በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ ብልጽግና

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ ብልጽግና

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ ብልጽግና

የልጆች አባት የሆነ ዳዊት a የተባለ አንድ ክርስቲያን፣ ያደረገው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ በመተማመን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደ። ምንም እንኳን ባለቤቱንና ልጆቹን ጥሎ በመሄዱ ቅር ቢለውም ሊያልፍላቸው የሚችለው ሠርቶ ተጨማሪ ገንዘብ ካገኘ ብቻ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። በመሆኑም ዘመዶቹ ወደ ኒው ዮርክ እንዲመጣ ያቀረቡለትን ግብዣ ተቀበሎ ሄደና ብዙም ሳይቆይ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ።

ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ዳዊት የነበረው የመተማመን ስሜት እየከሰመ መጣ። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ጊዜ ያጥረው ጀመር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአምላክ ላይ ያለውን እምነት ጨርሶ እስከማጣት ደርሶ ነበር። በሥነ ምግባር ፈተና ውስጥ እስኪወድቅ ድረስ ያለበትን ሁኔታ ማስተዋል ተስኖት ነበር። በቁሳዊ ብልጽግና ላይ ማተኮሩ በሕይወቱ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ቀስ በቀስ ገሸሽ ወደ ማድረግ መርቶታል። በመሆኑም ማስተካከያዎችን ማድረግ ነበረበት።

እንደ ዳዊት ሁሉ በድሃ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ያልፍልናል በሚል ተስፋ በየዓመቱ ወደ ሌሎች አገሮች ይሰደዳሉ። ያም ሆኖ ሁሉም ለማለት ይቻላል አብዛኛውን ጊዜ እጅግ አስከፊ ለሆነ መንፈሳዊ ውድቀት ይዳረጋሉ። ስለሆነም አንዳንዶች፣ ‘አንድ ክርስቲያን ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት እየጣረ በአምላክ ዘንድ ሀብታም ለመሆን ይችላል?’ በማለት ይጠይቃሉ። የታወቁ ጸሐፊዎችና የሃይማኖት መሪዎች እንደሚቻል ይናገራሉ። ሆኖም ዳዊትም ሆነ ሌሎች ሰዎች በተሞክሮ እንደተማሩት አንዱን መሥዋዕት ሳያደርጉ ሌላውን ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።​—⁠ሉቃስ 18:24

ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም

እርግጥ ነው፣ ገንዘብ የሰው ልጆች የፈጠራ ውጤት ነው። እንደ ሌሎቹ መልካም የፈጠራ ሥራዎች ሁሉ ገንዘብም በራሱ መጥፎ ወይም እርኩስ አይደለም። መገበያያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳም የለውም። ስለሆነም በአግባቡ ለተጠቀመበት ሰው ጥሩ አገልግሎት ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ከድህነት ጋር ተያያዥነት ላላቸው ችግሮች “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 7:​12) እንዲያውም ለአንዳንዶች ‘ገንዘብ ካለ ሁሉ ነገር እንዳለ’ ያህል ነው።​—⁠መክብብ 10:19

መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናን ያወግዛል፤ ጠንክሮ መሥራትን ደግሞ ያበረታታል። ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ማቅረብ የሚኖርብን ሲሆን ትንሽ ተረፍ ሲለን ደግሞ ‘ለተቸገሩት የምናካፍለው ነገር ይኖረናል።’ (ኤፌሶን 4:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የመናኝ ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ሳይሆን ባሉን ነገሮች እንድንደሰት ያበረታታል። እንዲሁም ‘እድል ፋንታችንን’ ወይም ድርሻችንን ‘እንድንወስድና’ በድካማችን ደስ እንዲለን ይመክረናል። (መክብብ 5:​18-​20 የ1954 ትርጉም ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሀብት ቢኖራቸውም እንኳ ታማኝ ስለነበሩ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል።

ሀብታም የነበሩ ታማኝ ሰዎች

የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው አብርሃም ብዙ የከብት መንጋ፣ ብርና ወርቅ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤት ውስጥ አገልጋዮች ነበሩት። (ዘፍጥረት 12:5፤ 13:2, 6, 7) ጻድቁ ኢዮብም በርካታ ከብቶች፣ አገልጋዮች እንዲሁም ወርቅና ብር ያሉት ባለጸጋ ሰው ነበር። (ኢዮብ 1:3፤ 42:11, 12) እነዚህ ሰዎች በአሁን ጊዜ ባለው ደረጃም ሀብታሞች የሚባሉ ሲሆን በአምላክም ዘንድ ቢሆን ሀብታም ነበሩ።

