በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገና በዓል ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው?

የገና በዓል ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው?

የገና በዓል ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው?

የገና በዓል በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር አብረው ጊዜ የሚያሳልፉበት እንዲሁም ፍቅራቸውን የሚያድሱበት ወቅት ነው። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ጊዜና እርሱ ከሰው ዘር መዳን ጋር በተያያዘ የሚጫወተውን ሚና የሚያስታውሱበት ጊዜ እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። በሩሲያ ግን ከሌሎች የምድር ክፍሎች በተለየ መልኩ፣ የገናን በዓል ማክበር የማይፈቀድበት ጊዜ ነበር። የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ ለዘመናት ገናን በይፋ ስታከብር የቆየች ብትሆንም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ግን በአብዛኛው እንዲህ ማድረግ አትችልም ነበር። ለዚህ ለውጥ ምክንያቱ ምን ነበር?

በ1917 የቦልሼቪክ የኮሚኒስት አብዮት ከፈነዳ ብዙም ሳይቆይ የሶቪየት ባለ ሥልጣናት መላው የአገሪቱ ሕዝብ አምላክ የለም የሚለውን ፓሊሲያቸውን እንዲከተል አስገደዱት። የገና በዓልም ሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተቀባይነት አጣ። መንግሥት ገናንና የዘመን መለወጫ በዓልን በመቃወም ፕሮፖጋንዳ መንዛት ጀመረ። ሌላው ቀርቶ ወቅቱ ተለይቶ የሚታወቅባቸው ምልክቶች ማለትም የገና ዛፍ እና ዴድ ማሮዝ [በሩሲያ የገና አባት የሚጠሩበት ስም ነው] እንኳ በግልጽ ይወገዙ ነበር።

ይሁን እንጂ በ1935 ሩሲያውያን በዓላቱን በሚያከብሩበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ነገር ተከሰተ። ሶቪየቶች ዴድ ማሮዝን፣ የገናን ዛፍ እና የዘመን መለወጫ በዓልን ወደ ቀድሞ ቦታቸው የመለሷቸው ቢሆንም ጎላ ያለ ለውጥ ተደርጎባቸው ነበር። ዴድ ማሮዝ በገና በዓል ሰሞን የሚሰጠው ስጦታ ከዘመን መለወጫ በዓል ጋር እንዲያያዝ ተደረገ። በተመሳሳይም የገና ዛፍ የሚባል ነገር ቀረና የአዲስ ዓመት ዛፍ ተባለ! ስለዚህም በሶቪየት ኅብረት የተካሄደው ይህ ለውጥ የገና በዓል በዘመን መለወጫ በዓል እንዲተካ አደረገ።

የገና ወቅት ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ መልክ እንደሌለው ይፋ ሆነ። የአዲስ ዓመት ዛፍም ሃይማኖታዊ በሆኑ ቅርጻ ቅርጾች ሳይሆን ሶቪየት የደረሰችበትን እድገት በሚያሳዩ ነገሮች እንዲያጌጥ ተደረገ። የሩሲያ ጋዜጣ የሆነው ቫክሩግ ሲቬታ (በዓለም ዙሪያ) እንዲህ ይላል:- “በአዲስ ዓመት ዛፍ ላይ በተለያዩ ዓመታት የተደረጉትን ጌጣጌጦች በማየት በሶቪየት የኮሚኒስቱ ሥርዓት ከተመሠረተ ጀምሮ ያለውን ታሪክ ማወቅ ይቻላል። [የአዲስ ዓመት ዛፉ] ላይ ከተለመዱት ነገሮች ማለትም ከጥንቸል ግልገሎች፣ ሾጣጣ ቅርጽ ካለው በረዶና ከክብ ዳቦ በተጨማሪ በማጭድና በመዶሻ እንዲሁም በትራክተር መልክ የተሠሩ ቅርጾች በማንጠልጠል ያስጌጡት ነበር። ትንሽ ቆይተውም እነዚህ ነገሮች በማዕድን ቆፋሪዎችና በጠፈር ተመራማሪዎች ምስል፣ በነዳጅ ማውጫ መሣሪያዎች፣ በሮኬቶች እንዲሁም ጨረቃ ላይ በሚነዱ መኪናዎች ቅርጽ ተተኩ።”

