በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች መጠቅለል

በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች መጠቅለል

በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች መጠቅለል

“በጎ ሐሳቡ . . . በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል [“እንደገና ለመጠቅለል፣” NW ] ነው።”​—⁠ኤፌሶን 1:9, 10

1. ሰማይንና ምድርን በተመለከተ የይሖዋ ‘በጎ ሐሳብ’ ምንድን ነው?

 አጽናፈ ዓለማዊ ሰላም! “የሰላም አምላክ” የሆነው የይሖዋ ታላቅ ዓላማ ይህ ነው። (ዕብራውያን 13:20) ይሖዋ “በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል [“እንደገና ለመጠቅለል፣” NW ]” በጎ ሐሳብ ያለው መሆኑን እንዲጽፍ ሐዋርያው ጳውሎስን በቅዱስ መንፈሱ መርቶት ነበር። (ኤፌሶን 1:9, 10) በዚህ ጥቅስ ላይ “እንደገና ለመጠቅለል” ተብሎ የተተረጎመው ግስ ምን ትርጉም አለው? ጆን ላይትፉት የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “ይህ አገላለጽ አጽናፈ ዓለም በሙሉ እርስ በርስ ስምም እንደሚሆን እንዲሁም የተለዩና መከፋፈል የሚፈጥሩ አካላት ተወግደው ሁሉም አባላት በክርስቶስ አንድ እንደሚሆኑ ያመለክታል። ኃጢአትና ሞት፣ ሐዘን . . . እንዲሁም ሥቃይ አይኖርም።”

‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’

2. በክርስቶስ የሚጠቀለሉት ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ እነማን ናቸው?

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” ብሎ ሲጽፍ የሁሉንም ክርስቲያኖች ድንቅ ተስፋ ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። (2 ጴጥሮስ 3:13) እዚህ ላይ ቃል የተገባው “አዲስ ሰማይ” አዲሱ አገዛዝ ማለትም መሲሐዊው መንግሥት ነው። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የጠቀሳቸው ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ የሚጠቀለሉት “በክርስቶስ ሥር” ሲሆን እነዚህ ነገሮች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ የተመረጡትን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ያመለክታሉ። (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ 144, 000 ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ባለው መንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ ‘ከምድር የተዋጁ’ እንዲሁም “ከሰዎች መካከል የተዋጁ” እንደሆኑ ተገልጿል።​—⁠ራእይ 5:9, 10፤ 14:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21፤ ኤፌሶን 1:11፤ 3:6

3. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ገና በምድር ላይ እያሉም ‘በሰማያዊ ስፍራ እንደተቀመጡ’ የተገለጸው ለምንድን ነው?

3 በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች የይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ዳግም ተወልደዋል። (ዮሐንስ 1:12, 13፤ 3:5-7) ይሖዋ እንደ “ልጆቹ” አድርጎ ስለተቀበላቸው የኢየሱስ ወንድሞች ሆነዋል። (ሮሜ 8:15፤ ኤፌሶን 1:5) በዚህ የተነሳ ምድር ላይ እያሉም እንኳ ‘ከክርስቶስ ጋር ተነስተው በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር እንደተቀመጡ’ ተደርገው ተገልጸዋል። (ኤፌሶን 1:3፤ 2:6) እንደዚህ ያለውን የላቀ መንፈሳዊ ቦታ ሊያገኙ የቻሉት “ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም [ስለታተሙ]” ነው፤ ይህ ማኅተም በሰማይ ለተቀመጠላቸው “[ርስት] ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው።” (ኤፌሶን 1:13, 14፤ ቈላስይስ 1:5) እንግዲያው፣ ይሖዋ አጠቃላይ ቁጥራቸውን አስቀድሞ በወሰነው መሠረት መጠቅለል የሚያስፈልጋቸው ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ እነዚህ ናቸው።

የመጠቅለሉ ሥራ ተጀመረ

4. ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ መጠቅለል የተጀመረው መቼና እንዴት ነው?

