በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው

ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው

ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው

“በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው?”—1 ነገሥት 18:21

1. የምንኖርበትን ጊዜ ከቀደሙት ዘመናት የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው?

 ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን ታምናለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የምንኖርበት ጊዜ የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ‘መጨረሻ ዘመን’ መሆኑን እንደሚጠቁሙስ ታምናለህ? (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከሆነ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ የሚገባን በአሁኑ ወቅት እንደሆነ ትስማማለህ ማለት ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የዚህን ዘመን ያህል የብዙ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ አልነበረም።

2. በንጉሥ አክዓብ የግዛት ዘመን በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ሕዝቡ ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ነበር?

2 በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የእስራኤል ብሔር ከባድ ውሳኔ ተደቅኖበት ነበር። ማንን ማገልገል ይኖርባቸዋል? ንጉሥ አክዓብ አረማዊ በሆነችው ሚስቱ በኤልዛቤል በመመራት በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የበኣል አምልኮ እንዲስፋፋ አድርጎ ነበር። በኣል ዝናብና ጥሩ ምርት እንደሚሰጥ የሚታመን የመራባት አምላክ ነው። በርካታ የበኣል አምላኪዎች ለበኣል ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹ ከመሆኑም በላይ ለአምላካቸው ጣዖት ይሰግዳሉ። የበኣል አምላኪዎች ሰብላቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲባርክላቸው ለመገፋፋት ሲሉ ከቤተ መቅደስ አመንዝራዎች ጋር የጾታ ብልግና በሚፈጸምበት አምልኮ ይካፈሉ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሰውነታቸውን በመቁረጥ ደማቸውን የማፍሰስ ልማድ ነበራቸው።—1 ነገሥት 18:28

3. የበኣል አምልኮ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር?

3 የጣዖት አምልኮ፣ የጾታ ብልግናና ጭካኔ በተሞላበት በዚህ የአምልኮ ሥርዓት ለመካፈል ፈቃደኞች ያልሆኑ 7,000 ያህል እስራኤላውያን ነበሩ። (1 ነገሥት 19:18) እነዚህ እስራኤላውያን ከይሖዋ አምላክ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን በታማኝነት የጠበቁ ሲሆን በዚህም የተነሳ ስደት ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ንግሥት ኤልዛቤል በርካታ የይሖዋ ነቢያትን አስገድላለች። (1 ነገሥት 18:4, 13) ሕዝቡ እንደዚህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለተደቀነበት አብዛኞቹ እስራኤላውያን ይሖዋንም ሆነ በኣልን ለማስደሰት በመጣር ቅልቅል አምልኮ ያካሂዱ ነበር። ይሁን እንጂ ለአንድ እስራኤላዊ ይሖዋን ትቶ የሐሰት አምላክ ማምለክ ክህደት ነበር። ይሖዋ እስራኤላውያን የሚወዱትና መመሪያዎቹን የሚታዘዙ ከሆነ እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ሆኖም እርሱን ብቻ ካላመለኩት እንደሚጠፉ አስጠንቅቋቸው ነበር።—ዘዳግም 5:6-10፤ 28:15, 63

4. ኢየሱስና ሐዋርያቱ በክርስቲያኖች መካከል ምን እንደሚፈጠር አስቀድመው ተናግረው ነበር? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

