በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ትዕግሥት ኮርጁ

የይሖዋን ትዕግሥት ኮርጁ

የይሖዋን ትዕግሥት ኮርጁ

“ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን . . . ይታገሣል።” ​—⁠2 ጴጥሮስ 3:9

1. ይሖዋ ለሰው ልጆች ያዘጋጀው ወደር የለሽ ስጦታ ምንድን ነው?

 ይሖዋ ማንም ሊሰጠን የማይችለውን ነገር አዘጋጅቶልናል። ይህ ያዘጋጀልን ነገር በጣም አስደሳችና ውድ ከመሆኑም በላይ በገንዘብ ሊገዛ ወይም እንደ ደሞዝ ሊከፈል አይችልም። ይሖዋ ሊሰጠን ያቀደው የዘላለም ሕይወት ሲሆን በዚህ ተስፋ መሠረት አብዛኞቻችን ገነት በሆነች ምድር ላይ መጨረሻ የሌለው ሕይወት እናገኛለን። (ዮሐንስ 3:16) እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! ከዚያ በኋላ ከባድ ሐዘን የሚያስከትሉ ችግሮች ማለትም ግጭት፣ ዓመጽ፣ ድህነት፣ ወንጀል፣ በሽታ አልፎ ተርፎም ሞት አይኖሩም። ሰዎች በአምላክ መንግሥት ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ፍጹም ሰላምና አንድነት አግኝተው ይኖራሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ ምንኛ የሚናፈቅ ነው!​—⁠ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ራእይ 21:4, 5

2. ይሖዋ የሰይጣንን ዓለም እስከ አሁን ያላጠፋው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ ራሱም ቢሆን ምድርን ገነት የሚያደርግበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠብቃል። ምክንያቱም እርሱ ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድድ አምላክ ነው። (መዝሙር 33:5) ይሖዋ ለጽድቅ ሥርዓቶቹ ግድየለሽ የሆነውን ወይም ጥላቻ የሚያሳየውን እንዲሁም ሥልጣኑን የሚንቀውንና ሕዝቡን የሚያሰቃየውን ዓለም መመልከት አያስደስተውም። ክፉውን የሰይጣን ዓለም እስከ አሁን ድረስ ያላስወገደው በቂ ምክንያቶች ስላሉት ነው። እነዚህ ምክንያቶች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ውሳኔ ለማድረግ ባለው ሥልጣን ላይ ከተነሳው ጥያቄ ጋር ግንኙነት አላቸው። ይሖዋ ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲገኝ ለማድረግ፣ ዛሬ ብዙዎች የሌላቸውንና ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋንን አንድ ልዩ ባሕርይ አሳይቷል፤ ይህ ባሕርይ ትዕግሥት ነው።

3. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ትዕግሥት” ተብለው የተተረጎሙት የግሪክና የዕብራይስጥ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? (ለ) ከዚህ በኋላ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ ሦስት ጊዜ “ትዕግሥት” ተብሎ የተተረጎመ አንድ ግሪክኛ ቃል አለ። ይህ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የመንፈስ ርዝማኔ” ማለት ሲሆን ብዙ ጊዜ “መቻል” ተብሎ ተተርጉሟል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ “ትዕግሥት ማሳየት” ተብሎ ተተርጉሟል። “ትዕግሥት” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ለቁጣ የዘገዩና ቻይ መሆን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። የይሖዋ ትዕግሥት የሚጠቅመን እንዴት ነው? ይሖዋ ካሳየው ትዕግሥትና ከታማኝ አገልጋዮቹ ጽናት ምን ትምህርት እናገኛለን? የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው እንዴት ማወቅ እንችላለን? እስቲ እነዚህን ጉዳዮች እያየን እንሂድ።

የይሖዋን ትዕግሥት ማጤን

4. ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ትዕግሥት በተመለከተ ምን ጽፏል?

