በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሜክሲኮ የሚገኙ ቻይናውያንን መርዳት

በሜክሲኮ የሚገኙ ቻይናውያንን መርዳት

በሜክሲኮ የሚገኙ ቻይናውያንን መርዳት

“ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል።” (ዘካርያስ 8:23) በዛሬው ጊዜ ይህ ግሩም ትንቢት በዓለም ዙሪያ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። “ከየወገኑና ከየቋንቋው” የተውጣጡ ሕዝቦች ይሖዋን ለማምለክ የመንፈሳዊ እስራኤላውያንን ልብስ እየያዙ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ለማየት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። አብዛኞቹ በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ላይ ለመሰማራት ሲሉ ሌላ ቋንቋ በመማር ላይ ናቸው።

በሜክሲኮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ እያደረጉ ነው። በሜክሲኮ ውስጥ ወደ 30,000 የሚጠጉ ቻይንኛ ተናጋሪዎች እንዳሉ ይገመታል። በ2003 በሜክሲኮ ሲቲ በተደረገው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 15 የሚሆኑት ተገኝተው ነበር። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሜክሲኮ በሚገኙ የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ሊኖር እንደሚችል እንዲያስተውሉ አደረጋቸው። ለእነዚህ የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚሰብኩ ተጨማሪ ሰዎች ለማግኘት ሲባል በሜክሲኮ የሚገኙትን ምሥክሮች በማንዳሪን ቻይንኛ ቀለል ያሉ አቀራረቦች ለማስተማር የሦስት ወር ኮርስ ተዘጋጀ። በአጠቃላይ 25 የሚሆኑ ምሥክሮች ኮርሱን ወሰዱ። ትምህርቱ ሲያልቅ በሜክሲኮ ሲቲ ከሚገኘው የማንዳሪን ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ የመጣ ባለ ሥልጣን ምርቃቱ ላይ የተገኘ ሲሆን ይህም ኮርሱ በቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ የሚጠቁም ነው። በአካባቢው የሚገኝ አንድ የቻይናውያን ትምህርት ቤት ወደ ውጭ አገር ሄደው የተማሩትን ቋንቋ እንዲያሻሽሉ ለሦስት ተማሪዎች የነጻ ትምህርት ዕድል ሰጥቷል።

ይህ የቋንቋ ኮርስ ልምምድ ማድረግንም ይጨምር ነበር። ተማሪዎቹ መሠረታዊ የሆኑ ሐረጎችን ከተማሩ በኋላ ሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው የንግድ አካባቢ ወዲያውኑ በቻይንኛ መስበክ ጀመሩ። ቀናተኛ ሰባኪዎች የሆኑት እነዚህ ተማሪዎች 21 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር ቻሉ። ፒንዪን ተብለው በሚጠሩት የሮማ ፊደላት በቻይንኛ ቋንቋ የተዘጋጀው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር ትልቅ እርዳታ አበርክቷል።

ምሥክሮቹ ገና ኮርሱን ከመጀመራቸው በቻይንኛ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት የቻሉት እንዴት ነው? መጀመሪያ ላይ የሚችሉት አንቀጹን ከዚያም ጥያቄውን በማመልከት “ቺንግ ዱ [እባክዎ ያንብቡት]” ማለት ብቻ ነበር። ግለሰቡ በቻይንኛ ካነበበና ከመለሰ በኋላ “ሼ ሼ [አመሰግናለሁ]” እንዲሁም “ሄንግ ሃኡ [በጣም ጥሩ]” ይሉት ነበር።

ቀደም ሲል የስመ ክርስትና አባል ከነበረች አንዲት ሴት ጋር በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይካሄድ ነበር። ከሦስተኛ ጥናታቸው በኋላ የምታስጠናት እህት ይህች ሴት እስካሁን የተማረችው ገብቷት እንደሆነ ለማወቅ ፈለገች። ስለዚህ እህት የአፍ መፍቻ ቋንቋው ቻይንኛ የሆነ ወንድም ይዛ ሄደች። ወንድም ሴትየዋን ጥያቄ እንዳላት ሲጠይቃት፣ ሴትየዋ “ለመጠመቅ ዋና መቻል አለብኝ?” ብላ ጠየቀችው።

ብዙም ሳይቆይ በአማካይ 9 የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችንና 23 የሜክሲኮ ወንድሞችን ያቀፈ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ተቋቋመ። ከእነርሱ መካከል አንድ ቻይናዊ ዶክተር የሚገኝ ሲሆን አንዲት ታካሚው በስፓንኛ ቋንቋ የተዘጋጁ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ሰጥታው ነበር። ሆኖም ስፓንኛ ማንበብ ስለማይችል አንድ ሰው ጥቂት ዓረፍተ ነገሮችን እንዲተረጉምለት አደረገ። መጽሔቶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሲያውቅ መጽሔቶቹን በቻይንኛ ቋንቋ ማምጣት ትችል እንደሆነ ታካሚውን ጠየቃት። እርሷም በቋንቋው የተዘጋጁ መጽሔቶችን ያመጣችለት ሲሆን በሜክሲኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑ ወንድሞች ሄደው እንዲያነጋግሩት ዝግጅት አደረገ። ይህ ሰው ቻይና እያለ እናቱ መጽሐፍ ቅዱስ የነበራት ሲሆን እርሱም ይህን መጽሐፍ ማንበብ ያስደስተው ነበር። ወደ ሜክሲኮ ሊመጣ ሲል እናቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡን እንዳይተው ነግራው ስለነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው አምላክ ይበልጥ ለማወቅ የሚረዳው ሰው እንዲያገኝ ይጸልይ ነበር። “አምላክ ጸሎቴን ሰምቷል!” በማለት በደስታ ተናገረ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ከምታጠና ሜክሲካዊት ሴት የመኖሪያ ክፍል የተከራየ አንድ የቻይናውያን ቤተሰብም በመጽሐፍ ጥናቱ ላይ ይገኝ ነበር። እነዚህ ቻይናውያን የስፓንኛ ቋንቋ ብዙም ባይገባቸውም ከሴትየዋ ጋር በሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ላይ ይገኙ ነበር። ከጊዜ በኋላ ጥናቱን ለምትመራው እህት በቻይንኛ የተዘጋጀ ጽሑፍ ይኖራት እንደሆነ ጠየቋት። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በቻይንኛ ተጀመረላቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዚህ ቤተሰብ አባላት ለአገራቸው ሰዎች መስበክ እንዲሁም ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰን እንደሚፈልጉ ገለጹ።

የቻይንኛ ቋንቋ ለመማር በጣም አስቸጋሪ መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ከላይ የቀረቡት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በሜክሲኮም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ቻይንኛን ጨምሮ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በይሖዋ እርዳታ አማካኝነት የአምላክን ፈቃድ እየተማሩ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሜክሲኮ ሲቲ የሚገኙት የቻይንኛ ቋንቋ ተማሪዎች

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ሜክሲካዊት እህት በቻይንኛ መጽሐፍ ቅዱስን ስታስጠና

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሜክሲኮ ሲቲ፣ በቻይንኛ ቋንቋ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