4 በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል። ምዕመናኑ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ቢናገሩም በዓሎቻቸው፣ ባሕርያቸውና እምነታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል። እንደ ኤልዛቤል ሁሉ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም የይሖዋ ምሥክሮች ቀንደኛ አሳዳጅ ናቸው። እነዚሁ ቀሳውስት ከጥንት ጀምሮ ጦርነቶችን ይደግፉ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት የሚያሳዩ ሲሆን በዚህም የተነሳ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት ሞት ተጠያቂ ናቸው። ሃይማኖት ለዓለም መንግሥታት የምታደርገው እንዲህ ያለው ድጋፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ ምንዝር ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 18:2, 3) ከዚህም በተጨማሪ ሕዝበ ክርስትና፣ ቀሳውስቱ እንኳ ሳይቀሩ ቃል በቃል የሚፈጽሙትን ምንዝር በቸልታ እየተመለከተች ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዲህ ያለ ታላቅ ክህደት እንደሚመጣ አስቀድመው ተናግረው ነበር። (ማቴዎስ 13:36-43፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 2) ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡት የሕዝበ ክርስትና አባላት መጨረሻቸው ምን ይሆናል? እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችስ እነዚህንና በሐሰት ሃይማኖት የተታለሉ ሌሎች ሰዎችን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው? ‘የበኣል አምልኮ ከእስራኤል እንዲወገድ’ ያደረጉትን አስደናቂ ክስተቶች በመመልከት ለእነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ እናገኛለን።—2 ነገሥት 10:28

አምላክ ዓመጸኛ ለሆኑት ሕዝቦቹ ያሳየው ፍቅር

5. ይሖዋ ዓመጸኛ ለነበሩት ሕዝቦቹ ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ አምላክ ለእርሱ ታማኝ ያልሆኑ ሰዎችን በመቅጣት የሚያገኘው ደስታ የለም። እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ሁሉ ኃጢአተኞች ንስሐ ገብተው ወደ እርሱ እንዲመለሱ ይፈልጋል። (ሕዝቅኤል 18:32፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) በአክዓብና በኤልዛቤል ዘመን የበኣል አምልኮ ስለሚያመጣው መዘዝ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ በርካታ ነቢያት መላኩ ለዚህ እንደ ማስረጃ ይሆነናል። ከእነዚህ ነቢያት አንዱ ኤልያስ ነው። አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በእስራኤል ምድር ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለ ረሃብ ተከስቶ ነበር። ከዚያም ኤልያስ ወደ ንጉሥ አክዓብ ሄዶ እስራኤላውያንንና የበኣል ነቢያትን በቀርሜሎስ ተራራ ላይ እንዲሰበስባቸው ነገረው።—1 ነገሥት 18:1, 19

6, 7. (ሀ) ኤልያስ በእስራኤል ውስጥ የነበረውን የክህደት አካሄድ ዋና መንስኤ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የበኣል ነቢያት ምን አደረጉ? (ሐ) ኤልያስስ ምን አደረገ?

6 ስብሰባው የተካሄደው የይሖዋ መሠዊያ በሚገኝበት አካባቢ ነው፤ ይህ መሠዊያ ኤልዛቤልን ለማስደሰት ሳይሆን አይቀርም “ፈርሶ” ነበር። (1 ነገሥት 18:30) የሚያሳዝነው፣ በቦታው ተገኝተው የነበሩት እስራኤላውያን በጣም ይፈለግ የነበረውን ዝናብ መስጠት የሚችለው ይሖዋ ይሁን በኣል እርግጠኞች አልነበሩም። በኣልን የሚወክሉ 450 ነቢያት የተገኙ ሲሆን ከይሖዋ ወገን ያለው ነቢይ ግን ኤልያስ ብቻ ነበር። ኤልያስ የችግራቸውን ሥረ መሠረት በመጥቀስ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው?” ሲል ሕዝቡን ጠየቀ። ከዚያም “እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” በማለት ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ አቀረበው። ኤልያስ ውሳኔ ማድረግ ያቃታቸውን እስራኤላውያን ለይሖዋ ብቻ አምልኮ እንዲያቀርቡ ለማነሳሳት ሲል እውነተኛው አምላክ ማን መሆኑን ለመለየት የሚያስችል ፈተና አቀረበ። ሁለት ወይፈኖች ከታረዱ በኋላ አንዱ ለይሖዋ አንዱ ደግሞ ለበኣል መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል። እውነተኛ የሆነው አምላክ የቀረበለትን መሥዋዕት በእሳት ይበላል። የበኣል ነቢያት መሥዋዕታቸውን ካዘጋጁ በኋላ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ሲጮኹ ዋሉ። ኤልያስ ሲያሾፍባቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን ያቆስሉ እንዲሁም ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ ይጮኹ ነበር። ያም ሆኖ ግን ምንም ምላሽ አላገኙም።—1 ነገሥት 18:21, 26-29

