በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ የምትተማመነው ምን ያህል ነው?

በአምላክ የምትተማመነው ምን ያህል ነው?

በአምላክ የምትተማመነው ምን ያህል ነው?

“ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት . . . እሹ።”​—⁠ማቴዎስ 6:33

1, 2. አንድ ወጣት ከሥራ ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ ወስዷል? ለምንስ?

 አንድ ወጣት ጉባኤውን ይበልጥ ለመርዳት ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ሰብዓዊ ሥራው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ እንዳይገኝ እንቅፋት ሆነበት። ሁኔታውን እንዴት አስተካከለ? አኗኗሩን ቀላል አደረገና ሥራውን ለቀቀ፤ ከጊዜ በኋላም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴውን የማያስተጓጉል ሥራ አገኘ። ይህ ወጣት አሁን የሚያገኘው ደሞዝ ከበፊቱ በጣም ያነሰ ቢሆንም የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ያስችለዋል፤ እንዲሁም ጉባኤውን በጥሩ ሁኔታ መርዳት ችሏል።

2 ይህ ወጣት እንዲህ ያለውን ማስተካከያ ያደረገው ለምን እንደሆነ ገብቶሃል? አንተ በእርሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ተመሳሳይ እርምጃ ትወስድ ነበር? በርካታ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰዳቸው የሚያስመሰግን ነው። ያደረጉት ነገር “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት ላይ እንደሚተማመኑ የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 6:33) የሚመኩት በይሖዋ እንጂ በዚህ ዓለም ውስጥ ባሏቸው ነገሮች አይደለም።​—⁠ምሳሌ 3:23, 26

3. በርካታ ሰዎች በዛሬው ጊዜ መንግሥቱን ማስቀደም የሚቻል መሆኑን የሚጠራጠሩት ለምን ሊሆን ይችላል?

3 አንዳንዶች ከምንኖርበት ዘመን አስቸጋሪነት አንጻር ወጣቱ የወሰደው እርምጃ ጥሩ መሆኑን ይጠራጠራሉ። ዛሬ አንዳንድ ሰዎች በከባድ ድህነት ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ የማይታወቅ በጣም የተንደላቀቀ ሕይወት ይመራሉ። በድሃ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ በመጠኑም ቢሆን የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚረዳቸው ማንኛውም አጋጣሚ እንዲያመልጣቸው አይፈልጉም። በሌላ በኩል ደግሞ በበለጸጉ አገሮች ያሉ በርካታ ሰዎች የኢኮኖሚ መዋዠቅ፣ የሥራው ዓለም መልክ መለዋወጥና ከአሠሪዎቻቸው ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑ የኑሮ ደረጃቸውን ጠብቆ መኖሩን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል። ሰዎች መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት የሚያስከትለውን ጫና በመመልከት ‘በአሁኑ ጊዜ እንዴት መንግሥቱን ማስቀደም ይቻላል?’ በማለት ይጠይቁ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንዲረዳን ኢየሱስ ይህንን በተመለከተ ንግግር ሲያቀርብላቸው የነበሩትን ሰዎች ሁኔታ እንመልከት።

“አትጨነቁ”

4, 5. የአምላክ ሕዝቦች በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለባቸው ኢየሱስ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በገሊላ ሆኖ ከተለያዩ ቦታዎች ለተሰበሰቡ በርካታ ሰዎች ንግግር እያቀረበ ነበር። (ማቴዎስ 4:25) በመካከላቸው ጥቂት ሀብታሞች ሊኖሩ ቢችሉም አብዛኞቹ ድሆች ሳይሆኑ አይቀሩም። ቢሆንም ኢየሱስ ቅድሚያውን መስጠት ያለባቸው ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ዋጋ ያለውን መንፈሳዊ ሀብት ለማከማቸት እንደሆነ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 6:19-21, 24) “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 6:25

