በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እርሱን እንዳገኘው ረድቶኛል

ይሖዋ እርሱን እንዳገኘው ረድቶኛል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ እርሱን እንዳገኘው ረድቶኛል

ፍሎረንስ ክላርክ እንደተናገረችው

የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ሰው እንደሚያደርገው እኔም በጠና የታመመውን ባለቤቴን እጅ በመያዝ ከሕመሙ እንዲያገግም እንዲረዳው ወደ አምላክ ጸለይኩ። ባለቤቴ ከሞት ከተረፈ አምላክን እስካገኘው ድረስ እንደምፈልገውና ለእርሱ ያደርኩ ሰው እንደምሆን ተሳልኩ።

በምዕራብ አውስትራሊያ ኪምበርሊ ፕላቱ በተባለ ገጠራማ ክልል በሚኖሩ ኡምቡልገሪ የሚባሉ የአቦርጅኖች ማኅበረሰብ ውስጥ መስከረም 18, 1937 የተወለድኩ ሲሆን ወላጆቼ ፍሎረንስ ቹሉንግ የሚል ስም አወጡልኝ።

ያለ አንዳች ሐሳብ ስላሳለፍኩት አስደሳች የልጅነት ጊዜዬ ጥሩ ትዝታ አለኝ። ቤተ ክርስቲያናችን በምትሰጠው ትምህርት አማካኝነት ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት መሠረታዊ ነገሮችን የተማርኩ ቢሆንም እንኳ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን ያስተማረችኝ እናቴ ነበረች። እናቴ ገና ከትንሽነቴ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራ ታነብልኝ ስለነበር ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር አደረብኝ። በተጨማሪም ለቤተ ክርስቲያኗ ሚስዮናዊ ሆና የምታገለግለውን አክስቴን በጣም አደንቃት ነበር። የእርሷን ፈለግ የመከተል ልባዊ ምኞት ነበረኝ።

ፎረስት ሪቨር ሚሽን ተብሎ ይጠራ የነበረው ማኅበረሰባችን እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ነበረው። በመሆኑም ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ለሁለት ሰዓት እማር ነበር። በመደበኛ ትምህርት የማገኘው እውቀት በጣም ውስን መሆኑ አባቴን ያሳስበው ጀመር። አባታችን ልጆቹ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ስለሚፈልግ ኡምቡልገሪን ለቅቆ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዊንደም ለመሄድ ወሰነ። ከኡምቡልገሪ የወጣን ቀን በጣም አዝኜ የነበረ ቢሆንም እንኳ ከ1949 እስከ 1952 ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ በዊንደም የሙሉ ቀን ትምህርት መከታተል ቻልኩ። አባቴ ለእኔ አስቦ ስላስተማረኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።

እናቴ በከተማችን ከሚገኝ አንድ ሐኪም ጋር ትሠራ ነበር። በ15 ዓመቴ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ዶክተሩ በዊንደም ሆስፒታል ነርስ ሆኜ እንድሠራ ግብዣ አቀረበልኝ። በዚያን ጊዜ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ስለነበር የቀረበልኝን ግብዣ በደስታ ተቀበልኩ።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አሌክ ከተባለ ከብት የሚያረባ አንድ ነጭ ሰው ጋር ተዋወቅንና ሁልጊዜ የምሄድበት የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በሚገኝባት ደርቢ ከተማ ውስጥ በ1964 ተጋባን። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጡ። ምንም የመስማት ፍላጎት እንደሌለኝና ተመልሰው እንዳይመጡ ነገርኳቸው። ያም ሆኖ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው ማለታቸው ትኩረቴን ስቦት ነበር።

“ራስሽ መጸለይ አትችይም?”