7 አሁን ደግሞ ተራው የኤልያስ ነው። በመጀመሪያ የይሖዋን መሠዊያ ካደሰ በኋላ የወይፈኑን ሥጋ በየብልቱ ቆርጦ በመሠዊያው ላይ አስቀመጠው። ቀጥሎም በአራት ትላልቅ ጋኖች ሙሉ ውኃ በመሥዋዕቱ ላይ እንዲያፈስሱበት አዘዘ። በመሠዊያው ዙሪያ ያለው ጉድጓድ በውኃ እስኪሞላ ድረስ ሦስት ጊዜ ደጋግመው እንዲህ አደረጉ። በመጨረሻም ኤልያስ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ። ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።”—1 ነገሥት 18:30-37

8. አምላክ ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ምን ምላሽ ሰጠ? ነቢዩስ ምን እርምጃ ወሰደ?

8 እውነተኛው አምላክ ከሰማይ እሳት ወርዶ መሥዋዕቱንም ሆነ መሠዊያውን እንዲበላው በማድረግ መልስ ሰጠ። እሳቱ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ጉድጓድ ውስጥ የነበረውን ውኃ እንኳ ሳይቀር ላሰው! ይህ በእስራኤላውያን ላይ ምን ስሜት እንዳሳደረ አስበው። “በግንባራቸው ተደፍተው፣ ‘አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!’ አሉ።” በዚህ ጊዜ ኤልያስ ሌላ ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ እስራኤላውያንን “የበአልን ነቢያት ያዟቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ” ሲል አዘዛቸው። አራት መቶ ሃምሳዎቹም የበኣል ነቢያት በቀርሜሎስ ተራራ ግርጌ ተገደሉ።—1 ነገሥት 18:38-40

9. እውነተኞቹ አምላኪዎች እንደገና ፈተና የተጋረጠባቸው እንዴት ነበር?

9 ይሖዋ፣ በዚህ የማይረሳ ቀን ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝናብ እንዲዘንብ አደረገ። (ያዕቆብ 5:17, 18) እስራኤላውያኑ ወደየቤታቸው ሲመለሱ ምን ሊያወሩ እንደሚችሉ ማሰብ አያዳግትም፤ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አረጋግጧል። ያም ሆኖ የበኣል አምላኪዎች ተስፋ አልቆረጡም። ኤልዛቤል የይሖዋን አገልጋዮች የማሳደድ ዘመቻዋን ገፋችበት። (1 ነገሥት 19:1, 2፤ 21:11-16) በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች ታማኝነት እንደገና ፈተና ላይ ወደቀ። አምላክ በበኣል አምላኪዎች ላይ የፍርድ እርምጃ በሚወስድበት ቀን ይሖዋን ብቻ እያመለኩ ያገኛቸው ይሆን?

ወሳኝ እርምጃ የምትወስዱበት ጊዜ አሁን ነው

10. (ሀ) በዘመናችን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ምን ሥራ አከናውነዋል? (ለ) በራእይ 18:4 ላይ የሚገኘውን መመሪያ መታዘዝ ምን ማድረግን ይጨምራል?

