በጎ ምግባር ክፋትን የሚያሸንፈው እንዴት ነው?
በጎ ምግባር ክፋትን የሚያሸንፈው እንዴት ነው?
ንጉሥ ዳዊት ጥሩ ሰው ነበር። አምላክን በጥልቅ የሚያፈቅር፣ ለፍትሕ የቆመና ለተቸገሩት ከልብ የሚራራ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ጥሩ የነበረው ይኸው ንጉሥ ከታማኝ አገልጋዮቹ መካከል ከአንዱ ሚስት ጋር ምንዝር ፈጸመ። ዳዊት የአገልጋዩ ሚስት ቤርሳቤህ ከእርሱ እንዳረገዘች ከሰማ በኋላ ባለቤቷ የሚገደልበትን ዘዴ አቀነባበረ። ከዚያም የሠራቸውን ወንጀሎች ለመሸፋፈን ቤርሳቤህን አገባት።—2 ሳሙኤል 11:1-27
ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን የማድረግ ችሎታ እንዳላቸው የታወቀ ነው። ታዲያ አሰቃቂ የሆኑ የክፋት ድርጊቶችን የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ መሠረታዊ ምክንያቶችን ያስቀምጣል። በተጨማሪም አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ተጠቅሞ ክፋትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጠፋበትን መንገድ ይገልጻል።
ወደ ክፋት ማዘንበል
ንጉሥ ዳዊት ራሱ ለክፋት ድርጊት ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንደኛውን ይጠቁመናል። የሠራው ወንጀል ከተጋለጠ በኋላ ለፈጸመው ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆኑን አምኗል። ከዚያም “ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ” በማለት በጸጸት ስሜት ጽፏል። (መዝሙር 51:5) አምላክ፣ እናቶች ኃጢአተኛ ልጆች እንዲወልዱ ዓላማው አልነበረም። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ሔዋን ከዚያም አዳም በአምላክ ላይ ካመጹ በኋላ ኃጢአት የማይሠሩ ልጆች የመውለድ ችሎታቸውን አጥተዋል። (ሮሜ 5:12) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ቁጥር ባደገ መጠን “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” መሆኑ ተረጋግጧል።—ዘፍጥረት 8:21
ይህ የክፋት ዝንባሌ ቁጥጥር ካልተደረገበት ወደ “ዝሙት፣ . . . ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቁጣ፣ ራስ ገላትያ 5:19-21) ንጉሥ ዳዊትን ስንመለከት ለሥጋዊ ስሜት በመሸነፉ ዝሙት ፈጸመ፤ ይህ ደግሞ ክፉ ነገር አስከትሎበታል። (2 ሳሙኤል 12:1-12) ዳዊት የኃጢአት ዝንባሌውን መቆጣጠር ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ ስለ ቤርሳቤህ በማሰላሰሉ ከጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የጻፈው ነገር እርሱ ላይ ተፈጽሟል:- “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15
ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነት” እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የሥጋ ሥራ” ወደተባሉ ሌሎች ጎጂ ባሕርያት ይመራል። (በፊተኛው ርዕስ ላይ የተመለከትናቸው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈርና ዝርፊያ የመሳሰሉት ድርጊቶች ሰዎች ክፉ ምኞት እንዲመራቸው ሲፈቅዱ ለሚከሰቱት መዘዞች ዓይነተኛ ምሳሌ ናቸው።
አለማወቅ ክፋትን ያባብሳል
የሐዋርያው ጳውሎስ ታሪክ ሰዎች ክፋት እንዲፈጽሙ የሚያደርጋቸውን ሁለተኛውን ምክንያት ይገልጽልናል። ጳውሎስ ሲሞት ጨዋና ሰው ወዳድ የሚል ጥሩ ስም አትርፎ ነበር። ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶቹን ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መንገድ ለማገልገል ይደክም ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:7-9) ቀደም ሲል ሳውል ተብሎ የሚጠራው ይህ ሰው ከዚህ በፊት ይህንን አነስተኛ የክርስቲያኖች ቡድን ‘ለመግደል ይዝት’ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2) ጳውሎስ በቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ላይ የክፋት ድርጊት እንዲፈጸም የተስማማውም ሆነ በድርጊቱ የተካፈለው ለምንድን ነው? እርሱ ራሱ “ባለማወቅ” እንደነበረ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) አዎን፣ ጳውሎስ ቀደም ሲል ‘ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ነበር፤ ቅናቱ ግን ከዕውቀት የተነሣ አልነበረም።’—ሮሜ 10:2
