በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መሲሑን አገኘነው”

“መሲሑን አገኘነው”

“መሲሑን አገኘነው”

“መሲሑን አገኘነው።” “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን . . . አግኝተነዋል።” እነዚህን አስደናቂ ቃላት የተናገሩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሁለት ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን ናቸው። በመጨረሻም ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መጣ። እነዚህ አይሁዳውያን በነገሩ እርግጠኞች ነበሩ!​—⁠ዮሐንስ 1:​35-45

በወቅቱ ከነበረው ታሪክና ሃይማኖታዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ እነዚህ ሰዎች ያሳዩት እምነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነበር። ከዚያ ቀደም ብዙ የተወራላቸውና የተለያየ ተስፋ የሰጡ በርካታ ነጻ አውጪ ነን ባዮች ተነስተው ነበር። ሆኖም እነዚህ ሰዎች አይሁዳውያንን ከሮማውያን ቀንበር ሊያላቅቁ ባለመቻላቸው የሰጡት ተስፋ ሁሉ መና ቀርቷል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 5:​34-37

ይሁን እንጂ ሁለቱ አይሁዳውያን ማለትም እንድርያስና ፊልጶስ እውነተኛውን መሲሕ እንዳገኙ ምንም ጥርጣሬ አልነበራቸውም። እንዲያውም በቀጣዮቹ ዓመታት ይህ ሰው ስለ መሲሑ በተነገሩት ትንቢቶች መሠረት ያከናወናቸውን ድንቅ ሥራዎች ሲመለከቱ ስለ ማንነቱ ይበልጥ እርግጠኞች መሆን ችለዋል።

እነዚህ ሁለት አይሁዳውያንም ሆኑ ሌሎች ብዙዎች ይህ ሰው የሐሰት ነቢይ ወይም አታላይ አለመሆኑን ተማምነው በእርሱ ላይ እምነት የጣሉት ለምንድን ነው? እርሱ እውነተኛው መሲሕ መሆኑን ያረጋገጡት አሳማኝ ማስረጃዎችስ ምንድን ናቸው?

ዘገባው እንደሚያሳየው እንድርያስና ፊልጶስ፣ አናጢ የነበረው የናዝሬቱ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበትና ሲጠብቁት የነበረው መሲሕ መሆኑን አወቁ። (ዮሐንስ 1:​45) በወቅቱ የነበረው ጠንቃቃ ታሪክ ጸሐፊ ሉቃስ ይህ መሲሕ የመጣው “ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት” እንደሆነ ጽፏል። (ሉቃስ 3:​1-3) የጢባርዮስ ቄሣር 15ኛ ዓመት የግዛት ዘመን የጀመረው በ28 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መስከረም ወር ላይ ሲሆን ያበቃው ደግሞ በመስከረም ወር 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ሉቃስ፣ አይሁዳውያን በዚያን ወቅት የመሲሑን መምጣት “በጕጕት እየተጠባበቁ” እንደነበረም አክሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 3:​15) መሲሑ በዚህ ወቅት ይጠበቅ የነበረው ለምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።

የመሲሑን ማንነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

መሲሑ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ መጠን ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ተስፋ የተደረገበትን መሲሕ በጥንቃቄና በታማኝነት እየጠበቁት ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ግልጽ የሆኑ ፍንጮች ይሰጣል ብሎ መጠበቁ ተገቢ ነው። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ በትጋት እየጠበቁ ያሉት ሰዎች እንደ ሌሎቹ በሐሰተኛ መሲሖች እንዳይታለሉ ስለሚረዳ ነው።

አንድ አምባሳደር ወደተመደበበት አገር ሲሄድ ስለ ሹመቱ የሚገልጽ ደብዳቤ ይዞ መቅረቡ የሚጠበቅ ነገር ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ መሲሑ ምን መሥፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት አስቀድሞ በግልጽ አስጽፏል። በመሆኑም ‘የእምነታችን ራስ’ የሆነው መሲሕ ሲገለጥ ማንነቱን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ይዞ የመጣ ያህል ነበር።​—⁠ዕብራውያን 12:​2 የ1954 ትርጉም

