በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

በዕዝራ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ የተዘገበው ታሪክ ከተፈጸመ አሥራ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። በመሲሑ መምጣት የሚደመደመው የሰባው ሱባዔ የመጀመሪያ ክንውን ማለትም ‘ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን አዋጅ የሚወጣበት’ ጊዜ ተቃርቧል። (ዳንኤል 9:​24-​27) የነህምያ መጽሐፍ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና በመገንባቱ ሥራ ላይ የተካፈሉትን የአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ይዘግባል። መጽሐፉ ከ456 እስከ 443 ከክርስቶስ ልደት በፊት ትንሽ አለፍ ብሎ ያሉትን ወሳኝ የሆኑ ከ12 የሚበልጡ ዓመታት ታሪክ ያቀፈ ነው።

በአገረ ገዥው በነህምያ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በይሖዋ አምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እውነተኛውን አምልኮ ከፍ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አስደሳች ዘገባ ይዟል። ይሖዋ ፈቃዱን ከግብ ለማድረስ ነገሮችን እንዴት እንደሚያስፈጽም በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም አንድ ጠንካራና ደፋር የሆነ መሪ ያሳለፈውን ታሪክ ይዘግባል። “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ” ስለሆነ የነህምያ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ጠቃሚ ትምህርት ይዟል።​—⁠ዕብራውያን 4:12

‘ቅጥሩ ተጠናቀቀ’

(ከነህምያ 1:1 እስከ 6:​19)

በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኘው ነህምያ በሱሳ ግንብ ሆኖ ንጉሥ አርጤክስስ ሎንጊማነስን እያገለገለ ነው። ነህምያ፣ ሕዝቦቹ ‘በታላቅ መከራና ውርደት ላይ እንደሚገኙ፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደፈረሰና በሮቿም በእሳት እንደተቃጠሉ’ በሰማ ጊዜ በጣም ስለተረበሸ አምላክ እንዲመራው ልባዊ ጸሎት አቀረበ። (ነህምያ 1:​3, 4) ከጊዜ በኋላ ንጉሡ በነህምያ ፊት ላይ ያጠላውን ሐዘን አስተዋለ። ይህ ደግሞ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚያስችለውን ፈቃድ እንዲያገኝ አጋጣሚ ከፈተለት።

ነህምያ ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ በሌሊት ተነስቶ የከተማዋን ቅጥር ተመለከተ። ከዚያም ለአይሁዳውያን ቅጥሩን እንደገና የመሥራት እቅድ እንዳለው ነገራቸው። የመልሶ ግንባታውም ሥራ እንደተጀመረ ተቃውሞ ተነሳ። ሆኖም በነህምያ ቆራጥ አመራር ‘ቅጥሩ ሊጠናቀቅ’ ቻለ።​—⁠ነህምያ 6:​15

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው ፦

1:1፤ 2:1—⁠በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ የሚገኘው “ሃያኛው ዓመት” የተሰላው ከተመሳሳይ ጊዜ ተነስቶ ነው? አዎን፣ 20ኛው ዓመት የሚያመለክተው የንጉሥ አርጤክስስን ሃያኛ የግዛት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው የአቆጣጠር ስልት የተለያየ ነው። ታሪካዊ መረጃ እንደሚጠቁመን አርጤክስስ ዙፋኑን የያዘው በ475 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ባቢሎናውያን ጸሐፍት የፋርሳውያን ነገሥታትን የግዛት ዘመን የሚቆጥሩት ከኒሳን (መጋቢት/ሚያዝያ) እስከ ኒሳን ድረስ ስለነበር የአርጤክስስ የግዛት ዘመን (regnal year) የጀመረው በኒሳን ወር በ474 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ በነህምያ 2:​1 ላይ የተጠቀሰው ሃያኛ የግዛት ዘመን የሚጀምረው በኒሳን ወር በ455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሆናል። በነህምያ 1:​1 ላይ የተጠቀሰው የካሴሉ ወር (ኅዳር/ታኅሣሥ) የሚያመለክተው ያለፈውን ዓመት ማለትም የ456ን ካሴሉ መሆን አለበት። ሆኖም ነህምያ ይህን ወር የጠቀሰው በአርጤክስስ 20ኛው ዓመት የግዛት ዘመን ላይ እንዳረፈ አድርጎ ነው። በዚህ ጊዜ ዓመታቱን ያሰላው ንጉሡ ወደ ሥልጣን ከወጣበት ቀን (accession date) ተነስቶ ሊሆን ይችላል። አሊያም ነህምያ በአይሁዳውያን አቆጣጠር በመጠቀም ከትሽሪ ወር (መስከረም/ጥቅምት) ተነስቶ አስልቶት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሩሳሌምን መልሶ ለመገንባት አዋጅ የወጣው በ455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው።

