በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጽድቅን መፈለግ ጥበቃ ይሆንልናል

ጽድቅን መፈለግ ጥበቃ ይሆንልናል

ጽድቅን መፈለግ ጥበቃ ይሆንልናል

‘ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እሹ።’​—⁠ማቴዎስ 6:33

1, 2. አንዲት ወጣት ክርስቲያን ምን ውሳኔ አድርጋለች? ይህንንስ ውሳኔ ያደረገችው ለምንድን ነው?

 በእስያ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ወጣት በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በጸሐፊነት ትሠራ ነበር። ይህች ወጣት ሥራዋን በሚገባ ታከናውን የነበረ ከመሆኑም በላይ ከሥራ መግቢያ ሰዓት ቀደም ብላ ቢሮዋ ትገኛለች፤ ልግመኛም አይደለችም። ይሁን እንጂ ቋሚ ሠራተኛ ባለመሆኗ ሥራዋ ይገመገም ነበር። የምትሠራበት ክፍል ኃላፊ ከእርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት ከፈጸመች ቋሚ ሠራተኛ እንድትሆን እንደሚያደርጋት አልፎ ተርፎም ትልቅ የሥራ ደረጃ እንደሚሰጣት ነገራት። ይህች እህት የተጠየቀችውን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነች ሥራዋን ታጣለች፤ ቢሆንም ድርጊቱን በጭራሽ እንደማትፈጽም ነገረችው።

2 ይህች ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ማድረጓ ስህተት ነበር? አልነበረም። ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እሹ’ በማለት የተናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ ተከትላለች። (ማቴዎስ 6:33) ለእርሷ የጾታ ብልግና በመፈጸም ከሚገኝ ጥቅም ይልቅ የጽድቅ መመሪያዎችን ማክበር ይበልጥባታል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:18

የጽድቅ አስፈላጊነት

3. ጽድቅ ምንድን ነው?

3 “ጽድቅ” የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በጥብቅ መከተልን የሚያመለክት ቃል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽድቅ ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛና የዕብራይስጥ ቃላት “ቀና” ወይም “ትክክለኛ” መሆን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። ቃሉ በራስ መሥፈርት ራስን በመለካት መመጻደቅን አያመለክትም። (ሉቃስ 16:15) ከዚህ ይልቅ በይሖዋ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ትክክል መሆንን ከማሳየቱም በተጨማሪ የአምላክን ጽድቅ የሚያመለክት ቃል ነው።​—⁠ሮሜ 1:17፤ 3:21

4. ክርስቲያኖች ጻድቅ መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

4 ጻድቅ መሆን ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም ‘ጻድቁ አምላክ’ ይሖዋ ለሕዝቡ ሞገሱን የሚያሳየው ጽድቅን ሲያደርጉ ነው። (መዝሙር 4:1፤ ምሳሌ 2:20-22፤ ዕንባቆም 1:13) ዓመጽ የሚፈጽም ማንኛውም ሰው የይሖዋ የቅርብ ወዳጅ መሆን አይችልም። (ምሳሌ 15:8) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ‘ከወጣትነት ክፉ ምኞት እንዲሸሽና ጽድቅን’ ጨምሮ ሌሎች በጣም አስፈላጊ ባሕርያትን እንዲያዳብር ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) እንዲሁም ጳውሎስ ስለተለያዩ መንፈሳዊ ትጥቆቻችን ሲዘረዝር “የጽድቅንም ጥሩር” የጠቀሰው ለዚህ ነው።​—⁠ኤፌሶን 6:14

5. ፍጹም ያልሆኑ ፍጥረታት ጽድቅን መሻት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 እርግጥ ነው፣ የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ጻድቅ ሊሆን አይችልም። ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ከአዳም አለፍጽምናን በመውረሱ ምክንያት ሲወለድ ጀምሮ ኃጢአተኛና ዓመጸኛ ነው። ቢሆንም ኢየሱስ ጽድቅን መሻት እንዳለብን ተናግሯል። ይህ እንዴት ይቻላል? ኢየሱስ ፍጹም ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በማቅረቡ ጽድቅን መሻት እንችላለን፤ በዚህ መሥዋዕት ላይ እምነት ካለን ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ፈቃደኛ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:8, 9, 12, 18) ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ በጸሎት እርዳታ እየጠየቅን የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች የምንማርና የተማርነውን ለመታዘዝ አቅማችን የፈቀደውን የምናደርግ ከሆነ፣ አምልኮታችን በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል። (መዝሙር 1:6፤ ሮሜ 7:19-25፤ ራእይ 7:9, 14) ይህን ማወቁ እንዴት ያጽናናል!