እንደ ጳውሎስ ሁሉ ብዙ ቅን ሰዎች ስለ አምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት ስለሌላቸው ክፉ ነገር ይፈጽማሉ። ለምሳሌ ኢየሱስ “የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳገለገለ የሚቈጥርበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐንስ 16:2) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስ ቃላት እውነት መሆናቸውን በራሳቸው ሕይወት ተመልክተውታል። በብዙ አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን እናገለግላለን በሚሉ ሰዎች ከመሰደዳቸውም ባሻገር ተገድለዋል። በግልጽ ማየት እንደምንችለው እንዲህ ያለው የተሳሳተ ቅንዓት እውነተኛውን አምላክ አያስደስተውም።—1 ተሰሎንቄ 1:6
የክፋት ምንጭ
ኢየሱስ ለክፋት መኖር ዋነኛ ምንጭ የሆነውን አካል ገልጿል። እርሱን ለመግደል ከቆረጡት የሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲነጋገር “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 8:44) በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ እንዲያምጹ ያደረገው ሰይጣን ነው። ይህ ዓመጽ ደግሞ በሰው ልጆች ላይ ኃጢአትና ሞት አስከትሏል።
ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያደረሰው ግፍ ነፍሰ ገዳይ መሆኑን ይበልጥ ግልጽ አድርጓል። ሰይጣን የኢዮብን ታማኝነት እንዲፈትን ይሖዋ በፈቀደለት ጊዜ የኢዮብን ንብረት በማሳጣት ብቻ አልረካም። አሥር ልጆቹንም ገድሎበታል። (ኢዮብ 1:9-19) ካለፉት አሥርተ ዓመታት ወዲህ የሰው ልጆች የሚፈጽሙት የክፋት ድርጊት በፍጥነት እያደገ መጥቷል። ይህ ሊሆን የቻለው በሰዎች አለፍጽምናና አለማወቅ እንዲሁም ሰይጣን በሰዎች ጉዳይ ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በመጨመሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ “ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” በማለት ይነግረናል። ይኸው ትንቢት በትክክል እንዳስቀመጠው ሰይጣን ወደ ሰማይ እንዳይሄድ መታገዱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ‘ወዮታ በምድር’ ላይ እንዲመጣ አድርጓል። ሰይጣን ሰዎች ክፉ ነገሮችን እንዲያደርጉ ማስገደድ ባይችልም እንኳ ‘ዓለምን ሁሉ በማሳት’ ረገድ ተሳክቶለታል።—ራእይ 12:9, 12
የክፋትን ዝንባሌ ማስወገድ
ክፋት ከሰብዓዊው ኅብረተሰብ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ከተፈለገ የሰው ልጅ በውርስ ያገኘው የክፋት ዝንባሌ፣ አላዋቂነትና ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ መወገድ ይኖርባቸዋል። በቅድሚያ፣ የሰው ልጅ የወረሰውን የኃጢአት ዝንባሌ ከልቡ ነቅሎ ማውጣት እንዴት ይቻላል?
ኃጢአትን ማስወገድ የሚችል ዶክተርም ይሁን ሰው ሠራሽ መድኃኒት የለም። ይሖዋ አምላክ ግን ዝግጅቱን ለሚቀበሉ ሁሉ ከኃጢአትና ከአለፍጽምና ፈውስ የሚያስገኝላቸውን መድኃኒት አዘጋጅቷል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 1:7) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በፈቃደኝነት የራሱን ሕይወት በሰጠን ጊዜ “ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር . . . በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ።” (1 ጴጥሮስ 2:24) የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት የአዳም ክፉ ሥራ ያስከተላቸውን መዘዞች ያስወግዳል። ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ “ለሰዎች ሁሉ ቤዛ” እንደሆነ ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) አዎን፣ የክርስቶስ ሞት ሰዎች ሁሉ አዳም ያጣውን ፍጽምና እንደገና የሚያገኙበትን መንገድ ከፍቷል።
ይሁንና ‘ኢየሱስ ከ2, 000 ዓመታት በፊት መሞቱ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ የሚያስችላቸው ከሆነ፣ ክፋትና ሞት እስከ ዛሬ ድረስ የኖሩት ለምንድን ነው?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ለክፋት ድርጊት ሁለተኛ ምክንያት የሆነውን የአምላክን ዓላማዎች አለማወቅን ለማስወገድ ይረዳል።
ትክክለኛ እውቀት በጎነትን ለማዳበር ይረዳል
ቅን የሆነ አንድ ሰው ይሖዋና ኢየሱስ ክፋትን ለማስወገድ በዛሬው ጊዜ እያደረጉት ስላለው ነገር ትክክለኛ እውቀት ማግኘቱ፣ ሳያውቀው የክፋት ድርጊቶችን እንዳያራግብ ይባስ ብሎም “ከእግዚአብሔር ጋር” እስከመጣላት እንዳይደርስ ይረዳዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:38, 39) ይሖዋ አምላክ ባለማወቅ የተፈጸሙ የክፋት ድርጊቶችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ እያለ እንዲህ ብሎ ነበረ:- “ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት ዐልፎአል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዛል፤ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።”—የሐዋርያት ሥራ 17:30, 31