4:​17, 18—⁠በመልሶ ግንባታው ላይ የተሠማራ አንድ ሰው በአንድ እጁ መሥራት የሚችለው እንዴት ነው? ለዕቃ ተሸካሚዎች ያን ያህል አስቸጋሪ አልነበረም። ዕቃውን በራሳቸው ወይም በትከሻቸው ላይ ከተሸከሙት በኋላ በአንድ እጃቸው ደግፈው “በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን [ይይዙ] ነበር።” ግንበኞቹ ግን ሁለቱንም እጃቸውን መጠቀም ስለሚያስፈልጋቸው እያንዳንዱ ግንበኛ “ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር።” ስለዚህ ከጠላት ጥቃት ቢሰነዘር እንኳ ለመመከት ዝግጁ ነበሩ።

5:​7—⁠ነህምያ ‘መኳንንቱንና ሹማምንቱን የገሠጻቸው’ ለምን ነበር? እነዚህ ሰዎች የሙሴን ሕግ በመጣስ ከአይሁዳውያን ወንድሞቻቸው አራጣ ይበሉ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:36፤ ዘዳግም 23:19) ከዚህም በላይ አራጣ አበዳሪዎቹ የሚጠይቁት ወለድ ከፍተኛ ነበር። በወር “አንድ መቶኛ” ወለድ ይቀበሉ ከነበረ በዓመት 12 በመቶ ይሆናል። (ነህምያ 5:11) ከባድ ቀረጥ በተጫናቸውና የምግብ እጥረት ባጎሳቆላቸው ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነቱን ሸክም መጨመር የጭካኔ ድርጊት ነው። ስለዚህ ነህምያ የአምላክን ሕግ ተጠቅሞ ሀብታሞቹን አይሁዳውያን ገሥጿቸዋል።

6:​5—⁠ምስጢራዊ ደብዳቤዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚላኩት ታሽገው ሆነው ሳለ ሰንባላጥ ለነህምያ “ያልታሸገ ደብዳቤ” የላከው ለምንድን ነው? ሰንባላጥ ደብዳቤውን ሳያሽግ የላከው በውስጡ የሰፈሩት የሐሰት ክሶች በሕዝቡ ዘንድ እንዲታወቁ ስለፈለገ ይሆናል። ምናልባትም ነህምያ በጉዳዩ በጣም ተናድዶ የግንባታውን ሥራ በማቆም ሄዶ ሙግት እንዲገጥመው አስቦ ሊሆን ይችላል። አሊያም አይሁዳውያን ወሬውን አምነው በመቀበል ሥራውን ከናካቴው ያቆማሉ ብሎ አስቦ ይሆናል። ይሁንና ነህምያ የእርሱን ማስፈራሪያ ወደ ጎን በመተው ከአምላክ የተሰጠውን ሥራ በተረጋጋ መንፈስ መሥራቱን ቀጥሏል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:​4፤ 2:​4፤ 4:​4, 5 አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አሊያም ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ስናደርግ ‘በጸሎት መጽናትና’ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ መከተል ይገባናል።​—⁠ሮሜ 12:12

