በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለታሰሩት መፈታትን ማወጅ’

‘ለታሰሩት መፈታትን ማወጅ’

‘ለታሰሩት መፈታትን ማወጅ’

ኢየሱስ ተልእኮው ‘ለታሰሩት መፈታትን ማወጅንም’ እንደሚጨምር በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:18) እውነተኛ ክርስቲያኖች የጌታቸውን ምሳሌ በመከተል “[ለ]ሰዎች ሁሉ” የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ከመንፈሳዊ ምርኮ ነጻ እንዲወጡና ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዷቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:4

በዛሬው ጊዜ ይህ ሥራ በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት ቃል በቃል ለታሰሩና መንፈሳዊ ነጻነት ማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች መስበክንም ይጨምራል። የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬንና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች በሚገኙ እስር ቤቶች ያከናወኑትን የስብከት ሥራ በተመለከተ ቀጥሎ የቀረበውን የሚያበረታታ ሪፖርት እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

ከዕፅ ሱሰኝነት ተላቅቆ ወደ ክርስትና መለወጥ

ሴርሂ a ከ38 ዓመታት የሕይወት ዘመኑ 20ውን ያሳለፈው በወኅኒ ቤት ነው። ትምህርቱን እንኳ የጨረሰው እስር ቤት ሆኖ ነው። ሴርሂ እንዲህ ይላል:- “ከዓመታት በፊት እስር ቤት የገባሁት በግድያ ወንጀል ተከስሼ ሲሆን አሁንም ገና የእስራት ጊዜዬን አልጨረስኩም። በእስር ቤት ውስጥ ጨካኝ ስለነበርኩ ሌሎች እስረኞች ይፈሩኝ ነበር።” ታዲያ ይህ ነጻ እንደወጣ እንዲሰማው አድርጎት ይሆን? በፍጹም፤ እንደውም ለበርካታ ዓመታት የዕፆች፣ የአልኮል መጠጥና የትንባሆ ባሪያ ነበር።

ከዚያም አብሮት ታስሮ የነበረ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነገረው። በዚህ ወቅት በጨለማ ውስጥ ብርሃን የፈነጠቀለት ያህል ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ ከሱሶቹ የተላቀቀ ሲሆን በኋላም የምሥራቹ ሰባኪ ሆነ፤ ከዚያም ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ ሴርሂ ይሖዋን በሙሉ ጊዜው ስለሚያገለግል በእስር ቤት ውስጥ ሥራ የበዛለት ሆኗል። ሰባት ወንጀለኞች መንገዳቸውን ለውጠው መንፈሳዊ ወንድሞቹ እንዲሆኑ ረድቷል። ስድስቱ ከእስር ቤት የወጡ ሲሆን ሴርሂ ግን አልተፈታም። ሴርሂ ከእስር ቤት ነጻ አለመውጣቱ አላሳዘነውም፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎችን ከመንፈሳዊ እስር ነጻ እንዲወጡ መርዳት መቻሉ አስደስቶታል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

በወኅኒ ቤት ከሚገኙት የሴርሂ ጥናቶች አንዱ ቀድሞ የዕፅ አዘዋዋሪና ሱሰኛ የነበረው ቪክቶር ነው። ቪክቶር ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ በዩክሬን በሚገኘው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ችሏል። በአሁኑ ጊዜ በሞልዶቫ ልዩ አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ቪክቶር እንዲህ ይላል:- “በስምንት ዓመቴ ማጨስ፣ በ12 ዓመቴ ደግሞ አልኮል አላግባብ መውሰድ የጀመርኩ ሲሆን በኋላም በ14 ዓመቴ የዕፅ ሱሰኛ ሆንኩ። ሕይወቴን ለመለወጥ ብፈልግም ያደረግኳቸው ሙከራዎች ሁሉ አልተሳኩም። ከዚያም በ1995 ከመጥፎ ጓደኞቼ ርቀን ለመኖር ከባለቤቴ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር እያቀድን ሳለ ባለቤቴን አንድ የአእምሮ በሽተኛ በስለት ወግቶ ገደላት። ሕይወቴ ተመሰቃቀለብኝ። ‘ባለቤቴ አሁን የት ነው ያለችው? ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?’ የሚሉትን ጥያቄዎች ብጠይቅም መልስ ላገኝ አልቻልኩም። የሚሰማኝን የባዶነት ስሜት ለማሸነፍ ስል በጣም ብዙ ዕፆችን መውሰድ ጀመርኩ። ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ተይዤ አምስት ዓመት ስለተፈረደብኝ ወኅኒ ቤት ገባሁ። እዚያም ሳለሁ ሴርሂ ለጥያቄዎቼ መልስ እንዳገኝ ረዳኝ። ከዕፆች ለመገላገል ብዙ ጊዜ ሙከራ ያደረግኩ ቢሆንም ሊሳካልኝ የቻለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት እርዳታ ብቻ ነው። የአምላክ ቃል ከፍተኛ ኃይል አለው!”—ዕብራውያን 4:12