10 በዘመናችንም በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች እንደ ኤልያስ ዓይነት ሥራ አከናውነዋል። ራሳቸው በሚያከናውኑት ስብከትም ሆነ በጽሑፎቻቸው አማካኝነት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙና ከእርሷ ውጭ ያሉ ሰዎችን በሙሉ የሐሰት ሃይማኖት ስለሚያስከትለው አደጋ አስጠንቅቀዋል። በዚህም የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት አባል ላለመሆን ወሳኝ እርምጃ ወስደዋል። ከዚህም በላይ ሕይወታቸውን ለይሖዋ በመወሰን የተጠመቁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። አዎን፣ አምላክ የሐሰት ሃይማኖትን አስመልክቶ “ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ” በማለት ያቀረበውን ልመና ሰምተው እርምጃ ወስደዋል።—ራእይ 18:4

11. የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

11 ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰራጩት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልእክት ቢማርካቸውም ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ግን እርግጠኞች አይደሉም። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የመታሰቢያውን በዓል ወይም የአውራጃ ስብሰባን በመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አልፎ አልፎ ይገኛሉ። እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ሁሉ “መሃል ሰፋሪ የምትሆኑት እስከ መቼ ነው?” የሚለውን የኤልያስ አባባል ልብ እንዲሉት እናሳስባቸዋለን። (1 ነገሥት 18:21ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ከመዘግየት ይልቅ አሁኑኑ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም ራሳቸውን ወስነውና ተጠምቀው የይሖዋ አምላኪዎች ለመሆን ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋቸው አደጋ ላይ ወድቋል!—2 ተሰሎንቄ 1:6-9

12. አንዳንድ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል? ምን ማድረግስ ይኖርባቸዋል?

12 ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች አዘውትረው ጉባኤ የማይመጡና በአምልኳቸው ረገድም የቀዘቀዙ መሆናቸው ያሳዝናል። (ዕብራውያን 10:23-25፤ 13:15, 16) ሌሎች ስደትን በመፍራት፣ በኑሮ ጭንቀት፣ ለመበልጸግ በሚደረግ ሩጫ ወይም በራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ምክንያት የነበራቸው ቅንዓት ቀዝቅዟል። ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች ከተከታዮቹ ለአንዳንዶቹ እንቅፋትና ወጥመድ ሊሆኑባቸው እንዲሁም ሊያንቋቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 10:28-33፤ 13:20-22፤ ሉቃስ 12:22-31፤ 21:34-36) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ አነጋገር በሁለት ሐሳብ ከማነከስ ይልቅ ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው ለመኖር ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ ‘መትጋትና ንስሓ መግባት’ ይኖርባቸዋል።—ራእይ 3:15-19

የሐሰት ሃይማኖት ድንገተኛ ጥፋት

13. ኢዩ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት በእስራኤል የነበረውን ሁኔታ ግለጽ።

13 እውነተኛው አምላክ ማን ነው የሚለው ጥያቄ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ መልስ ካገኘ ከ18 ዓመታት በኋላ በእስራኤል የተፈጸመው ነገር የሰው ልጆች አሁኑኑ ወሳኝ እርምጃ መውሰዳቸው አጣዳፊ የሆነበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። የኤልያስ ተተኪ በሆነው በኤልሳዕ የአገልግሎት ዘመን፣ ይሖዋ በበኣል አምልኮ ላይ የፍርድ እርምጃ የሚወስድበት ቀን ሳይታሰብ በድንገት ከተፍ አለ። በወቅቱ እስራኤልን የሚገዛው የንጉሥ አክዓብ ልጅ ኢዮራም ሲሆን እናቱ ንግሥት ኤልዛቤልም በሕይወት ነበረች። ኤልሳዕ፣ የእስራኤል ጦር ሠራዊት አለቃ የነበረውን ኢዩን ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው አገልጋዩን በድብቅ ላከው። በወቅቱ ኢዩ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሬማት በምትገኘው ገለዓድ ሆኖ የእስራኤልን ጠላቶች እየተዋጋ ነበር። ንጉሥ ኢዮራም ደግሞ በውጊያ ላይ ከደረሰበት ቁስል ለማገገም በመጊዶ አቅራቢያ ባለው ሜዳ ላይ ወደምትገኘው ኢይዝራኤል ወርዷል።—2 ነገሥት 8:29 እስከ 9:4

14, 15. ኢዩ ምን ተልእኮ ተሰጠው? እርሱስ ምን እርምጃ ወሰደ?