ኢየሱስ ራሱ ከትንሣኤው በኋላ ጳውሎስን አነጋግሮትና የቀድሞ ክርስቲያኖችን ማሳደዱን እንዲያቆም አድርጎት ስለነበር ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:3-7) ጳውሎስ ስለ አምላክ ዓላማ ትክክለኛውን እውቀት ከቀሰመ በኋላ አመለካከቱን ቀይሮ ልክ እንደ ክርስቶስ ጥሩ ሰው ለመሆን በቅቷል። (1 ቆሮንቶስ 11:1፤ ቈላስይስ 3:9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በቅንዓት ሰብኳል። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ባሉት ወደ 2, 000 የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር የሚገዙ እንደ ጳውሎስ ያሉ ሰዎችን መርጧል።—ራእይ 5:9, 10
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” በማለት የሰጠውን ተልእኮ ካለፈው መቶ ዘመን ጀምሮ በትጋት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ለዚህ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች በሰማይ በሚገኘው የክርስቶስ አገዛዝ ሥር ሆነው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያገኛሉ። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) አንድ ሰው ለሌላው ሊያደርግ የሚችለው ከሁሉም የላቀ በጎ ምግባር ቢኖር ይህን እውቀት እንዲያገኝ መርዳት ነው።
የመንግሥቱን ምሥራች የተቀበሉ ሰዎች በዙሪያቸው ያለው ዓለም በክፋት ድርጊቶች የተዋጠ ቢሆንም እንኳ እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ግሩም ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። (ገላትያ 5:22, 23) ኢየሱስን በመምሰል ‘ለማንም ክፉን በክፉ አይመልሱም።’ (ሮሜ 12:17) ሁሉም በግሉ ‘ክፉን በመልካም ለማሸነፍ’ ይጥራል።—ሮሜ 12:21፤ ማቴዎስ 5:44
ክፋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሸነፋል
የሰው ልጆች የክፋት ምንጭ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን በራሳቸው ፈጽሞ ማጥፋት አይችሉም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል። (ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 16:20) እንዲሁም በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለተፈጸመው ክፉ ድርጊት መንስዔ የሆኑትን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ሥርዓቶች ‘እንዲያደቅና እስከ መጨረሻው እንዲያጠፋቸው’ ለኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ ይሰጣል። (ዳንኤል 2:44፤ መክብብ 8:9) በመጪው የፍርድ ቀን ‘ለጌታችን ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙት በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።’—2 ተሰሎንቄ 1:8, 9፤ ሶፎንያስ 1:14-18
ኢየሱስ ሰይጣንንና አጫፋሪዎቹን አንዴ ካስወገደ በኋላ ከጥፋቱ የተረፉት ሰዎች ምድርን ወደ ቀድሞ ውበቷ እንዲመልሱ ከሰማይ ሆኖ ይረዳቸዋል። ከዚህም በላይ በታደሰችው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሙታንን በሙሉ ያስነሳል። (ሉቃስ 23:32, 39-43፤ ዮሐንስ 5:26-29) እንዲህ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ የደረሰው ክፋት ያስከተለውን ጠባሳ ይሽራል።
ይሖዋ ስለ ኢየሱስ የሚነገረውን ምሥራች እንዲቀበሉ ሰዎችን አያስገድድም። ሆኖም ወደ ሕይወት የሚመራውን እውቀት እንዲቀስሙ አጋጣሚዎችን ከፍቶላቸዋል። ከዚህ አጋጣሚ አሁኑኑ መጠቀምህ ወሳኝ ነው! (ሶፎንያስ 2:2, 3) እንዲህ ካደረግህ በአሁኑ ጊዜ ሕይወትህን ሊያበላሹ የሚችሉ መጥፎ ድርጊቶችን እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል ትማራለህ። ከዚህም በላይ ክርስቶስ ክፋትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ድል እንደሚነሳ ትመለከታለህ።—ራእይ 19:11-16፤ 20:1-3, 10፤ 21:3, 4
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳውል ትክክለኛ እውቀት ስላልነበረው የክፋት ድርጊት ፈጽሟል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ሰው ለሌላው ሊያደርግ የሚችለው ከሁሉም የላቀ በጎ ምግባር ቢኖር ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት እንዲኖረው መርዳት ነው