በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

 በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

የመጀመሪያው ኃጢአት ማለትም የአዳም አለመታዘዝ በዘር ከሚተላለፍ በሽታ ጋር የተመሳሰለው ለምንድን ነው?

ልክ እንደ አንድ ተላላፊ በሽታ አዳም ለልጆቹ ኃጢአትን ስላስተላለፈ ነው። ስለዚህም አንዳንድ ልጆች ከወላጆቻቸው አንድ በሽታ እንደሚተላለፍባቸው ሁሉ እኛም ኃጢአት የሚያስከትለውን ጉድለት ወርሰናል።—8/15 ገጽ 5

ዛሬ ላለው ዓመጽ መጨመር ዋነኛ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ በፊልሞች፣ በሙዚቃዎች እንዲሁም ለጭካኔ ድርጊቶችና ለግድያ በሚያነሳሱ የኮምፒውተር ጨዎታዎች በመጠቀም በልባቸው ውስጥ የዓመጽ መንፈስ ይዘራል። በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉት የዓመጽ ድርጊቶችም ለዓመጽ መጨመር ምክንያት ናቸው።—9/1 ገጽ 29

ጳንጥዮስ ጲላጦስ ማን ነበረ?

ከዝቅተኛው የገዥ መደብ የመጣ ሮማዊ ወታደር የነበረ ይመስላል። የሮማው ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ በ26 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጲላጦስን የይሁዳ ገዥ አድርጎ ሾመው። የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን በከሰሱት ወቅት ክሱን ያዳመጠው እርሱ ነበር። ሕዝቡን ለማስደሰት ሲል በኢየሱስ መገደል ተስማምቷል።—9/15 ገጽ 10-12

በማቴዎስ 24:3 ላይ የተጠቀሰው “ምልክት” ምንድን ነው?

ይህ ምልክት ወቅቱን ልዩ የሚያደርጉትን የተለያዩ ክስተቶች ያካተተ ነው። ምልክቱ ጦርነትን፣ ረሃብን፣ ቸነፈርን እንዲሁም የምድር መናወጥን የሚጨምር ሲሆን ይህም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የእርሱን “መገኘት NW” እንዲሁም ‘የዓለምን መጨረሻ’ ማስተዋል እንዲችሉ ይረዳቸዋል።—10/1 ገጽ 4-5

ፈላሻ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? የፈለሱትስ ወደየትኞቹ አካባቢዎች ነው?

ቃሉ የሚያመለክተው ከጳለስጢና ምድር ውጪ የሚኖሩትን አይሁዳውያን ነው። በአንደኛው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ዋነኛ መኖሪያ የነበሩት ሶርያ፣ ትንሿ እስያ፣ ባቢሎንና ግብጽ ሲሆኑ የአውሮፓ ክፍል በሆኑ የሮማ ግዛቶች ውስጥም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁድ ይኖሩ ነበር።—10/15 ገጽ 12

አንድ ክርስቲያን የጦር መሣሪያ መያዝ በሚጠይቅ ሥራ ላይ ቢሰማራ ንጹሕ ሕሊና ሊኖረው ይችላል?

ጠመንጃ ወይም ሌላ ዓይነት የጦር መሣሪያ መያዝ በሚጠይቅ ሰብዓዊ ሥራ ላይ መሰማራትም ሆነ አለመሰማራት ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። ሆኖም የጦር መሣሪያን መያዝ የሚጠይቅ ሥራ አንድን ግለሰብ መሣሪያውን በሌሎች ላይ እንዲጠቀምና የደም ባለዕዳ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል፤ እንዲሁም አስቀድሞ ለማጥቃት ወይም አጸፋውን ለመመለስ ሲባል ሊተኮስበትና በዚህም ሳቢያ የመቁሰል ወይም የሞት አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል። እነዚህን መሣሪያዎች የሚይዝ አንድ ክርስቲያን በጉባኤ ውስጥ ልዩ መብቶችን ለማግኘት ብቁ አይሆንም።(1 ጢሞቴዎስ 3:3, 10)—11/1 ገጽ 31

“አርማጌዶን” የሚለው ቃል የመጣው “የመጊዶ ተራራ” ከሚለው ሐረግ መሆኑ የአርማጌዶን ጦርነት የሚካሄደው በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ እንደሆነ ያመለክታል?

በጭራሽ። በመጀመሪያ ደረጃ በእስራኤል ውስጥ መጊዶ የሚባል ተራራ የለም። ከዚህ ይልቅ ሥፍራውን ከሚያዋስኑት ሜዳማ ቦታዎች አንጻር ከፍ ብሎ የሚታይ በዚህ ስም የሚጠራ ጉብታ ይገኛል። ከዚህም በላይ የመጊዶ አካባቢ ‘የምድር ነገሥታትንና ሰራዊታቸውን’ የመያዝ አቅም የለውም። የአምላክ ታላቅ ጦርነት የሚካሄደው በመላው ምድር ላይ ከመሆኑም በላይ ሁሉንም ዓይነት ጦርነቶች ይደመስሳል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:19፤ መዝሙር 46:8, 9)—12/1 ገጽ 4-7