14 ይሖዋ ለኢዩ የሰጠው ትእዛዝ እንዲህ የሚል ነበር:- “የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ . . . ኤልዛቤልን ግን በኢይዝራኤል ዕርሻ ውሾች ይበሏታል፤ የሚቀብራትም አይኖርም።”—2 ነገሥት 9:7-10

15 ኢዩ ፈጣን እርምጃ የሚወስድ ሰው ነበር። ወዲያውኑ ሠረገላው ላይ ወጣና ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ። በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ ኢዩን በሠረገላ አነዳዱ ስለለየው ለንጉሡ አሳወቀው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም በሠረገላው ላይ ተቀምጦ የሠራዊቱን አለቃ ለመገናኘት ወጣ። ሲገናኙም “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢዩ የሰጠው ምላሽ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና [“ግልሙትናዋና፣” የ1954 ትርጉም] መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” የሚል ነበር። ከዚያም ንጉሥ ኢዮራም ለመሸሽ እንኳ እድል ሳያገኝ ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ወጋው፤ ፍላጻውም ወደ ልቡ ዘልቆ በመግባት ገደለው።—2 ነገሥት 9:20-24

16. (ሀ) የኤልዛቤል ጃንደረቦች በድንገት ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጠማቸው? (ለ) ይሖዋ ስለ ኤልዛቤል የተናገረው ቃል የተፈጸመው እንዴት ነው?

16 ኢዩ ጊዜ ሳያጠፋ በሠረገላው ወደ ከተማ ሄደ። ኤልዛቤል ተኳኩላ በመስኮት በኩል ብቅ በማለት ኢዩን ገና ሲመጣ በቁጣ ተቀበለችው። ኢዩ ግን ለእርሷ መልስ ከመስጠት ይልቅ “ማነህ አንተ? ማነው የሚተባበረኝ”? በማለት እንዲያግዙት ጠየቀ። በዚህ ወቅት የኤልዛቤል አገልጋዮች ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸው ነበር። ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ ጃንደረቦች በመስኮቱ በኩል ብቅ አሉ። ወዲያው ታማኝነታቸውን የሚፈትን ሁኔታ ገጠማቸው። ኢዩ “ወደ ታች ወርውሩአት!” ሲል አዘዘ። ጃንደረቦቹ ኤልዛቤልን ወደ ታች ወረወሯት፤ በዚያም በኢዩ ፈረሶችና ሠረገሎች ተረጋገጠች። በዚህ መንገድ በእስራኤል የበኣል አምልኮ ጠንሳሽ የሆነችው ሴት የእጅዋን አገኘች። አስቀድሞ እንደተነገረው በድኗን ለመቅበር እንኳ ጊዜ ሳያገኙ ውሾች ሥጋዋን በሉት።—2 ነገሥት 9:30-37

17. አምላክ በኤልዛቤል ላይ የወሰደው የፍርድ እርምጃ ወደፊት ስለሚፈጸመው ስለየትኛው ክንውን ያለንን እምነት ሊያጠናክርልን ይገባል?

17 “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ የምትጠራው ምሳሌያዊ አመንዝራም በተመሳሳይ አስደንጋጭ ጥፋት ይደርስባታል። ይህቺ አመንዝራ በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ከጥንቷ ባቢሎን የመነጩ የሐሰት ሃይማኖቶች ትወክላለች። የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ይሖዋ አምላክ የሰይጣን ዓለም ክፍል ወደሆኑት ሰዎች ትኩረቱን ይመልሳል። ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት ሲል እነዚህንም ያጠፋቸዋል።—ራእይ 17:3-6፤ 19:19-21፤ 21:1-4

18. ኤልዛቤል ከሞተች በኋላ በእስራኤል የነበሩ የበኣል አምላኪዎች ምን ደረሰባቸው?