5 ንግግሩን ሲያዳምጡ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ነገር እንደተናገረ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ጠንክረው ካልሠሩ ቤተሰባቸው ችግር ላይ እንደሚወድቅ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ ወፎች ጠቀሰላቸው። ወፎች የሚመገቡትን ነገርና መጠለያቸውን በየዕለቱ ማግኘት አለባቸው፤ እነዚህን ነገሮች እንዲያገኙ የሚረዳቸው ይሖዋ ነው። አክሎም ታላቅ ክብር ከነበረው ከሰሎሞን የሚበልጥ ውበት ላላቸው የሜዳ አበቦች ይሖዋ እንክብካቤ ስለሚያደርግበት መንገድ ነገራቸው። ይሖዋ ለወፎችና ለአበቦች የሚያስብ ከሆነ ለእኛ የበለጠ እንክብካቤ አያደርግም? (ማቴዎስ 6:26-30) ኢየሱስ እንዳለው ሕይወታችንና ሰውነታችን፣ በሕይወት ለመኖር ከምንገዛው ምግብና አካላችንን ከምንሸፍንበት ልብስ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ምግብና ልብስ ለማግኘት ብቻ የምንጥር ከሆነና ለይሖዋ አገልግሎት የምናውለው ምንም ነገር ከሌለን የምንኖርበትን ዋነኛ ዓላማ ዘንግተናል።​—⁠መክብብ 12:13

ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

6. (ሀ) ክርስቲያኖች ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑት በማን ላይ ነው?

6 በእርግጥ ኢየሱስ አድማጮቹ መሥራት እንዲያቆሙና አምላክ በሆነ መንገድ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ያቀርብልናል ብለው እንዲጠብቁ ማበረታታቱ አልነበረም። ወፎች እንኳን ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ምግብ መፈለግ አለባቸው። ስለዚህ ክርስቲያኖች መብላት ከፈለጉ መሥራትና ቤተሰባቸው የሚጠብቅባቸውን ሌሎች ኃላፊነቶች መወጣት ይገባቸው ነበር። በሠራተኝነትና በባሪያነት የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችም ጌቶቻቸውን በትጋት ማገልገል ያስፈልጋቸው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 3:10-12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 1 ጴጥሮስ 2:18) ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ድንኳን ይሰፋ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:1-4፤ 1 ተሰሎንቄ 2:9) ቢሆንም እነዚህ ክርስቲያኖች ይተማመኑ የነበረው በሥራቸው ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው። በመሆኑም ሌሎች የሌላቸውን ውስጣዊ ሰላም ማግኘት ችለዋል። መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣ ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው” ብሏል።​—⁠መዝሙር 125:1

7. በይሖዋ ላይ ጠንካራ የመተማመን ስሜት የሌለው ሰው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይችላል?

7 በይሖዋ ላይ ጠንካራ የመተማመን ስሜት የሌለው የትኛውም ሰው ከዚህ ለየት ያለ ነገር ሊያስብ ይችላል። ብዙ ሰዎች ትልቁ አስተማማኝ ነገር ሀብት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ስለዚህ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ወደፊት ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንዲይዙ በማሰብ አብዛኛውን የወጣትነት ዕድሜያቸውን ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል እንዲያሳልፉ ያበረታቷቸዋል። የሚያሳዝነው ግን ልጆች ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት መስጠታቸውን አቁመው ቁሳዊ ግቦችን ወደ መከታተል ዘወር በማለታቸው አንዳንድ ክርስቲያን ቤተሰቦች ለከፍተኛ ትምህርት ብዙ ጊዜና ጉልበት ማዋል ለሚያስከትለው ከባድ ኪሳራ ተዳርገዋል።

8. ክርስቲያኖች ምን ሚዛናዊ አመለካከት አላቸው?

8 ስለዚህ ጥበበኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ምክር ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም እንደሚሠራ በመገንዘብ ሚዛናቸውን ይጠብቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን ግዴታቸውን ለመወጣት ለረጅም ሰዓት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋቸው ይሆናል፤ ያም ቢሆን ገንዘብ የማግኘት ፍላጎታቸው ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ችላ እንዲሉ እንዲያደርጋቸው ፈጽሞ አይፈቅዱም።​—⁠መክብብ 7:12

መጨነቅ እንደማይገባ የተሰጠ ተጨማሪ ምክር

9. ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ለሚተማመኑ ሰዎች ምን የሚያጽናና ሐሳብ ተናግሯል?

