በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱስ—ያሳለፈው በችግር የተሞላ ታሪክ

የጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱስ—ያሳለፈው በችግር የተሞላ ታሪክ

የጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱስ—ያሳለፈው በችግር የተሞላ ታሪክ

“መጽሐፍ ቅዱስ በአገራችን [በጣሊያን] ውስጥ ሰፊ ስርጭት ካላቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢሆንም እምብዛም ከማይነበቡት መጻሕፍት መካከልም ሳይሆን አይቀርም። የእምነቱ ተከታዮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲተዋወቁ ያን ያህል ማበረታቻ የማይሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ እንደ አምላክ ቃል አድርገው እንዲያነቡት የሚደረግላቸው እርዳታ በጣም አናሳ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የሚያስተምራቸው ሰው አያገኙም።”

በ1995 የጣሊያን ሊቀ ጳጳሳት ጉባኤ ያቀረበው ይህ ሐሳብ በርካታ ጥያቄዎች ያስነሳል። ባለፉት መቶ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ ጣሊያን ውስጥ ምን ያህል ይነበብ ነበር? የመጽሐፉ ስርጭት ከሌሎች አገሮች አንጻር ሲታይ ወደኋላ የቀረው ለምንድን ነው? አሁንም ቢሆን በጣሊያን እምብዛም የማይነበብ መጽሐፍ የሆነው ለምንድን ነው? በጣሊያንኛ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞችን ታሪክ መመርመራችን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያስገኝልናል።

ከላቲን የተወለዱት እንደ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ስፓንኛ፣ የፖርቱጋል ቋንቋና የመሳሰሉት እየዳበሩ የመጡት በብዙ መቶ ዘመናት ሂደት ነው። ላቲን ይናገሩ በነበሩ በርካታ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ተራው ሕዝብ ይጠቀምባቸው የነበሩት ከላቲን የተወረሱ መግባቢያ ቋንቋዎች ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኙ የመጡ ከመሆኑም በላይ ለጽሑፍ ሥራም ይውሉ ጀመር። አዳዲስ ቋንቋዎች እየዳበሩ መምጣታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ነበረው። እንዴት? በጊዜ ሂደት፣ ቤተ ክርስቲያን በምትጠቀምበት ቅዱስ ቋንቋ ይኸውም በላቲንና ሕዝቡ በሚጠቀምባቸው በርካታ ቀበሌኛዎች እንዲሁም ከቦታ ቦታ መጠነኛ ልዩነት ባላቸው አዳዲስ ቋንቋዎች መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ ሄደ። በመሆኑም ላቲን መደበኛ ትምህርት ያላገኙ ሰዎች የሚረዱት ቋንቋ መሆኑ አከተመ።

በ1000 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጣሊያን ልሳነ ምድር የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች በላቲን የተዘጋጀውን ቩልጌት ቢያገኙ እንኳ አንብበው ለመረዳት ግን ይቸገሩ ነበር። ለብዙ መቶ ዓመታት፣ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በወቅቱ በነበሩት ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት ጨምሮ የትምህርት ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር። ከዚህ ተጠቃሚ የሆኑት ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ነበሩ። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ቀስ በቀስ “የማይታወቅ መጽሐፍ” ሆነ። ይሁንና ብዙዎች የአምላክን ቃል ማግኘት ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ቋንቋ የመረዳት ፍላጎትም ነበራቸው።

በጥቅሉ ሲታይ ቀሳውስት “መናፍቅነት” እንዲስፋፋ ያበረታታል በሚል ፍራቻ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይተረጎም ይቃወሙ ነበር። የታሪክ ምሑር የሆኑት ማስሲሞ ፊርፖ እንዳሉት መጽሐፍ ቅዱስ “በጣሊያንኛ ተተረጎመ ማለት ቀሳውስቱ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ፍጹም የበላይነት ያስከብርላቸው የነበረው የቋንቋ አጥር [ላቲን] ተወገደ [ማለት ይሆናል]።” ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው እስካሁን ድረስ በጣሊያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስን እንዲሆን ያደረገው መሠረታዊ ችግር ከባሕል፣ ከሃይማኖትና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው።

