በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታሰላስልበትን ጊዜ አስደሳች አድርገው

የምታሰላስልበትን ጊዜ አስደሳች አድርገው

የምታሰላስልበትን ጊዜ አስደሳች አድርገው

አንዳንድ ሰዎች ማሰላሰል የሚለው ሐሳብ ያስፈራቸዋል። እነዚህ ሰዎች ማሰላሰልን ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ከባድ ሥራ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ማሰላሰል ስለማይወዱ በተለይ አስፈላጊነቱን ሲያነቡ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) ይሁን እንጂ ይሖዋን በተመለከተ ስለተማርናቸው እውነታዎች፣ ስለ ግሩም ባሕርያቱ፣ ስለ አስደናቂ ሥራዎቹ፣ ስለ መሥፈርቶቹ እንዲሁም ስለ ታላቅ ዓላማው በማሰላሰል የምናሳልፈውን ጊዜ አስደሳች ማድረግ እንችላለን፤ ደግሞም እንደዚያ ማድረግ ይገባናል። ለምን?

ይሖዋ አምላክ የጽንፈ ዓለም የበላይ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ታላቅ ዓላማውን ከዳር ለማድረስ ሁልጊዜ ይሠራል። (ዮሐንስ 5:17) ያም ሆኖ ግን የሚያመልኩት ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ ይጓጓል። መዝሙራዊው ዳዊት ይህን ስለሚያውቅ በመንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ።”​—⁠መዝሙር 139:1, 2

አንድ ሰው መዝሙራዊው የጻፋቸውን እነዚህን ቃላት ሲያነብ ጥሩ ስሜት ላያድርበት ይችላል። ‘አምላክ ወደ አእምሮዬ የሚመጣውን መጥፎ ሐሳብ ሁሉ “ገና ከሩቁ” ያስተውላል’ በማለት ፍርሃቱን ይገልጽ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ የራሱ ጥቅም አለው። ይህን ማወቃችን ወደ አእምሯችን የሚመጡ መጥፎ አስተሳሰቦችን እንድንዋጋ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ስለ እነዚህ ነገሮች ብናስብ እንኳ አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር እንደሚለን ተማምነን ኃጢአታችንን ለእርሱ እንድንናዘዝ ሊያነሳሳን ይችላል። (1 ዮሐንስ 1:8, 9፤ 2:1, 2) ይሁን እንጂ ይሖዋ የአገልጋዮቹን መልካም ጎንም እንደሚመረምር መዘንጋት አይኖርብንም። በአድናቆት ስሜት ስለ እርሱ ስናሰላስል ትኩረት ሰጥቶ ይከታተለናል።

“በእርግጥ ይሖዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ የሚያስቡትን መልካም ነገር ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እንደሚከታተል ምንም አያጠራጥርም። ኢየሱስ ትንንሽ ድንቢጦች እንኳ በይሖዋ ዘንድ እንደሚታወሱ ከገለጸ በኋላ “ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ” በማለት ይሖዋ ለእኛ ያለውን አሳቢነት አጉልቶ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:6, 7) ድንቢጦች ስለ ይሖዋ ማሰላሰል አይችሉም። ለእነርሱ የዚህን ያህል የሚያስብ ከሆነ ለእኛማ ምን ያህል የበለጠ ያስብ! እያንዳንዳችን ስለ እርሱ ስናሰላስል በጣም ይደሰታል። አዎን፣ እኛም ልክ እንደ ዳዊት “መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን” ብለን በሙሉ ልብ መጸለይ እንችላለን።​—⁠መዝሙር 19:14

ነቢዩ ሚልክያስ በመንፈስ ተነሳስቶ የጻፋቸውን ቃላት ስንመለከት ይሖዋ ታማኝ አምላኪዎቹ ለሚያሰላስሉት ነገር ትኩረት እንደሚሰጥ ተጨማሪ ማስረጃ እናገኛለን። ሚልክያስ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔር አዳመጠ፤ ሰማቸውም፤ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ስሙን ለሚያከብሩ [“ለሚያስቡ፣” የ1954 ትርጉም ] በእርሱ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።” (ሚልክያስ 3:16) ይሖዋ ስለ እርሱ በአእምሯችን የምናወጣውንና የምናወርደውን ሐሳብ ምንጊዜም ‘እንደሚያዳምጥ’ ወይም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ማስታወሳችን ስለ አምላክ የምናሰላስልበትን ጊዜ አስደሳች ያደርግልናል። ስለዚህ “ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ” ብሎ የጻፈውን የመዝሙራዊውን ቃላት እናስተጋባ።​—⁠መዝሙር 77:12