በዓመጸኛ ዓለም ውስጥ ጻድቅ መሆን

6. ዓለም ለጥንት ክርስቲያኖች አደገኛ ቦታ የነበረው ለምንድን ነው?

6 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” የእርሱ ምሥክር የመሆን ተልእኮ በተሰጣቸው ጊዜ ከፊታቸው ከባድ ሁኔታ ይጠብቃቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) የተመደቡበት ክልል በጠቅላላ “በክፉው ሥር” ማለትም በሰይጣን እጅ ውስጥ ነበር። (1 ዮሐንስ 5:19) ዓለም ሰይጣን በሚያስፋፋው ክፉ መንፈስ ተበክሎ የነበረ በመሆኑ ክርስቲያኖች ለዚህ በካይ ተጽዕኖ መጋለጣቸው አልቀረም። (ኤፌሶን 2:2) ለእነርሱ ዓለም አደገኛ የሆነ ቦታ ነበር። ጽኑ አቋማቸውን እንደጠበቁ መኖር የሚችሉት ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን ጽድቅ በመሻት ብቻ ነው። አብዛኞቹ የጥንት ክርስቲያኖች በአቋማቸው የጸኑ ቢሆንም ‘የጽድቅን መንገድ’ የተዉ ጥቂት ሰዎችም ነበሩ።​—⁠ምሳሌ 12:28፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:10

7. አንድ ክርስቲያን መጥፎ ተጽዕኖዎችን እንዲቋቋም የሚጠይቁበት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?

7 ዓለም ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖችስ ከአደጋ ነጻ የሆነ ስፍራ ነው? በጭራሽ! እንዲያውም ዓለም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው በከፋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። በተጨማሪም ሰይጣን ወደ ምድር ተባርሯል፤ በቅቡዓን ክርስቲያኖችም ላይ ከባድ ጦርነት እንደከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።” (ራእይ 12:12, 17 የ1954 ትርጉም ) እንዲሁም ሰይጣን የሴቲቱን ‘ዘር’ የሚደግፉትን ሁሉ ያጠቃል። ቢሆንም ክርስቲያኖች ከዓለም የትም መሄድ አይችሉም። የዓለም ክፍል ባይሆኑም እንኳ በውስጡ መኖራቸው የግድ ነው። (ዮሐንስ 17:15, 16) በተጨማሪም ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘትና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለማስተማር በዓለም ውስጥ መስበክ አለባቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ስለዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ካለው መጥፎ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ መሸሽ ስለማይችሉ ተጽዕኖውን መቋቋም ይጠበቅባቸዋል። እስቲ ከተጽዕኖዎቹ መካከል አራቱን እንመልከት።

የጾታ ብልግና ወጥመድ

8. እስራኤላውያን የሞዓባውያንን አማልክት ማምለክ የጀመሩት ለምን ነበር?

8 እስራኤላውያን የ40 ዓመቱን የበረሃ ጉዞ ወደ ማጠናቀቁ ሲቃረቡ ብዙዎቹ ከጽድቅ ጎዳና ወጥተው ነበር። ይሖዋ እነርሱን ነጻ ለማውጣት ሲል ያደረጋቸውን ብዙ ነገሮች ከመመልከታቸውም በተጨማሪ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ይሁንና በዚያ የመጨረሻ ሰዓት ላይ የሞዓባውያንን አማልክት ማምለክ ጀመሩ። ለምን? “የሥጋ ምኞት” አሸንፏቸው ስለነበረ ነው። (1 ዮሐንስ 2:16) ዘገባው “ወንዶቹ ከሞዓብ ሴቶች ጋር ማመንዘር ጀመሩ” ይላል።​—⁠ዘኍልቍ 25:1

9, 10. የተሳሳቱ ሥጋዊ ምኞቶች አቋም የማበላሸት ኃይል እንዳላቸው ሁልጊዜ የማስታወስን አስፈላጊነት የሚያሳዩ ምን ሁኔታዎች አሉ?