ከ1965 ጀምሮ ሕይወት በጣም አስቸጋሪ እየሆነብኝ መጣ። ባለቤቴ በጣም ከባድ የሆኑ ሦስት አደጋዎች ደረሱበት። ሁለቱ ከፈረሱ የወደቀባቸው ጊዜያት ሲሆኑ አንደኛው ደግሞ የመኪና አደጋ ነበር። ደስ የሚለው ሦስቱንም ጊዜያት ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ወደ ሥራው ተመለሰ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ከፈረስ ላይ ወድቆ ሌላ አደጋ አጋጠመው። በዚህ ጊዜ በጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። ሆስፒታል እንደደረስኩ ዶክተሩ ባለቤቴ ለመሞት እያጣጣረ እንደሆነ ነገረኝ። ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። አንዲት ነርስ የመንደሩ ቄስ መጥቶ እንዲያነጋግረኝ የጠየቀችው ቢሆንም “አሁን አልችልም። ነገ እመጣለሁ!” አላት።

ቄሱ ከአጠገቤ ሆኖ እንዲጸልይልኝ እንደምፈልግ ለመነኩሲቷ ነገርኳት። “ምን ሆነሻል? ራስሽ መጸለይ አትችይም?” አለችኝ። ስለዚህ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ምሥሎች ጸለይኩ፤ ሆኖም ወደዚያ መጸለዬ ምንም እርባና አልነበረውም። አሌክ እስትንፋሱ ጸጥ ሊል የተቃረበ ይመስል ነበር። ‘ባለቤቴ ከሞተ ምን ይውጠኛል?’ ክርስቲን፣ ናኔትና ጄፈሪ የተባሉት ሦስቱ ልጆቼም ነገር ያሳስበኝ ጀመር። ያለ አባት የሚያሳልፉት ሕይወት ምን ዓይነት ይሆን? የሚያስደስተው ነገር ባለቤቴ ከሦስት ቀናት በኋላ ራሱን ያወቀ ሲሆን ታኅሣሥ 6, 1966 ከሆስፒታል ወጣ።

ባለቤቴ በሚደንቅ ሁኔታ የተሻለው ቢሆንም እንኳ በአንጎሉ ላይ ዘላቂ ጉዳት ደርሶ ነበር። አንዳንድ ነገሮችን ጨርሶ ማስታወስ የተሳነው ከመሆኑም በላይ ጠበኛና ጸባዩ የሚለዋወጥ ሰው ሆነ። ከልጆቹ ጋር መግባባት ያቃተው ሲሆን እንደ ትልቅ ሰው ካልመለሱለት ለዱላ ይጋበዛል። ለእርሱ እንክብካቤ ማድረግ አስቸጋሪ ነበር። ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነገር የማደርግለት እኔ ነበርኩ። ሌላው ቀርቶ ማንበብና መጻፍ እንኳ አንደ አዲስ አስተማርኩት። በቤት ውስጥ ከማከናውናቸው ሌሎች ሥራዎች በተጨማሪ እርሱን መንከባከብ የፈጠረብኝ ከባድ ውጥረት የአእምሮና የስሜት ቀውስ አስከተለብኝ። በመሆኑም ባለቤቴ አደጋ ከደረሰበት ከሰባት ዓመት በኋላ ጤንነቴ እስኪመለስልኝ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተለያይተን ለመኖር ተስማማን።

ልጆቼን ይዤ በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ፐርዝ ወደምትባል ከተማ ተዛወርኩ። እኛ ፐርዝ ከመሄዳችን በፊት ምዕራብ አውስትራሊያ በምትገኘው ከነነረ በተባለች አነስተኛ ከተማ የምትኖረው እህቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት a ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የሚያመለክት አንድ ሥዕል አሳየችኝ። አምላክ ይሖዋ የሚባል የግል ስም እንዳለው ከዚሁ መጽሐፍ ላይ ስታሳየኝ በጣም ተደሰትኩ። በነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሰምቼ ስለማላውቅ ፐርዝ ደርሼ ከተረጋጋሁ በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች እደውላለሁ ብዬ ወሰንኩ።

ይሁንና እዚያ ከደረስኩ በኋላ እነርሱን ደውሎ ለማግኘት አመነታሁ። አንድ ቀን ምሽት ላይ የቤታችን መጥሪያ ጮኸ። ወንዱ ልጄ በሩን ከፈተና እየሮጠ ወደ እኔ ተመልሶ “እማዬ፣ እደውልላቸዋለሁ ስትይ የነበሩት ሰዎች ናቸው” አለኝ። ሁኔታው ቢያስገርመኝም “የለችም በላቸው!” አልኩት። ይሁን እንጂ “እማዬ፣ ውሸት መናገር እንደሌለብኝ ታውቂያለሽ” አለኝ። የልጄን እርምት ተቀብዬ ወደ በሩ ሄድኩ። ሰዎቹን ሰላም ስላቸው በፊታቸው ላይ ግራ የመጋባት ስሜት አነበብኩ። ለካ የመጡት ቤቱን የለቀቀውን ተከራይ ፈልገው ነበር። ወደ ቤት እንዲገቡ ከጋበዝኳቸው በኋላ የጥያቄ መዓት አወረድኩባቸው፤ ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ አጥጋቢ መልስ ሰጡኝ።

በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረኝን ፍቅር ቀሰቀሰብኝ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኘሁ። እሁድ እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት የጀመርኩ ሲሆን ብዙም ሳልቆይ በአዘቦቱ ቀናት ወደሚደረጉት ስብሰባዎችም እሄድ ጀመር። ከዚህም በላይ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ሰዎች መስበክ ጀመርኩ። ሌሎች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ መርዳቴ አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነቴን እንዳሻሻለልኝ ተረዳሁ። ከስድስት ወራት በኋላ ፐርዝ ውስጥ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ።

በመንፈሳዊ እያደግሁ ስሄድ ይሖዋ ጋብቻን እንደ ቅዱስ ነገር እንደሚያየው ያስተዋልኩ ሲሆን በ1 ቆሮንቶስ 7:​13 ላይ “ያላመነ ባል ያላት ሴት ብትኖርና እርሱም አብሮአት ለመኖር የሚፈቅድ ከሆነ፣ ልትፈታው አይገባትም” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ተረዳሁ። ይህ ጥቅስ ወደ አሌክ ተመልሼ እንድሄድ ልቤን አነሳሳው።

ወደ ደርቢ ተመለስኩ

ከባለቤቴ ጋር ከተለያየን ከአምስት ዓመት በኋላ ማለትም ሰኔ 21, 1979 ወደ ደርቢ ተመለስኩ። እርግጥ ነው፣ በመመለሴ ደስ ብሎኝ የነበረ ቢሆንም ምን ዓይነት አቀባበል እንደሚያደርግልኝ ስላላወቅሁ ውስጤ ተረብሾ ነበር። የሚደንቀው ነገር ወደ እርሱ በመመለሴ በጣም ተደሰተ፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ትንሽ ቅር አለው። ወዲያውኑ፣ ወደ ፐርዝ ከመሄዴ በፊት እንካፈልበት የነበረውን ቤተ ክርስቲያን እንድከተል ነገረኝ። እኔ ደግሞ እዚያ ልሄድ እንደማልችል አስረዳሁት። እንደ አንድ ክርስቲያን ሚስት በተቻለኝ መጠን የራስነት መብቱን ለማክበር ጥረት አደረግሁ። ስለ ይሖዋና ወደፊት ስለሚፈጸሙት ግሩም ተስፋዎቹ ላወያየው ብሞክርም እንኳ አድናቆት አላሳየም።

ከጊዜ በኋላ ግን አሌክ አዲሱን የሕይወት ጎዳናዬን መቃወሙን ከማቆም አልፎ በትልልቅ ስብሰባዎችም ሆነ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የሚያስፈልገኝን ወጪ ይሸፍንልኝ ጀመር። መኪና እንደ ውድ ሀብት በሚታይበት በዚህ የአውስትራሊያ ገጠራማ ክልል ውስጥ ለክርስቲያናዊ አገልግሎቴ እንዲያግዘኝ መኪና ስለገዛልኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጨምሮ ወንድሞችና እህቶች ቤታችን እየመጡ ለብዙ ቀናት ያርፉ ነበር። ይህ ደግሞ አሌክ ከብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዲተዋወቅ ያስቻለው ሲሆን ከእነርሱ ጋር መሆን ደስ እያለው እንደመጣ ይሰማኛል።

እንደ ሕዝቅኤል ተሰማኝ

ወንድሞችና እህቶች ሲጠይቁኝ ደስ ቢለኝም አንድ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሞኝ ነበር። ደርቢ ከተማ ከእኔ ሌላ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ቅርብ የሚባለው ጉባኤ የሚገኘው እኛ ከምንኖርበት 220 ኪሎ ሜትር በሚርቀው በብሩም ነበር። ስለዚህ ምሥራቹን ለመስበክ የቻልኩትን ያህል ጥረት ለማድረግ ወሰንኩ። በይሖዋ እርዳታ በደንብ ተደራጅቼ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ጀመርኩ። ብቻዬን ሆኜ መስበክ አስቸጋሪ ቢሆንብኝም እንኳ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ሁልጊዜ አስታውስ ነበር።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:13