እውነተኛው መሲሕ ሊያሟላቸው የሚገቡት መሥፈርቶች ከዘመናት በፊት በተጻፉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ሰፍረዋል። እነዚህ ትንቢቶች መሲሑ የሚመጣበትን መንገድ፣ ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚያከናውን፣ በሌሎች እጅ ስለሚደርስበት ሥቃይ እንዲሁም አሟሟቱን በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዘዋል። እነዚህ የሚታመኑ ትንቢቶች ስለ ትንሣኤው፣ በአምላክ ቀኝ በክብር ስለመቀመጡና በመጨረሻም መንግሥቱ ወደፊት ስለሚያመጣው በረከት እንደዘገቡ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንድ ሰው ብቻ ሊኖረው ከሚችለው የእጅ አሻራ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ልዩ ምልክት ሰጥተዋል።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መሲሕ ሆኖ ሲገለጥ ሁሉም ትንቢቶች በዚያው ወቅት አልተፈጸሙም። ለምሳሌ ያህል እንደሚሞትና ትንሣኤ እንደሚያገኝ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን አላገኘም ነበር። የሆነ ሆኖ እንድርያስ፣ ፊልጶስና ሌሎችም በኢየሱስ ላይ እምነት ያሳደሩት እርሱ ባስተማራቸውና በሠራቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተው ነው። መሲሕ ስለ መሆኑ ብዙ አሳማኝ ማረጋገጫዎች አይተው ነበር። በዚያ ዘመን ኖረህ ቢሆንና አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ ማስረጃዎቹን ብትመለከት ኖሮ ምናልባት አንተም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አምነህ ትቀበል ነበር።

የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ማስረጃ

እንዲህ ዓይነቱ መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ምን ሊረዳህ ይችላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ነቢያት መሲሑን በማያሻማ መንገድ ለመለየት የሚያስችሉ ግልጽ መስፈርቶችን በጊዜ ሂደት ሲመዘግቡ ቆይተዋል። እነዚህ ነቢያት በተለያዩ ጊዜያት ያቀረቧቸው ዝርዝር መረጃዎች የመሲሑን ማንነት ቀስ በቀስ አሳይተዋል። ሄነሪ ሃሌይ እንዲህ ብለዋል:- “ከዚህ ቀደም ተያይተውም ሆነ በምንም መንገድ ተገናኝተው የማያውቁ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች የአንድ ከእብነ በረድ የተሠራ ቅርጽ ክፍልፋዮችን አንድ ክፍል ውስጥ ቢያስቀምጡና እነዚህ ክፍልፍዮች አንድ ላይ ሲገጣጠሙ ቅርጹ የተሟላ ቢሆን፣ አንድ ግለሰብ ምስሉን በዝርዝር ከሠራ በኋላ ለእያንዳንዳቸው ክፍልፍዮቹን ልኮላቸዋል ከማለት በስተቀር ምን ሊባል ይቻላል?” ቀጥሎም እንዲህ በማለት ጠይቀዋል:- “ኢየሱስ ከመምጣቱ ከብዙ ዓመታት በፊት ስለ እርሱ ሕይወትና ስለሚያከናውነው ሥራ በተለያዩ ዘመናት በኖሩ የተለያዩ ሰዎች የተጻፉት ድንቅ መረጃዎች ከሰው የማሰብ ችሎታ በላይ የሆነ አእምሮ ባለው አካል አመራር ካልሆነ በቀር እንዴት ሊጻፉ ይችላሉ?” ሃሌይ ሲደመድሙ “ይህ እስከ ዛሬ ከታዩት ሁሉ የላቀ ተአምር ነው!” ብለዋል።

ይህ “ተአምር” የሚጀምረው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ነው። የመሲሑን ሚና ከሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው የመጀመሪያው ትንቢት በተጨማሪ የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ መሲሑ ከአብርሃም የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ዘግቧል። (ዘፍጥረት 3:​15፤ 22:​15-18) ሌላኛው ፍንጭ ደግሞ መሲሑ ከይሁዳ ነገድ እንደሚመጣ ገለጸ። (ዘፍጥረት 49:​10) አምላክ፣ መሲሑ ከሙሴም ጭምር የሚበልጥ ቃል አቀባይና ነጻ አውጪ እንደሚሆን በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል።​—⁠ዘዳግም 18:​18