ልበ ደንዳና የነበሩ እስረኞች ተለውጠዋል

ቫሲል የዕፅ ሱሰኛ ባይሆንም ከመታሰር ግን አላመለጠም። እንዲህ ሲል ይናገራል:- “በእርግጫና በቡጢ ድብድብ የሚካሄድበት የስፖርት ዓይነት ሱስ ሆኖብኝ ነበር። ሰውነታቸው ሳይበልዝ ሰዎችን ለመምታት ራሴን አሠለጠንኩ።” ቫሲል ይህን የዓመጽ ድርጊቱን የሰዎችን ንብረት ለመዝረፍ ተጠቅሞበታል። “ሦስት ጊዜ በመታሰሬ ምክንያት ባለቤቴ ፈታችኝ። የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ ሳለሁ የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች አገኘሁ። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳነብ ቢያነሳሳኝም በጣም የምወደውን ድብድብ ግን ልተው አልቻልኩም።

“መጽሐፍ ቅዱስን ለስድስት ወር ካነበብኩ በኋላ ግን በውስጤ የሆነ ለውጥ ተሰማኝ። ተደባድቤ ሳሸነፍ እንደ ቀድሞው መደሰት አልቻልኩም። ስለዚህ ኢሳይያስ 2:4ን መሠረት በማድረግ ሕይወቴን አንድ በአንድ ማጤን የጀመርኩ ሲሆን አስተሳሰቤን ካልለወጥኩ ዕድሜዬን በሙሉ ከወኅኒ ቤት እንደማልወጣ ተገነዘብኩ። በዚህም ምክንያት ለድብድብ የምጠቀምባቸውን መሣሪያዎች በጠቅላላ አውጥቼ በመጣል ባሕርዬን ለማሻሻል መጣር ጀመርኩ። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም ማሰላሰልና ጸሎት መጥፎ ባሕርያቴን ለማስወገድ ረድተውኛል። አንዳንድ ጊዜ ካለብኝ ሱስ መላቀቅ እንድችል ኃይል እንዲሰጠኝ እያነባሁ ይሖዋን እለምነው ነበር። በመጨረሻም ተሳካልኝ።

“ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ከቤተሰቦቼ ጋር እንደገና ተገናኘሁ። በአሁኑ ጊዜ በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ እሠራለሁ። ይህ ደግሞ ከባለቤቴ ጋር ሆኜ በስብከቱ ሥራ ለመካፈልና በጉባኤ ውስጥ ያሉብኝን ኃላፊነቶች ለመወጣት በቂ ጊዜ እንዳገኝ አስችሎኛል።”

ሚኮላና ጓደኞቹ በዩክሬን የሚገኙ በርካታ ባንኮችን ዘርፈዋል። በዚህ ምክንያት የአሥር ዓመት እስራት ተበየነበት። ከመታሰሩ በፊት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄደው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ይህም ቤተ ክርስቲያኑን መዝረፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነበር። ሚኮላ ያሰበው ነገር ባይሳካለትም ቤተ ክርስቲያን መሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት፣ ስለ ሻማዎቿና ስለ ሃይማኖታዊ በዓላቷ የሚያወራ አሰልቺ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲያምን አድርጎታል። ሚኮላ እንዲህ ይላል:- “ለምን እንደሆነ ባላውቀውም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ካሰብኩት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ሳውቅ በጣም ተደነቅኩ!” መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የጠየቀ ሲሆን በ1999 ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ ትሑት የጉባኤ አገልጋይ የሆነው ይህ ሰው ከዚህ ቀደም መሣሪያ የሚታጠቅ አስቸጋሪ የባንክ ዘራፊ ነበር ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል!

ቭላዲሚር የሞት ፍርድ የተበየነበት ሰው ነበር። የሞት ፍርዱ የሚፈጸምበትን ወቅት በሚጠባበቅበት ጊዜ ከሞት ከተረፈ አምላክን እንደሚያገለግለው ቃል በመግባት ጸለየ። በዚህ መሃል የአገሪቱ ሕግ በመቀየሩ የሞት ቅጣቱ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተለወጠ። ቭላዲሚር ቃሉን ለመጠበቅ ሲል እውነተኛውን ሃይማኖት መፈለግ ጀመረ። በተልእኮ ትምህርት አማካኝነት ከአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዲፕሎማውን ቢያገኝም ይህ እርካታ አልሰጠውም።