1:⁠11–​2:​8፤ 4:​4, 5, 15, 16፤ 6:​16 ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት ይሰማል።​—⁠መዝሙር 86:​6, 7

1:​4፤ 4:​19, 20፤ 6:​3, 15 ነህምያ ርኅሩኅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ለጽድቅ ሲባል ቁርጥ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።

1:⁠11–​2:​3 ለነህምያ ዋነኛ የደስታ ምንጭ የሆነለት በጠጅ አሳላፊነት ያገኘው ከፍተኛ ሥልጣን ሳይሆን የእውነተኛው አምልኮ መስፋፋት ነበር። በዋነኝነት ሊያሳስቡንና የደስታ ምንጭ ሊሆኑልን የሚገቡት የይሖዋ አምልኮና ይህን አምልኮ ለማስፋፋት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች መሆን አይኖርባቸውም?

2:​4-8 ይሖዋ፣ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ቅጥሯን እንደገና እንዲገነባ የሚያስችለውን ፈቃድ እንዲያገኝ የአርጤክስስን ልብ አነሳስቷል። ምሳሌ 21:​1 “የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል” ይላል።

3:​5, 27 የቴቁሐ ‘መኳንንቶች’ እንደተሰማቸው እኛም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ብለን የጉልበት ሥራ ብንሠራ ክብራችን እንደሚነካ ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን ተራ ቴቁሐውያን መምሰል እንችላለን።

3:​10, 23, 28-​30 አንዳንዶች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ማገልገል ቢችሉም አብዛኞቻችን ባለንበት አካባቢ እውነተኛውን አምልኮ እንደግፋለን። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ በመሳተፍም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ለተጠቁ ሰዎች እርዳታ በመስጠት ድጋፋችንን ማሳየት ብንችልም እውነተኛውን አምልኮ የምናስፋፋበት ዋነኛው መንገድ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ላይ መካፈላችን ነው።

4:​14 ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ እኛም “ታላቁንና የተፈራውን” በማሰብ ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን።

5:​14-​19 ትሑትና ጠንቃቃ በመሆን እንዲሁም የራስን ጥቅም ባለማስቀደም ረገድ ነህምያ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። የአምላክን ሕግ በቅንዓት ያስከበረ ቢሆንም እንኳ ለግል ጥቅሙ ሲል ሌሎችን አልጨቆነም። ከዚህ በተቃራኒ ለተጨቆኑትና ለድሆች ይቆረቆር ነበር። ነህምያ ለጋስ በመሆን ረገድ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የላቀ ምሳሌ ትቷል።

“አምላኬ ሆይ፤ በቸርነት አስበኝ”

(ከነህምያ 7:​1 እስከ 13:​31)

ነህምያ የኢየሩሳሌም ቅጥር ተሠርቶ እንዳለቀ መዝጊያዎቹን ገጠመ። ከዚያም የከተማዋን ደኅንነት ለመ​ጠበቅ አንዳንድ ዝግጅቶችን አደረገ። ቀጥሎም የሕዝቡን የትውልድ ሐረግ መመዝገብ ጀመረ። ካህኑ ዕዝራ “ ‘ከውሃ በር’ ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ” ለተሰበሰበው ሕዝብ የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ያነበበላቸው ሲሆን ነህምያና ሌዋውያን ደግሞ ሕጉን አስረዷቸው። (ነህምያ 8:1) ሕዝቡ ስለ ዳስ በዓል ያገኘው እውቀት በዓሉን በደስታ እንዲያከብር አድርጎታል።