4 ከይሖዋ “አስተዳደር” ማለትም ነገሮችን ከሚያከናውንበት መንገድ ጋር በሚስማማ መልኩ ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ የመጠቅለሉ ሥራ የሚጀምረው “በዘመን ፍጻሜ” ወይም እርሱ በወሰነው ጊዜ ማብቂያ ላይ ነበር። (ኤፌሶን 1:10) በዚህም መሠረት፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ይህ የመጠቅለል ሥራ ጀመረ። በዚያን ዕለት ሐዋርያቱ እንዲሁም ሌሎች ወንድና ሴት ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው። (የሐዋርያት ሥራ 1:13-15፤ 2:1-4) ይህም አዲሱ ቃል ኪዳን መሥራት እንደጀመረ የሚጠቁም ነበር፤ በዚህም የተነሳ የክርስቲያን ጉባኤ እንዲሁም ‘የእግዚአብሔር የሆነው እስራኤል’ ማለትም መንፈሳዊ እስራኤልን ያቀፈው አዲሱ ብሔር ተወለደ።​—⁠ገላትያ 6:16፤ ዕብራውያን 9:15፤ 12:23, 24

5. ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን የሚተካ አዲስ “ሕዝብ” የፈጠረው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ጋር የገባው የሕጉ ቃል ኪዳን በሰማይ ለዘላለም የሚያገለግሉ “የመንግሥት ካህናት [እና] የተቀደሰ ሕዝብ” አላስገኘም። (ዘፀአት 19:5, 6) ኢየሱስ ለአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 21:43) ይህ ሕዝብ ማለትም መንፈሳዊው እስራኤል በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱትን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል።” (1 ጴጥሮስ 2:9, 10) ሥጋዊ እስራኤላውያን የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝቦች መሆናቸው ቀረ። (ዕብራውያን 8:7-13) ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው የመሲሐዊው መንግሥት ክፍል የመሆኑ መብት ከእነርሱ ተወስዶ ለ144, 000ዎቹ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ተሰጠ።​—⁠ራእይ 7:4-8

የመንግሥት ቃል ኪዳን ገቡ

6, 7. ኢየሱስ በመንፈስ ከተወለዱ ወንድሞቹ ጋር ምን ልዩ ቃል ኪዳን ገብቷል? ይህስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?

6 ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ባቋቋመበት ዕለት ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።” (ሉቃስ 22:28-30) ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረው “እስከ ሞት ድረስ ታማኝ” ከሆኑትና ‘ድል ከነሱት’ 144, 000 በመንፈስ የተወለዱ ወንድሞቹ ጋር ስለገባው ልዩ ቃል ኪዳን ነበር።​—⁠ራእይ 2:​10፤ 3:​21

7 ጥቂት ቁጥር ያላቸው የዚህ ቡድን አባላት ሰብዓዊ አካል ኖሯቸው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ተስፋ መሥዋዕት አድርገዋል። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ይገዛሉ፤ እንዲሁም በዙፋን ላይ ተቀምጠው በሰው ልጆች ላይ ይፈርዳሉ። (ራእይ 20:​4, 6) እስቲ አሁን ደግሞ በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ብቻ የተጻፉትንና “ሌሎች በጎች” በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ የማይካፈሉበትን ምክንያት የሚጠቁሙ ጥቅሶችን እንመልከት።​—⁠ዮሐንስ 10:​16

8. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከቂጣው መካፈላቸው ምን ትርጉም አለው? (በገጽ 23 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

8 በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉ ሲሆን እንደ እርሱ ያለ ሞት ለመሞትም ፈቃደኞች ናቸው። የዚህ ቡድን አባል የሆነው ጳውሎስ ‘ክርስቶስን ያገኝ ዘንድ . . . ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል ለማወቅ እንዲሁም በሥቃዩ ተካፋይ ለመሆን’ ሲል ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። አዎን፣ ጳውሎስ ‘በሞቱም እርሱን ለመምሰል’ ፈቃደኛ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:8, 10) በርካታ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በምድር ላይ እያሉ “የኢየሱስን ሞት” ይኸውም በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ዓይነት ለሞት ሊዳርግ የሚችል መከራ ዘወትር በሰውነታቸው ተሸክመዋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​10

9. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው ቂጣ ምን ያመለክታል?

