በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብና ጥሩ ሥነ ምግባር—ከታሪክ የምናገኘው ትምህርት

ገንዘብና ጥሩ ሥነ ምግባር—ከታሪክ የምናገኘው ትምህርት

ገንዘብና ጥሩ ሥነ ምግባር—ከታሪክ የምናገኘው ትምህርት

ሚያዝያ 7, 1630 አራት መቶ የሚሆኑ ሰዎች በአራት መርከቦች ተሳፍረው ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ አቀኑ። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ የተማሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሀብታም ነጋዴዎች እንዲያውም አንዳንዶቹ የፓርላማ አባላት ነበሩ። ከ1618 እስከ 1648 በአውሮፓ የተካሄደው የሠላሳው ዓመት ጦርነት እየተዳከመ የነበረውን የእንግሊዝ ኢኮኖሚ ይባስ አደቀቀው። ስለሆነም ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል ባያውቁትም እንኳ ቤታቸውን፣ ንግዳቸውንና ዘመዶቻቸውን ትተው የተሻለ ነገር ፍለጋ ወደ ባዕድ አገር ለመሄድ ተነሱ።

ይሁን እንጂ ተስፋን ሰንቀው ጉዞ የጀመሩት እነዚህ ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ለመበልጸግ ብቻ የተነሱ ነጋዴዎች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው ስደት በመሸሽ ላይ ያሉ ቀናተኛ ፒዩሪታኖች ነበሩ። a ዋናው ግባቸውም፣ እነርሱም ሆኑ ዘሮቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ሳያጎድፉ ቁሳዊ ብልጽግና አግኝተው ለመኖር የሚያስችላቸውን ፊሪሃ አምላክ ያለው ኅብረተሰብ መመሥረት ነበር። በመርከብ ተጉዘው በመምጣት ሴለም፣ ማሳቹሴትስ ከደረሱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የሚገኝ አነስተኛ መሬት ያዙ። ይህን አዲሱን መኖሪያቸውን ቦስተን ብለው ሰየሙት።

ሚዛናዊ መሆን አስቸጋሪ ነበር

የሰፋሪዎቹ መሪና ገዥ የነበረው ጆን ዊንትረፕ በአዲሱ መኖሪያቸው የግል ሀብትንና ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ሕዝቡ በሀብት እንዲበለጽግ እንዲሁም ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖረው ይፈልግ ነበር። ይሁንና እነዚህን ሁለት ነገሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ አልተቻለም። ሊመጣ የሚችለውን ፈታኝ ሁኔታ በመገንዘብ፣ ሀብት ፈሪሃ አምላክ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አስመልክቶ ለሕዝቡ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷቸዋል።

እንደ ሌሎቹ የፒዩሪታን መሪዎች ሁሉ ዊንትረፕ ሀብት ማግኘት በራሱ ስህተት እንዳልሆነ ያምን ነበር። ሀብታም የመሆን ዋነኛ ዓላማም ሌሎችን ለመርዳት እንደሆነ ይናገር ነበር። በመሆኑም አንድ ሰው ሀብቱ በጨመረ መጠን የዚያኑ ያህል መልካም ነገሮችን ለሌሎች ማድረግ ይችላል። የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፐትሪሻ ኦቱል የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “የሀብትን ያህል ፒዩሪታኖችን የሚያስጨንቅ ጉዳይ የለም። ሀብት አምላክ እንደባረካቸው የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር ኃጢአት ወደሆነው ወደ ኩራት . . . እንዲሁም ሌሎች ኃጢአቶችን ወደመሥራት የሚመራ ኃይለኛ ማባበያ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።”

ዊንትረፕ በሀብትና በቅንጦት ምክንያት ሊመጡ በሚችሉ ኃጢአቶች ላለመጠመድ ልከኝነትንና ራስን መግዛትን አበረታቷል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ የግል ትርፍ ለማግኘት የሚያደርገው ሩጫ አምላካዊ ባሕርያትን እንዲያፈሩና እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ ሲል ዊንትረፕ ከሚያደርገው ሙከራ ጋር ይጋጭ ጀመር። ተቃዋሚዎች፣ ዊንትረፕ በግል ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ እንደገባ ስለተሰማቸው ይቃረኑት ጀመር። አንዳንዶቹም ውሳኔ የማድረጉን ኃላፊነት የሚጋራ በሕዝብ የተመረጠ አካል መኖር አለበት በማለት ቅስቀሳ ማድረግ ጀመሩ። ሌሎቹ ደግሞ አቋማቸውን በይፋ ከመግለጽ ይልቅ ወደ አጎራባቿ ከነቲከት በመሄድ የግል ጥቅማቸውን ማሳደዱን ቀጠሉበት።

ኦቱል እንዳሉት “አጋጣሚ፣ ብልጽግናና ዲሞክራሲ በሁሉም ማሳቹሴትስ ፒዩሪታኖች ሕይወት ውስጥ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆነዋል፤ እንዲሁም ከዊንትረፕ አስተሳሰብ በተለየ መንገድ በግላቸው ለመበልጸግ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት አቀጣጥለውላቸዋል።” ዊንትረፕ በ1649 በ61 ዓመቱ ሲሞት ቤሳ ቤስቲን አልነበረውም። በመፈራረስ ላይ የነበረው ማኅበረሰብ ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ቢችልም፣ ዊንትረፕ የተሻለ ዓለም ለማየት የነበረው ሕልም እውን ሲሆን ለመመልከት አልታደለም።

ጥረቱ ቀጥሏል

ጆን ዊንትረፕ የተሻለ ዓለም ለማስገኘት የነበረው ሕልም አብሮት አልተቀበረም። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተሻለ ሕይወት እናገኛለን በሚል ተስፋ ከአፍሪካ፣ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ ከምሥራቅ አውሮፓና ከላቲን አሜሪካ አገሮች ይሰደዳሉ። አንዳንዶቹ እንዲህ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ሀብታም መሆን የሚቻልበትን ምስጢር እናካፍላለን በሚሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ መጻሕፍት፣ ሴሚናሮችና በየዓመቱ በሚከፈቱ ድረ ገጾች መማረካቸው ነው። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አሁንም ቢሆን ብዙ ሰዎች የሥነ ምግባር አቋማቸውን ሳያላሉ ገንዘብን ለማካበት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

እውነቱን ለመናገር ውጤቱ አሳዛኝ ነው። ብዙውን ጊዜ ሀብትን ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎች ለገንዘብ ሲሉ ያሏቸውን ግሩም የሥነ ምግባር እሴቶች አንዳንዴም በአምላክ ላይ ያሳደሩትን እምነት መሥዋዕት ሲያደርጉ ይታያሉ። በመሆኑም “አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያንም ሀብታምም መሆን ይችላል? በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ የበለጸገ ፈሪሃ አምላክ ያለው ኅብረተሰብ ሊኖር ይችላል?” እንደሚሉት ያሉ ተገቢ ጥያቄዎችን ትሰነዝር ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ፒዩሪታን የሚለው መጠሪያ የተሰጠው በ16ኛው መቶ ዘመን በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩትና ቤተ ክርስቲያናቸውን ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዝራዥ ሙሉ ለሙሉ ለማጥራት ሲጥሩ ለነበሩት ፕሮቴስታንቶች ነው።

[ምንጭ]

መርከቦች:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck; ዊንትረፕ:- ብራውን ብራዘርስ