የገና በዓልስ ምን ሆነ? ሙሉ በሙሉ አልተቀበሉትም ነበር። እንዲያውም የሶቪየት ባለ ሥልጣናት ከሌሎች የሥራ ቀናት ጋር እኩል እንዲታይ አደረጉት። የገና በዓልን ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ ለማክበር የሚፈልጉ ሰዎችም እንዲህ ማድረጋቸው በመንግሥት ዘንድ ጥላቻና ሌሎች መዘዞችን ሊያስከትልባቸው የሚችል በመሆኑ በዓሉን ማክበር የሚችሉት በድብቅ ብቻ ነበር። በእርግጥም በሩሲያ ውስጥ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የበዓላት ቀናትን አስመልክቶ ትልቅ ለውጥ ታይቶ ነበር፤ ይኸውም በዓላት ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው መሆኑ ቀረ።

በቅርቡ የተደረገ ለውጥ

በ1991 ሶቪየት ኅብረት ስትፈራርስ ነዋሪዎቿ ትልቅ ነፃነት አገኙ። መንግሥትም ያራምደው የነበረው አምላክ የለም የሚለው ፖሊሲ ቀረ። አዳዲሶቹ መንግሥታትም ቢሆኑ በአብዛኛው ለሃይማኖት ግድ የማይሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መሆን እንዳለባቸው የሚያምኑ ነበሩ። ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ብዙ ሰዎች ከዚህ በኋላ እምነታቸውን በነፃነት እንደሚያራምዱ ተሰማቸው። ይህን ማድረግ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ የገና በዓልን በሃይማኖታዊ መልኩ ማክበር ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሆኖም እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ለነበራቸው ለብዙዎቹ ሁኔታው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቷል። ለምን?

ዓመታት ባለፉ ቁጥር በዓሉ ንግድ የሚጧጧፍበት ሆነ። በምዕራቡ ዓለም እንደሚታየው ሁሉ እዚህም የገና በዓል ሰሞን አምራቾች፣ የጅምላ ነጋዴዎች እና ቸርቻሪዎች ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱበት ወቅት እየሆነ መጣ። የገና በዓል ማጋጌጫዎች በሱቆች ፊት ለፊት ላይ ተደርድረው መታየት ጀመሩ። ከዚህ ቀደም በሩሲያ የማይታወቁ የምዕራቡ ዓለም የገና በዓል ሙዚቃዎችና የልደት መዝሙሮች በሱቆች ውስጥ መሰማት ጀመሩ። ትልቅ ሻንጣ የያዘ ሱቅ በደረቴ በባቡሮችና በሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርቶች ውስጥ የገና ዕቃዎችን ሲሸጥ ማየት የተለመደ ነው። በአጠቃላይ ዛሬ በሩሲያ የሚታየው ሁኔታ ይህን ይመስላል።

በዚህ በበዓል ሰሞን ይህን መሰሉ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩ ብዙም የማይረብሻቸው ሰዎች ደግሞ ስካርና ከዚያም ጋር ተያይዘው የሚመጡት ሌሎች መጥፎ ችግሮች ደስታቸውን ያሳጧቸዋል። በሞስኮ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የሚሠራ ሐኪም እንዲህ ብሏል:- “ዶክተሮች የዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርበት ወቅት በመኪና ተገጭቶ፣ ተጋግጦ ወይም በስለት ተወግቶ አሊያም በጥይት ቆስሎ የሚመጣ ሰው እንደሚያጋጥማቸው ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው። እነዚህም በቤት ውስጥ በሚከሰቱ ጠቦች፣ ጠጥቶ በመደባደብ እና በመኪና አደጋ የሚከሰቱ ናቸው።” በሩሲያ የሳይንስ አካዳሚ ቅርንጫፍ ውስጥ የሚሠራ አንድ ሳይንቲስት ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ከአልኮል ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ችግሮች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ መንገድ እየጨመረ ነው። በይበልጥ ደግሞ በ2000 ቁጥሩ አሻቅቦ የነበረ ከመሆኑም በተጨማሪ ራስን ማጥፋትና ነፍስ ግድያ ከሌላው ጊዜ ከፍ ያለ ነበር።”