የአካባቢው ቀሳውስት በማደርገው እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ ለአቦርጅኖቹ በመስበኬ አልተደሰቱም። በዚህ ምክንያት የስብከት እንቅስቃሴዬን እንዳቆም ሊያስፈራሩኝ ሞከሩ። ተቃውሟቸው ይበልጥ በሥራዬ እንድቀጥል ያደረገኝ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እንዲረዳኝ ያለማቋረጥ እጸልይ ነበር። “እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ። ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ። . . . አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር” የሚለው ለሕዝቅኤል የተሰጠው ማበረታቻ ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኝ ነበር።​—⁠ሕዝቅኤል 3:8, 9

በአውስትራሊያ የሚገኝ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑ ሁለት ሰዎች ወደ ገበያ ስወጣ በተደጋጋሚ ጊዜያት ያስቸግሩኝ ነበር። እነዚህ ሰዎች እየጮሁ በማፌዝ የሌሎች ገበያተኞችን ትኩረት ለመሳብ ይሞክሩ ነበር። እንዲህ ሲያደርጉ ሰምቼ እንዳልሰማሁ ዝም እላቸዋለሁ። አንድ ቀን ደግሞ ፍላጎት ላሳየች ለአንዲት ሴት ተመላልሶ መጠየቅ ሳደርግ የዚያ መንደር ቤተ ክርስቲያን ቄስ መጣና ‘በክርስቶስ አታምኚም’ ብሎ ወነጀለኝ። መጽሐፍ ቅዱሴን ከእጄ መንጭቆ ከወሰደው በኋላ ፊቴ ላይ አራገበውና መለሰልኝ። ትኩር ብዬ ዓይን ዓይኑን እያየሁ በረጋ ሆኖም በቆራጥነት መንፈስ ዮሐንስ 3:​16ን ጠቀስኩለትና በኢየሱስ እንደማምን ገለጽኩለት። በልበ ሙሉነት ስመልስለት ደንግጦ አንዲት ቃል ሳይተነፍስ ከአጠገቤ ሄደ።

በደርቢ አካባቢ ለሚገኙት አቦርጅኖች መስበክ በጣም ያስደስተኝ ነበር። በአንድ የአቦርጅኖች ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ ቄስ ወደዚያ ገብቼ እንዳልሰብክ የከለከለኝ ቢሆንም ቄሱ ሌላ ቦታ ተቀይሮ ሄደ። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎቹ ማድረስ ችያለሁ። እንደ አክስቴ ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ፤ አሁን እኔ ራሴ ሌሎች ሰዎች የአምላክን ቃል እንዲያውቁ በመርዳት የሚስዮናዊነት ሥራ አያከናወንኩ ነው። የሰበክሁላቸው ብዙ አቦርጅኖች ጥሩ ምላሽ በመስጠታቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማግኘት ችያለሁ።

ለመንፈሳዊ ፍላጎቴ ትኩረት ሰጠሁ

ለአምስት ዓመት በደርቢ ከእኔ ሌላ የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ከእምነት ባልንጀሮች ጋር አዘውትሮ መሰብሰብ የሚያስገኘው ማበረታቻ ስለጎደለብኝ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ መቀጠል አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። አንድ ቀን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ መኪናዬን ይዤ ወጣሁ። ከሰዓት በኋላ አመሻሹ ላይ ወደ ቤት ስገባ አንዲት እህት ከሰባት ልጆቿ ጋር ሆና እየጠበቀችኝ አገኘኋት። ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከሚገኘው ከብሩም ጉባኤ የተወሰኑ ጽሑፎች አምጥተውልኝ ነበር። ቤቲ በተርፊልድ የተባለችው ይህች እህት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በወር አንዴ ደርቢ እየመጣች ቅዳሜና እሁድን አብራኝ ለማሳለፍ ወሰነች። እርሷ በምትመጣበት ጊዜ አገልግሎት አብረን ከወጣን በኋላ እኔ ቤት ሆነን መጠበቂያ ግንብ እናጠናለን። እኔም በተራዬ በወር አንድ ጊዜ ወደ ብሩም መሄድ ጀመርኩ።