ሌላ ስብሰባ ተደርጎ “የእስራኤላውያን ዘር የሆኑት” የሕዝባቸውን ኃጢአት የተናዘዙ ሲሆን ሌዋውያኑ ደግሞ አምላክ ከእስራኤል ጋር ስለነበረው ግንኙነት ከለሱላቸው። ከዚያም ሕዝቡ ‘የእግዚአብሔርን ሕግ ለመታዘዝ’ ቃለ መሐላ ፈጸመ። (ነህምያ 9:​1, 2፤ 10:​29) ሆኖም በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ሰዎች አነስተኛ ከመሆናቸው የተነሳ ከከተማዋ ውጪ ከሚኖሩት 10 ወንዶች መካከል አንዱ መኖሪያውን በኢየሩሳሌም እንዲያደርግ ዕጣ ተጣጣሉ። ከዚያም ቅጥሩ ሲመረቅ “በኢየሩሳሌም የነበረው የደስታ ድምፅ እስከ ሩቅ ድረስ ይሰማ ነበር።” (ነህምያ 12:43) ነህምያ ኢየሩሳሌም ከደረሰ ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላ የቀድሞ ሥራውን ለማከናወን ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ተመለሰ። ወዲያውኑም ርኩሰት ወደ አይሁዳውያን ሰርጎ መግባት ጀመረ። ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ሁኔታውን ለማስተካከል ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። ስለ ራሱ ደግሞ “አምላኬ ሆይ፤ በቸርነት አስበኝ” በማለት በትሕትና ጸሎት አቅርቧል።​—⁠ነህምያ 13:31

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው ፦

7:​6-​67—⁠ነህምያ፣ ከዘሩባቤል ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ስለተመለሱ አይሁዳውያን ቀሪዎች ያሰፈረው የአንዳንድ ቤተሰቦች ቁጥር ዕዝራ ከዘገበው የሚለየው ለምንድን ነው? (ዕዝራ 2:​1-​65) ልዩነቱ የተፈጠረበት አንደኛው ምክንያት ዕዝራና ነህምያ የተለያየ ምንጭ ስለተጠቀሙ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል:- ወደ ኢየሩሳሌም እንመለሳለን ብለው የተመዘገቡት አይሁዳውያን ቁጥር በእርግጥ ከተመለሱት ግዞተኞች ቁጥር ሊለይ ይችላል። ሁለቱ ዘገባዎች የተለያዩበት ሌላው ምክንያት ደግሞ መጀመሪያ ላይ ትክክለኛ የትውልድ ሐረጋቸውን መለየት ያልቻሉ አይሁዳውያን በኋላ ላይ አስተካክለው በመናገራቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሁለቱም ዘገባዎች በአንድ ነገር ይስማማሉ:- ከአገልጋዮቹና ከመዘምራኖቹ ውጪ መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሰዎች ቁጥር 42, 360 ነበር።

10:​34—⁠ሕዝቡ እንጨት ማቅረብ የነበረበት ለምንድን ነው? የሙሴ ሕግ ሕዝቡ የእንጨት መሥዋዕት እንዲያቀርብ አያዝም። እንዲህ ለማድረግ የተገደዱት በወቅቱ በቂ የእንጨት አቅርቦት ስላልነበረ ነው። በመሠዊያው ላይ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ለማቃጠል በጣም ብዙ እንጨት ያስፈልግ ነበር። ምናልባትም ናታኒም ተብለው የሚጠሩት እስራኤላዊ ያልሆኑ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በበቂ መጠን አልነበሩ ይሆናል። ስለዚህ የእንጨት አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚያመጡበትን ጊዜ ለመወሰን ዕጣ ተጣጣሉ።

13:​6—⁠ነህምያ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “በቀናት መጨረሻ ላይ” ንጉሡን ፈቃድ እንደጠየቀ ብቻ ነው። ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ መገመት አይቻልም። ይሁንና ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ሕዝቡ ለክህነት አገልግሎት ድጋፍ እንደማያደርግ እንዲሁም የሰንበት ሕግ እንደማይከበር ተመለከተ። ብዙ አይሁዳውያን እስራኤላዊ ያልሆኑ ሚስቶችን ያገቡ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ልጆቻቸው የአይሁዳውያንን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር። ሁኔታዎች የዚህን ያህል መበላሸታቸው ነህምያ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቶ መሆን እንዳለበት ይጠቁማል።

