በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጎ ምግባር በክፋት ተውጧል

በጎ ምግባር በክፋት ተውጧል

በጎ ምግባር በክፋት ተውጧል

በዛሬው ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሌሉ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ለሌሎች በጎ በማድረግ “ለውጥ የማምጣት” ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ። በእያንዳንዱ ዓመት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለሚያምኗቸው የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ይሰጣሉ። ለምሳሌ በብሪታንያ በ2002 ለእርዳታ የተሰጠው ገንዘብ ወደ 13 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይጠጋል። ከ1999 ወዲህ አሥር የሚሆኑ በጎ አድራጊዎች ለተቸገሩ ሰዎች የለገሱት ገንዘብ ከ38 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል።

በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ብዙ መልካም ሥራዎችን ያከናውናሉ። ከእነዚህም ውስጥ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች የሕክምና ወጪዎችን መሸፈን፣ በነጠላ ወላጅ የሚያድጉ ልጆችን ማስተማርና በሥነ ምግባር ማሠልጠን፣ በታዳጊ አገሮች የሚካሄዱ የክትባት ፕሮግራሞችን በገንዘብ መደገፍ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳቸው መጽሐፍ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ድሃ በሆኑ አገሮች ለሚገኙ ገበሬዎች የእርባታ ከብቶችን መለገስና በተፈጥሮ አደጋ ለተጠቁ ሰዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ይገኙበታል።

ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች እንደሚጠቁሙት የሰው ልጆች ለሌሎች በጎ ነገር የማድረግ ችሎታ አላቸው። ይሁንና በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግቱ የክፋት ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎችም መኖራቸው የሚያሳዝን ነው።

ክፋት እየበዛ ነው

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ወዲህ ወደ 50 የሚጠጉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና በፖለቲካ ሳቢያ የተቀሰቀሱ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተዘግበዋል። አሜሪካን ፖለቲካል ሳይንስ ሪቪው የተባለው መጽሔት እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “እነዚህ ክስተቶች ቢያንስ ቢያንስ የ12 ሚሊዮን ቢበዛ ደግሞ የ22 ሚሊዮን ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ይህ አኃዝ ከ1945 ወዲህ በብሔርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱት ጦርነቶች ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል።”

በ20ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ካምቦዲያ ውስጥ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል። በሩዋንዳ የተቀሰቀሰው የዘር ጥላቻ ከ800, 000 ለሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሞት ምክንያት ሆኗል። ቦስኒያ ውስጥ በሃይማኖትና በፖለቲካ ሰበብ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ200, 000 በላይ ይሆናል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ በቅርብ ዓመታት የተፈጸሙትን የክፋት ድርጊቶች ሲዘረዝሩ በ2004 እንዲህ ብለዋል:- “በኢራቅ ሰላማዊ ሰዎች ያለምንም ርኅራኄ ሲጨፈጨፉ እንዲሁም የእርዳታ ሠራተኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ንጹሐን ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ እጅግ በሚሰቀጥጥ መንገድ ሲገደሉ አይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢራቃውያን እስረኞች ክብር በሚነካ መንገድ ግፍ ሲደርስባቸው ተመልክተናል። በዳርፉር መላው ሕዝብ ከቀዬው ሲፈናቀል፣ የእያንዳንዱ ሰው ቤት ሲወድምና አስገድዶ መድፈር እንደ አንድ የማጥቂያ ዘዴ ጥቅም ላይ ሲውል ተመልክተናል። በሰሜን ኡጋንዳ ደግሞ ልጆች አካላቸው ሲቆራረጥና አሰቃቂ በሆኑ የክፋት ድርጊቶች ላይ እንዲካፈሉ ሲገደዱ አይተናል። በቤስላንም ሕፃናት ታግተው በጭካኔ ሲጨፈጨፉ አይተናል።”

ሌላው ቀርቶ ሰልጥነዋል በተባሉ አገሮች ውስጥ እንኳ በጥላቻ ምክንያት የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየበዙ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በብሪታንያ “ከዘር ጋር በተያያዘ ጥቃት ወይም በደል የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ በአሥራ አንድ እጥፍ እንደጨመረ” ኢንዲፔንደንት ኒውስ በ2004 ሪፖርት አድርጓል።

ብዙ በጎ ነገሮችን የማድረግ ችሎታ ያላቸው የሰው ልጆች እንዲህ የመሰሉትን የክፋት ድርጊቶች የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? ከክፋት ነጻ የምንሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

COVER: Mark Edwards/Still Pictures/Peter Arnold, Inc.