በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለሕዝብ ሁሉ የሚሰጥ ምስክርነት’

‘ለሕዝብ ሁሉ የሚሰጥ ምስክርነት’

‘ለሕዝብ ሁሉ የሚሰጥ ምስክርነት’

“እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 1:8

1. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማቴዎስ 24:14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት መቼና የት ነበር?

 ኢየሱስ በማቴዎስ 24:14 ላይ የተናገራቸው ቃላት በጣም የሚታወቁ በመሆናቸው ብዙዎቻችን በቃል ልንወጣቸው እንችላለን። እንዴት ያለ አስደናቂ ትንቢት ነው! ደቀ መዛሙርቱ ይህን ትንቢት መጀመሪያ ሲሰሙ ምን አስበው ሊሆን እንደሚችል ገምት! ጊዜው 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር ሦስት ዓመት ገደማ አሳልፈዋል፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ አብረውት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ነበር። የፈጸማቸውን ተአምራት አይተዋል፤ ያስተማራቸውንም ትምህርቶች አዳምጠዋል። እነዚህ ጠቃሚ ትምህርቶች ቢያስደስቷቸውም ሁሉም ሰው እንደ እነርሱ እንደማይደሰት በሚገባ ተገንዝበው ነበር። ኢየሱስ ኃይለኞችና ተደማጭነት ያላቸው ጠላቶች ነበሩት።

2. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?

2 ከኢየሱስ ጋር ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጠው የነበሩት አራት ደቀ መዛሙርት፣ ወደፊት ስለሚከሰቱት አደገኛ ሁኔታዎችና ስለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ሲነግራቸው በጥሞና ያዳምጡት ነበር። ቀደም ሲል እርሱ ራሱ እንደሚገደል ገልጾላቸዋል። (ማቴዎስ 16:21) አሁን ደግሞ እነርሱም ጭካኔ የተሞላበት ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው በግልጽ ነገራቸው። “ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ተናገረ። ይሁን እንጂ ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። ሐሰተኛ ነቢያት ብዙዎችን ያስታሉ። ሌሎች ደግሞ ይሰናከላሉ፣ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ ይጠላላሉ። ከዚህም በላይ “ብዙ ሰዎች” ለአምላክና ለቃሉ ያላቸው ፍቅር ይቀዘቅዛል።​—⁠ማቴዎስ 24:9-12

3. በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት በእርግጥ የሚያስደንቁ የሆኑት ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ እንዲህ የመሰሉ አሳዛኝ ክስተቶችን ከጠቀሰ በኋላ የተናገረው አንድ ሐሳብ ደቀ መዛሙርቱን ሳያስደንቃቸው አልቀረም። “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” አላቸው። (ማቴዎስ 24:14) አዎን፣ ኢየሱስ በእስራኤል የጀመረው ‘ስለ እውነት የመመስከር’ ሥራ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ በዓለም ዙሪያ ይስፋፋል። (ዮሐንስ 18:37) እውነትም እንዴት ያለ አስገራሚ ትንቢት ነው! ወንጌሉን “ለሕዝብ ሁሉ” ማዳረስ በራሱ ከባድ ሥራ ሲሆን በተለይ ‘በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠሉ’ ሆኖ ይህን ሥራ መሥራት መቻል ተአምር ነው። እጅግ ሰፊ የሆነው ይህ ሥራ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ የይሖዋን ሉዓላዊነትና ኃያልነት ብቻ ሳይሆን እርሱ አፍቃሪ፣ መሐሪና ታጋሽ መሆኑን ጭምር ያረጋግጣል። በተጨማሪም ሥራው የይሖዋ አገልጋዮች እምነታቸውንና ፍቅራቸውን የሚያሳዩበትን አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።

4. የምሥክርነቱን ሥራ እንዲሠሩ የተነገራቸው እነማን ናቸው? ኢየሱስስ ምን የሚያጽናና ሐሳብ ነገራቸው?

4 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የተሰጣቸው ሥራ እጅግ ታላቅ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል። ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ተገለጠላቸውና እንዲህ አላቸው:- “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ከጥቂት ጊዜ በኋላ አብረዋቸው የሚሠሩ ሌሎች ሰዎች የሚጨመሩ ቢሆንም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር ጥቂት ነበር። ኃያሉ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ይህንን መለኮታዊ ተልእኮ እንዲወጡ ኃይል እንደሚሰጣቸው ማወቃቸው ምንኛ ያጽናናቸው!

5. ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሥክርነቱ ሥራ ምን የማያውቁት ነገር ነበር?

5 ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን መስበክና ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት ማድረግ’ እንዳለባቸው ተረድተው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ነገር ግን በምን ያህል ስፋት ምሥክርነት እንደሚሰጥና መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ አያውቁም ነበር። እኛም ምንም የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህ ይሖዋ ብቻ የሚያውቃቸው ጉዳዮች ናቸው። (ማቴዎስ 24:36) እርሱ፣ የተሰጠው ምሥክርነት በቂ ነው በሚልበት ጊዜ ይህን ክፉ ዓለም ያጠፋዋል። ክርስቲያኖች የስብከቱ ሥራ ይሖዋ ባቀደው መጠን እንደተከናወነ የሚገነዘቡት በዚያን ጊዜ ብቻ ነው። የጥንት ደቀ መዛሙርት፣ የምሥክርነቱ ሥራ በዚህ የፍጻሜ ዘመን እየተሰጠ ባለበት መጠን ይከናወናል የሚል ግምት ፈጽሞ ሊኖራቸው አይችልም።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተሰጠው ምሥክርነት

6. በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ምን ተከሰተ?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ አስደናቂ ውጤቶች አስገኝቶ ነበር። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት 120 ገደማ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። በዚያን ጊዜ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፈሰሰባቸው፤ ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህ ተአምር ምን ትርጉም እንዳለው የሚገልጽ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር ካደረገላቸው በኋላ 3, 000 ሰዎች አመኑና ተጠመቁ። ይህ ጅምር ብቻ ነበር። የሃይማኖት መሪዎች ምሥራች የመስበኩን ሥራ ለማስቆም ታጥቀው የተነሱ ቢሆንም ይሖዋ “የሚድኑትን በቊጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።” ብዙም ሳይቆይ ‘የወንዶቹ ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ።’ ከዚያ በኋላ “ብዙ ወንዶችና ሴቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጌታ እያመኑ ወደ እነርሱ ይጨመሩ ነበር።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 8, 14, 41, 47፤ 4:4፤ 5:14

7. የቆርኔሌዎስ መለወጥ ትልቅ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው?

7 በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንድ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ተከሰተ፤ ይህም ከአሕዛብ ወገን የነበረው የቆርኔሌዎስ ወደ ክርስትና መለወጥና መጠመቅ ነው። ይሖዋ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስን ፈሪሃ አምላክ ወደነበረው ወደዚህ ሰው በመላክ፣ ኢየሱስ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት በሰጠው ትእዛዝ ላይ የተጠቀሱት ሕዝቦች በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ አይሁዳውያንን ብቻ የሚያመለክቱ እንዳልሆኑ አሳይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 10:44, 45) ሥራውን የሚመሩት ክርስቲያኖች ምን ተሰማቸው? ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት ሽማግሌዎች፣ አይሁዳውያን ያልሆኑ አሕዛብ ምሥራቹ ሊነገራቸው እንደሚገባ ከሁኔታው በተረዱ ጊዜ አምላክን አመሰገኑ። (የሐዋርያት ሥራ 11:1, 18) አይሁዳውያንም ምሥራቹ ሲሰበክላቸው በደስታ ይቀበሉ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ማለትም በ58 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ከአሕዛብ በተጨማሪ “በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ” ተገልጿል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 21:20

8. ምሥራቹ በግለሰቦች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ቁጥር ማደጉ አስደናቂ ቢሆንም ስለጭማሪው ብቻ ሳይሆን ስለግለሰቦቹም ማንነት ማሰባችን አስፈላጊ ነው። የሰሙት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ኃይል ነበረው። (ዕብራውያን 4:12) መልእክቱን የተቀበሉ ሰዎች ሕይወት በአስገራሚ ሁኔታ ተለውጧል። እነዚያ ግለሰቦች ንጹሕ ሥነ ምግባር ይዘው መኖር ከመጀመራቸውም በላይ አዲሱን ሰው በመልበስ ከአምላክ ጋር ታርቀዋል። (ኤፌሶን 4:22, 23) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ምሥራቹን የሚቀበሉ ሁሉ ለዘላለም የመኖር ግሩም ተስፋ አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 3:16

ከአምላክ ጋር የሚሠሩ ነበሩ

9. የጥንት ክርስትያኖች ምን መብትና ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተገንዝበው ነበር?