13:​25, 28—⁠ነህምያ ወደ ኃጢአት የተመለሱትን አይሁዳውያን ‘ከመገሠጽ’ በተጨማሪ ምን ሌሎች እርምጃዎችን ወስዷል? ነህምያ ‘ርግማን ያወረደባቸው’ ሲሆን ይህም በአምላክ ሕግ ውስጥ የሰፈሩትን የፍርድ ቃላት እንደነገራቸው ያሳያል። ‘አንዳንዶቹን የመታቸው’ ደግሞ እንዲገረፉ የፍርድ ውሳኔ በማስተላለፍ ሊሆን ይችላል። ለሥነ ምግባር አቋም ከመቆርቆሩ የተነሳ ‘ጠጉራቸውን ነጭቷል።’ በተጨማሪም ነህምያ፣ የሖሮናዊውን የሰንባላጥን ልጅ ያገባውን የሊቀ ካህኑን የኤልያሴብን የልጅ ልጅ አባሮታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

8:​8 የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ቃላቶችን በትክክል በመጥራት፣ ነጥቦችን በማጉላት፣ ጥቅሶችን በትክክል በማብራራትና እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችሉ በመግለጽ ሰዎች ትምህርቱን ‘እንዲረዱ’ ማድረግ እንችላለን።

8:​10 አንድ ሰው ‘የይሖዋን ደስታ’ ማግኘት ከፈለገ መንፈሳዊ ረሃብ እንዳለበት አውቆ ፍላጎቱን ማርካትና ቲኦክራሲያዊውን አመራር መከተል አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናታችን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በቅንዓት መካፈላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

11:​2 አንድ እስራኤላዊ ውርሱን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት የግል ወጪዎችን ማድረግና አንዳንድ ጥቅሞችን መተው ይጠይቅበት ነበር። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑት ሰዎች የግል ጥቅምን የመሠዋት መንፈስ አሳይተዋል። እኛም በአውራጃ ስብሰባዎችና በተለያዩ ጊዜያት ሌሎችን በፈቃደኝነት ለማገልገል የሚያስችሉን አጋጣሚዎች ሲከፈቱልን እንዲህ ዓይነቱን መንፈስ ማሳየት እንችላለን።

12:​31, 38, 40-​42 መዝሙር ይሖዋን እንድናወድስና አመስጋኝነታችንን እንድንገልጽ የሚያስችለን ግሩም መንገድ ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ ልባችን መዘመር ይገባናል።

13:​4-​31 ፍቅረ ንዋይ፣ ምግባረ ብልሹነትና ክህደት እንዳይጠናወቱን መጠንቀቅ ይኖርብናል።

13:​22 ነህምያ በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆኑን ያውቅ ነበር። እኛም በይሖዋ ፊት ተጠያቂ መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም።

የይሖዋን ሞገስ ማግኘት አስፈላጊ ነው!

መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 127:1) የነህምያ መጽሐፍ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት በጥሩ ሁኔታ ይገልጻል።

ነጥቡ ግልጽ ነው። የምናደርገው ጥረት ሁሉ እንዲሳካልን ከፈለግን የይሖዋን ሞገስ ማግኘት አለብን። ታዲያ በሕይወታችን ውስጥ ለእውነተኛው አምልኮ ቅድሚያ ሳንሰጥ ይሖዋ ይባርከናል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ስለዚህ እኛም እንደ ነህምያ በዋነኝነት ስለ ይሖዋ አምልኮና ይህን አምልኮ ስለማስፋፋት እናስብ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ እንዳለ የቦይ ውሃ ነው’

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተግባር ሰውና ርኅሩኅ የነበረው ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል እንዴት ‘ማስረዳት’ እንዳለብህ ታውቃለህ?