በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በወቅቱ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’

‘በወቅቱ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’

‘በወቅቱ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’

በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ቀን ስብሰባ ላይ ነው፤ ኪም በአንድ በኩል የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ልጇን በጸጥታ እንድትቀመጥ ለማድረግ እየሞከረች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰጠውን ትምህርት ለማዳመጥና ማስታወሻ ለመያዝ የተቻላትን ሁሉ ታደርግ ነበር። ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ በእነርሱ መደዳ የተቀመጠች አንዲት እህት ወደ ኪም በመዞር ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ወቅት እሷም ሆነች ባለቤቷ ልጃቸውን ለመያዝ ሲያደርጉት ለነበረው ጥረት ከልብ አመሰገነቻት። ይህ ምስጋና ለኪም አሁን ድረስ ትልቅ ትርጉም አለው፤ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በተለይም ስብሰባ ላይ እያለሁ የድካም ስሜት ሲሰማኝ እህት ያለችኝ ትዝ ይለኛል። ደግነት የተላበሰው አነጋገሯ እስካሁን ድረስ ልጄን በማሠልጠን እንድገፋ ትልቅ ብርታት ሆኖኛል።” እውነት ነው በጊዜው የተነገረ ቃል አንድን ሰው ያበረታታል። መጽሐፍ ቅዱስም ‘በወቅቱ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’ በማለት ይገልጻል።​—⁠ምሳሌ 15:23

ሆኖም ለአንዳንዶቻችን ሰዎችን ማመስገን ቀላል ላይሆንልን ይችላል። በተለይ ድክመት እንዳለብን ሲሰማን እንዲህ ማድረጉ ይበልጥ ይከብደናል። አንድ ወንድም “ለእኔ ሁኔታው ልክ ማጥ ውስጥ የመቆም ያህል ነው። ሌሎችን ከፍ ባደረኩ ቁጥር እኔ ራሴ ወደ ታች የምሰምጥ ያህል ሆኖ ይሰማኛል” ሲል ተናግሯል። በተጨማሪም ዓይናፋርነት፣ በራስ ያለመተማመን ስሜት ወይም በተሳሳተ መንገድ ይረዱኝ ይሆናል ብሎ መስጋት ሌሎችን ለማመስገን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ከዚህም በላይ በልጅነታችን እምብዛም ካልተመሰገንን አሊያም ትኩረት ተነፍጎን ከነበረ አሁን ሌሎችን ማመስገን ይቸግረን ይሆናል።

ይሁንና ማመስገን በአመስጋኙም ሆነ በተመስጋኙ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መገንዘባችን፣ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሌሎችን ለማመስገን የተቻለንን ያህል እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ምሳሌ 3:​27) እንዲህ ማድረጋችን የሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች ምንድን ናቸው? እስቲ አንዳንዶቹን በአጭሩ እንመልከት።

የሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች

በተገቢው ጊዜ የተለገሰ ምስጋና በተቀባዩ ዘንድ በራስ የመተማመን ስሜት ይፈጥራል። አንዲት ኢሌን የተባለች ክርስቲያን ሚስት “ሰዎች ሲያመሰግኑኝ በእኔ እንደሚተማመኑና እምነት እንደጣሉብኝ ሆኖ ይሰማኛል” ብላለች። በራስ የመተማመን ስሜት የጎደለውን ሰው ማመስገን ችግሮቹን ለመወጣት የሚያስችል ድፍረት ያስገኝለታል፤ ይህም ደስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በተለይ ወጣቶች ተገቢ ምስጋና ማግኘታቸው ጥቅም ያስገኝላቸዋል። አፍራሽ አመለካከት እንደሚያስቸግራት የምትናገር አንዲት ወጣት እንደሚከተለው ብላለች:- “ይሖዋን ለማስደሰት የቻልኩትን ያህል እጥራለሁ፤ ይሁንና አንዳንዴ የአቅሜን ያህል ባደርግም እንኳ አጥጋቢ ሥራ እንደሠራሁ ሆኖ አይሰማኝም። አንድ ሰው ሲያመሰግነኝ ግን ውስጤ በደስታ ይሞላል።” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው” ማለቱ በእርግጥም ትክክል ነው።​—⁠ምሳሌ 25:11

ማመስገን አንድን ሰው ለሥራ ሊያነሳሳውና ሊያበረታታው ይችላል። አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ “ምስጋና ይበልጥ ጠንክሬ እንድሠራና የአገልግሎቴን ጥራት እንዳሻሻል ይገፋፋኛል” በማለት ተናግሯል። አንዲት የሁለት ልጆች እናት ልጆቿ ጉባኤ ውስጥ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ከሌሎች የጉባኤው አባላት አድናቆት ሲቸራቸው ይበልጥ ሐሳብ ለመስጠት መገፋፋታቸውን አስተውላለች። አዎን፣ ምስጋና ወጣቶች በክርስቲያናዊ አኗኗራቸው ይበልጥ እድገት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። እውነት ነው ሁላችንም ብንሆን አድናቆትና ፍቅር እንዲለገሰን እንፈልጋለን። ይህ በውጥረት የተሞላ ዓለም እንድንዝልና ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ተስፋ በምቆርጥበት ጊዜ ሌሎች ሲያመሰግኑኝ ለጸሎቴ መልስ እንዳገኘሁ ሆኖ ይሰማኛል” ብሏል። ኢሌንም እንዲሁ “አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘሁ በሌሎች ሰዎች ተጠቅሞ እየገለጸልኝ እንዳለ ሆኖ ይሰማኛል” ስትል ተናግራለች።