የመጀመሪያዎቹ ከፊል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

በ13ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ለመጀመሪያ ጊዜ ከላቲን ወደ ጣሊያንኛ ይተረጎሙ ጀመር። እነዚህ ከፊል የትርጉም ሥራዎች በእጅ የተገለበጡና በጣም ውድ ነበሩ። በ14ኛው መቶ ዘመን፣ የትርጉም ሥራው የተካሄደው በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በልዩ ልዩ ሰዎች ቢሆንም የተተረጎሙት መጻሕፍት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ይቻላል በጣሊያንኛ ሊገኝ ቻለ። ስማቸው ባልተገለጸ ተርጓሚዎች የተዘጋጁት አብዛኞቹ የትርጉም ሥራዎች ሀብታሞችና የተማሩ ሰዎች እጅ የገቡ ሲሆን የማግኘት አጋጣሚ የነበራቸውም እነርሱ ብቻ ነበሩ። የማተሚያ መሣሪያ መፈልሰፍ መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶች ለማዘጋጀት የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ያደረገ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ “የማግኘት አጋጣሚ የነበራቸው ጥቂቶች” እንደነበሩ የታሪክ ምሑር የሆኑት ጂልዮላ ፍራንዪቶ ገልጸዋል።

ለበርካታ መቶ ዘመናት አብዛኛው ሕዝብ የመማር አጋጣሚ ሳያገኝ ቀርቷል። በ1861 ጣሊያን በተዋሃደችበት ወቅት እንኳ 74.7 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር። የሚገርመው፣ አዲሱ የጣሊያን መንግሥት ሁሉም ሰው በነፃ ትምህርት እንዲያገኝና መማር ግዴታ እንዲሆን ዝግጅት ባደረገበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ፓየስ ዘጠነኛ በ1870 ለንጉሡ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት” የታለመ “ወረርሽኝ” ሲሉ የገለጹትን ይህን ሕግ እንዲቃወም አሳስበዋል።

የመጀመሪያው የጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱስ

በጣሊያንኛ የተዘጋጀው የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ በ1471 በቬኒስ የታተመ ሲሆን ይህም ተንቀሳቃሽ ማተሚያ በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ ከዋለ ከ16 ዓመታት ገደማ በኋላ መሆኑ ነው። የካማልዶላውያን ቡድን መነኩሴ የሆኑት ኒኮሎ ማሌርቢ በስምንት ወራት ውስጥ የትርጉም ሥራቸውን አጠናቀቁ። ይህ መጽሐፍ ማሌርቢ በአመዛኙ በወቅቱ በነበሩት የትርጉም ሥራዎች ላይ ተመሥርተው የላቲኑን ቩልጌት እያመሳከሩ ማስተካከያዎች በማድረግና አንዳንድ ቃላትን በአካባቢያቸው በቬኔሺያ የተለመዱ በሆኑት በመተካት ያዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ይህ የትርጉም ሥራ ለሕትመት ከበቁት ጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ሁሉ ከፍተኛ ስርጭት ያገኘ የመጀመሪያው እትም ነው።