9 የጥንት ክርስቲያኖች ስኬት ያገኙት በራሳቸው ጥረት እንደሆነ አድርገው አላሰቡም። የስብከት ሥራቸው “በመንፈስ ቅዱስ ኀይል” እንደሚታገዝ ተገንዝበው ነበር። (ሮሜ 15:13, 19) መንፈሳዊ እድገት እንዲገኝ ያደረገው ይሖዋ ነበር። ቢሆንም ‘ከእግዚአብሔር ጋር የመሥራት’ መብትና ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተገንዝበዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6-9) በዚህ ምክንያት በኢየሱስ ማሳሰቢያ መሠረት፣ የተሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ብርቱ ጥረት ያደርጉ ነበር።​—⁠ሉቃስ 13:24

10. አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ለሕዝብ ሁሉ ምሥራቹን ለመስበክ ምን ጥረት አድርገዋል?

10 ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” እንደመሆኑ መጠን በየብስና በባሕር በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ በእስያ በሚገኙ የሮም ግዛቶችና በግሪክ በርካታ ጉባኤዎችን አቋቁሟል። (ሮሜ 11:13) እንዲሁም ወደ ሮም ምናልባትም ወደ ስፔን ተጉዟል። በሌላ በኩል ደግሞ “ለተገረዙት ወንጌልን” የመስበክ አደራ የተሰጠው ሐዋርያው ጴጥሮስ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩበት በነበረው በባቢሎን ለማገልገል በተቃራኒ አቅጣጫ ተጉዟል። (ገላትያ 2:7-9፤ 1 ጴጥሮስ 5:13) በጌታ ሥራ ከደከሙት መካከል ፕሮፊሞናና ጢሮፊሞሳ የሚባሉ ሴቶች ይገኙበታል። ጠርሲዳ የምትባል ሌላ ሴት ደግሞ “በጌታ ሆና እጅግ ለደከመችው” ተብሎላታል።​—⁠ሮሜ 16:12

11. ይሖዋ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያደረጉትን ጥረት የባረከው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ የእነዚህንም ሆነ የሌሎች ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎችን ጥረት ባርኳል። ኢየሱስ ለሕዝብ ሁሉ ምሥክርነቱ እንደሚሰጥ ትንቢት በተናገረ 30 ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጳውሎስ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ . . . ወንጌል” እንደተሰበከ ጽፏል። (ቈላስይስ 1:23) ታዲያ መጨረሻው በዚያን ጊዜ መጥቷል? በተወሰነ መንገድ መጥቶ ነበር። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ወታደሮች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ባጠፉ ጊዜ የአይሁድ ሥርዓት መጨረሻ ሆነ። ሆኖም ይሖዋ ይህን ክፉ የሰይጣን ዓለም በጠቅላላ ከማጥፋቱ በፊት ምሥክርነቱ በስፋት እንዲሰጥ ወስኗል።

በዛሬው ጊዜ እየተሰጠ ያለው ምሥክርነት

12. ቀደም ሲል የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከቱን ሥራ በተመለከተ የተሰጠውን ትእዛዝ የተረዱት እንዴት ነበር?

12 በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ሃይማኖታዊ ክህደት ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የበላይነቱን እንደያዘ ቢሆንም ንጹሕ አምልኮ በድጋሚ ተቋቋመ። በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ምድር ላይ ደቀ መዛሙርት ስለማፍራት የተሰጠውን ትእዛዝ በሚገባ ተረድተው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) በ1914 በስብከቱ ሥራ በንቃት ይካፈሉ የነበሩት ሰዎች 5, 100 ገደማ ነበሩ፤ ምሥራቹም በ68 አገሮች ተዳርሶ ነበር። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የማቴዎስ 24:14ን ትንቢት ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት፣ ምሥራቹን ወይም ወንጌልን የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቋንቋዎች በመተርጎምና በማሳተም በዓለም ዙሪያ አሰራጩ። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምሥክርነቱ ለሕዝብ ሁሉ እንደተሰጠ አድርገው ለጥቂት አሥርተ ዓመታት ሲያስቡ ቆዩ።

13, 14. በ1928 የወጣው መጠበቂያ ግንብ የአምላክን ፈቃድና ዓላማ በሚመለከት ምን ጥልቅ ግንዛቤ እንደተገኘ ገልጾ ነበር?

