በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ

ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ

ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ

“ስላዳመጥከኝ አመሰግንሃለሁ።” በቅርቡ እንዲህ ያለህ ሰው አለ? ይህ ምንኛ የሚያበረታታ አባባል ነው! ጥሩ አድማጭ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ይወደዳል ማለት ይቻላል። በችግር የተደቆሱ ወይም የተጨነቁ ሰዎችን ከልብ በማዳመጥ ልናጽናናቸው እንችላለን። ደግሞስ ጥሩ አድማጭ መሆን ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን አያደርግም? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ የሚያስችለን ዋነኛ መንገድ ነው።—ዕብራውያን 10:24

ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ጥሩ አድማጮች አይደሉም። ሌሎች የሚነግሯቸውን ጆሯቸውን ሰጥተው ከማዳመጥ ይልቅ ምክር መስጠት፣ የራሳቸውን ተሞክሮ መናገር ወይም አመለካከታቸውን መግለጽ ይቀናቸዋል። እውነትም ማዳመጥ ጥበብ ነው። ታዲያ ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥን እንዴት መማር ይቻላል?

ዋነኛው ቁልፍ

ይሖዋ ታላቅ ‘አስተማሪያችን’ ነው። (ኢሳይያስ 30:20) ማዳመጥን በተመለከተም ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለው። እስቲ ነቢዩ ኤልያስን እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ኤልያስ የንግስት ኤልዛቤልን ዛቻ ፈርቶ ወደ ምድረ በዳ የሸሸ ከመሆኑም ሌላ ሞትን ተመኝቶ ነበር። በእዚያ እያለም የአምላክ መልአክ አነጋገረው። ይሖዋ ነቢዩ ምን ያህል እንደፈራ ሲናገር ካዳመጠው በኋላ ታላቅ ኃይሉን አሳየው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኤልያስ ፍርሃቱ ስለተወገደለት ወደተሰጠው ሥራ ተመለሰ። (1 ነገሥት 19:2-15) ይሖዋ አገልጋዮቹ የደረሰባቸውን ጭንቀት ጊዜ ሰጥቶ የሚያዳምጠው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ስለ እነርሱ ስለሚያስብ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:7) አዎን፣ ጥሩ አድማጭ ለመሆን የሚያስችለው ቁልፍ ለሌሎች ከልብ ማሰብ ነው።

አንድ በቦሊቪያ የሚኖር ሰው ከባድ ኃጢአት በፈጸመ ጊዜ ከእምነት ባልንጀራው ይህን መሰሉን እርዳታ በማግኘቱ የተሰማውን አድናቆት ገልጿል። ግለሰቡ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በሕይወቴ ውስጥ በጣም ያዘንኩበት ወቅት ነበር። አንድ ወንድም ጊዜ ወስዶ ባያዳምጠኝ ኖሮ በቀላሉ ተስፋ ቆርጬ ይሖዋን ማገልገሌን አቆም ነበር። ይህ ወንድም ብዙ ያልተናገረ ቢሆንም ሲያዳምጠኝ በእርግጥ እንደሚያስብልኝ ስለተገነዘብኩ አበረታታኝ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቅ ስለነበር ለችግሮቼ መፍትሔውን እንዲነግረኝ አልፈለግኩም። በወቅቱ የሚያስፈልገኝ ስለ ስሜቴ የሚያስብልኝ ሰው እንዳለ ማወቅ ብቻ ነበር። የእርሱ ማዳመጥ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል።”

ፍቅር በተንጸባረቀበት መንገድ በማዳመጥ ረገድ ታላቁ ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኝ አንዲት መንደር እየተጓዙ ነበር። ተስፋ ቆርጠው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ከሞት የተነሳው ኢየሱስም አብሮአቸው መጓዝ ጀመረ። ከዚያም በውስጣቸው ያለውን ለማወቅ ሲል አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቃቸው። እነርሱም ምን ተስፋ አድርገው እንደነበር እንዲሁም በወቅቱ የተሰማቸውን ሐዘንና ግራ መጋባት ገለጹለት። ኢየሱስ የአሳቢነት መንፈስ ስላሳያቸውና ፍቅር እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ስላዳመጣቸው ሁለቱ ደቀ መዛሙርት እርሱን ለማዳመጥ ዝግጁ ሆኑ። ከዚያም ኢየሱስ “በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።”—ሉቃስ 24:13-27