በቬኒስ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም ያዘጋጀው ሌላው ሰው አንቶንዮ ብሩቾሊ ነበር። ይህ ሰው የሥልጣኔ አቀንቃኝና የፕሮቴስታንቶችን አመለካከት የሚቀበል ቢሆንም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ግን አላቋረጠም። በ1532 ብሩቾሊ ከመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎመ። ይህ ከበኩረ ጽሑፉ ወደ ጣሊያንኛ የተተረጎመ የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ትርጉሙ ግሩም በሆነ የጣሊያንኛ የጽሑፍ ቋንቋ የተዘጋጀ ባይሆንም በወቅቱ ከነበረው ውስን የጥንት ቋንቋዎች እውቀት አንጻር ሲታይ በኩረ ጽሑፎቹን በጥብቅ የተከተለ መሆኑ አስደናቂ ነው። ብሩቾሊ በአንዳንድ ቦታዎችና እትሞች ላይ የአምላክን ስም “ዬኦቫ” ብሎ በመጻፍ ወደ ቀድሞ ቦታው መልሶታል። ብሩቾሊ ያዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ለአንድ መቶ ዓመት ገደማ በጣሊያን ፕሮቴስታንቶችና ሃይማኖታዊ ተገንጣዮች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አግኝቶ ቆይቷል።

ከጊዜ በኋላ የብሩቾሊን መጽሐፍ ቅዱስ በማረም የተዘጋጁ ሌሎች የጣሊያንኛ ትርጉሞች የታተሙ ሲሆን አንዳንዶቹን ያሳተሙት ካቶሊኮች ነበሩ። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የጎላ ስርጭት አልነበራቸውም። በ1607፣ የካልቪን ቡድን ፓስተር የነበረውና ወላጆቹ ሃይማኖታዊ ስደት እንዳይደርስባቸው ሸሽተው ወደ ስዊዘርላንድ የሄዱት ጆቫኒ ዲዮዳቲ ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ወደ ጣሊያንኛ የተተረጎመ ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ በጄኔቫ አሳተመ። ዲዮዳቲ ያዘጋጀው እትም የጣሊያን ፕሮቴስታንቶች ለብዙ መቶ ዘመናት የተጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ ለመሆን በቅቷል። መጽሐፍ ቅዱሱ ከተዘጋጀበት ጊዜ አንጻር ሲታይ ግሩም የጣሊያንኛ ትርጉም ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። የዲዮዳቲ ትርጉም ጣሊያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዲረዱ አስችሏል። ሆኖም ቀሳውስቱ ያካሂዱ የነበረው ቁጥጥር ይህም ሆነ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች እንዳይሰራጩ እንቅፋት ሆኗል።

መጽሐፍ ቅዱስ—“የማይታወቅ መጽሐፍ”

ኢንሳይክሎፒዲያ ካቶሊካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ቤተ ክርስቲያን በመጻሕፍት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የነበራትን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥታለች። የማተሚያ መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊት ባለው ጊዜ አደገኛ እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ መጻሕፍት በእሳት ይቃጠሉ ስለነበር የታገዱ መጻሕፍትን ዝርዝር ማዘጋጀቱ አስፈላጊ መስሎ አልታያትም።” የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ከጀመረ በኋላ እንኳ በበርካታ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የነበሩ ቀሳውስት የመናፍቃን መጻሕፍት የሚሏቸውን ጽሑፎች ስርጭት ለመገደብ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። በ1546 በትሬንት ጉባኤ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ወደተለያዩ ቋንቋዎች የመተርጎሙ ጉዳይ ለውይይት ከቀረበ በኋላ መሠረታዊ ለውጥ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች ተፈጠሩ። በትርጉም ሥራ ላይ እገዳ እንዲጣል የፈለጉ ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ ልሳን መዘጋጀቱ “የመናፍቃን ሁሉ መቀፍቀፊያና ምንጭ” እንዲሆን እንዳደረገው ገለጹ። ይህን የተቃወሙ ወገኖች ደግሞ “ጠላቶቻቸው” የሆኑት ፕሮቴስታንቶች፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ ቋንቋ እንዳይተረጎም የምትከለክለው “ማታለያዋና ውሸቷ” እንዳይጋለጥ ነው በማለት ሊከራከሩ ይችላሉ የሚል ሐሳብ አቀረቡ።