13 ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ፈቃዱንና ዓላማውን ቀስ በቀስ እንዲረዱ አደረጋቸው። (ምሳሌ 4:18) የታኅሣሥ 1, 1928 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር:- “መጽሐፍ ቅዱስ መሰራጨቱ የመንግሥቱ ወንጌል እንደሚሰበክ አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው ማለት እንችላለን? በፍጹም እንደዚያ ማለት አንችልም! መጽሐፍ ቅዱስ ቢሰራጭም በዓለም ያሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ምሥክሮች የአምላክን [ዓላማ] የሚያብራሩ ጽሑፎችን ማተምና መጽሐፍ ቅዱስ የደረሳቸውን ሰዎች ቤታቸው እየሄዱ ማነጋገር ያስፈልጋቸዋል። አለበለዚያ ሰዎች በዘመናችን መሲሐዊው መንግሥት መቋቋሙን ማወቅ አይችሉም።”

14 ይህ መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ተጨማሪ ሐሳብ ይዟል:- “በ1920 . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘውን ጌታችን የተናገረውን ትንቢት በትክክል ተረዱ። በመሠረቱ ለአሕዛብ ወይም ለሕዝብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በዓለም ዙሪያ መሰበክ ያለበት ‘ይህ ወንጌል’ የሚናገረው፣ ወደፊት ስለሚመጣ መንግሥት ሳይሆን በምድር ላይ መግዛት ስለጀመረው መሲሐዊ መንግሥት እንደሆነ በዚያን ጊዜ ተገነዘቡ።”

15. ከ1920 ጀምሮ የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ የመጣው እንዴት ነው?

15 በ1920 የነበሩት “አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ምሥክሮች” ጥቂት እንደሆኑ አልቀሩም። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል አባላት የሆኑት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ማንነታቸው ታወቀና እነርሱን መሰብሰብ ተጀመረ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) በአሁኑ ጊዜ በ235 አገሮች ውስጥ ወደ 6,613,829 የሚጠጉ ምሥራቹን የሚያውጁ ሰዎች አሉ። ትንቢቱ በአስደናቂ ሁኔታ ፍጻሜውን እያገኘ ነው! ከዚህ በፊት “ይህ የመንግሥት ወንጌል” እንዲህ ባለ ስፋት ተሰብኮ አያውቅም። ከዚህም በላይ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በምድር ላይ ኖረው አያውቁም።

16. ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ምን ተከናውኗል? (ከገጽ 27-30 የሚገኘውን ሰንጠረዥ ተመልከት።)

16 እነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአጠቃላይ በ2005 የአገልግሎት ዓመት በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል። ምሥራቹ በ235 አገሮች ከአንድ ቢሊዮን ለሚበልጥ ሰዓት ተሰብኳል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመላልሶ መጠየቆች ተደርገዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥናቶችም ተመርተዋል። ይህንን ሁሉ ሥራ ያከናወኑት፣ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን ሰውተው የአምላክን ቃል ያለ ምንም ክፍያ ለሌሎች የሚያስተምሩት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። (ማቴዎስ 10:8) ይሖዋ ኃያል በሆነው ቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት፣ ለአገልጋዮቹ ፈቃዱን መፈጸም የሚያስችላቸውን ብርታት መስጠቱን ቀጥሏል።​—⁠ዘካርያስ 4:6

ምሥክርነት ለመስጠት በትጋት መሥራት

17. የይሖዋ ሕዝቦች ኢየሱስ ምሥራቹን ስለመስበክ የሰጠውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ያሉት እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ምሥራቹ እንደሚሰበክ ከተናገረ 2, 000 የሚያህሉ ዓመታት ቢያልፉም የአምላክ ሕዝቦች ለሥራው ያላቸው ቅንዓት አልቀነሰም። በጽናት በጎ የሆነውን ነገር ስናደርግ የይሖዋን ፍቅር፣ ምህረትና ትዕግሥት እያንጸባረቅን እንደሆነ እናውቃለን። ልክ እንደ ይሖዋ ሰዎች ለንስሐ እንዲበቁና ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ እንጂ ማንም እንዲጠፋ አንሻም። (2 ቆሮንቶስ 5:18-20፤ 2 ጴጥሮስ 3:9) በመንፈስ የጋሉት የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም ምሥራቹን በቅንዓት ማወጃቸውን ቀጥለዋል። (ሮሜ 12:11) በዚህ ምክንያት በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች እውነትን ተቀብለው የይሖዋን ፍቅራዊ መመሪያ እየተከተሉ ነው። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