9 ኢየሱስ የጌታ እራትን ባቋቋመበት ወቅት “ይህ ሥጋዬ ነው” ብሏል። (ማርቆስ 14:​22) ይህን ሲል፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚገረፈውንና በደም የሚበከለውን ሰውነቱን ማመልከቱ ነበር። እርሾ የሌለበት ቂጣ ለኢየሱስ ሥጋ ተስማሚ ምሳሌ ነው። ለምን? ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ ኃጢአትን ወይም ክፋትን ሊያመለክት ይችላል። (ማቴዎስ 16:4, 11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 5:6-8) ኢየሱስ ፍጹም የነበረ ከመሆኑም በላይ ሰብዓዊ አካሉ ከኃጢአት የጸዳ ነበር። ይህንን ፍጹም ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። (ዕብራውያን 7:26፤ 1 ዮሐንስ 2:2) ይህን ማድረጉ በሰማይ የመኖርም ሆነ ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ ይጠቅማል።​—⁠ዮሐንስ 6:​51

10. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከወይኑ የሚካፈሉት ክርስቲያኖች “ከክርስቶስ ደም ጋር ኀብረት” የሚኖራቸው በምን መንገድ ነው?

10 ጳውሎስ፣ በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ስለሚጠጡት የወይን ጠጅ ሲጽፍ “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኀብረት ያለው አይደለምን?” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:16) ከወይኑ የሚካፈሉት ክርስቲያኖች “ከክርስቶስ ደም ጋር ኀብረት” የሚኖራቸው በምን መንገድ ነው? እነርሱ ራሳቸው መዳን ስለሚያስፈልጋቸው ከክርስቶስ ጋር ሆነው ለሰው ልጆች ቤዛዊ መሥዋዕት ሊያቀርቡ አይችሉም። የክርስቶስ ደም ባለው የማዳን ኃይል በማመናቸው ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ከመሆኑም በላይ በሰማይ ሕይወት ለማግኘት እንዲችሉ ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። (ሮሜ 5:8, 9፤ ቲቶ 3:4-7) ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች የሆኑት 144, 000 ክርስቲያኖች ‘የተቀደሱት፣’ የተለዩት እንዲሁም “ቅዱሳን” ለመሆን ከኃጢአት የነጹት በፈሰሰው የክርስቶስ ደም አማካኝነት ነው። (ዕብራውያን 10:29፤ ዳንኤል 7:18, 27፤ ኤፌሶን 2:19) በእርግጥም ክርስቶስ “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር [የዋጀውና] ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት [ያደረጋቸው]” በፈሰሰው ደሙ አማካኝነት ነው፤ “እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”​—⁠ራእይ 5:9, 10

11. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበውን ወይን በመጠጣት ምን ያሳያሉ?

11 ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያቋቁም ለታማኝ ሐዋርያቱ ወይን የያዘ ጽዋ ከሰጣቸው በኋላ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:27, 28) አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር የገባው የሕጉ ቃል ኪዳን በበሬዎችና በፍየሎች ደም እንደጸና ሁሉ፣ ይሖዋ ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር የገባው አዲስ ቃል ኪዳንም በኢየሱስ ደም ጸንቷል። (ዘፀአት 24:5-8፤ ሉቃስ 22:20፤ ዕብራውያን 9:14, 15) በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ‘የአዲስ ኪዳን ደሙን’ የሚወክለውን ወይን በመጠጣት በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንደተካተቱና ይህ ቃል ኪዳን ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች እየተካፈሉ መሆናቸውን ያሳያሉ።

12. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቁት እንዴት ነው?