ጉባኤው ስምምነት ላይ ባለመድረሱ በጉዳዩ ላይ አንድ ቁርጥ ያለ አቋም ሳይወስድ ቀርቷል። ሆኖም ጉባኤው ቩልጌት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሆነ በማጽደቅ ያለፈ ሲሆን መጽሐፉም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ማስተማሪያ ለመሆን በቅቷል። ይሁን እንጂ በሮም የሳሌስያነም ጳጳሳት ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆኑት ካርሎ ቡድሴቲ ቩልጌትን “ትክክለኛ” ብሎ መሰየም “ተቀባይነት ያለው ብቸኛው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ከማለት ተለይቶ እንደማይታይ” ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ የታየው ሁኔታ የዚህን አባባል እውነተኝነት አረጋግጧል።

በ1559 ሊቀ ጳጳስ ፖል አራተኛ ካቶሊኮች ማንበብ፣ መሸጥ፣ መተርጎም ወይም መያዝ የሌለባቸውን መጻሕፍት ዝርዝር የያዘ የመጀመሪያውን ማውጫ አሳተሙ። እነዚህ መጻሕፍት ለእምነትና ለሥነ ምግባራዊ አቋም መጥፎና አደገኛ እንደሆኑ ተደርገው የተቆጠሩ ናቸው። ዝርዝሩን የያዘው ማውጫ በብሩቾሊ የተዘጋጀውን ጨምሮ በጣሊያንኛ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማንበብን ያወግዛል። መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ ሰዎች ከአባልነት ተሰርዘዋል። በ1596 የተዘጋጀው ማውጫ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ጥብቅ ነበር። ከዚህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በጣሊያንኛ የመተርጎምም ሆነ የማተም ፈቃድ መሰጠቱ አቆመ። እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሶች እንዲቃጠሉም ተወሰነ።

ከዚህም የተነሳ ከ16ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ በኋላ በቤተ ክርስቲያን አደባባዮች ላይ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማቃጠል የተለመደ ነገር ሆነ። በጥቅሉ ሲታይ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የመናፍቃን መጽሐፍ ተደርገው ይታዩ ጀመር፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እስካሁን ድረስ እንዳለ ነው። በሕዝብም ሆነ በግል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተገኙ መጽሐፍ ቅዱሶችና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ መጻሕፍት በሙሉ ማለት ይቻላል የተቃጠሉ ከመሆኑም ሌላ በቀጣዮቹ 200 ዓመታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጣሊያንኛ ለመተርጎም የተነሳ አንድም ካቶሊክ አልነበረም። በጣሊያን ልሳነ ምድር የተሰራጩት ብቸኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች የፕሮቴስታንት ምሑራን የተረጎሟቸው ነበሩ፤ ይህም ቢሆን የተካሄደው እንዳይወረስ በመፍራት በድብቅ ነበር። በመሆኑም ታሪክ ጸሐፊው ማርዮ ቺንዮኒ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለብዙ መቶ ዓመታት ተራው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል የማይታወቅ መጽሐፍ ሆነ፤ በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጣሊያናውያን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አንድም ገጽ የማንበብ አጋጣሚ ሳያገኙ አልፈዋል።”

እገዳው ላላ

ከጊዜ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት አሥራ አራተኛ ሰኔ 13, 1757 በተዘጋጀው ማውጫ ላይ ባወጡት ድንጋጌ “ቅዱስ ሲኖዶሱ ፈቃድ የሰጠባቸውንና ጳጳሳቱ በሚሰጡት አመራር በየቋንቋው የተዘጋጁትን እትሞች ማንበብ እንደሚቻል በመፍቀድ” የበፊተኛውን ውሳኔ አሻሽለዋል። ይህም በመሆኑ፣ ከጊዜ በኋላ የፍሎረንስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አንቶንዮ ማርቲኒ ቩልጌትን ለመተርጎም ተነሱ። የመጀመሪያው ክፍል የታተመው በ1769 ሲሆን ሥራው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው ደግሞ በ1781 ነበር። አንድ የካቶሊክ ዘገባ የማርቲኒ ትርጉም “ጥሩ የትርጉም ሥራ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል የመጀመሪያው [ጣሊያንኛ] መጽሐፍ ቅዱስ ነው” ሲል ገልጿል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ላቲን የማያውቁ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያን የፈቀደችውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበው መረዳት አይችሉም ነበር። ማርቲኒ ያዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በቀጣዮቹ 150 ዓመታት በጣሊያናውያን ካቶሊኮች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ብቸኛው እትም ነበር።

