ 16:1-3, 31-33) እኛም “በቃየን [የነፍሰ ገዳይነት] መንገድ” መሄድ፣ “በበለዓም ስሕተት” መውደቅ ወይም ‘በቆሬ ዐመፅ’ መጥፋት እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (ይሁዳ 11) ይሁን እንጂ ማናችንም ብንሳሳት የሆሴዕ ትንቢት ማጽናኛ ይሰጠናል።

ኃጢአተኞች ወደ ይሖዋ መመለስ ይችላሉ

19, 20. ንስሐ የገቡት እስራኤላውያን ምን ዓይነት መሥዋዕት ማቅረብ ይችሉ ነበር?

19 ከባድ ኃጢአት በመሥራት የተደናቀፉ እንኳን ወደ ይሖዋ መመለስ ይችላሉ። በሆሴዕ 14:1, 2 ላይ የሚከተለውን ልመና እናገኛለን:- “እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ። የምትሉትን ቃል ይዛችሁ፣ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እንዲህም በሉት፤ ‘ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣ በምሕረትህ ተቀበለን።’”

20 ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን ‘የከንፈራቸውን ፍሬ’ ማቅረብ ችለው ነበር። ይህም ከልብ የሚቀርብ የውዳሴ መሥዋዕት ነው። ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ . . . ለእግዚአብሔር እናቅርብ” ሲል የመከረው ይህን ትንቢት በማስታወስ ነበር። (ዕብራውያን 13:15) ዛሬም ከአምላክ ጋር መሄድና እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት ማቅረብ መቻላችንን እንደ ታላቅ መብት እንቆጥረዋለን!

21, 22. ንስሐ የገቡት እስራኤላውያን ምን ዓይነት ተሐድሶ ያገኛሉ?

21 የክህደት አካሄዳቸውን ትተው ወደ አምላክ የተመለሱ እስራኤላውያን ‘የከንፈራቸውን ፍሬ’ ለአምላክ አቅርበዋል። ይህን በማድረጋቸውም አምላክ ቃል እንደገባው የመንፈሳዊ ተሐድሶ ዘመን መጥቶላቸዋል። ሆሴዕ 14:4-7 እንዲህ ይላል:- “እኔ [ይሖዋ] ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤ እንዲሁ እወዳቸዋለሁ፤ ቁጣዬ ከእነርሱ ተመልሶአልና። እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤ እንደ ውብ አበባ ያብባል፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣ ሥር ይሰዳል፤ ቅርንጫፉ ያድጋል፤ ውበቱ እንደ ወይራ ዛፍ፣ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይሆናል። ሰዎች እንደ ገና ከጥላው በታች ያርፋሉ፤ እርሱም እንደ እህል ይለመልማል፤ እንደ ወይን ተክል ያብባል፤ ዝናውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ይወጣል።”

22 ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን መንፈሳዊ ፈውስ የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ዳግመኛ የአምላክን ፍቅር ያገኛሉ። ይሖዋ አብዝቶ ስለሚባርካቸው እንደሚያረካ ጠል ይሆንላቸዋል። ሕዝቦቹ ተመልሰው በሚቋቋሙበት ጊዜ ‘ውበታቸው እንደ ወይራ ዛፍ’ ይሆናል፤ በአምላክ መንገድም ይሄዳሉ። እኛስ ከይሖዋ አምላክ ጋር ለመሄድ የቆረጥን እንደመሆናችን ምን ይፈለግብናል?

ቀና በሆነው የይሖዋ መንገድ መሄዳችሁን ቀጥሉ

23, 24. የሆሴዕ መጽሐፍ የሚደመደመው በየትኛው የሚያበረታታ ትንቢት ነው? ይህስ እኛን የሚነካን እንዴት ነው?

23 ከአምላክ ጋር መሄዳችንን ለመቀጠል ‘ከሰማይ የሆነችውን ጥበብ’ በሥራ ማዋልና ቀና ከሆነው መንገዱ ጋር ሁልጊዜ ተስማምተን መኖር አለብን። (ያዕቆብ 3:17, 18) የሆሴዕ ትንቢት የመጨረሻ ቁጥር እንዲህ ይላል:- “ጥበበኛ የሆነ እነዚህን ነገሮች ያስተውላል፤ አስተዋይም እነዚህን ነገሮች ይረዳል። የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነውና፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ዐመፀኞች ግን ይሰናከሉበታል።”—ሆሴዕ 14:9

24 በዚህ ዓለም ጥበብና መሥፈርት ከመመራት ይልቅ ቀና በሆነው የአምላክ መንገድ ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ዘዳግም 32:4) ሆሴዕ ለ59 ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት በአምላክ ቀና መንገድ ሄዷል። ጥበበኛና ልባም የሆኑ ሁሉ የሚናገረውን እንደሚረዱ በመገንዘብ መለኮታዊውን መልእክት በታማኝነት አሰምቷል። እኛስ? ይሖዋ ምሥራቹን እንድንሰብክ እስከፈቀደልን ድረስ የእርሱን ጸጋ የሚቀበሉ ጥበበኛ ሰዎችን መፈለጋችንን እንቀጥላለን። የምሥክርነቱን ሥራ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ጋር ሙሉ በሙሉ ተባብረን በመሥራታችን ደስተኞች ነን።—ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም

25. የሆሴዕን ትንቢት መመርመራችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

25 የሆሴዕን ትንቢት መመርመራችን አምላክ በሚያዘጋጅልን አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የመውረስ ተስፋ ለማግኘት ከእርሱ ጋር መሄዳችንን እንድንቀጥል ሊረዳን ይገባል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ይሁዳ 20, 21) ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! ‘የይሖዋ መንገድ ቅን ነው’ የምንለው ከልባችን መሆኑን በቃልም ሆነ በተግባር ማሳየታችንን ብንቀጥል ይህ ተስፋ በግለሰብ ደረጃ ይፈጸምልናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ካቀረብንለት ምን ያደርግልናል?

• ዘወትር በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

• የይሖዋ መንገድ ቅን መሆኑን የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

• ቀና በሆነው የይሖዋ መንገድ መመላለሳችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጡህን መንፈሳዊ እርዳታ ተቀበል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሆሴዕ ትንቢት ይሖዋ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት ለማሳደር ምክንያት ይሆነናል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ከይሖዋ ጋር መሄድህን ቀጥል