ለማዳመጥ ቅድሚያውን መውሰድ ሌሎች እንዲያዳምጡን የምንረዳበት ፍቅራዊ መንገድ ነው። አንዲት ቦሊቪያዊት ሴት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “የእኔም ሆኑ የባለቤቴ ወላጆች ልጆቼን በማሳድግበት መንገድ ላይ ተቃውሞ ነበራቸው። የእነርሱን ምክር ለመቀበል የከበደኝ ቢሆንም እንደ አንድ ወላጅ እኔ ራሴ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብኝ አላውቅም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ አንዲት የይሖዋ ምሥክር አምላክ ስለገባው ተስፋ ነገረችኝ። ይህች ሴት አመለካከቴን ትጠይቀኝ የነበረበትን መንገድ በማየት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነች ማለት ነው ብዬ ደመደምኩ። ወደ ውስጥ እንድትገባ ከጋበዝኳት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ያሉብኝን ችግሮች በዝርዝር ነገርኳት። እርሷም በትዕግሥት አዳመጠችኝ። ልጆቼ ምን እንዲሆኑ እንደምፈልግና በዚህ ረገድ ባለቤቴ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ ጠየቀችኝ። ሌላውን ለመረዳት ከሚጥር ሰው ጋር አብሮ መሆን እንዴት እረፍት ይሰጣል! ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ሕይወት አስመልክቶ ምን እንደሚል አሳየችኝ። በዚህ ወቅት ያለሁበት ሁኔታ ከሚያሳስባት ሴት ጋር እየተነጋገርኩ እንዳለሁ ገባኝ።”

መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር . . . ራስ ወዳድ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ሌሎችን ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ የራሳችንን ፍላጎቶች ለመተው ፈቃደኛ መሆንን ይጨምራል። ይህም ሰዎች ቁም ነገር በሚያወሩን ሰዓት ቴሌቪዥኑን መዝጋት፣ ጋዜጣ እያነበብን ከሆነም ማስቀመጥ ወይም ሞባይል ስልካችንን ማጥፋት ሊጠይቅብን ይችላል። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ማለት ሌሎች ችግራቸውን ሲነግሩን በተመስጦ ማዳመጥ ማለት ነው። “እንዲህ ስትል በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን ነገር አስታወስከኝ” እንደሚሉ ያሉትን ቃላት በመጠቀም ስለራሳችን ማውራት መጀመር የለብንም። እንዲህ ዓይነቱን ንግግር በሌላ ጊዜ በምናደርጋቸው ወዳጃዊ ውይይቶች ላይ መጠቀማችን ምንም ችግር የሌለው ቢሆንም አንድ ሰው ያጋጠመውን ከበድ ያለ ችግር ሲያወያየን ግን የራሳችንን ጉዳይ ልንተወው ይገባል። ለሌሎች ከልብ እንደምናስብ የምናሳይበት ሌላም መንገድ አለ።

የሌሎችን ስሜት ለመረዳት በማሰብ ማዳመጥ

የኢዮብ ወዳጆች እርሱ ያደረጋቸውን አሥር የሚያክሉ ንግግሮች የሰሙት ቢሆንም እንኳ “ምነው የሚሰማኝ ባገኝ!” በማለት በምሬት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:35) ለምን? ምክንያቱም ያዳመጡበት መንገድ ለእርሱ እረፍት የሚሰጥ አልነበረም። ለኢዮብ ምንም የአሳቢነት መንፈስ አላሳዩም፤ እንዲሁም ስሜቱን አልተረዱለትም። እነዚህ ወዳጆቹ ከልባቸው እንደሚያዳምጡ ሰዎች ዓይነት የሌሎችን ችግር የመረዳት መንፈስ የሚያሳዩ አልነበሩም። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ምክር ሰጥቷል:- “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) እርስ በርስ እንደምንተሳሰብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ለሌሎች ስሜት በመጨነቅና ስሜታቸውን እንደተረዳን በማሳየት ነው። “በጣም ያሳዝናል፣” “ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱህ ሳይሰማህ አይቀርም” እንደሚሉ ያሉትን ስሜታቸውን እንደተረዳንላቸው የሚያሳዩ ሐሳቦች መሰንዘር አሳቢነታችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ሌላው ደግሞ ግለሰቡ የነገረንን በራሳችን አባባል በመድገም እንደተረዳነው ማሳየት ነው። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ሲባል ቃላቱን መስማት ብቻ ሳይሆን ስሜቱንም ጭምር ማስተዋል ማለት ነው።