9 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ወቅት “‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ለአድማጮቹ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:31, 32) እንዴት የሚያበረታቱ ቃላት ናቸው! ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ከተማመንን እርሱ ሁልጊዜ ሊረዳን ዝግጁ ነው። ይሁንና የኢየሱስ ቃላት ማሳሰቢያ ጭምር ይዘዋል። እነዚህ ቃላት፣ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ‘የምንጨነቅ’ ከሆነ አስተሳሰባችን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዳልሆኑት እንደ “አሕዛብ” መሆኑን እንድናስተውል ይረዱናል።

10. ኢየሱስ፣ ምክር የጠየቀው አንድ ጎልማሳ ይበልጥ የሚወደው ነገር ግልጽ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?

10 በአንድ ወቅት አንድ ሀብታም ጎልማሳ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባው ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። ኢየሱስ፣ በወቅቱ ይሠራ የነበረው የሙሴ ሕግ ምን እንደሚያዝ ጠቀሰለት። ጎልማሳውም “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” በማለት በእርግጠኝነት ለኢየሱስ ነገረው። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ የሰጠው መልስ ለብዙዎች የማይሆን ነገር ሊመስል ይችላል። እንዲህ አለው:- “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ፣ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም ሀብት ታገኛለህ። ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ።” (ማቴዎስ 19:16-21) ጎልማሳውም ሀብቱን የማጣቱ ሐሳብ ስላልተዋጠለት እያዘነ ሄደ። ከይሖዋ ይልቅ ለንብረቱ ያለው ፍቅር አይሎበት ነበር።

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ ሀብትን በተመለከተ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል? (ለ) ሀብት ይሖዋን እንዳናገለግል እንቅፋት የሚሆነው እንዴት ነው?

11 ይህ ክስተት ኢየሱስ የሚከተለውን ያልተጠበቀ ሐሳብ እንዲናገር አደረገው:- “ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው። . . . ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።” (ማቴዎስ 19:23, 24) ኢየሱስ ሀብታም ሰው የአምላክን መንግሥት አይወርስም ማለቱ ነበር? አይደለም። ምክንያቱም “በእግዚአብሔር ዘንድ . . . ሁሉም ነገር ይቻላል” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:25, 26) እንዲያውም በዚያን ጊዜ አንዳንድ ሀብታሞች በይሖዋ እርዳታ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሆነው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) የሆነ ሆኖ እነዚህን አስገራሚ ቃላት የተናገረበት በቂ ምክንያት ነበረው። ኢየሱስ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ነበር።

12 አንድ ሰው ልክ እንደዚያ ጎልማሳ ንብረቱን በጣም የሚወድ ከሆነ ይሖዋን በሙሉ ልብ እንዳያገለግል እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። ይህ ሁኔታ ሀብታም በሆኑትም ሆነ ‘ባለጠጋ መሆን በሚፈልጉ’ ላይ ሊከሰት ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) አንድ ሰው በቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ የሚመካ ከሆነ ‘ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ንቁ’ ላይሆን ይችላል። (ማቴዎስ 5:3 NW ) ይህ ደግሞ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው እንዲዘነጋ ያደርገው ይሆናል። (ዘዳግም 6:10-12) በጉባኤው ውስጥም ልዩ አክብሮት እንዲሰጠው ሊጠብቅ ይችላል። (ያዕቆብ 2:1-4) እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜውን ይሖዋን ለማገልገል ከመጠቀም ይልቅ በሀብቱ በመዝናናት ሊያሳልፍ ይችላል።

ትክክለኛውን አመለካከት አዳብር

13. የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው?