9 ይህ ታሪክ እንደሚያሳየው መጥፎ የሥጋ ምኞት ጠንቃቃ ያልሆኑ ሰዎችን አቋም ሊያበላሽ ይችላል። በተለይ የሥነ ምግባር ብልግና ተቀባይነት ያለው የአኗኗር ዘይቤ ተደርጎ መታየት ስለጀመረ ከተጠቀሰው ታሪክ ትምህርት ማግኘት ይገባናል። (1 ቆሮንቶስ 10:6, 8) ከዩናይትድ ስቴትስ የተገኘ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ከ1970 በፊት በነበሩት ጊዜያት በሕግ ሳይጋቡ አብሮ መኖር በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች እንደ ሕገ ወጥ ድርጊት ይታይ ነበር። አሁን ግን የተለመደ ሆኗል። የመጀመሪያ ጋብቻቸውን ከሚፈጽሙት ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ከሠርጋቸው በፊት አብረው ኖረዋል።” ይህም ሆነ ሌሎች መጥፎ ሥነ ምግባራዊ ድርጊቶች በአንድ አገር ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ችግሮች ናቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖችም ይህን የዓለም ጎዳና መከተላቸው የሚያሳዝን ነው፤ የሚገርመው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን አቋም እስከማጣት የደረሱም አሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:11

10 በተጨማሪም ሰዎች የጾታ ብልግና እንዲፈጽሙ በየትኛውም ቦታ ይበረታታሉ ለማለት ይቻላል። ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸማቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ድርጊት እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ። ግብረ ሰዶም ምንም ስህተት እንደሌለው የሚያስመስል ነገር ይተላለፋል። እንዲሁም የጾታ ግንኙነት ሲፈጸም ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያሳዩ ፊልሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የጾታ ግንኙነት ሲፈጸም የሚያሳዩ ምስሎችንም በኢንተርኔት በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆነ አንድ ሰው የሰባት ዓመት ልጁ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ሲመለስ፣ የትምህርት ቤት ጓደኛው ሴቶች ራቁታቸውን ሆነው የጾታ ግንኙነት እየፈጸሙ እንዳሉ የሚያስመስል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚያሳይ የኢንተርኔት ገጽ እንዳገኘ በስሜት ነገረው። ነገሩ አባትየውን ክፉኛ አስደነገጠው፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ድረ ገጾችን እንደሚመለከቱ ለወላጆቻቸው የሚናገሩት ምን ያህል ልጆች ናቸው? ልጆቻቸው የሚጫወቱባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች ያላቸውን ይዘት የሚያውቁትስ ምን ያህል ወላጆች ናቸው? ተወዳጅነት ያላቸው በርካታ ጨዋታዎች ጸያፍ የሥነ ምግባር ብልግናዎችን፣ አጋንንታዊ ሥራዎችንና ዓመጽን ያካተቱ ናቸው።

11. አንድ ቤተሰብ ከዓለም የሥነ ምግባር ብልግና መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?

11 አንድ ቤተሰብ እንዲህ ካሉት ወራዳ “መዝናኛዎች” መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው? በአንደኛ ደረጃ ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና ላለመፈጸም ጽኑ አቋም ይዞ የአምላክን ጽድቅ በማስቀደም ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:14፤ ኤፌሶን 5:3) የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በሚገባ የሚቆጣጠሩ እንዲሁም በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የይሖዋን ፍቅርና የጽድቅ ሕጎቹን የሚቀርጹ ወላጆች ልጆቻቸው ከወሲባዊ ምስሎች፣ ብልግና ከሚታይባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ፊልሞችና ለፈተና ከሚያጋልጡ ሌሎች ነገሮች እንዲታቀቡ ይረዷቸዋል።​—⁠ዘዳግም 6:4-9 a

የአካባቢ ተጽዕኖ የሚያስከትለው አደጋ

12. በአንደኛው መቶ ዘመን ምን ችግር ተከስቶ ነበር?

12 ጳውሎስ በትንሹ እስያ በምትገኘው ልስጥራን እያለ አንድ ሰው በተአምር ፈወሰ። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ ‘አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!’ ብለው ጮኹ፤ በርናባስን ‘ድያ’ አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር ‘ሄርሜን’ አሉት።” (የሐዋርያት ሥራ 14:11, 12) ከዚያ በኋላ ግን ይኸው ሕዝብ ጳውሎስንና በርናባስን ለመግደል ፈልጎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 14:19) ሰዎቹ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃቸው እንደነበር ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚህ ስፍራ ከነበሩት መካከል አንዳንዶቹ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላም አጉል እምነታቸውን እንደያዙ ሳይቀጥሉ አልቀሩም። ጳውሎስ ለቈላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የመላእክትን አምልኮ” የሚቃወም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር።​—⁠ቈላስይስ 2:18

13. አንድ ክርስቲያን ሊርቃቸው ከሚገቡ ልማዶች መካከል ጥቂቶቹ የትኞቹ ናቸው? እንዲህ ለማድረግ የሚያስችለውን ብርታት የሚያገኘው እንዴት ነው?