12 በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከጽዋው ሲጠጡ ሌላም የሚያስታውሱት ነገር አለ። ኢየሱስ ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማርቆስ 10:38, 39) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን እንደ ተጠመቁ’ ተናግሯል። (ሮሜ 6:​3) በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል። በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋቸውን በፈቃዳቸው ስለሚተዉ ሞታቸው መሥዋዕታዊ ሞት ነው። እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ታማኝ ሆነው ከሞቱ በኋላ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ‘ለመንገሥ’ መንፈሳዊ ፍጡሮች ሆነው ትንሣኤ ሲያገኙ፣ ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን የሚጠመቁት ጥምቀት ያበቃል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:10-12፤ ሮሜ 6:5፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42-44, 50

ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል

13. ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከቂጣና ወይኑ የማይካፈሉት ለምንድን ነው? ታዲያ በመታሰቢያው በዓል ላይ ለምን ይገኛሉ?

13 በመታሰቢያው በዓል ወቅት ከሚዞረው ቂጣና ወይን መካፈል ይህንን ሁሉ የሚያካትት በመሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከቂጣና ወይኑ መካፈላቸው ተገቢ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ አካል አባላት እንዳልሆኑና ይሖዋ ከክርስቶስ ጋር ከሚገዙት ሰዎች ጋር ባደረገው አዲስ ቃል ኪዳን እንደማይታቀፉ ይገነዘባሉ። ‘ጽዋው’ አዲሱን ቃል ኪዳን የሚያመለክት በመሆኑ ከቂጣና ወይኑ መካፈል የሚችሉት በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት አግኝተው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን አልተጠመቁም፤ ከእርሱ ጋር በሰማይ ለመግዛትም አልተመረጡም። እነዚህ ክርስቲያኖች ከቂጣውና ከወይኑ ቢካፈሉ እንዲህ ማድረጋቸው ስለ እነርሱ የተሳሳተ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። በመሆኑም በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው ሥነ ሥርዓቱን በአክብሮት ይከታተላሉ እንጂ ከቂጣና ወይኑ አይካፈሉም። ይሖዋ፣ በፈሰሰው የክርስቶስ ደም አማካኝነት ይቅርታ የሚያገኙበትን መንገድ ማዘጋጀቱን ጨምሮ በልጁ በኩል ላደረገላቸው ነገሮች በሙሉ አመስጋኝ ናቸው።

14. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈላቸው በመንፈሳዊ የሚበረታቱት እንዴት ነው?

14 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውና ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ የተጠሩት ክርስቲያኖች በሙሉ ታትመው የሚጠናቀቁበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች፣ በምድር ላይ የሚኖሩት መሥዋዕት አድርገው የሚሰጡት ምድራዊ ሕይወት እስኪያበቃ ድረስ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈል መንፈሳዊ ማበረታቻ ያገኛሉ። እንዲህ በማድረጋቸው የክርስቶስ አካል ክፍል ከሆኑት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አንድነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። ምሳሌያዊ ከሆኑት ቂጣና ወይን መካፈላቸው እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆነው የመቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስታውሳቸዋል።​—⁠2 ጴጥሮስ 1:10, 11

‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ መጠቅለል

15. በመንፈስ ከተቀቡት ክርስቲያኖች ጎን የቆሙት እነማን ናቸው?

15 ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ‘የታናሹ መንጋ’ አባላት ያልሆኑና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ቁጥራቸው እያደገ የመጣ “ሌሎች በጎች” በመንፈስ ከተቀቡት ክርስቲያኖች ጋር ተባብረዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም ፤ ዘካርያስ 8:23) እነዚህ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት የሚደግፉ ከመሆኑም በላይ ለሕዝብ ሁሉ ምስክር የሚሆነውን “የመንግሥት ወንጌል” በመስበኩ ሥራ ላይ ትልቅ እርዳታ አበርክተዋል። (ማቴዎስ 24:​14፤ 25:40) እንዲህ በማድረጋቸውም ክርስቶስ በአሕዛብ ላይ ለመፍረድ ሲመጣ “በጎቹ” እንደሆኑ ከሚፈረድላቸውና ተቀባይነት አግኝተው “በቀኙ” በኩል ከሚቆሙት መካከል የመቆጠር አጋጣሚ ይኖራቸዋል። (ማቴዎስ 25:33-36, 46) በክርስቶስ ደም በማመናቸው “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አባላት ይሆናሉ።​—⁠ራእይ 7:9-14

16. ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ እነማንን ይጨምራሉ? እነዚህ ሁሉ ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ የመሆን አጋጣሚ የሚያገኙት እንዴት ነው?

16 ቀሪዎቹ የ144, 000 አባላት ታትመው ሲያበቁ የጥፋት “ነፋሶች” በምድር ላይ በሚገኘው ክፉ የሰይጣን ሥርዓት ላይ ይለቀቃሉ። (ራእይ 7:1-4) ኢየሱስ አብረውት ካሉት ነገሥታትና ካህናት ጋር ለሺህ ዓመት በሚገዛበት ወቅት ትንሣኤ የሚያገኙት ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከእጅግ ብዙ ሕዝብ ጋር ይቀላቀላሉ። (ራእይ 20:12, 13) እነዚህም በመሲሐዊው ንጉሥ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ግዛት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል። በሺህ ዓመቱ ግዛት መደምደሚያ ላይ እነዚህ ሁሉ ‘በምድር ያሉ ነገሮች’ ለመጨረሻ ጊዜ ፈተና ይቀርብላቸዋል። ፈተናውን በታማኝነት ያለፉት ሰዎች በምድር የሚገኙ ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ ሆነው ይቆጠራሉ።​—⁠ኤፌሶን 1:10፤ ሮሜ 8:21፤ ራእይ 20:7, 8

17. የይሖዋ ዓላማ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

17 በዚህ መንገድ ይሖዋ በአንድ “አስተዳደር” ወይም ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ አማካኝነት “በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል [“እንደገና ለመጠቅለል፣” NW ]” ያለውን ዓላማ ይፈጽማል። በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኙ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ ዓላማውን በመፈጸም ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ለሆነው ለይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ በደስታ በመገዛት በአጽናፈ ዓለማዊ ሰላም ይጠቃለላሉ።

18. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖችም ሆኑ ባልንጀሮቻቸው በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘታቸው ምን ጥቅም ያገኛሉ?

18 ጥቂት ቁጥር ያላቸው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችም ሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ ባልንጀሮቻቸው ሚያዝያ 12, 2006 በሚከበረው በዓል ላይ መገኘታቸው እምነታቸውን በጣም ያጠናክርላቸዋል! ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት እንዳዘዘው የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ። (ሉቃስ 22:19) በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሁሉ ይሖዋ በውድ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ያደረገላቸውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል።

ለክለሳ ያህል

• በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው?

• ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ እነማን ናቸው? እነዚህስ የተሰበሰቡት እንዴት ነው?

• ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ እነማን ናቸው? ተስፋቸውስ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘የክርስቶስ አካል’

ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:​16, 17 ላይ በመንፈስ ለተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች የቂጣውን ትርጉም ሲያብራራ “አካል” የሚለውን ቃል ለየት ባለ መንገድ ተጠቅሞበታል። “የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ [“አካል፣” NW ] ጋር ኀብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” በማለት ጽፎላቸዋል። በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ቂጣ መካፈላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ካቀፈው ጉባኤ ጋር ያላቸውን አንድነት ያሳያል፤ ይህ ጉባኤ እንደ አንድ አካል ሲሆን ራሱ ደግሞ ክርስቶስ ነው።​—⁠ማቴዎስ 23:​10፤ 1 ቆሮንቶስ 12:​12, 13, 18

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ አስተዳደር አማካኝነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት ፍጥረታት በሙሉ አንድነት ይኖራቸዋል