ሐዋርያው ጳውሎስ አብርሃምን ‘የሚያምኑ ሁሉ አባት’ ሲል ጠርቶታል። አብርሃም ንፉግ አሊያም ገንዘብ የሚወድ አልነበረም። (ሮሜ 4:​11፤ ዘፍጥረት 13:9፤ 18:⁠1-⁠8) በተመሳሳይም ኢዮብ ‘ነቀፋ የሌለበትና ቅን’ መሆኑን አምላክ ራሱ መስክሮለታል። (ኢዮብ 1:8) የተቸገሩና የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነበር። (ኢዮብ 29:12-​16) አብርሃምም ሆነ ኢዮብ ይታመኑ የነበረው ባላቸው ሀብት ሳይሆን በይሖዋ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 14:22-​24፤ ኢዮብ 1:​21, 22፤ ሮሜ 4:​9-​12

ሌላው ምሳሌ ደግሞ ንጉሥ ሰሎሞን ነው። በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአምላክ ዙፋን ወራሽ እንደመሆኑ መጠን አምላካዊ ጥበብን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ብልጽግናን እና ክብርን በማግኘት ተባርኳል። (1 ነገሥት 3:​4-​14) አብዛኛውን ዕድሜውን ታማኝ ሆኖ ኖሯል። ይሁንና በሸመገለ ጊዜ “ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።” (1 ነገሥት 11:1-8) የሰሎሞን አሳዛኝ የሕይወት ተሞክሮ ቁሳዊ ብልጽግና ሊያስከትል የሚችላቸውን አንዳንድ ችግሮች ይጠቁመናል። ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ተመልከት።

ቁሳዊ ብልጽግና ያሉት አደጋዎች

ከሁሉም በላይ አስከፊ የሆነው አደጋ ገንዘብንና ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮችን ማፍቀር መጀመር ነው። ሀብት በአንዳንዶች ላይ ፍጹም የማይረካ ፍላጎት ያሳድርባቸዋል። በግዛቱ የመጀመሪያ ዓመታት ሰሎሞን ይህን ዓይነት ዝንባሌ በሌሎች ላይ አስተውሎ ስለነበር እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም፤ ይህም ከንቱ ነው።” (መክብብ 5:​10) ቆየት ብሎም ኢየሱስና ጳውሎስ እንዲህ ስላለው አሳሳች የገንዘብ ፍቅር ክርስቲያኖችን አስጠንቅቀዋል።​—⁠ማርቆስ 4:​18, 19፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:2

ገንዘብ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የሚያስችል መሣሪያ ብቻ እንደሆነ አድርገን ከመመልከት ይልቅ ለእርሱ ፍቅር ካደረብን መዋሸትን፣ ስርቆትንና ክህደትን ጨምሮ ለሌሎች በርካታ የሥነ ምግባር ፈተናዎች እንጋለጣለን። የክርስቶስ ሐዋርያ የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታውን አሳልፎ የሰጠው ለ30 ብር ብሎ ነበር። (ማርቆስ 14:11፤ ዮሐንስ 12:6) አንዳንድ ሰዎች ለአምላክ ከማደር ይልቅ በገንዘብ በመተማመን ከዚህ የከፋ ነገር ፈጽመዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​10) ስለሆነም ክርስቲያኖች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት የፈለጉበትን ዋነኛ ምክንያት ለማወቅ ዘወትር ራሳቸውን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርባቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 13:5

ሀብትን ማሳደድ ረቀቅ ላሉ ሌሎች አደጋዎችም ሊያጋልጥ ይችላል። በመጀመሪያ፣ እጅግ ባለጸጋ መሆን በራስ ወደ መመካት ሊመራ ይችላል። ኢየሱስ ‘ብልጽግና ስላለው የማታለል’ ኃይል በተናገረ ጊዜ ይህንንም ገልጿል። (ማቴዎስ 13:22) በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ክርስቲያኖች ለመነገድ ሲያስቡ እንኳን አምላክን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው አሳስቧል። (ያዕቆብ 4:​13-​16) ገንዘብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የፈለግነውን የማድረግ ነፃነት ስለሚሰጥ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከአምላክ ይልቅ በገንዘባቸው የመታመን አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል።​—⁠ምሳሌ 30:​7-9፤ የሐዋርያት ሥራ 8:​18-​24