13 በአንደኛው መቶ ዘመን የነበረው የሎዶቅያ ጉባኤ አባላት ለሀብት የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “‘ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።” የሎዶቅያ ክርስቲያኖች እንዲህ የመሰለውን አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ያስከተለባቸው ሀብታቸው አልነበረም። እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሳቸው ከይሖዋ ይልቅ በሀብት መታመናቸው ነው። ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ ከአፉ ‘አውጥቶ ሊተፋቸው’ እስኪፈልግ ድረስ በመንፈሳዊ ለብ ያሉ ሆነው ነበር።​—⁠ራእይ 3:14-17

14. ዕብራውያን ክርስቲያኖች የጳውሎስ ምስጋና ይገባቸው የነበረው ለምንድን ነው?

14 በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከዚያ ቀደም ሲል ተቀስቅሶ በነበረው ስደት ወቅት ለያዙት አመለካከት እንዲህ በማለት አመስግኗቸዋል:- “እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ።” (ዕብራውያን 10:34) እነዚህ ክርስቲያኖች ሀብታቸውን በማጣታቸው ምክንያት ብዙም አልተጨነቁም። በጣም ውድ የሆነውን “የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት” እንደያዙ በመቆየታቸው ደስታቸውን አላጡም ነበር። አንድ ውድ ዕንቁ ለመግዛት ሲል ያለውን ሁሉ መሥዋዕት እንዳደረገው በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ነጋዴ፣ ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅባቸውም በመንግሥቱ ላይ ያላቸው ተስፋ እንዳይደበዝዝ ለማድረግ ቆርጠው ነበር። (ማቴዎስ 13:45, 46) እንዴት ያለ መልካም አመለካከት ነው!

15. በላይቤሪያ የምትገኝ አንዲት ክርስቲያን ሴት መንግሥቱን ያስቀደመችው እንዴት ነው?

15 ዛሬም ተመሳሳይ የሆነ መልካም አመለካከት ያዳበሩ በርካታ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በላይቤሪያ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ወጣት በዩኒቨርሲቲ የመማር አጋጣሚ አግኝታ ነበር። በዚያ አገር፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መማር ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መሠረት እንደሚጥል ይታሰባል። ይቺ እህት ግን አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከመሆኗም በላይ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆና እንድታገለግል ግብዣ ቀርቦላት ነበር። እህት መንግሥቱን ለማስቀደም በመምረጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቷ ቀጠለች። ወደተመደበችበት ቦታ ሄዳ በማገልገል በሦስት ወር ውስጥ 21 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ችላለች። ይቺ ወጣት እህትና እርሷን የመሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ሊያገኙ የሚችሉትን ቁሳዊ ጥቅም ሳይቀር ሰውተው መንግሥቱን አስቀድመዋል። ቁሳዊ ሀብት በሚያሳድደው በዚህ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ አመለካከት መያዝ የቻሉት እንዴት ነው? በርካታ መልካም ባሕርያትን በማዳበራቸው ነው። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

16, 17. (ሀ) በይሖዋ ለመታመን ትሕትና የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ መተማመን የሚገባን ለምንድን ነው?

16 ትሕትና:- መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል” ይላል። (ምሳሌ 3:5-7) አንዳንድ ጊዜ ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ አንድ ድርጊት ተገቢ ሊመስል ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) ሆኖም ቅን የሆነ ክርስቲያን መመሪያ ማግኘት የሚፈልገው ከይሖዋ ነው። (መዝሙር 48:14) ‘በመንገዱ ሁሉ’ ማለትም ጉባኤን፣ ትምህርትን፣ ሥራን፣ መዝናኛን ወይም ሌላ ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት በትሕትና ይጥራል።​—⁠መዝሙር 73:24

17 ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች መተማመን:- ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” ብሏል። (ዕብራውያን 11:6) ይሖዋ የሰጠው ተስፋ መፈጸሙን የምንጠራጠር ከሆነ ሙሉ በሙሉ ‘በዓለም መጠቀም’ ምክንያታዊ ሊመስለን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:31) በሌላ በኩል ደግሞ እምነታችን ጠንካራ ከሆነ መንግሥቱን ለማስቀደም እንቆርጣለን። ጠንካራ እምነት ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው? ዘወትር ከልብ በሚቀርብ ጸሎትና በቋሚነት በሚደረግ የግል ጥናት አማካኝነት ወደ ይሖዋ በመቅረብ ነው። (መዝሙር 1:1-3፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ ያዕቆብ 4:8) ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . በአንተ እታመናለሁ፤ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ እልሃለሁ” በማለት መጸለይ እንችላለን።​—⁠መዝሙር 31:14, 19