ማመስገን የመቀራረብ ስሜት ይፈጥራል። ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረብ አሳቢነትን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የፍቅርና የደኅንነት ስሜት እንዲሁም የአድናቆት መንፈስ እንዲሰፍን ይረዳል። ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን ከልብ እንደምንወዳቸውና ከፍ አድርገን እንደምንመለከታቸው ያረጋግጣል። ጆሲ የምትባል እናት እንደሚከተለው ብላለች:- “ያለፉት ጊዜያት በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ እውነትን ይዤ መጽናት ጠይቀውብኛል። እነዚህን ጊዜያት በጽናት እንዳልፍ የረዳኝ በመንፈሳዊ በጎለመሱ ወንድሞች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቴ ነበር።” በእርግጥም “ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነን።”​—⁠ኤፌሶን 4:⁠25

ማመስገን የሌሎች ሰዎች መልካም ጎን እንዲታየን ያደርጋል። ትኩረታችን የሚያርፈው ሰዎች ባሏቸው መልካም ባሕርያት እንጂ በድክመታቸው ላይ አይደለም። ዴቪድ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ሌሎች ለሚያከናውኗቸው ነገሮች አድናቂዎች መሆን ይበልጥ እንድናመሰግናቸው ያነሳሳናል” ሲል ተናግሯል። ይሖዋና ልጁ ፍጽምና የሚጎድላቸውን የሰው ልጆች ከማመስገን ወደኋላ እንደማይሉ ማወቃችን እኛም ለሌሎች እንዲህ እንድናደርግ ይገፋፋናል።​—⁠ማቴዎስ 25:21-​23፤ 1 ቆሮንቶስ 4:5

ምስጋና ይገባቸዋል

ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉ የላቀ ውዳሴ ይገባዋል። (ራእይ 4:11) እርግጥ ይሖዋን የምናወድሰው በራስ የመተማመን ስሜቱን ለማጎልበት አሊያም እርሱን ለማበረታታት አይደለም፤ ስለ አስደናቂ ግርማው እንዲሁም ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ ስናወድሰው ይበልጥ ወደ እኛ ስለሚቀርብ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ይኖረናል። በተጨማሪም ይሖዋን ማወደሳችን ስላገኘነው ስኬት ጤናማና ልከኛ አስተሳሰብ እንዲኖረንና የውጤታችን ማማር የተመካው በእርሱ ላይ እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል። (ኤርምያስ 9:​23, 24) ይሖዋ ለሚገባቸው ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ከፊታቸው ዘርግቶላቸዋል፤ ይህ እርሱን እንድናወድስ የሚገፋፋን ተጨማሪ ምክንያት ነው። (ራእይ 21:3, 4) በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ዳዊት ‘የእግዚአብሔርን ስም ለማወደስና በምስጋና ከፍ ከፍ ለማድረግ’ ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። (መዝሙር 69:30) እኛም ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎት ይኑረን።

የእምነት አጋሮቻችን ተገቢ የሆነ ምስጋና ይገባቸዋል። እንዲህ ስናደርግ “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ” የሚለውን መለኮታዊ ትእዛዝ እናከብራለን። (ዕብራውያን 10:24) ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚሆነን ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። በሮም ለሚገኘው ጉባኤ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁም አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።” (ሮሜ 1:⁠8) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ክርስቲያን ባልንጀራውን ጋይዮስን ‘በእውነት በመመላለሱ’ አመስግኖታል።​—⁠3 ዮሐንስ 1-4

በዛሬው ጊዜም የእምነት አጋሮቻችን የክርስቶስን የመሰለ ባሕርይ ሲያንጸባርቁ፣ ክፍላቸውን በደንብ ተዘጋጅተው ሲያቀርቡ አሊያም ደግሞ በስብሳባ ላይ ልብ የሚነካ ሐሳብ ሲሰጡ እነርሱን ለማመስገን የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እናገኛለን። አለበለዚያም አንድ ትንሽ ልጅ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ጥቅሶችን እያወጣ ለማንበብ ሲጥር ስናይ ልናመሰግነው እንችላለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኢሌን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች:- “እያንዳንዳችን ያለን ተሰጥኦ ይለያያል። ሌሎች የሚያደርጉትን በማስተዋል የአምላክ ሕዝቦች ላላቸው የተለያየ ተሰጥኦ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።”