13 በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከክርስትና መመሪያዎች ጋር በሚጋጩ የሐሰት ሃይማኖት አስተሳሰቦች ላይ ከተመሠረቱ፣ ሆኖም ሰፊ ተቀባይነት ካገኙ ልማዶች ይርቃሉ። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች ከሞትና ከልጅ መወለድ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑት ልማዳዊ ሥነ ሥርዓቶች፣ ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል መንፈስ አለ በሚለው የሐሰት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። (መክብብ 9:5, 10) ሴቶችን የመግረዝ ልማድ ያለባቸው አገሮችም አሉ። ይህ ክርስቲያን ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ሊያሳዩት ከሚገባው ፍቅራዊ አሳቢነት ጋር የሚቃረን አላስፈላጊ የጭካኔ ድርጊት ነው። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ኤፌሶን 6:4) ክርስቲያኖች የአካባቢያቸውን ተጽዕኖ በመቋቋም እንዲህ ያሉ ልማዶችን ከመከተል መታቀብ የሚችሉት እንዴት ነው? ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ በመታመን ነው። (መዝሙር 31:6) ጻድቁ አምላክ ከልባቸው “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” ለሚሉት ሰዎች ብርታት ከመስጠቱም በላይ እንክብካቤ ያደርግላቸዋል።​—⁠መዝሙር 91:2፤ ምሳሌ 29:25

ይሖዋን አትርሳ

14. እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ጥቂት ሲቀራቸው ይሖዋ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር?

14 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ጥቂት ሲቀራቸው እርሱን እንዳይረሱ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር:- “በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ። አለበለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣ ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣ ልብህ ይታበይና . . . አምላክህን እግዚአብሔርን ትረሳለህ።”​—⁠ዘዳግም 8:11-14

15. ይሖዋን እንዳልረሳን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ዛሬስ ተመሳሳይ ሁኔታ ይከሰት ይሆን? ቅድሚያ ሊሰጠው የማይገባ ነገር የምናስቀድም ከሆነ ተመሳሳይ ነገር ሊፈጠር ይችላል። የአምላክን ጽድቅ ካስቀደምን ግን ንጹሕ አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ላቅ ያለውን ስፍራ ይይዛል። ጳውሎስ እንዳበረታታን ‘ዘመኑን እንዋጃለን፤’ አገልግሎታችንንም በጥድፊያ ስሜት እናከናውናለን። (ቈላስይስ 4:5 የ1954 ትርጉም፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2) ነገር ግን ስብሰባዎችንና አገልግሎትን ከመዝናኛ ወይም ከሚያስደስቱ ሌሎች የጊዜ ማሳለፊያዎች አሳንሰን የምንመለከት ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን ልንረሳው እንችላለን፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ለይሖዋ ሁለተኛውን ቦታ ሰጥተናል ማለት ነው። ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:4) ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች ይህን የመሰለው አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳላደረገባቸው ለማረጋገጥ ራሳቸውን አዘውትረው ይመረምራሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 13:5

በራስ የመመራት መንፈስ እንዳያጠቃህ ተጠንቀቅ

16. ሔዋንና በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ያሳዩት ተገቢ ያልሆነ መንፈስ ምንድን ነው?

16 በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን፣ ሔዋን በራስ የመመራት የስስት ፍላጎት እንዲያድርባት ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል። ሔዋን ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ራሷ ለመወሰን ፈልጋ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-6) በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል በራስ የመመራት መንፈስ ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ከጳውሎስ የተሻለ እውቀት እንዳላቸው ያስቡ ስለነበር ጳውሎስ ታላላቅ ሐዋርያት ብሎ በምጸት ጠርቷቸዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 11:3-5፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:3-5