18, 19. (ሀ) ታታሪነት በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን ስሜት የሚያጠነክረው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

18 ይሖዋን በትጋት ማገልገል:- ጳውሎስ “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን” በማለት ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ መተማመንን ከታታሪነት ጋር አያይዞታል። (ዕብራውያን 6:11) በይሖዋ አገልግሎት ከተጠመድን እርሱም ይደግፈናል። የእርሱን ድጋፍ በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ በይሖዋ ላይ ያለን የመተማመን ስሜት እየተጠናከረ ይሄዳል፤ እንዲሁም ‘ጸንተን የምንቆምና በምንም ነገር የማንናወጥ’ እንሆናለን። (1 ቆሮንቶስ 15:58) እምነታችን ይታደሳል፣ ተስፋችንም ይረጋገጣል።​—⁠ኤፌሶን 3:16-19

19 መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን:- ጳውሎስ ኢየሱስን ለመከተል ሲል ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚ​ያስችለውን አጋጣሚ መሥዋዕት አድርጓል። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ አንዳንድ ጊዜ ይቸገር የነበረ ቢሆንም ትክክለኛ ምርጫ እንዳደረገ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:11-13) ይሖዋ አገልጋዮቹ የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖሩ ቃል አልገባም፤ ስለሆነም አንዳንድ ጊዜ ችግር ያጋጥማቸዋል። ኑሯችንን ቀላል ለማድረግና መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች መሆናችን ይሖዋን ለማገልገል መቁረጣችንን የሚያረጋግጥ ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:6-8

20. መንግሥቱን የሚያስቀድም ሰው ታጋሽ መሆን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

20 ታጋሽ መሆን:- ሐዋርያው ያዕቆብ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ” በማለት ክርስቲያን ወንድሞቹን አሳስቧቸዋል። (ያዕቆብ 5:7) በዚህ ጥድፊያ በበዛበት ዓለም ውስጥ ታጋሽ መሆን አስቸጋሪ ነው። ነገሮች በፍጥነት እንዲከናወኑ እንፈልጋለን። ጳውሎስ ግን “በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን” እንድንመስል አሳስቦናል። (ዕብራውያን 6:12) ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሁን። ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት በእርግጥም በትዕግሥት ሊጠበቅ የሚገባው ተስፋ ነው!

21. (ሀ) መንግሥቱን ስናስቀድም ምን እያሳየን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?

21 አዎን፣ ኢየሱስ መንግሥቱን እንድናስቀድም የሰጠው ምክር ሊተገበር የሚችል ነው። እንዲህ ስናደርግ በእርግጥም በይሖዋ ላይ እንደምንታመንና ክርስቲያኖች ሊጓዙበት የሚገባውን ብቸኛ አስተማማኝ መንገድ እንደመረጥን እናሳያለን። የሆነ ሆኖ ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እሹ’ የሚል ተጨማሪ ምክር ሰጥቷል። ይህ ምክር በተለይ በዛሬው ጊዜ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ምን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን አበረታቶናል?

• ኢየሱስ፣ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ስለመሽሎኩ ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

• የአምላክን መንግሥት እንድናስቀድም የሚረዱን ክርስቲያናዊ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስን ንግግር ያዳመጡት አብዛኞቹ ሰዎች ድሆች ነበሩ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀብታሙ ጎልማሳ ከይሖዋ ይልቅ ለንብረቱ ያለው ፍቅር አይሎበት ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ነጋዴ ለአንድ ውድ ዕንቁ ሲል ያለውን ሁሉ ሠውቷል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ አገልግሎት ከተጠመድን እርሱ ይደግፈናል