በቤተሰብ ውስጥ

አድናቆታችንን ለቤተሰባችን አባላት ስለ መግለጽስ ምን ማለት ይቻላል? ወላጆች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት ማርካት በፍቅር ተነሳስተው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ትኩረታቸውን መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። በመሆኑም አንዳቸው ከሌላው እንዲሁም ከልጆቻቸው አንደበት የምስጋና ቃላት ሊሰነዘሩላቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም። (ኤፌሶን 5:​33) ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል መልካም ጸባይ ስላላት ሚስት ሲገልጽ ‘ልጆቿ ተነሥተው ቡርክት ያሏታል፤ ባሏም እንዲሁ ያመሰግናታል’ ይላል።​—⁠ምሳሌ 31:10, 28

ልጆችም ቢሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንድ ወላጆች እነርሱ የፈለጉትን ነገር እንዲያደርጉ ለልጆቻቸው መንገር እንጂ ትሕትናን እንዲሁም ታዛዥነትን ለማሳየት ለሚያደርጉት ጥረት ማመስገን አይቀናቸውም። (ሉቃስ 3:22) አንድ ልጅ ከትንሽነቱ አንስቶ የሚመሰገን ከሆነ የተፈላጊነትና የደኅንነት ስሜት ይሰማዋል።

ሌሎችን ማመስገን ጥረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው፤ ይሁንና ይህን ማድረግ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኛል። እንዲያውም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሌሎችን ለማመስገን ይበልጥ በተጋን ቁጥር ደስታችን የዚያኑ ያህል ይጨምራል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 20:⁠35

ስንመሰገንም ሆነ ስናመሰግን ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ መንፈስ

አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የሚቀርብላቸው ምስጋና ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። (ምሳሌ 27:21) ለምሳሌ ያህል፣ ኩሩ የሆነ ሰው መመስገኑ ከሌሎች ልቆ የመታየት መንፈስ ሊያሳድርበት ይችላል። (ምሳሌ 16:18) ስለሆነም በዚህ ረገድ ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ተግባራዊ ማሳሰቢያ ለግሷል:- “እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።” (ሮሜ 12:3) ሌሎች ስለ ራሳቸው ከልክ በላይ በማሰብ ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ለመርዳት ስንል በምናመሰግናቸው ጊዜ በችሎታቸውና በአካላዊ ውበታቸው ላይ ባናተኩር ጥበብ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ስላከናወኗቸው መልካም ተግባራት ልናመሰግናቸው እንችላለን።

ምስጋና ስናቀርብም ሆነ ስንቀበል ትክክለኛውን መንፈስ ማንጸባረቃችን መልካም ተጽዕኖ ያሳድርብናል። ማንኛውንም መልካም ተግባር ስናከናውን ይህን ነገር ያደረግነው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ ለመግለጽ እንገፋፋለን። ከዚህም በላይ ምስጋና ያለንን መልካም ባሕርይ ይዘን እንድንቀጥል ሊያበረታታን ይችላል።

ከልብ የመነጨና ተገቢ የሆነ ምስጋና ሁላችንም ለሌሎች ልንሰጠው የምንችለው ስጦታ ነው። በሚገባ አስበንበት የምንሰጠው ይህ ስጦታ በተቀባዩ ዘንድ ከጠበቅነው በላይ መልካም ውጤት ያስገኛል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልቧን የነካው ደብዳቤ

አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከባለቤቱ ጋር በአንድ ብርዳማ የክረምት ዕለት አገልግሎት ውለው ወደ ማረፊያ ክፍላቸው በመመለስ ላይ እያሉ የገጠማቸውን ሁኔታ መቼም አይረሳውም። እንዲህ ይላል:- “ባለቤቴ በጣም በርዷትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቷት ስለነበር በዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል እንደማትችል ነገረችኝ። በመቀጠልም ‘በአንድ ጉባኤ ውስጥ ሆነን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብንቀጥል፣ ተረጋግተን ብንኖርና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን መምራት ብንችል የተሻለ’ እንደሚሆን ገለጸችልኝ። ለጊዜው ምንም ዓይነት ውሳኔ ሳላደርግ የያዝነው ሳምንት እስኪያልቅ ድረስ እያገለገልን ስሜቷን ለማየት አሰብኩ። በዚያ ጊዜ ውስጥ የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን የመተዉን ሐሳብ ከገፋችበት ስሜቷን ላከብር ወሰንኩ። በዚሁ ዕለት ወደ ፖስታ ቤት ጎራ ብለን ሣጥኑን ስንከፍት ከቅርንጫፍ ቢሮው በስሟ የተላከላትን ደብዳቤ አገኘን። ደብዳቤው በየሳምንቱ በተለያየ አልጋ ላይ መተኛትን የመሳሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥማትም እንኳ ስለምታከናውነው ትጋት የተሞላበት አገልግሎትና ስላሳየችው ጽናት ከፍተኛ ምስጋና የያዘ ነበር። በዚህ የምስጋና ደብዳቤ በጥልቅ በመነካቷ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ስለማቆም አንስታ አታውቅም። እንዲያውም እኔ ለማቆም ሳስብ እንድቀጥል ብዙ ጊዜ አበረታትታኛለች።” እነዚህ ባልና ሚስት 40 ለሚያህሉ ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግለዋል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉባኤህ ውስጥ ምስጋና የሚገባው ማን ነው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ትኩረት ሲሰጣቸውና ሲመሰገኑ ይበልጥ ይጥራሉ