4 ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ትዕግሥት በተመለከተ እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:8, 9) ይሖዋ የሚታገሠው ለምን እንደሆነ ለመረዳት እዚህ ላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነጥቦች ልብ እንበል።

5. ይሖዋ ስለ ጊዜ ያለው አመለካከት በሚያደርገው ነገር ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

5 አንደኛው ነጥብ፣ ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከእኛ የተለየ መሆኑ ነው። ዘላለም ለሚኖረው ለይሖዋ አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው። ይሖዋን ጊዜ አይገታውም ወይም ጫና አይፈጥርበትም፤ እንዲሁም አንድን ችግር ለማስተካከል የሚያስፈልገውን እርምጃ ለመውሰድ አይዘገይም። ገደብ የለሽ ጥበብ ያለው ይሖዋ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ በሚጠቅም መልኩ እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛ ጊዜ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ጊዜው እስከሚደርስም በትዕግሥት ይጠብቃል። ነገር ግን እርምጃ እስከሚወስድበት ጊዜ ድረስ በአገልጋዮቹ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ሥቃይ ግድ የለውም ብለን መደምደም አይገባንም። የፍቅር ተምሳሌት የሆነው ይሖዋ ‘የምሕረትና የርኅራኄ’ አምላክ ነው። (ሉቃስ 1:78 የ1954 ትርጉም ፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ሥቃይና መከራ ለጊዜው እንዲኖር መፍቀዱ ያስከተለውን ጉዳት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይችላል።​—⁠መዝሙር 37:10

6. ስለ አምላክ ምን ብለን ማሰብ የለብንም? ለምንስ?

6 ሰዎች የሚጓጉለትን ነገር እስኪያገኙ በትዕግሥት መጠበቅ ሊከብዳቸው እንደሚችል እሙን ነው። (ምሳሌ 13:12) በመሆኑም አንድ ሰው የገባውን ቃል በፍጥነት ካልፈጸመ ሌሎች ግለሰቡ የተናገረውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው አድርገው ሊደመድሙ ይችላሉ። ስለ አምላክ እንዲህ ብሎ ማሰብ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! የአምላክን ትዕግሥት እንደ መዘግየት አድርገን የምናስብ ከሆነ፣ ጊዜ ባለፈ ቁጥር ለጥርጣሬና ለተስፋ መቁረጥ እንዳረጋለን። ይህም መንፈሳዊ ድብታ እንዲይዘን ያደርጋል። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ጴጥሮስ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ላይ የተጠቀሱት እምነት የለሽ ፌዘኞች ሊያታልሉን የሚችሉ መሆኑ ነው። እንዲህ ያሉት ሰዎች “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” በማለት ያፌዛሉ።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:4

7. የይሖዋ ትዕግሥት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ካለው ፍላጎት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

7 ከጴጥሮስ ቃላት የምናገኘው ሁለተኛው ነጥብ፣ ይሖዋ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ፍላጎት ስላለው የሚታገሥ መሆኑን ነው። ይሖዋ ከመጥፎ መንገዳቸው ለመመለስ ፈጽሞ አሻፈረኝ የሚሉትን ክፉ ሰዎች ይቀጣል። ቢሆንም አምላክ በክፉዎች ሞት አይደሰትም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ፣ ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱና በሕይወት እንዲኖሩ ይፈልጋል። (ሕዝቅኤል 33:11) በመሆኑም ይሖዋ የሚታገሥ ከመሆኑም በላይ ምሥራቹ በመላው ዓለም እንዲሰበክ አድርጓል፤ ይህ ደግሞ ሰዎች ሕይወት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።

8. ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ የያዘበት መንገድ ታጋሽ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ የጥንቱን የእስራኤል ሕዝብ የያዘበት መንገድ ምን ያህል ታጋሽ እንደሆነ ያሳያል። እስራኤላውያን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሳይታዘዙት ቢቀሩም እንኳ በትዕግሥት ይዟቸዋል። በነቢያቱ አማካኝነት እንደሚከተለው በማለት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር:- “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ።” ውጤቱስ ምን ነበር? የሚያሳዝነው እስራኤላውያን ይሖዋን “አልሰሙም።”​—⁠2 ነገሥት 17:13, 14

9. ኢየሱስ የአባቱን ዓይነት ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?