ቭላዲሚር ወኅኒ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጻሕፍት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ካነበበ በኋላ አንድ ሰው መጥቶ እንዲያነጋግረው በመጠየቅ በዩክሬን ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ ጻፈ። የአካባቢው ወንድሞች ሊጠይቁት ሲመጡ ቭላዲሚር ራሱን እንደ አንድ ምሥክር በመቁጠር በወኅኒ ቤት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መስበክ ጀምሮ ነበር። የመንግሥቱ ሰባኪ መሆን እንዲችል እርዳታ ተደረገለት። ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ቭላዲሚርና በዚያ ወኅኒ ቤት የሚገኙ ሌሎች ሰባት ሰዎች የጥምቀታቸውን ቀን እየተጠባበቁ ነው። ሆኖም አንድ ያጋጠማቸው ችግር አለ። ተመሳሳይ እምነት ያላቸውና የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸው የሕግ ታራሚዎች የሚታሰሩት አንድ ላይ ነው። በመሆኑም ከቭላዲሚር ጋር አብረውት ያሉት ሁሉ እምነታቸው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ለማን መስበክ ይችላሉ? በእስር ቤት ውስጥ ላሉ ዘበኞች በመመሥከርና ደብዳቤ በመጻፍ ምሥራቹን ማካፈል ችለዋል።

ናዛር ከዩክሬን ወደ ቼክ ሪፑብሊክ ሲዛወር ከዘራፊዎች ቡድን ጋር ተቀላቀለ። ይህ ደግሞ ለሦስት ዓመት ተኩል እንዲታሰር አድርጎታል። በእስር ቤት ሳለ ከካርሎቪ ቫሪ ከተማ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ሲያናግሩት በጎ ምላሽ ሰጠ፤ እውነትን ተማረ፣ ከዚያም ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ናዛር ያደረገውን ለውጥ ያየ አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ከናዛር ጋር ለታሰሩት “ሁላችሁም እንደዛ ዩክሬናዊ ብትሆኑ ሥራዬን መለወጥ እችል ነበር” በማለት ተናግሯል። ሌላው ደግሞ “እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በሥራቸው የተዋጣላቸው ናቸው። ወንጀለኛ ሆኖ እስር ቤት የገባ ሰው መልካም ምግባር ያለው ሆኖ ይወጣል” በማለት ተናግሯል። አሁን ናዛር ከእስር ተፈትቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል። የአናጢነት ሞያ የተማረ ሲሆን በኋላም አገባ፤ በአሁኑ ጊዜ እሱና ባለቤቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ናዛር ምሥክሮቹ በእስር ቤት ውስጥ ላከናወኑት ሥራ በጣም አመስጋኝ ነው!

እውቅና ተሰጣቸው

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን አገልግሎት የሚያደንቁት እስረኞች ብቻ አይደሉም። በፖላንድ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ቃል አቀባይ ሆኖ የሚሠራው ሚሮስላቭ ኮቫልስኪ እንዲህ ብሏል:- “[የይሖዋ ምሥክሮች] ወኅኒ ቤት መጥተው እስረኞችን ማነጋገራቸውን በጣም እናደንቃለን። አንዳንድ እስረኞች አሳዛኝ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ምናልባትም እንደ ሰዎች ተደርገው አይቆጠሩም ነበር። . . . እስረኞችን የሚረዱ በቂ ባለሞያዎችና አስተማሪዎች ስለሌሉን [የይሖዋ ምሥክሮች] የሚያበረክቱት እርዳታ በጣም ጠቃሚ ነው።”

በፖላንድ የሚገኝ የሌላ እስር ቤት ተቆጣጣሪ፣ ምሥክሮቹ እሱ በሚሠራበት ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያከናውኑትን ሥራ እንዲያስፋፉት በመጠየቅ ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጽፏል። ለምን? እንዲህ በማለት ገልጿል:- “የመጠበቂያ ግንብ ተወካዮች በወኅኒ ቤት ውስጥ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉብኝት በርካታ የሕግ ታራሚዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ባሕርያትን እንዲያፈሩና በመካከላቸው የሚፈጠረውን ጠብ እንዲያስወግዱ ሊረዳቸው ይችላል።”

አንድ የዩክሬን ጋዜጣ ራሱን ለመግደል ሙከራ ያደረገ በመንፈስ ጭንቀት የሚሰቃይ እስረኛ ከይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ እንዳገኘ ዘግቧል። ጋዜጣው “ይህ ሰው በአሁኑ ጊዜ ስሜቱ እየተረጋጋ ነው። የወኅኒ ቤቱን ሥርዓት ከማክበሩም በላይ ለሌሎች እስረኞች ምሳሌ ይሆናል” ይላል።