17. በራስ የመመራትን መንፈስ ከማዳበር መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች “ችኩሎች” እና “በትዕቢት የተወጠሩ” ናቸው፤ እንዲህ የመሰሉት አስተሳሰቦች በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ አድርገዋል። እንዲያውም አንዳንዶች የእውነት ተቃዋሚዎች ሊሆኑ ችለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:4፤ ፊልጵስዩስ 3:18) በንጹሕ አምልኮ ረገድ ግን የይሖዋን መመሪያ መታዘዛችን እንዲሁም ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ እና ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መተባበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ ጽድቅን መፈለግ የምንችል ከመሆኑም በላይ በራስ ከመመራት መንፈስ እንጠበቃለን። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 25:9, 10፤ ኢሳይያስ 30:21) የቅቡዓን ጉባኤ “የእውነት ዐምድና መሠረት” ነው። ይሖዋ ይህንን ጉባኤ ያቋቋመው እኛን ለመጠበቅና ለመምራት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ለይሖዋ የጽድቅ ፈቃድ በትሕትና በምንገዛበት ጊዜ የዚህን ጉባኤ ወሳኝ ሚና መገንዘባችን ‘በራስ ወዳድነት ምኞት አንዳች እንዳናደርግ’ ይረዳናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:2-4፤ ምሳሌ 3:4-6

ኢየሱስን ምሰሉ

18. በምን መንገዶች ኢየሱስን እንድንመስል ተበረታተናል?

18 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 45:7፤ ዕብራውያን 1:9) እንዴት ያለ ሊኮረጅ የሚገባው አስተሳሰብ ነው! (1 ቆሮንቶስ 11:1) ኢየሱስ የይሖዋን የጽድቅ ደረጃዎች ማወቅ ብቻ ሳይሆን ይወዳቸውም ነበር። ስለዚህ ሰይጣን በምድረ በዳ ሲፈትነው አሻፈረኝ ለማለት ምንም አላቅማማም፤ ‘ከጽድቅ መንገድ’ ላለመውጣት ቁርጥ ያለ አቋም ይዞ ነበር።​—⁠ምሳሌ 8:18-20፤ ማቴዎስ 4:​3-11

19, 20. ጽድቅን መፈለግ የሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች የትኞቹ ናቸው?

19 ያለብን የዓመጸኝነት ዝንባሌ ኃይለኛ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። (ሮሜ 7:19, 20) ጽድቅን የምንወድድ ከሆነ ግን ክፋትን ለማሸነፍ ጥንካሬ ይኖረናል። (መዝሙር 119:165) ለጽድቅ ጥልቅ ፍቅር ማዳበራችን መጥፎ ነገር ሲያጋጥመን ጥበቃ ይሆነናል። (ምሳሌ 4:4-6) በፈተና በምንሸነፍበት ጊዜ ሁሉ ሰይጣን ድል እንዲያገኝ እያደረግን መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሰይጣንን መቋቋምና ይሖዋ ድል እንዲነሳ ማድረጉ ምንኛ የተሻለ ነው!​—⁠ምሳሌ 27:11፤ ያዕቆብ 4:7, 8

20 እውነተኛ ክርስቲያኖች ጽድቅን ስለሚሹ ‘ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞሉ’ ናቸው። (ፊልጵስዩስ 1:10, 11) “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” ለብሰዋል። (ኤፌሶን 4:24) የይሖዋ ንብረት ከመሆናቸውም በላይ የሚኖሩት ራሳቸውን ለማስደሰት ሳይሆን እርሱን ለማገልገል ነው። (ሮሜ 14:8፤ 1 ጴጥሮስ 4:2) አስተሳሰባቸውንና እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠረው ይህ ነው። የሰማዩ አባታቸው ልብ እንዴት ይደሰት!​—⁠ምሳሌ 23:24

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ወላጆች ቤተሰባቸውን ከመጥፎ የሥነ ምግባር ተጽዕኖዎች እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዟል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ጽድቅን መሻት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ፍጹም ያልሆነ ክርስቲያን ጽድቅን መፈለግ የሚችለው እንዴት ነው?

• አንድ ክርስቲያን ሊርቃቸው ከሚገቡ በዓለም የተለመዱ ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ የትኞቹ ናቸው?

• ጽድቅን መፈለግ ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓለም ለኢየሱስ ተከታዮች አደገኛ ቦታ ነበር

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል27]

ይሖዋን ስለመውደድ የተማሩ ልጆች የሥነ ምግባር ብልግና ከመፈጸም ይታቀባሉ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ገብተው ከበለጸጉ በኋላ ይሖዋን ረስተውታል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ልክ እንደ ኢየሱስ ዓመጽን ይጠላሉ