9 በመጨረሻም ይሖዋ፣ አይሁዳውያን ከአምላክ ጋር መታረቅ እንዳለባቸው ለማሳመን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የጣረውን ልጁን ላከ። ኢየሱስ የአባቱን ትዕግሥት በሚገባ አንጸባርቋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚገደል ያውቅ የነበረው ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ሐዘኑን ገልጿል:- “አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም።” (ማቴዎስ 23:37) እንዲህ ያሉ ልብ የሚነኩ ቃላት የሚወጡት ለመቅጣት አጋጣሚ ከሚፈላልግ ጨካኝ ዳኛ አንደበት ሳይሆን ታጋሽና አፍቃሪ ከሆነ ጓደኛ ነው። ኢየሱስ ልክ በሰማይ እንዳለው አባቱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና ከከባድ ፍርድ እንዲያመልጡ ይፈልግ ነበር። አንዳንዶች የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመታዘዝ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌም ላይ ከወረደው ታላቅ ፍርድ አምልጠዋል።​—⁠ሉቃስ 21:20-22

10. የይሖዋ ትዕግሥት የጠቀመን በምን መንገድ ነው?

10 የአምላክ ትዕግሥት እንዴት ያስደንቃል! የሰው ልጆች ታዛዥ ባይሆኑም እንኳ ይሖዋ እኛን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እርሱን እንዲያውቁና የመዳን ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹ ለሆኑት ክርስቲያኖች “የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደ ሆነ አስቡ” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:15) የይሖዋ ትዕግሥት መዳን የምናገኝበትን መንገድ ስለከፈተልን አመስጋኝ ልንሆን አይገባም? ይሖዋን በየዕለቱ ስናገለግለው እኛን በትዕግሥት መያዙን እንዲቀጥል መጸለይ አይገባንም?​—⁠ማቴዎስ 6:12

11. ስለ ይሖዋ ትዕግሥት መገንዘባችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

11 ይሖዋ ለምን ትዕግሥተኛ እንደሆነ መገንዘባችን፣ እርሱ የሚያስገኘውን መዳን በትዕግሥት መጠበቁን ቀላል የሚያደርግልን ከመሆኑም በላይ ቃሉን ለመፈጸም ይዘገያል ብለን ከመደምደም እንቆጠባለን። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26) የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ሳናቋርጥ ብንጸልይም ይሖዋ ለዚህ ጸሎት መልስ የሚሰጥበትን ትክክለኛ ጊዜ እንደሚያውቅ እንተማመናለን። በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከምንሰብክላቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የይሖዋን ዓይነት ትዕግሥት በማሳየት እርሱን ለመምሰል እንጥራለን። ልክ እንደ ይሖዋ፣ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡና የእኛ ዓይነት የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው እንጂ እንዲጠፉ አንፈልግም።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

ነቢያት ያሳዩት ትዕግሥት

12, 13. ነቢዩ ኢሳይያስ በያዕቆብ 5:10 ላይ የተገለጸው ዓይነት ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?

12 የይሖዋን ትዕግሥት ስናጤን ይህንን ባሕርይ ለማድነቅና ለማዳበር እንገፋፋለን። ፍጹም ያልሆነ ሰው ትዕግሥት ማሳየት ይከብደዋል፤ ቢሆንም ይህን ባሕርይ ማፍራት ይቻላል። በዚህ ረገድ ከጥንት የአምላክ አገልጋዮች ትምህርት እናገኛለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 5:10) ዛሬ በእኛ ላይ እየደረሱ ያሉትን ችግሮች ሌሎች በተሳካ ሁኔታ እንደተወጧቸው ማወቃችን የሚያጽናና ብሎም የሚያበረታታ ነው።

13 ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኢሳይያስ የተሰጠው ሥራ ትዕግሥት የሚጠይቅ ነበር። ይሖዋ ራሱ ኢሳይያስ ይህ ባሕርይ እንደሚያስፈልገው ሲጠቁመው እንዲህ ብሎታል:- “ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ ‘መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም’ ብለህ ንገራቸው። የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሮአቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሮአቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።” (ኢሳይያስ 6:9, 10) ሕዝቡ እምቢተኛ ቢሆንም እንኳን ኢሳይያስ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ቢያንስ ለ46 ዓመታት በትዕግሥት አውጆአል! ትዕግሥት፣ አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን ባይቀበሉም በስብከቱ ሥራችን እንድንጸና እኛንም ይረዳናል።

14, 15. ኤርምያስ መከራንና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?