18, 19. ምሥራቹን በደስታ ስለተቀበሉ ሰዎች የሚገልጹ ተሞክሮዎች ተናገር።

18 ቻርልስ በምዕራብ ኬንያ የሚኖር ገበሬ ነው። በ1998 ከ8, 000 ኪሎ ግራም የሚበልጥ የትምባሆ ተክል በመሸጡ፣ ምርጥ የትምባሆ አምራች የሚል የምሥክር ወረቀት ተሸለመ። በዚያው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ትምባሆ የሚያመርት ሰው ኢየሱስ ጎረቤትን መውደድ እንደሚገባ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር የሚጋጭ ድርጊት እየፈጸመ እንደሆነ ተገነዘበ። (ማቴዎስ 22:39) ከዚያም ‘ምርጥ የትምባሆ አምራች ገበሬ’ በእርግጥም ‘ምርጥ ነፍሰ ገዳይ’ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ የትምባሆ እርሻውን መርዝ ረጭቶ አወደመው። ቻርልስ እድገት አድርጎ ራሱን በመወሰን ተጠመቀ፤ ይህ ሰው በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚና የጉባኤ አገልጋይ ነው።

19 ይሖዋ በዓለም ዙሪያ እየተሰጠ ባለው ምሥክርነት አማካኝነት ሕዝቦችን እያናወጠ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፤ በዚህም ምክንያት የተመረጡ ዕቃዎች ማለትም ሰዎች ወደ ቤቱ በመምጣት ላይ ናቸው። (ሐጌ 2:7 የ1954 ትርጉም ) በፖርቹጋል የሚኖረው ፔትሩ የ13 ዓመት ልጅ እያለ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገባ። ግቡ ሚስዮናዊ መሆንና መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ነበር። ነገር ግን በትምህርት ክፍለ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሰው አልፎ አልፎ ብቻ ስለነበር ከጥቂት ቆይታ በኋላ ትምህርት ቤቱን ለቀቀ። ከስድስት ዓመት በኋላ ሊዝበን በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ትምህርት መከታተል ጀመረ። ይኖር የነበረው የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው አክስቱ ጋር በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና አበረታታችው። በዚያን ጊዜ ፔትሩ አምላክ መኖሩን ይጠራጠር የነበረ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይኑርበት አይኑርበት መወሰን አልቻለም። ከዚያም የሥነ ልቦና መምህሩ የሆነውን ፕሮፌሰር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ስላለመቻል አነጋገረው። ፕሮፌሰሩም እንደ ሥነ ልቦና ትምህርት ከሆነ ውሳኔ ማድረግ የሚያቅታቸው ሰዎች ራሳቸውን ይጎዳሉ አለው። በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰነ። ፔትሩ በቅርቡ የተጠመቀ ሲሆን እርሱ ራሱ ሌሎች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀምሯል።

20. ምሥክርነቱ በስፋት እየተሰጠ መሆኑ የሚያስደስተን ለምንድን ነው?

20 ምሥራቹ ምን ያህል እንደሚሰበክ እንዲሁም መጨረሻው የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት አሁንም ቢሆን አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ይህ ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ብቻ ነው። እንዲህ ባለ ስፋት ምሥራቹ መሰበኩ፣ ሰብዓዊ አገዛዝ በአምላክ መንግሥት የሚተካበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ከሚያሳዩት ምልክቶች አንዱ መሆኑን ስናውቅ ደስ ይለናል። (ዳንኤል 2:44) በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል፤ ይህ ደግሞ አምላካችንን ይሖዋን ያስከብረዋል። ታማኝነታችንን እንደያዝን ለመቀጠልና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ወንድሞቻችን ጋር እያከናወንን ያለነውን ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ላለማቋረጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ በማድረግ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:16

ታስታውሳለህ?

በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኙት ቃላት አስደናቂ የሆኑት ለምንድን ነው?

• የጥንት ክርስቲያኖች የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ምን ጥረት አድርገዋል? ምን ውጤትስ አገኙ?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክርነት የመስጠቱን አስፈላጊነት የተገነዘቡት እንዴት ነበር?

• ባለፈው የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ሕዝቦች ያደረጉትን እንቅስቃሴ ስትመረምር ያስገረመህ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 27-30 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2005 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

ጳውሎስ ምስራቹን ለመስበክ በየብስና በባሕር ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዟል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ፣ ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ እንዲመሰክር ይሖዋ መርቶታል