በሁለተኛ ደረጃ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳዊት አጋጥሞት እንደነበረው ሀብትን ማሳደድ ብዙውን ጊዜ የአንድን ሰው ጊዜና ጉልበት በማሟጠጥ ከመንፈሳዊ ነገሮች ቀስ በቀስ እንዲርቅ ያደርገዋል። (ሉቃስ 12:​13-​21) ከዚህም በላይ ሀብታም የሆኑ ሰዎች ሀብታቸውን በዋነኝነት ለመዝናናት አሊያም የግል ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ብቻ እንዲጠቀሙበት ዘወትር ይፈተናሉ።

ለሰሎሞን መንፈሳዊ ውድቀት አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል የቅንጦት አኗኗሩ ልቡን እንዲያዝለው መፍቀዱ ይገኝበት ይሆን? (ሉቃስ 21:34) ሰሎሞን፣ አምላክ ከባዕድ አገር ሕዝቦች ጋር እንዳይጋቡ መከልከሉን ያውቅ ነበር። ይሁንና አንድ ሺህ የሚያህሉ ሴቶችን ሰበሰበ። (ዘዳግም 7:3) ከባዕድ አገር ያመጣቸውን ሚስቶቹን ለማስደሰትና እነርሱን ለመጥቀም ሲል ሃይማኖትን ለመቀላቀል ሞከረ። ቀደም ሲል እንዳየነው የሰሎሞን ልብ ቀስ በቀስ ከይሖዋ ራቀ።

እነዚህ ምሳሌዎች ኢየሱስ “እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም” ሲል የሰጠው ምክር እውነት መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 6:24) ታዲያ አንድ ክርስቲያን ዛሬ ብዙዎችን የሚጫነውን የኢኮኖሚ ችግር በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ ለወደፊቱ ጊዜ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ምን ተስፋ አለ?

ወደፊት የሚኖረው እውነተኛ ብልጽግና

የእምነት አባቶች ከሆኑት ከአብርሃምና ከኢዮብ እንዲሁም ከእስራኤል ብሔር በተለየ መልኩ የኢየሱስ ተከታዮች ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህን ተልእኮ መወጣት ደግሞ ሥጋዊ ነገሮችን በማሳደድ በቀላሉ ልናባክን የምንችለውን ጊዜና ጥረት መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። ስለሆነም ስኬታማነታችን የተመካው ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረጋችን ላይ ነው።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

ዳዊት ቤተሰቡንና መንፈሳዊነቱን ለማጣት ጥቂት ቀርቶት የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ስህተቱን አርሞ ሕይወቱን ማስተካከል ችሏል። ልክ ኢየሱስ ቃል እንደገባው፣ ዳዊት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና፣ ሲጸልይና ለአገልግሎቱ ቅድሚያ ሲሰጥ ሕይወቱ መሻሻል ጀመረ። ውሎ አድሮ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ታደሰ። ደስታውና እርካታውም ተመለሰለት። ዳዊት አሁንም ቢሆን በትጋት ይሠራል። ከበርቴ መሆን ባይችልም እንኳ ካሳለፈው ተሞክሮ ጥሩ ትምህርት አግኝቷል።

ዳዊት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ መወሰኑ ጥበብ የጎደለው እንደነበረ ይሰማዋል፤ ከዚህ በኋላም ቢሆን ገንዘብ፣ በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድርበት ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። በሕይወት ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች ይኸውም አፍቃሪ ቤተሰብ፣ ጥሩ ጓደኞችና ከአምላክ ጋር የሚመሠረት ወዳጅነት ገንዘብ ሊገዛቸው እንደማይችል ተገንዝቧል። (ምሳሌ 17:17፤ 24:27፤ ኢሳይያስ 55:​1, 2) እርግጥ ነው፣ ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም ከቁሳዊ ሀብት እጅግ የላቀ ነው። (ምሳሌ 19:1፤ 22:1) ዳዊትና ቤተሰቡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​10

ሰዎች የበለጸገና ንጹሕ ሥነ ምግባር የተላበሰ ማኅበረሰብ ለማቋቋም ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉንን ቁሳዊም ሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልን ቃል ገብቶልናል። (መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 65:21-​23) ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻችን ንቁ ስንሆን እንደሆነ አስተምሯል። (ማቴዎስ 5:3) በመሆኑም በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሀብታምም እንሁን ድሃ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ አምላክ ከፊታችን ለዘረጋው አዲስ ዓለም ራሳችንን ማዘጋጀት እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:​17-​19) በመጪው አዲስ ዓለም በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ የበለጸገ ፈሪሃ አምላክ ያደረበት ኅብረተሰብ ይመሠረታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተቀይሯል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ በሀብቱ ሳይሆን በይሖዋ ታምኗል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕይወት ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸውን ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው አይችልም