በብሩም የሚገኙት ወንድሞች ብዙ ረድተውኛል፤ አንዳንድ ጊዜ ረጅም መንገድ ተጉዘው ደርቢ ድረስ በመምጣት አብረውኝ አገልግሎት ይወጡ ነበር። በደርቢ በኩል የሚያልፉ የሌላ ከተማ ወንድሞች ወይም እህቶች ካሉ ጎራ ብለው እንዲጠይቁኝና አብረውኝ እንዲያገለግሉ ይነግሯቸዋል። እነዚህ መንገደኞች በካሴት የተቀዱ የሕዝብ ንግግሮች ጭምር ያመጡልኝ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ አብረውኝ መጠበቂያ ግንብ ያጠናሉ። እነዚህ ወንድሞች የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ቢሆንም እንኳ በጣም አበረታተውኛል።

ተጨማሪ እገዛ አገኘሁ

በደቡባዊው ምዕራብ አውስትራሊያ የሚኖሩ አርተርና ሜሪ ዊሊስ የተባሉ ጡረተኛ ባልና ሚስት በቀዝቃዛው ወራት እኔ ወደምኖርበት አካባቢ እየመጡ ለሦስት ወር ያህል አብረውኝ ማገልገላቸው ተጨማሪ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። እነዚህ ባልና ሚስት በዚህ ሁኔታ ለተወሰኑ ዓመታት እገዛ አድርገውልኛል። ወንድም ዊሊስ አብዛኛውን ስብሰባ የሚመራልን ሲሆን በመስክ አገልግሎት ላይ ግንባር ቀደም ሆኖ ያገለግላል። በኪምበርሊ ፕላቱ ላይ ወደሚገኙት ይበልጥ ሩቅ ወደሆኑት የከብት ርባታ ጣቢያዎች ሄደን እንሰብክ ነበር። ወንድምና እህት ዊሊስ መሄጃቸው ደርሶ በተለዩኝ ቁጥር የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።

በመጨረሻም በ1983 መገባደጃ ላይ ዳኒና ደኒዝ ስተርጀን የተባሉ ወንድምና እህት ከአራት ልጆቻቸው ጋር መጥተው ደርቢ ሊኖሩ እንደሆነ ስሰማ በጣም ተደሰትኩ። ይህ ቤተሰብ ወደ ደርቢ ከመጣ በኋላ በየሳምንቱ መሰብሰብ የቻልን ከመሆኑም በላይ በአንድነት ሆነን ወደ መስክ አገልግሎት እንወጣ ነበር። በ2001 አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። በዛሬው ጊዜ ደርቢ 24 የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንዲሁም ጥሩ መንፈሳዊ እንክብካቤ የሚያደርጉልን ሁለት ሽማግሌዎችና አንድ የጉባኤ አገልጋይ ያቀፈ ጠንካራ ጉባኤ አለው። አንዳንድ ጊዜ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 30 ይደርሳል።

ያለፉትን ዓመታት መለስ ብዬ ስቃኝ አፍቃሪው ይሖዋ እርሱን እንዳገለግለው እንዴት እንደረዳኝ ስለሚያስታውሰኝ ልቤ በሐሴት ይሞላል። ባለቤቴ እምነቴን ባይጋራኝም እንኳ በተለያዩ መንገዶች እኔን መደገፉን አላቆመም። ከቅርብ የቤተሰቤ አባላት መካከል አምስቱ ማለትም ሁለት ሴት ልጆቼ፣ ሁለት የልጅ ልጆቼና አንድ የእህቴ ልጅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ዘመዶቼ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ነው።

ይሖዋ እርሱን እንዳገኘው ስለረዳኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ። እስከ ዕለተ ሞቴ የእርሱ ለመሆን ቆርጫለሁ።​—⁠መዝሙር 65:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አውስትራሊያ

ዊንደም

ኪምበርሊ ፕላቱ

ደርቢ

ብሩም

ፐርዝ

[ምንጭ]

ካንጋሮና ወፍ:- Lydekker; koala: Meyers

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 ዊንደም ሆስፒታል ውስጥ ነርስ ሆኜ ስሠራ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2005 ደርቢ ጉባኤ