14 በእርግጥ ነቢያት አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ መቋቋም የነበረባቸው የሰዉን ግድየለሽነት ብቻ ሳይሆን ይደርስባቸው የነበረውንም ስደት ነው። ኤርምያስ በእግር ግንድ ተጠርቋል፣ ‘በግዞት ቤት’ ታስሯል እንዲሁም በውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። (ኤርምያስ 20:2፤ 37:15፤ 38:6) ይህን ሁሉ ስደት ያደረሱበት ሊረዳቸው ይፈልግ የነበሩት ሰዎች ናቸው። ቢሆንም ኤርምያስ በሁኔታው ካለመማረሩም በላይ አጸፋውን ለመመለስ አልተነሳሳም። ለአሥርተ ዓመታት በትዕግሥት ጸንቷል።

15 ስደትና ፌዝ ኤርምያስን አፉን እንዳላዘጉት ሁሉ እኛንም ዝም አያሰኙንም። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። ኤርምያስም ተስፋ የቆረጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። “የእግዚአብሔር ቃል፣ ቀኑን ሙሉ ስድብና ነቀፋ አስከተለብኝ” በማለት ጽፎ ነበር። ቀጥሎም “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም፤ በስሙም አልናገርም” አለ። ከዚያ በኋላ ምን ተከሰተ? ስብከቱን አቆመ? ኤርምያስ እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል:- “ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም።” (ኤርምያስ 20:8, 9) ለሕዝቡ ፌዝ ትኩረት ሲሰጥ ደስታውን ያጣ እንደነበር ልብ በል። የመልእክቱን አስደሳችነትና ጠቀሜታ ሲያስብ ግን ደስታው እንደገና ይቀጣጠላል። ከዚህም በላይ ይሖዋ “እንደ ኀያል ተዋጊ” ከኤርምያስ ጋር በመሆን ቃሉን በቅንዓትና በድፍረት ለማወጅ የሚያስችለውን ጥንካሬ ይሰጠው ነበር።​—⁠ኤርምያስ 20:11

16. በስብከቱ ሥራችን ሁልጊዜ ደስተኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

16 ነቢዩ ኤርምያስ ሥራው ደስታ አስገኝቶለት ይሆን? እንዴታ! “ቃልህ በተገኘ ጊዜ በላሁት፤ . . . እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ” በማለት ለይሖዋ ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 15:16) ኤርምያስ እውነተኛውን አምላክ የመወከልና ቃሉን የመስበክ መብት በማግኘቱ ተደስቷል። ይህ እኛንም የሚያስደስት ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ በሰማይ እንዳሉት መላእክት ሁሉ እኛም በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሲቀበሉ፣ ንስሐ ሲገቡና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዝ ሲጀምሩ መመልከት ያስደስተናል።​—⁠ሉቃስ 15:10

‘የኢዮብ ጽናት’

17, 18. ኢዮብ የጸናው በምን መንገድ ነው? የመጨረሻው ውጤትስ ምን ነበር?

17 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ስለ ጥንት ነቢያት ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።” (ያዕቆብ 5:11) እዚህ ላይ “ጸና” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል፣ በቁጥር 10 ላይ ያዕቆብ ከተጠቀመበት “ትዕግሥት” ተብሎ ከተተረጎመው ቃል ጋር ተመሳሳይ ፍቺ አለው። አንድ ምሁር በእነዚህ ሁለት ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጹ “የመጀመሪያው ቃል ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽሙብን የምናሳየውን ትዕግሥት ያመለክታል፤ በኋላ የተጠቀሰው ቃል ደግሞ ችግር ሲያጋጥመን በድፍረት መጽናትን ያመለክታል” ብለዋል።

18 ኢዮብ ከባድ ችግር አጋጥሞት ነበር። ንብረቱን አጥቷል፣ ልጆቹ ሞተውበታል እንዲሁም በጣም ታምሞ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ እየቀጣህ ነው በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ነበር። ኢዮብ ችግሩን ተሸክሞ ዝም ከማለት ይልቅ ስላለበት ሁኔታ በምሬት ተናግሯል፤ እንዲያውም ከአምላክ ይልቅ ጻድቅ እንደሆነ በተዘዋዋሪ ተናግሯል። (ኢዮብ 35:2፤ የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) ሆኖም የነበረው እምነት አልጠፋም፤ ጽኑ አቋሙንም አላጎደፈም። ሰይጣን እንዳለውም አምላክን አልረገመም። (ኢዮብ 1:11, 21) የመጨረሻው ውጤትስ ምን ሆነ? ይሖዋ “ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ።” (ኢዮብ 42:12) ይሖዋ ኢዮብ ከሕመሙ እንዲድን ከማድረጉም በላይ በፊት ከነበረው በእጥፍ የሚበልጥ ሀብት ሰጠው፤ በተጨማሪም ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር አርኪና አስደሳች ሕይወት እንዲኖር አደረገው። ከዚህም በላይ ኢዮብ በታማኝነት መጽናቱ ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንዲያውቅ አስችሎታል።

19. ከኢዮብ ጽናት ምን ትምህርት እናገኛለን?

19 ከኢዮብ ጽናት ምን ትምህርት እናገኛለን? እንደ ኢዮብ ሕመም ወይም ሌላ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። ይሖዋ አንድ የተለየ ችግር እንዲደርስብን ለምን እንደፈቀደ ሙሉ በሙሉ አንረዳ ይሆናል። ቢሆንም በታማኝነታችን ከጸናን በረከት እንደምናገኝ እርግጠኛ ነን። ይሖዋ ከልብ ለሚሹት ያለ ምንም ጥርጥር ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል። (ዕብራውያን 11:6) ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 10:22፤ 24:13

‘የይሖዋ ቀን ይመጣል’

20. የይሖዋ ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ታጋሽ ቢሆንም ጻድቅ ስለሆነ ክፋትን ለዘላለም አይታገሥም። ትዕግሥቱ ገደብ አለው። ጴጥሮስ አምላክ ‘ለቀድሞው ዓለም እንዳልራራ’ ተናግሯል። በወቅቱ ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ሲተርፉ ያን ጊዜ የነበረው የኃጢአተኞች ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል። ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ሰዶምና ገሞራ የተባሉትን ከተሞች አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሏቸዋል። እነዚህ የቅጣት ፍርዶች “ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ” ይሆናሉ። ከዚህ በመነሳት ‘የይሖዋ ቀን እንደሚመጣ’ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:5, 6፤ 3:10

21. ትዕግሥተኞችና በመከራ የምንጸና መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?

21 ስለዚህ ሌሎች ከጥፋት መዳን ይችሉ ዘንድ ንስሐ እንዲገቡ በመርዳት የይሖዋን ዓይነት ትዕግሥት እናሳይ። በተጨማሪም ሰዎች ለስብከታችን በጎ ምላሽ ባይሰጡ እንኳ በትዕግሥት ምሥራቹን በማብሰር ነቢያትን እንምሰል። እንዲሁም እንደ ኢዮብ ችግሮችን በጽናት ከተቋቋምንና ታማኝነታችንን ከጠበቅን ይሖዋ አብዝቶ እንደሚባርከን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይሖዋ አገልጋዮቹ ምሥራቹን በመላው ምድር ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ምን ያህል እየባረከው እንዳለ መመልከታችን ራሱ በአገልግሎታችን እንድንደሰት የሚያደርገን ምክንያት ነው። ይህንን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ የሚታገሠው ለምንድን ነው?

• ነቢያት ካሳዩት ትዕግሥት ምን ትምህርት እናገኛለን?

• ኢዮብ የጸናው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?

• የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው እንዴት እናውቃለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የአባቱን ትዕግሥት በሚገባ አንጸባርቋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ፣ ኤርምያስ ላሳየው ትዕግሥት ምን ወሮታ ከፍሎታል?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ በመጽናቱ ይሖዋ ምን አድርጎለታል?