በንጉሥ ዳዊት የንግሥና ዘመን፣ መሲሑ የዳዊት ዙፋን ወራሽ እንደሚሆንና መንግሥቱም ‘ለዘላለም እንደሚጸና’ የሚገልጽ ትንቢት ተነገረ። (2 ሳሙኤል 7:​13-16) የሚክያስ መጽሐፍ ደግሞ መሲሑ የሚወለደው የዳዊት ከተማ በሆነችው በቤተልሔም እንደሆነ ገለጸ። (ሚክያስ 5:​2) ኢሳይያስም ቢሆን ከድንግል እንደሚወለድ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 7:​14) ሚልክያስ ደግሞ እንደ ኤልያስ ዓይነት ነቢይ የመሲሑን መምጣት እንደሚያውጅ ትንቢት ተናግሯል።​—⁠ሚልክያስ 4:​5, 6

ከዚህ በተጨማሪ ስለ መሲሑ አመጣጥ በዝርዝር ተዘግቦ የሚገኘው በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ነው። ትንቢቱ መሲሑ የሚገለጥበትን ዓመት ለይቶ ሲያመለክት እንዲህ ይላል:- “ይህንን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል። ኢየሩሳሌም ከጐዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋር ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።”​—⁠ዳንኤል 9:​25

የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ በ20ኛው የግዛት ዘመኑ ኢየሩሳሌም እንድትታደስና እንድትጠገን ‘ዐዋጅ’ አወጣ። የእርሱ የግዛት ዘመን የጀመረው በ474 ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለሆነ 20ኛው የግዛት ዘመኑ 455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሆናል። (ነህምያ 2:​1-8) ስለዚህ እነዚህ በትንቢት የተነገሩት 69 (62 ሲደመር 7) ሳምንታት ኢየሩሳሌም እንድትታደስና እንድትጠገን ትእዛዝ ከወጣበት ጀምሮ መሲሑ እስከሚመጣበት ያለውን ጊዜ ይሸፍናሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሥልሳ ዘጠኝ ሳምንታት ቃል በቃል ከተወሰዱ 483 ቀናት ወይም ሁለት ዓመት የማይሞላ ጊዜ ይሆናሉ። ነገር ግን “አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ . . . ሰጥቼሃለሁ” በሚለው ትንቢታዊ ደንብ መሠረት መሲሑ መገለጥ ያለበት ከ483 ዓመታት በኋላ ማለትም በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር።​—⁠ሕዝቅኤል 4:​6 የ1954 ትርጉም  a

ምንም እንኳ በተለያዩ ዘመናት መሲሕ ነን የሚሉ ሰዎች ቢነሱም በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መሲሕ ሆኖ የተገለጠው ግን የናዝሬቱ ኢየሱስ ብቻ ነበር። (ሉቃስ 3:​1, 2) ልክ በዚያው ዓመት ኢየሱስ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በመምጣት በውኃ ተጠመቀ። በዚህ ወቅት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት መሲሕ ሆነ። ብዙም ሳይቆይ፣ እንደ ኤልያስ ያለ ነቢይ የተባለውና መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን አስቀድሞ የተነገረለት ዮሐንስ፣ ለእንድርያስና ለአንድ ሌላ ደቀ መዝሙር “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ኢየሱስን አስተዋወቃቸው።​—⁠ዮሐንስ 1:​29፤ ሉቃስ 1:​13-17፤ 3:​21-23

መሲሑን ለመለየት የሚያስችል የዘር ሐረግ

በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ትንቢቶች መሲሑ ከየትኞቹ የአይሁዳውያን ቤተሰቦች እንደሚመጣ ጠቁመዋል። በመሆኑም ሁሉን አዋቂ የሆነው ፈጣሪ የመሲሑን የትውልድ መስመር ማረጋገጥ እንዲቻል የዘር ሐረግ ዝርዝር የያዙት መዛግብት ባሉበት ወቅት መሲሑ እንዲገለጥ ማድረጉ ምክንያታዊ ነው።

በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ “የአይሁዳውያን ቤተሰቦች የትውልድ መዝገብ የጠፋው ኢየሩሳሌም [በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ] በወደመችበት ጊዜ እንጂ ከዚያ በፊት እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም” በማለት ይናገራል። ማቴዎስና ሉቃስ የወንጌል ዘገባቸውን ያሰፈሩት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ70 ቀደም ብለው እንደሆነ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች አሉ። በመሆኑም የኢየሱስን የትውልድ ሐረግ በሚዘግቡበት ወቅት እነዚያን መዛግብት አመሳክረው ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 1:​1-16፤ ሉቃስ 3:​23-38) ከዚህም በላይ በዚህ ትልቅ ግምት በሚሰጠው ጉዳይ ረገድ በዘመኑ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች የኢየሱስን የዘር ሐረግ ራሳቸው ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው።

ትንቢቱ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው በአጋጣሚ ነበር?

በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙት መሲሐዊ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዲያው በአጋጣሚ ነበር? አንድ የሃይማኖት ምሁር ለተደረገላቸው ቃለ ምልልስ መልስ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “በፍጹም አይሆንም። ይህ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። አንድ ግለሰብ በሒሳብ ቀመር አማካኝነት ያገኘው ውጤት እንደሚያሳየው ስምንቱ [መሲሐዊ] ትንቢቶች ብቻ እንኳ የመፈጸማቸው አጋጣሚ ከመቶ ሚሊዮን ቢሊዮን አንድ እጅ ነው።” ሁኔታውን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “አንድ መቶ ሚሊዮን ቢሊዮን የሚያህሉ የአሜሪካ የብር ሣንቲሞች በሁለት ጫማ ከፍታ [0.6 ሜትር] ቢደረደሩ [690, 000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላትን] የቴክሳስን ከተማ ይሸፍናሉ። ከእነዚህ ሣንቲሞች መካከል አንዷ ላይ ምልክት ካደረግህ በኋላ አንድ ሰው ዓይኑ ታስሮ ያቺን ሣንቲም በመላው አገሪቱ እንዲፈልግ ቢደረግ ሳንቲሟን የማግኘቱ አጋጣሚ ምን ያህል ነው?” አክለውም “በታሪክ ዘመናት ከኖሩት ሰዎች ሁሉ [ስለ መሲሑ ከተነገሩት] ትንቢቶች መካከል ስምንቱ ብቻ እንኳ የሚፈጸሙበት ሰው ይኖራል ብሎ ማለት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል በቆየው ምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ስምንት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በጣም የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፈጽሟል። እነዚህን በርካታ ማስረጃዎች በመመልከት፣ ከላይ የተጠቀሱት ምሁር “በታሪክ ዘመናት ሁሉ እነዚህን ትንቢቶች መፈጸም የቻለው ኢየሱስ ብቻ ነው” ብለው ለመደምደም ችለዋል።

የመሲሑ ‘መምጣት’

መሲሑ በ29 ከክርስቶስ ልደት በፊት የመጣው የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚህ ወቅት የመጣው ትሑትና የተዋረደ አዳኝ ሆኖ ነበር። ኢየሱስ የመጣው አይሁዳውያንም ሆኑ ተከታዮቹ እንደጠበቁት እነርሱን ከሮማውያን ቀንበር እንደሚያላቅቅ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ አልነበረም። (ኢሳይያስ ምዕራፍ 53፤ ዘካርያስ 9:​9፤ የሐዋርያት ሥራ 1:​6-8) ወደፊት ግን የሚመጣው በኃይልና በታላቅ ሥልጣን እንደሆነ ተገልጿል።​—⁠ዳንኤል 2:​44፤ 7:​13, 14

በምድር ዙሪያ ያሉ ምክንያታዊ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በጥንቃቄ ማጥናታቸው መሲሑ በአንደኛው መቶ ዘመን እንደመጣና እንደገናም እንደሚመለስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት አስቀድሞ የተነገረው የክርስቶስ ‘መምጣት’ ወይም መገኘት የጀመረው በ1914 ነው። b (ማቴዎስ 24:​3-​14) በዚያ ዓመት ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። በኤደን የተነሳው ዓመጽ ያስከተለውን ችግር ለማስወገድ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅትም “የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ” ተስፋ የተደረገበት ዘር ወይም መሲሕ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎችን ይባርካቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 1:​29፤ ራእይ 21:​3, 4

የይሖዋ ምሥክሮች ማስረጃዎቹን አስመልክቶ ከአንተ ጋር ለመወያየት እንዲሁም የመሲሑ አገዛዝ ለአንተም ሆነ ለወዳጆችህ ምን ትርጉም እንዳለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ ዳንኤል 9:​25 ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግህ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 899-904 እና የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 186-191 ተመልከት። ሁለቱም የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።

b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና 11ን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

455 ከክ.ል.በፊት፦ ‘ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጅ ወጣ’

29 ከክ.ል.በኋላ፦ መሲሑ ተገለጠ

483 ዓመታት (69 ትንቢታዊ ሳምንታት)​—ዳንኤል 9:25

በ1914 መሲሑ በሰማይ ንጉሥ ሆነ

መሲሑ በቅርቡ ክፋትን አስወግዶ ምድርን ገነት ያደርጋታል