የሚያሳዝነው በበዓል ሰሞን እነዚህ ድርጊቶች በሩሲያ ይበልጥ እንዲባባሱ የሚያደርግ ሌላም ምክንያት አለ። ኢዝቬስቲያ የተባለ ጋዜጣ “ሩሲያውያን ገናን የሚያከብሩት ሁለት ጊዜ ነው” በሚለው ርዕሰ አንቀጹ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ቢያንስ ከ10 የሩሲያ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ገናን ሁለት ጊዜ ያከብራል። የሩሲያ የሕዝብ አስተያየትና ገበያ ጥናት እንደሚያመለክተው ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 8 በመቶ የሚሆኑት ገናን፣ በካቶሊክ የቀን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 እንዲሁም እንደ ኦርቶዶክስ የቀን አቆጣጠር ጥር 7 እንደሚያከብሩ ተናግረዋል . . . አንዳንዶች ስለ ገና በዓል ሲያስቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለሃይማኖታዊ ገጽታው ሳይሆን ለፈንጠዝያው ነው።” a

በአሁኑ ጊዜ ያለው የበዓሉ ሥርዓትስ በእርግጥ ለክርስቶስ ክብር ያመጣል?

በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው በበዓል ሰሞን ብዙ አምላክን የማያስደስቱ ድርጊቶች ይታያሉ። ይህ ጉዳይ የሚያሳዝን ቢሆንም አንዳንዶች ለአምላክና ለኢየሱስ ካላቸው አክብሮት የተነሳ በዓላቱን ማክበር እንዳለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። አምላክን ለማስደሰት መፈለግ የሚያስመሰግን ነገር ነው። ይሁን እንጂ በእርግጥ በገና በዓል ሰሞን አምላክና ክርስቶስ ይደሰታሉ? እስቲ የዚህን በዓል አመጣጥ እንመልከት።

ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሶቪየቶች ስለ ገና በዓል ካላቸው አመለካከት ጋር በተያያዘ የሚሰማው ስሜት ምንም ይሁን ምን ግሬት ሶቪየት ኢንሳይክሎፒዲያ ያስቀመጠውን የሚከተለውን ታሪካዊ ሐቅ ግን ማስተባበል አይችልም:- “ገና . . . ከክርስትና በፊት ከነበረው፣ አማልክት ‘እንደሚሞቱና ከሞት እንደሚነሱ’ ከሚታመንበት አምልኮ የተወሰደ በዓል ነው። በዓሉ ከታኅሣሥ 21-25 ባለው ጊዜ ውስጥ ቀኑ አጭር በሚሆንበት የክረምቱ ወቅት ላይ የሚከበር ሲሆን በተለይ በግብርና በሚተዳደሩ ሰዎች ዘንድ በጣም የተለመደ ነበር። በዚህ መንገድ ተፈጥሮን አዲስ ሕይወት የሚዘራበት የአዳኙ አምላክ ‘ልደት’ በየዓመቱ ይከበራል።”

ምናልባት ኢንሳይክሎፒዲያው በግልጽ ያስቀመጠው የሚከተለው ሐሳብ ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል:- “የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ስለ ገና በዓል መከበር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። . . . የሚትረ አምላኪዎች ቀኑ አጭር በሚሆንበት የክረምቱ ወቅት ላይ የሚያከብሩት በዓል ከአራተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በክርስትና ውስጥ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን እርሱም ወደ ገና በዓልነት ተቀየረ። የገና በዓልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበሩት በሮም የሚኖሩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ናቸው። በአሥረኛው ክፍለ ዘመን የገና በዓልም ሆነ ክርስትና ወደ ሩሲያ ገቡና የጥንት ስላቮች የቀድሞ አያቶቻቸውን መንፈስ ለማክበር ሲሉ የክረምቱን ወቅት ጠብቀው ከሚያከብሩት በዓል ጋር ውሕደት ፈጠሩ።”

‘የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ታኅሣሥ 25 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ስለመወለዱ ምን ይላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን አይናገርም። ኢየሱስም ቢሆን ልደቱ እንዲከበር ሊያዝ ቀርቶ የተወለደበትን ቀን እንኳ እንደተናገረ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደው በዓመት ውስጥ በየትኛው ወቅት ላይ እንደሆነ ማስላት እንድንችል ፍንጭ ይሰጠናል።

እንደ ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 እና 27 ዘገባ ከሆነ ኢየሱስ የተገደለው ኒሳን 14 መገባደጃ ላይ ሲሆን የአይሁድ የማለፍ በዓል መከበር የጀመረው ደግሞ መጋቢት 31, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። የሉቃስ ወንጌል ደግሞ ኢየሱስ ተጠምቆ አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው 30 ዓመት እንደነበር ይነግረናል። (ሉቃስ 3:21-23) ኢየሱስ ይህን አገልግሎት ያበቃው ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ዕድሜው 33 ዓመት ተኩል ይሆናል ማለት ነው። ወደ ጥቅምት 1, 33 ገደማ ደግሞ 34 ዓመት ይሞላው ነበር። ሉቃስ እንደዘገበው ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት “በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ።” (ሉቃስ 2:8) እረኞች በታኅሣሥ ብርድ መንጎቻቸውን ይዘው በሜዳ አያድሩም ነበር። በተጨማሪም በቤተልሔም አካባቢ በዚህ ወቅት በረዶ ሊጥል ይችላል። ነገር ግን ጥቅምት 1 አካባቢ መንጎቻቸውን ይዘው ውጭ ማደር ይችሉ የነበረ ሲሆን መረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ የተወለደው በዚህ ጊዜ ነው።

ስለ ዘመን መለወጫ በዓልስ ምን ማለት ይቻላል? እርሱም ቢሆን እስካሁን እንዳየነው በጥሩ ጎኑ የሚታወቅ በዓል አይደለም። ምንም እንኳ ከሃይማኖት ጋር ንክኪ እንዳይኖረው ለማድረግ ጥረት ቢደረግም አመጣጡ ግን አጠያያቂ ነው።

በበዓላት ወቅት በግልጽ ከሚታዩት ድርጊቶች አንጻር ሲታይ ‘በዓሉ የጌታ ነው’ እንደሚሉት ያሉ መርሆች ትርጉም አልባ ይሆናሉ። በገና በዓል ሰሞን የሚታየውን የተጧጧፈ ንግድና የሥነ ምግባር ጉድለት መመልከትህ እንዲሁም ምንጩ አረማዊ መሆኑን ማወቅህ አሳዝኖህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ለአምላክም ሆነ ለክርስቶስ ክብር ለመስጠት እግረ መንገዱንም የቤተሰባችንን አንድነት ለማጠናከር የሚረዳ ትክክለኛ ጎዳና አለ።

አምላክንና ኢየሱስን ለማክበር የሚያስችል የተሻለ መንገድ

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበትን ዓላማ ሲገልጽ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት’ እንደሆነ ይናገራል። (ማቴዎስ 20:28) ስለ ኃጢአታችን ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ። ምናልባት አንዳንዶች የገና በዓል ወቅት ኢየሱስን ማክበር የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የገናም ሆነ የዘመን መለወጫ በዓል ከኢየሱስ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለና ከአረማውያን የመጡ መሆናቸውን ቀደም ሲል ተመልክተናል። በተጨማሪም የገና በዓል ሰሞን ለአንዳንዶች የሚማርክ ቢሆንም ይበልጥ የሚታወቀው ግን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወቅት በመሆኑ ነው። ከዚህም በላይ የገና በዓል አምላክንና ክርስቶስን በማያስደስቱ አስጸያፊ ተግባራት የተሞላ መሆኑ የተረጋገጠ ነው።

አምላክን ለማስደሰት የሚፈልግ አንድ ሰው ምን ማድረግ ይኖርበታል? አምላክንና ክርስቶስን ለማስደሰት የፈለገ ቅን ሰው መንፈሳዊ እንደሆነ እንዲሰማው የሚያደርጉትን ሆኖም ከቅዱስ ጽሑፉ የራቁ የሰው ወጎችን የሙጥኝ ብሎ ከመያዝ ይልቅ እውነተኛውን መንገድ ይፈልጋል። ታዲያ እውነተኛው መንገድ የትኛው ነው? ምንስ ማድረግ ይኖርብናል?

ኢየሱስ ራሱ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) እውነት ነው፣ አንድ ከልቡ ቅን የሆነ ሰው አምላክንና ክርስቶስን እንዴት ማክበር እንደሚቻል ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ይፈልጋል። ከዚያም ይህንን የተማረውን እውነት በዓመት ውስጥ በተወሰነ ወቅት ላይ ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ተግባራዊ ያደርጋል። አምላክም በዚህ ልባዊ የሆነ ጥረት በጣም ይደሰታል። ይህን ማድረጉም ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራዋል።

ቤተሰቦችህ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በሚስማማ መንገድ በእውነት አምላክንና ኢየሱስን እያከበሩ ካሉት ሰዎች መካከል እንዲሆኑልህ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ይህን አስፈላጊ እውቀት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያገኙ ረድተዋል። አንተም በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልገህ እንድታገኝ አሊያም በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች በአንዱ ተጠቅመህ እንድትጽፍላቸው እናበረታታሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሩሲያ፣ ከጥቅምት 1917 አብዮት በፊት የምትጠቀመው በጁልየስ የዘመን አቆጣጠር ነበር። ይሁንና ብዙ አገሮች አቆጣጠራቸውን በጎርጎርዮስ የቀን አቆጣጠር ቀየሩ። በ1917 የጁልየስ የቀን መቁጠሪያ ከጎርጎርዮስ የቀን መቁጠሪያ 13 ቀናት ወደኋላ ይቀር ነበር። ከአብዮቱ በኋላ ሶቪየቶች የዘመን አቆጣጠራቸውን በጎርጎርዮስ የቀን መቁጠሪያ በመተካታቸው ሩሲያም ሌሎች አገሮች የሚጠቀሙበትን የዘመን አቆጣጠር መጠቀም ጀመረች። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን በዓላቶቿን ለማክበር “የጥንቱ” የዘመን አቆጣጠር ብላ በሰየመችው በጁልየስ የቀን መቁጠሪያ መጠቀሟን አላቆመችም። ምናልባትም ሩሲያ የገናን በዓል የምታከብረው ጥር 7 መሆኑን ሰምተህ ይሆናል። ሆኖም በጎርጎርዮስ አቆጣጠር ጥር 7 ማለት በጁልየስ የቀን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 መሆኑን አትዘንጋ። ስለዚህም አብዛኞቹ ሩሲያውያን ታኅሣሥ 25 የምዕራቡ ዓለም የሚያከብረውን ገና፣ ጥር 1 የዘመን መለወጫ በዓልን፣ ጥር 7 የኦርቶዶክስን ገና እንዲሁም ጥር 14 በጥንቱ የቀን አቆጣጠር የዘመን መለወጫ በዓልን ያከብራሉ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዘመን መለወጫ በዓል አመጣጥ

የጆርጂያ ኦርቶዶክስ መነኩሴ የተናገሩት

“የዘመን መለወጫ በዓል በጥንቷ ሮም ይከበሩ ከነበሩ ብዛት ያላቸው የአረማውያን ክብረ በዓላት የመጣ ነው። ጃንዋሪ (ጥር) 1 የአረማውያኑ አምላክ ለሆነው ለጃኑስ የተወሰነ የበዓል ቀን ሲሆን የዚህ ወር መጠሪያ እንኳ የተወሰደው ከዚሁ ጣዖት ስም ነው። የጃኑስ ምስል በተቃራኒ አቅጣጫ የሚያዩ ሁለት ፊቶች ያሉት ሲሆን ይህም ያለፈውንም ሆነ የአሁኑን ጊዜ ያያል የሚል ትርጉም አለው። አንድ ሰው ጥር 1ን በደስታ ካሳለፈ እንዲሁም በደንብ ከበላና ከጠጣ ዓመቱን በሙሉ በደስታና በእርካታ ይኖራል የሚል አንድ የተለመደ አባባል ነበረ። በአገራችን ያሉ ብዙ ሰዎችም የዘመን መለወጫ በዓልን የሚያከብሩት ይህንን አጉል እምነት መሠረት በማድረግ ነው . . . አንዳንድ ሰዎች በእነዚህ የአረማውያን በዓላት ላይ ለአንድ ጣዖት በቀጥታ መሥዋዕት ያቀርባሉ። አንዳንዶቹ ያላቸው ስም በጣም መጥፎ ከመሆኑም በተጨማሪ ፈንጠዝያ፣ ዝሙትና ምንዝር የሚካሄድባቸው ናቸው። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ፣ ለምሳሌ የጃኑስ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት፣ ስካር እንዲሁም የትኛውም ዓይነት ርኩሰት ይፈጸማል። እኛ ራሳችን ከዚህ ቀደም የዘመን መለወጫን እንዴት እንዳከበርን ካስታወስን ሁላችንም በዚህ አረማዊ በዓል ላይ እንደተካፈልን አምነን መቀበል ይኖርብናል።”—አንድ የጆርጂያ ጋዜጣ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝበ ክርስትና የሚትራን አምልኮ ተቀብላለች

[ምንጭ]

Museum Wiesbaden

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እረኞች በታኅሣሥ ብርድ መንጎቻቸውን ይዘው በሜዳ አያድሩም ነበር