ሮበርት a ተሞክሮ ያለውና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በአንድ ወቅት ላይ በአገልግሎቴ ተስፋ ቆርጬ ስለነበር አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አነጋገርኩ። እርሱም ከልቡ ያዳመጠኝ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን ለመረዳት ጥረት ያደርግ ነበር። ዝንባሌዬን በተመለከተ ይወቅሰኛል የሚል ፍርሃት እንዳደረብኝ ጭምር የተረዳ ይመስላል። ይህ ወንድም እርሱ ራሱ የዚህ ዓይነቱ ስሜት ተሰምቶት እንደሚያውቅና ስሜቴንም እንደተረዳልኝ ነገረኝ። ይህ ደግሞ በጣም አበርትቶኛል።”

እየተነገረን ባለው ነገር ባንስማማም እንኳ ማዳመጥ እንችላለን? አንድ ሰው ምን እንደሚሰማው ስለነገረንስ ልናመሰግነው ይገባል? አዎን። ወንድ ልጅህ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደተደባደበ ቢነግርህ ወይም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ልጅህ ፍቅር እንደያዛት ብትነግርህስ? በዚህ ወቅት ወላጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ለማስረዳት ከመሞከራቸው በፊት በልጆቹ አእምሮ ውስጥ እየተመላለሰ ያለውን ነገር ለማወቅ ማዳመጥ አይኖርባቸውም?

“የሰው ልብ ሐሳብ [“ምክር፣” የ1954 ትርጉም] እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” በማለት ምሳሌ 20:5 ይናገራል። አንድ ጥበብና ተሞክሮ ያካበተ ሰው ካልጠየቁት በቀር ምክር የማይሰጥ ከሆነ ምክሩን ለማግኘት መጠየቅ ይኖርብን ይሆናል። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ በምናዳምጥበትም ጊዜ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ግለሰቡ ሐሳቡን አውጥቶ እንዲነግረን ለማድረግ ማስተዋል ያስፈልጋል። ጥያቄዎችን መጠየቅ ተገቢ ቢሆንም የግል ጉዳዮቹን የሚያውጣጡ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለብን። እንዲያውም እርሱ ለማውራት ከማይከብዱት ጉዳዮች እንዲጀምር ማበረታታት ጥሩ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ በትዳሯ ውስጥ ያለውን ችግር ለመናገር የፈለገች አንዲት ሚስት ምናልባት ወሬውን ለመጀመር ቀላል ሆኖ የምታገኘው ከባለቤቷ ጋር እንዴት እንደተገናኙና ለመጋባት እንደበቁ በመናገር ሊሆን ይችላል። በአገልግሎት የቀዘቀዘ አንድ ወንድምም እውነትን እንዴት እንደሰማ በመናገር መጀመሩ ይቀለው ይሆናል።

ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ከባድ ነው

በተፈጥሯችን ራሳችንን መከላከል ስለሚቀናን በእኛ የተበሳጨን ሰው ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ይህን ችግር እንዴት ልናስወግደው እንችላለን? ምሳሌ 15:1 “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” በማለት ይናገራል። ግለሰቡ እንዲናገር በደግነት ማበረታታትና ከዚያም ቅሬታውን በሚገልጽበት ወቅት በትዕግሥት ማዳመጥ የለዘበ መልስ የምንሰጥበት አንደኛው መንገድ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ መነታረክ ሁለቱ ግለሰቦች በፊት የተነጋገሩትን ነገር ከመድገም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ሁለቱም ሌላው ወገን እንዳላዳመጣቸው ይሰማቸዋል። አንደኛው ወገን ዝም ብሎ ቢያዳምጥ ኖሮ ሁኔታው እንዴት የተሻለ በሆነ ነበር! በእርግጥም ራስን የመግዛት ባሕርይ ማንፀባረቅ እንዲሁም ፍቅራዊ በሆነ መንገድና በጥበብ ሐሳብን መግለጽ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው” ይላል።—ምሳሌ 10:19

ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የማዳመጥ ችሎታ ይዘነው የምንወለደው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ በጥረትና ራስን በማሠልጠን የምንማረው ጥበብ ነው። በእርግጥም ይህ በጣም ጠቃሚ ችሎታ ነው። ሌሎች ሲናገሩ ማዳመጥ የፍቅር መግለጫ ከመሆኑም ሌላ ለደስታችንም አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የማዳመጥ ችሎታን ማዳበር እንዴት ብልህነት ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምናዳምጥበት ወቅት የራሳችንን ፍላጎቶች ለመተው ፈቃደኞች መሆን አለብን

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድን የተበሳጨ ሰው ማዳመጥ ፈታኝ ሊሆን ይችላል