በሁለተኛው የቫቲካን አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ ተላለፈ። በ1965 የተዘጋጀው ዴኢ ዌርቡም የተባለው ሰነድ “በተለይ ከቅዱሳን መጻሕፍት በኩረ ጽሑፎች፣ ወደተለያዩ ቋንቋዎች . . . የሚተረጎሙ ጥሩና ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሶች” ማሳተም የሚበረታታ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ገለጸ። ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ በ1958 ፖንቲፊቾ ኢስቲቱቶ ቢብሊኮ (የጳጳሳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተቋም) “ከበኩረ ጽሑፎቹ ላይ የመጀመሪያውን የተሟላ የካቶሊክ ትርጉም” አሳትሞ ነበር። ይህ እትም መለኮታዊውን ስም “ጃህቬ” ብሎ በመጻፍ በጥቂት ቦታዎች ላይ መልሶ አስገብቷል።

በተራው ሕዝብ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይዘጋጅ የተሰነዘረው ተቃውሞ መጥፎ ውጤት ያስከተለ ከመሆኑም ሌላ ጉዳቱ እስካሁን ድረስ ዘልቋል። ይህ ተጽዕኖ ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ጂልዮላ ፍራንዪቶ “አማኞች አእምሯቸውንና ሕሊናቸውን የመጠቀም ነፃነት ያላቸው መሆኑን እንዲጠራጠሩ አድርጓል” ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሃይማኖታዊ ወጎችን ማክበር ግዴታ በመሆኑ ብዙ ካቶሊኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ አስበልጠው የሚያዩት እነዚህን ወጎች ነው። ምንም እንኳ መሃይምነት ሙሉ በሙሉ የተወገደ ቢሆንም ይህ ሁሉ ተጽዕኖ ሰዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች እንዲርቁ አድርጓል።

ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት የወንጌላዊነት ሥራ ለጣሊያንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል። በ1963 የይሖዋ ምሥክሮች የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን በጣሊያንኛ አዘጋጁ። በ1967 ደግሞ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወጣ። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ጣሊያን ውስጥ ብቻ እንኳ ከ4,000,000 በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ተሰራጭቷል። ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም በቦታው መልሶ ያስገባው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የበኩረ ጽሑፉን መንፈስ በጥብቅ የሚከተል በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል።

የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ፣ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ቅዱስ ጽሑፉ የያዘውን የተስፋ መልእክት እያነበቡ ያብራራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) ወደፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስትገናኝ በቅርቡ “ጽድቅ የሚኖርበት . . . አዲስ ምድር” እንደሚቋቋም አምላክ የሰጠውን ግሩም ተስፋ በተመለከተ የራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዲያሳዩህ ለምን አትጠይቃቸውም?—2 ጴጥሮስ 3:13

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቬኒስ

ሮም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሩቾሊ ባዘጋጀው ትርጉም ውስጥ ዬኦቫ በሚለው መለኮታዊ ስም ተጠቅሟል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታገዱ መጻሕፍትን ዝርዝር የያዘው ማውጫ ወደ ጣሊያንኛ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች አደገኛ እንደሆኑ ይገልጻል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ርዕሱ የሚገኝበት ገጽ:- Biblioteca Nazionale Centrale di Roma

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ብሩቾሊ ያዘጋጀው ትርጉም:- Biblioteca Nazionale Centrale di Roma; ማውጫ:- Su concessione del Ministero per i Beni e le Attività Culturali