እስረኞቹ ከወኅኒ ቤት ከወጡም በኋላ የሚያገኙት ጥቅም

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ የሚያስገኘው ጥቅም በእስር ቤት ብቻ የተወሰነ አይደለም። እስረኞቹ ከተፈቱም በኋላ ምሥክሮቹ ይረዷቸዋል። ብሪጂት እና ሬናቴ የተባሉ ሁለት ክርስቲያን እህቶች ለተወሰኑ ዓመታት ሴቶች እስረኞችን በዚህ መልክ ሲረዱ ቆይተዋል። ማይን-ኤኮ አሻፈንቡርክ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ስለ እነርሱ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል:- “እስረኞቹ ከተፈቱ በኋላም ከሦስት እስከ አምስት ለሚያህሉ ወራት ክትትል በማድረግ ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመሩ ይረዷቸዋል። . . . በአመክሮ እንዲቆዩ የሚደረጉ የሕግ ታራሚዎችን ሁኔታ እየተከታተሉ ሪፖርት ለማድረግ በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቅርበው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። . . . ከእስር ቤቱ ሠራተኞች ጋርም ጠቃሚና ገንቢ የሆነ ግንኙነት አላቸው።” ይህን የመሰለ እርዳታ በማግኘታቸው ቀድሞ እስረኞች የነበሩ ብዙዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የወኅኒ ቤት ሠራተኞችም ተጠቅመዋል። በዩክሬን ማረሚያ ቤት በውትድርና መስክ ሻለቃና የሥነ ልቦና ባለሞያ የነበረውን ሮማንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ምሥክሮቹ ቤቱ ሲመጡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። ከዚያም ምሥክሮቹ እርሱ በሚሠራበት ወኅኒ ቤት ውስጥ እስረኞችን ማናገር እንደማይፈቀድላቸው ተገነዘበ። ስለዚህም የወኅኒ ቤቱን ተቆጣጣሪ ከእስረኞቹ ጋር በተያያዘ በሚያከናውነው ሥራ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይችል እንደሆነ ጠየቀው። የጠየቀው ነገር የተፈቀደለት ሲሆን አሥር የሚሆኑ እስረኞች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ፍላጎት አሳዩ። ሮማን እየተማረ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አዘውትሮ ለእስረኞቹ ማካፈሉ በጣም ጥሩ ውጤት አስገኘለት። ከእስር ከተፈቱ በኋላ አንዳንዶቹ እድገት አድርገው የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሆነዋል። ሮማን የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው በመመልከቱ ጥናቱን ይበልጥ በቁም ነገር ማየት ጀመረ። የውትድርና ሥራውን በመተው መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሩን ቀጠለ። በአሁኑ ጊዜ ቀድሞ እስረኛ ከነበረ ሰው ጋር ሆኖ በስብከቱ ሥራ ይካፈላል።

አንድ የሕግ ታራሚ “መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብርታት እንድናገኝ ረድተውናል” ሲል ጽፏል። እነዚህ ቃላት በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ምን ያህል እንደሚፈለጉ የሚያሳዩ ናቸው። በዩክሬን የሚገኝ አንድ ጉባኤ በአካባቢያቸው በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩን ሥራ በተመለከተ ሲዘግብ:- “አስተዳደሩ ለምንሰጣቸው ጽሑፍ በጣም አመስጋኝ ነው። ከእያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም 60 ቅጂዎች እንልክላቸዋለን።” ሌላም ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “20 ትንንሽ ቤተ መጻሕፍት ላሉት ማረሚያ ቤት እርዳታ እናደርጋለን። ለእያንዳንዱ ቤተ መጻሕፍት ዋና ዋናዎቹን ጽሑፎቻችንን በ20 ሣጥኖች ሞልተን ልከናል።” በአንድ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ጠባቂዎች፣ እስረኞች እያንዳንዱን እትም አግኝተው እንዲጠቀሙ ሲሉ መጽሔቶቻችንን በፋይል አድርገው ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ያስቀምጧቸዋል።

በ2002 በዩክሬን የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ከእስር ቤት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚከታተል ክፍል አቋቋመ። ይህ ክፍል እስካሁን ከ120 ማረሚያ ቤቶች ጋር ግንኙነት ያደረገ ሲሆን እነሱን ለመርዳት ጉባኤዎችን መድቧል። በየወሩ 50 የሚያህሉ ደብዳቤዎች ከእስረኞቹ የሚደርሱት ሲሆን አብዛኞቹ ጽሑፎችን ማግኘት የሚፈልጉ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ናቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው የአካባቢው ወንድሞች ሄደው እስኪያነጋግሯቸው ድረስ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን ይልክላቸዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ “በእስር ላይ ያሉትን . . . ዐስቡአቸው” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:3) ይህን ሲል በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩትን ማለቱ ነበር። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ላይ የሚገኙትን በማሰብ ወኅኒ ቤት ድረስ ሄደው ‘ለታሰሩት መፈታትን ያውጃሉ።’—ሉቃስ 4:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዩክሬን፣ ለቪቭ የሚገኘው እስር ቤት ግንብ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚኮላ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቫሲል ከባለቤቱ ከኢሪና ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቪክቶር