በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትታዘዘው አምላክን ነው ወይስ ሰውን?

የምትታዘዘው አምላክን ነው ወይስ ሰውን?

የምትታዘዘው አምላክን ነው ወይስ ሰውን?

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!”የሐዋርያት ሥራ 5:29

1. (ሀ) ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተው በየትኛው ጥቅስ ላይ ነው? (ለ) ሐዋርያት የታሰሩት ለምን ነበር?

 የአይሁድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በንዴት የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተዋል። ወኅኒ ቤት ያስገቧቸውን ሰዎች ሊያገኟቸው አልቻሉም። እስረኞቹ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፍርድ ቤቱ ሞት የበየነበት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ነበሩ። አሁን ደግሞ ሸንጎው በቅርብ ተከታዮቹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል። ሆኖም ጠባቂዎቹ እስረኞቹን ለማምጣት ሲሄዱ ወኅኒ ቤቱ እንደተቆለፈ ቢሆንም ውስጡ ባዶ ሆኖ አገኙት። ብዙም ሳይቆይ ግን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያለምንም ፍርሃት ሕዝቡን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማሩ እንደሆነ ለጠባቂዎቹ ተነገራቸው። ሐዋርያት ወኅኒ ቤት እንዲወርዱ የተደረጉትም በዚሁ ሥራቸው ምክንያት ነበር! ጠባቂዎቹ በቀጥታ ወደ ቤተ መቅደሱ በመሄድ ሐዋርያቱን ይዘው ሸንጎው ፊት አቀረቧቸው።—የሐዋርያት ሥራ 5:17-27

2. አንድ መልአክ ሐዋርያቱን ምን እንዲያደርጉ አዘዛቸው?

2 ሐዋርያቱን ከእስር ቤት ያወጣቸው አንድ መልአክ ነበር። ይህን ያደረገው የሚደርስባቸውን ስደት ለማስቆም ይሆን? አይደለም። መልአኩ ከወኅኒ ቤት ያወጣቸው የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች እንዲሰሙ ለማድረግ ነበር። ሐዋርያቱን “የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:19, 20) በዚህም የተነሳ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ወደ ቤተ መቅደሱ ሲሄዱ ሐዋርያት በታዛዥነት ይህን ተልእኮ ሲፈጽሙ አገኟቸው።

3, 4. (ሀ) ጴጥሮስና ዮሐንስ መስበካቸውን እንዲያቆሙ ሲታዘዙ ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) የሌሎቹ ሐዋርያት ምላሽስ ምን ነበር?

3 ዮሴፍ ቀያፋ የተባለው የመሐል ዳኛ፣ ከእነዚህ ቆራጥ ሰባኪዎች ሁለቱ ማለትም ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ ከዚህ በፊትም ሸንጎው ፊት ቀርበው እንደነበረ በማስታወስ በቁጣ ደነፋባቸው። “[በኢየሱስ] ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት” አላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 5:28) ቀያፋ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ በሸንጎው ፊት በድጋሚ መቅረባቸው ሊያስደንቀው አይገባም ነበር። ሐዋርያት መጀመሪያውኑም ቢሆን መስበካቸውን እንዲያቆሙ በታዘዙ ጊዜ የሰጡት መልስ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም [“ዝም ማለት አንችልም፣” የ1954 ትርጉም]” የሚል ነበር። በጥንት ዘመን እንደነበረው እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ሁሉ ጴጥሮስና ዮሐንስም እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ ማከናወናቸውን ማቆም አልቻሉም።—የሐዋርያት ሥራ 4:18-20፤ ኤርምያስ 20:9

4 በዚህ ወቅት፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ብቻ ሳይሆኑ በቅርብ የተመረጠውን ማትያስን ጨምሮ ሐዋርያቱ በሙሉ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ በተመለከተ ምን አቋም እንዳላቸው በሕዝብ ፊት የመናገር አጋጣሚ አገኙ። (የሐዋርያት ሥራ 1:21-26) መስበካቸውን እንዲያቆሙ ሲታዘዙ እነርሱም “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በድፍረት መለሱ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

መታዘዝ ያለብን አምላክን ነው ወይስ ሰውን?

5, 6. ሐዋርያት የፍርድ ቤቱን መመሪያ ያልታዘዙት ለምን ነበር?

5 ሐዋርያት በሌላ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የፍርድ ቤት ትእዛዝ የማይጥሱ ሕግ አክባሪ ሰዎች ነበሩ። ሆኖም ማንኛውም ሰው፣ የቱንም ያህል ኃይል ቢኖረው አንድን ሰው የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥስ የማዘዝ ሥልጣን የለውም። ይሖዋ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” ነው። (መዝሙር 83:18) እርሱ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ብቻ ሳይሆን ከፍተኛው ሕግ አውጪ እንዲሁም የዘላለም ንጉሥ ነው። የአምላክን መመሪያ ለመሻር የሚሞክር ማንኛውም የፍርድ ቤት ትእዛዝ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።—ዘፍጥረት 18:25፤ ኢሳይያስ 33:22

6 በዓለም ላይ ምርጥ የተባሉት የሕግ ባለሞያዎች ይህን ሐቅ ተቀብለውታል። ለአብነት ያህል፣ በ18ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ስመ ጥር እንግሊዛዊ ዳኛ ዊልያም ብላክስቶን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን “መለኮታዊ ሕግ” የሚጻረር ሰብዓዊ ሕግ ማውጣት ተገቢ አለመሆኑን ጽፈዋል። በመሆኑም የሳንሄድሪን ሸንጎ ሐዋርያት የስብከት ሥራቸውን እንዲያቆሙ የማዘዝ ሥልጣን አልነበረውም። ይህንን ትእዛዝ መቀበል ለሐዋርያቱ የማይቻል ነገር ነበር።

7. የስብከቱ ሥራ የካህናት አለቆችን ያስቆጣቸው ለምን ነበር?

7 ሐዋርያት መስበካቸውን ለመቀጠል ያደረጉት ቁርጥ ውሳኔ የካህናት አለቆቹን አስቆጣቸው። ቀያፋን ጨምሮ ከካህናት አለቆች አንዳንዶቹ ሰዱቃውያን ስለሆኑ በትንሣኤ አያምኑም ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 4:1, 2፤ 5:17) ሐዋርያት ግን ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን አስረግጠው እየተናገሩ ናቸው። ከዚህም በላይ ከካህናት አለቆች አንዳንዶቹ በሮም ባለ ሥልጣናት ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ብዙ ደክመዋል። ኢየሱስ ለፍርድ ቀርቦ በነበረበት ወቅት እርሱን ንጉሣቸው አድርገው የመቀበል አጋጣሚ ሲቀርብላቸው የካህናት አለቆች “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው እስከመናገር ደርሰው ነበር። (ዮሐንስ 19:15) a ሐዋርያት ደግሞ ኢየሱስ ትንሣኤ ማግኘቱን በእርግጠኝነት ከመናገርም አልፈው “እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ [ከኢየሱስ] ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለም” ብለው እያስተማሩ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:36፤ 4:12) ካህናቱ፣ ሕዝቡ ከሞት የተነሳው ኢየሱስን መሪያቸው አድርገው መመልከት ከጀመሩ ሮማውያን መጥተው ‘ሥፍራቸውንና ሕዝባቸውን’ እንዳይወስዱባቸው ፈርተው ነበር።—ዮሐንስ 11:48

8. ገማልያል ለሳንሄድሪን አባላት ምን ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ሰጣቸው?

8 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ተስፋ ያላቸው አይመስልም ነበር። የሳንሄድሪን ዳኞች ሊያስገድሏቸው ቆርጠው ተነስተዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:33) ይሁን እንጂ ባልታሰበ መንገድ ሁኔታዎች መልካቸው ተለወጠ። ገማልያል የተባለ የሕግ ባለሞያ ከመካከላቸው ተነሳና ባልንጀሮቹን የችኰላ እርምጃ እንዳይወስዱ አስጠነቀቃቸው። ይህ ሰው “ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም” በማለት ጥበብ የተንጸባረቀበት ሐሳብ አቀረበ። ከዚያም “እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል” በማለት ትልቅ ቁም ነገር ተናገረ።—የሐዋርያት ሥራ 5:34, 38, 39

9. ሐዋርያት ያከናውኑት የነበረው ሥራ ከአምላክ የተሰጣቸው መሆኑን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?

9 የሚገርመው ፍርድ ቤቱ የገማልያልን ምክር ተቀበለ። የሳንሄድሪን አባላት “ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዘው ለቀቋቸው።” ሐዋርያት ግን በፍርሃት ከመሸበር ይልቅ መልአኩ እንዲሰብኩ የሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ቆርጠው ነበር። በመሆኑም ከተለቀቁ በኋላ “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም።” (የሐዋርያት ሥራ 5:40, 42) ይሖዋም ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል። “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ የደቀ መዛሙርቱም ቍጥር በኢየሩሳሌም እጅግ እየበዛ ሄደ። ከካህናትም ብዙዎቹ ለእምነት የታዘዙ ሆኑ” የሚለው ጥቅስ ሥራቸው ምን ያህል እንደተባረከ ያሳያል። (የሐዋርያት ሥራ 6:7) ይህ የካህናት አለቆችን ምንኛ አበሳጭቷቸው ይሆን! እየጨመሩ የመጡት ማስረጃዎች እንዳረጋገጡት በእርግጥም ሐዋርያት የሚያከናውኑትን ሥራ የሰጣቸው አምላክ ነበር።

ከአምላክ ጋር የሚጣሉ አይሳካላቸውም

10. ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር፣ ቀያፋ በነበረው ቦታ የተማመነው ለምን ሊሆን ይችላል? ሆኖም ይህ ስህተት የነበረው ለምንድን ነው?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የካህናት አለቆችን የሚሾሟቸው የሮም ባለ ሥልጣናት ነበሩ። ባለጸጋ የሆነውን ዮሴፍ ቀያፋን ሥልጣን ላይ ያስቀመጠው ቫሌርዩስ ግራቱስ ሲሆን ቀያፋም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ከብዙዎቹ ሊቀ ካህናት ይበልጥ ረዘም ላለ ጊዜ በዚህ ቦታ መቆየት ችሎ ነበር። ቀያፋ እንዲህ ሊሳካለት የቻለው አምላክ በጉዳዩ ጣልቃ ስለገባ ሳይሆን በራሱ የማግባባት ችሎታና ከጲላጦስ ጋር በነበረው ወዳጅነት ምክንያት እንደሆነ አድርጎ ሳያስብ አልቀረም። ያም ሆነ ይህ በሰው መታመኑ ስህተት ነበር። ሐዋርያት በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረቡ በሦስተኛው ዓመት ቀያፋ በሮም ባለ ሥልጣናት ዘንድ የነበረውን ተወዳጅነት በማጣቱ ከሊቀ ካህንነቱ አወረዱት።

11. ጳንጥዮስ ጲላጦስና የአይሁድ ሥርዓት መጨረሻቸው ምን ሆነ? ከዚህስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 ቀያፋ ከሥልጣኑ እንዲወርድ ትእዛዝ ያስተላለፈው የሶርያ ገዥና የጲላጦስ የበላይ የነበረው ሉኪየስ ቪቴሊየስ በመሆኑ የቀያፋ የቅርብ ወዳጅ ጲላጦስ ይህ እንዳይሆን መከላከል አልቻለም። እንዲያውም ቀያፋ በወረደ ልክ በዓመቱ ጲላጦስ ራሱ ከሥልጣኑ የተነሳ ከመሆኑም በላይ ለቀረበበት ከባድ ክስ መልስ እንዲሰጥ ወደ ሮም ተጠርቶ ነበር። በቄሣር የተማመኑት የአይሁድ መሪዎችም ቢሆኑ እንደፈሩት ሮማውያን ‘ሥፍራቸውንና ሕዝባቸውን’ ወሰዱባቸው። ይህም የሆነው በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ሠራዊት ቤተ መቅደሱንና የሳንሄድሪንን አዳራሽ ጨምሮ የኢየሩሳሌምን ከተማ ሙሉ በሙሉ በደመሰሰበት ወቅት ነው። “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት እውነተኛ መሆናቸው በዚህ ጊዜ ታይቷል!—ዮሐንስ 11:48፤ መዝሙር 146:3

12. የኢየሱስ ሁኔታ ለአምላክ መታዘዝ የጥበብ አካሄድ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

12 በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ፣ ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን የታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህን አድርጎ ሾሞታል። ማንም ሰው ይህንን ሹመት ሊሽረው አይችልም። በእርግጥም ኢየሱስ “ክህነቱ የማይሻር” ነው። (ዕብራውያን 2:9፤ 7:17, 24፤ 9:11) አምላክ፣ ኢየሱስን በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎም ሾሞታል። (1 ጴጥሮስ 4:5) ኢየሱስ በዚህ ሥልጣኑ በመጠቀም ዮሴፍ ቀያፋም ሆነ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ወደፊት በሕይወት የመኖር አጋጣሚ ያገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ይወስናል።—ማቴዎስ 23:33፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

በዘመናችን ያሉ ደፋር የመንግሥቱ ሰባኪዎች

13. በዘመናችን ከሰው እንደሆነ የታየው የማን ሥራ ነው? ከአምላክ ሆኖ የተገኘውስ የትኛው ሥራ ነው? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

13 እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዘመናችንም ‘ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ’ ሰዎች አልታጡም። (የሐዋርያት ሥራ 5:39) ለአብነት ያህል፣ በጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አዶልፍ ሂትለርን እንደ መሪያቸው አድርገው ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ሂትለር ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋቸው ዝቶ ነበር። (ማቴዎስ 23:10) ዓላማውን ለማሳካት የሚጠቀምበት ድርጅት ደግሞ ይህን ለማድረግ ያለው ችሎታ ከበቂ በላይ ነበር። ናዚዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን አፍሰው ወደ ማጎሪያ ካምፖች በመላክ ረገድ በእርግጥም ተሳክቶላቸዋል። ከዚህም በላይ አንዳንዶቹን መግደል ችለዋል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ብቻ ለማምለክ የወሰዱትን ቁርጥ አቋም ማስቀየርም ሆነ የአምላክን አገልጋዮች በሙሉ ማጥፋት አልቻሉም። እነዚህ ክርስቲያኖች ያከናውኑት የነበረው ሥራ ከሰው ሳይሆን ከአምላክ የመጣ ነበር፤ የአምላክን ሥራ መግታት ደግሞ የማይቻል ነገር ነው። ይህ ታሪክ ከተፈጸመ 60 ዓመታት ያለፉ ሲሆን ከሂትለር ማጎሪያ ካምፖች የተረፉ ታማኝ የይሖዋ ሕዝቦች አምላካቸውን ‘በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም ሐሳባቸው’ እያገለገሉት ነው፤ በሌላ በኩል ግን ሂትለርና የናዚ ፓርቲው ድምጥማጣቸው የጠፋ ሲሆን የሚታወሱትም በመጥፎ ሥራቸው ብቻ ነው።—ማቴዎስ 22:37

14. (ሀ) ተቃዋሚዎች የአምላክ አገልጋዮችን ስም ለማጥፋት ምን ጥረት አድርገዋል? ይህስ ምን አስከትሏል? (ለ) እንዲህ ያሉት ጥረቶች በአምላክ አገልጋዮች ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ? (ዕብራውያን 13:5, 6)

14 ናዚዎች የአምላክን አገልጋዮች ለማጥፋት ጥረት ካደረጉ በኋላ ባሉት ዓመታት ሌሎችም ይሖዋንና ሕዝቡን በመቃወም የወሰዷቸው እርምጃዎች መና ቀርተዋል። አውሮፓ ውስጥ በሚገኙ በርካታ አገራት በተንኰል የተሞሉ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ኃይሎች የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ “የእምነት ክፍል” ወይም ኑፋቄ ተብለው እንዲጠሩ ለማድረግ ሲጥሩ ቆይተዋል፤ ይህም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኖሩት ክርስቲያኖች ላይ ከተሰነዘረው ክስ ጋር ተመሳሳይ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 28:22) ሆኖም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን እንደ ኑፋቄ ሳይሆን እንደ አንድ ሃይማኖት አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ተቃዋሚዎች ይህንን ሐቅ ቢያውቁም የይሖዋ ምሥክሮችን ስም ከማጥፋት ግን አልተመለሱም። በዚህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት ከእነዚህ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ከሥራቸው ተባርረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች በትምህርት ቤት ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። ፍርሃት ያደረባቸው አከራዮችም የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የቆዩ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን ኮንትራት ሰርዘዋል። በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክር ስለሆኑ ብቻ የመንግሥት ቢሮዎች የዜግነት መብታቸውን ነፍገዋቸዋል። ይህ ሁሉ ግን ምሥክሮቹ ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም።

15, 16. በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ሥራቸው ተቃውሞ ሲገጥመው ምን አደረጉ? መስበካቸውን የሚቀጥሉትስ ለምንድን ነው?

15 ለምሳሌ ያህል፣ ፈረንሳይ ውስጥ ሕዝቡ በአብዛኛው ምክንያታዊ ነው። ሆኖም ጥቂት ተቃዋሚዎች የአምላክን መንግሥት ሥራ ለማሽመድመድ የታቀደ ሕግ እንዲወጣ አደረጉ። በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምን አደረጉ? በስብከቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያጧጧፉት ሲሆን አስደሳች ውጤቶችም አግኝተዋል። (ያዕቆብ 4:7) በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር 33 በመቶ በመጨመሩ በዚያች አገር አስደናቂ እድገት ታይቷል! ፈረንሳይ ውስጥ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ መስጠታቸው ሰይጣንን ክፉኛ እንደሚያስቆጣው ግልጽ ነው። (ራእይ 12:17) በፈረንሳይ የሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ” የሚለው ትንቢት በእነርሱ ላይ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ናቸው።—ኢሳይያስ 54:17

16 የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስደት በራሱ ደስታ አያመጣላቸውም። ሆኖም አምላክ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሰጠውን መመሪያ ስለሚታዘዙ የሰሟቸውን ነገሮች ከመናገር ወደኋላ ማለት አይችሉም፤ ወደኋላም አይሉም። ምሥክሮቹ ጥሩ ዜጎች ሆነው ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። በአምላክና በሰው ሕግ መካከል ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ ግን ከሰው ይልቅ ለአምላክ መታዘዝ ይኖርባቸዋል።

አትፍሯቸው

17. (ሀ) ጠላቶቻችንን ልንፈራቸው የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ለሚያሳድዱን ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

17 ጠላቶቻችን የሚዋጉት ከአምላክ ጋር በመሆኑ በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። በመሆኑም እነርሱን ከመፍራት ይልቅ ከኢየሱስ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ ለሚያሳድዱን እንጸልይላቸዋለን። (ማቴዎስ 5:44) እንደ ጠርሴሱ ሳውል ባለማወቅ አምላክን የሚቃወሙ ካሉ ይሖዋ በደግነት ዓይናቸውን ለእውነት ብርሃን እንዲገልጥላቸው እንጸልያለን። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሳውል ከጊዜ በኋላ ወደ ክርስትና ተለውጦ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለ ሲሆን በወቅቱ በነበሩት ባለ ሥልጣናት እጅ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ያም ሆኖ ግን የእምነት ባልንጀሮቹን “ለገዦችና ለባለ ሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ . . . እንዲሁም በማንም ላይ [በቀንደኛ ጠላቶቻቸው ላይም እንኳ] ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ” አሳስቧቸዋል። (ቲቶ 3:1, 2) በፈረንሳይም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ።

18. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን ሊያድናቸው የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) የመጨረሻው ውጤትስ ምን ይሆናል?

18 አምላክ ነቢዩ ኤርምያስን “እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝ” ብሎት ነበር። (ኤርምያስ 1:8) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከስደት ሊያድነን የሚችለው እንዴት ነው? እንደ ገማልያል ያለ ጥሩ አመለካከት ያለው ዳኛ እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል። ወይም ደግሞ ምግባረ ብልሹና ተቃዋሚ የሆነ ባለ ሥልጣን ሳይታሰብ ከቦታው ተነስቶ ምክንያታዊ በሆነ ሌላ ሰው እንዲተካ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግን ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰው ስደት እንዲቀጥል ይፈቅድ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) አምላክ ስደት እንዲደርስብን ከፈቀደ ምንጊዜም ቢሆን ለመጽናት የሚያስችለንን ኃይል ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ደግሞም አምላክ ምንም ዓይነት ሁኔታ እንዲኖር ቢፈቅድ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ፈጽሞ አንጠራጠርም:- ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የሚዋጉ ከአምላክ ጋር እየተዋጉ ነው፤ ከአምላክ ጋር የሚዋጉ ደግሞ አያሸንፉም።

19. የ2006 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ ተከታዮቹን ስደት እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐንስ 16:33) ከዚህ አንጻር በሐዋርያት ሥራ 5:29 ላይ የሚገኘው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” የሚለው ጥቅስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ወቅታዊ ነው። በዚህም የተነሳ ይህ ሐሳብ በ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ እንዲሆን ተመርጧል። በመጪው ዓመትም ሆነ ከዚያም በኋላ ለዘላለም ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን አምላክን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የካህናት አለቆች በዚህ ወቅት በሕዝቡ ፊት የደገፉት “ቄሣር” የተጠላው የሮም ንጉሠ ነገሥት ጢባሪዮስ ነው። ይህ ሰው ግብዝና ነፍሰ ገዳይ ከመሆኑም በላይ ርካሽ የጾታ ድርጊቶች በመፈጸም የታወቀ ነበር።—ዳንኤል 11:15, 21

መመለስ ትችላለህ?

• ሐዋርያት ተቃውሞ ሲደርስባቸው በወሰዱት እርምጃ ምን የሚያበረታታ ምሳሌ ትተውልናል?

• ምንጊዜም ቢሆን ከሰው ይልቅ አምላክን መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

• ተቃዋሚዎቻችን በእርግጥ የሚዋጉት ከማን ጋር ነው?

• ስደት ሲደርስባቸው የሚጸኑ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን መጠበቅ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2006 የዓመት ጥቅስ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” የሚለው ይሆናል። —የሐዋርያት ሥራ 5:29

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል19]

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል”

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀያፋ ከአምላክ ይልቅ በሰው ታምኖ ነበር