18 ኤልዛቤል ከሞተች በኋላ ንጉሡ ኢዩ ጊዜ ሳያባክን የአክዓብን ዝርያዎች በሙሉ እንዲሁም ዋነኛ ደጋፊዎቻቸውን ጠራርጎ አጠፋቸው። (2 ነገሥት 10:11) ያም ሆኖ በምድሪቱ በርካታ በኣል አምላኪ እስራኤላውያን ይቀሩ ነበር። ኢዩ እነዚህን በተመለከተም ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ ‘ለእግዚአብሔር መቅናቱን’ አሳይቷል። (2 ነገሥት 10:16) ኢዩ ራሱ የበኣል አምላኪ እንደሆነ በማስመሰል አክዓብ በሰማርያ በሠራው የበኣል ቤተ መቅደስ ውስጥ ታላቅ ግብዣ አዘጋጀ። በእስራኤል የነበሩ በኣል አምላኪዎች ሁሉ በዝግጅቱ ላይ ተገኙ። ቤተ መቅደሱ ውስጥ ከገቡ በኋላ የኢዩ ሰዎች ሁሉንም ገደሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ዘገባውን ሲደመድም “በዚህ ሁኔታም ኢዩ የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል አስወገደ” ይላል።—2 ነገሥት 10:18-28

19. “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሆኑት ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ምን አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል?

19 የበኣል አምልኮ ከእስራኤል ሙሉ በሙሉ እንደተወገደ ሁሉ የዓለም የሐሰት ሃይማኖቶችም ልክ እንደዚሁ አስደንጋጭ በሆነ መንገድ በድንገት ጥፋት ይደርስባቸዋል። በዚያ ታላቅ የፍርድ ቀን ከማን ጎን ትቆማለህ? አሁኑኑ ወሳኝ እርምጃ ከወሰድክ “ከታላቁ መከራ” ከሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መካከል የመሆን መብት ታገኝ ይሆናል። ከዚያም ያለፈውን ጊዜ በደስታ መለስ ብለህ መቃኘትና “በዝሙቷ ምድርን ያረከሰችውን፣ ታላቂቱን አመንዝራ” ስለፈረደባት አምላክን ማወደስ ትችላለህ። ከሌሎች እውነተኛ አምላኪዎች ጋር በአንድነት በመሆን ከሰማይ በተሰማው “ሃሌ ሉያ! ሁሉን ቻይ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና” በሚለው ድምጽ ትስማማለህ።—ራእይ 7:9, 10, 14፤ 19:1, 2, 6

ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

• የጥንቷ እስራኤል በበኣል አምልኮ ልትካፈል የቻለችው እንዴት ነበር?

• መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ታላቅ ክህደት እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር? ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?

• ኢዩ የበኣል አምልኮን ጠራርጎ ያጠፋው እንዴት ነው?

• ከአምላክ የጥፋት ቀን ለመትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሰኰት

አፌቅ

ሔልቃት

ዮቅንዓም

መጊዶ

ታዕናክ

ዶታይን

ሰማርያ

ዓይንዶር

ሱነም

ዖፍራ

ኢይዝራኤል

ይብለዓም (ጋትሪሞን)

ቴርሳ

ቤት ሳሚስ

ቤትሳን

ኢያቢስ ገለዓድ?

አቤልሞሖላ

ቤት አርብኤል

በሬማት ያለችው ገለዓድ

ተራሮች

የቀርሜሎስ ተራራ

የታቦር ተራራ

ሞሬ

የጊልቦዓ ተራራ

[የውኃ አካላት]

የሜድትራንያን ባሕር

የገሊላ ባሕር

[ወንዝ]

የዮርዳኖስ ወንዝ

[ምንጭ እና የውኃ ጉድጓድ]

የሐሮድ ምንጭ

[ምንጭ]

Based on maps copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

አዘውትሮ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የእውነተኛ አምልኮ አቢይ ክፍሎች ናቸው

[በገጽ 28 እና 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ ቀን መትረፍ የሚፈልጉ ሁሉ ልክ እንደ ኢዩ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው