በቦሊቪያ፣ ርቀው የሚገኙት ከተሞች ምሥራቹን ሰሙ
በቦሊቪያ፣ ርቀው የሚገኙት ከተሞች ምሥራቹን ሰሙ
ሃያ የምንሆን ሰዎች በወንዙ መነሻ አካባቢ የሚገኙ መንደሮችን ለመጎብኘት የምናደርገውን የአንድ ቀን ጉዞ ለመጀመር በጉጉት እየተጠባበቅን በወንዙ ዳርቻ ተሰባስበናል። ያለነው የቤኒ ወንዝ ሰፊ ወደሆነው የአማዞን አካባቢ በሚደርስበት በአንዲስ ተራሮች ግርጌ ሲሆን ይህ ቦታ ልዩ የሆነ ውበት አለው።
ይሁን እንጂ እዚህ የመጣነው አገር ለመጎብኘት አይደለም። አንዳንዶቻችን የአገሬው ተወላጆች ስንሆን ብዙዎቻችን ግን እዚህ ሩሬናባኪ ለመኖር ራቅ ካሉ ከተሞች የመጣን ነን። በዚህች የምታምር አነስተኛ ከተማ አበባ ያላቸው ዛፎችና ጣሪያቸው በሣር የተሸፈነ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን መንገዶቿም አንዳንድ ጊዜ የሞተር ብስክሌት ታክሲ ሲያልፍ ከሚያሰማው ድምጽ በስተቀር ረጭ ያሉ ናቸው። ሆኖም ይህንን ጉዞ ያደረግነው ለምንድን ነው?
እንደዚህ የመሰለው ጉዞ በተለያዩ የቦሊቪያ ክፍሎች ውስጥም ይደረጋል። በቦሊቪያ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩም ሆኑ ከሌሎች አገሮች የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት የምሥራች ወደ ትንንሽ ከተሞች እያዳረሱ ነው።—ማቴዎስ 24:14
ቦሊቪያ በማዕከላዊ ደቡብ አሜሪካ የምትገኝ አገር ናት። የቦሊቪያ የቆዳ ስፋት የፈረንሳይን ሁለት እጥፍ ቢሆንም የሕዝቧ ብዛት ግን ከፈረንሳይ ሕዝብ አሥር በመቶ ያህል ነው። አብዛኛው የቦሊቪያ ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች እንዲሁም ደስ የሚል እይታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የማእድን ማውጫ ከተሞች ወይም ደግሞ የግብርና ሥራዎች በሚካሄዱባቸው ሸለቆዎች ውስጥ ነው። ሞቃት በሆኑት ቆላማ ቦታዎች በሚገኙት ከተሞች መካከል ሰፋፊ ደኖች አሉ።
በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ዓመታት እንደ ቤቲ ጃክሰን፣ ኤልሲ ሜየንበርግ፣ ፓምላ ሞዝሊና ሻርሎት ቶማሻፍስኪ ያሉ ደፋር ሚስዮናውያን ራቅ ባሉ ከተሞች የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት አከናውነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ቅን ለሆኑ ሰዎች አስተምረዋል፤ እንዲሁም ትንንሽ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ረድተዋል። በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በስድስት እጥፍ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን አብዛኛው እድገት የተገኘው በከተሞች ውስጥ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢው ጉባኤዎች አሉ። በረጃጅም ፎቆች ላይ በሚገኙ ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ፣ በሚያማምሩ ትላልቅ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩና በገበያ ማዕከሎች ውስጥ ዕቃ የሚገዙ ሀብታም ሰዎች ባሉባቸው አካባቢዎችም ሆነ ከጡብ በተሠሩ ጎጆዎች ውስጥ የሚኖሩ፣ በጉሊቶች የሚገበያዩና በቀለማት ያሸበረቁ የአገር ልብሶችን የሚለብሱ ሰዎች ባሉባቸው ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ጉባኤዎች አሉ። ሆኖም በእነዚህ ራቅ ያሉ ሥፍራዎች የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል?
ምቹ የሆነውን የከተማ ሕይወት መሥዋዕት ማድረግ
ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት፣ በቦሊቪያ የማዕድን ማውጫ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሰዎች ወደ ከተማ ፈልሰዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ከከተማ ወደ ገጠር መሄድ ያልተለመደ ነገር ነው። በአብዛኞቹ ገጠራማ መንደሮች ውስጥ አንድ ስልክ ብቻ የሚገኝ ሲሆን በቀን ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚኖረው ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ነው። በእነዚህ ትንንሽ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከእምነት ወንድሞቻቸው ጋር የሚገናኙት በዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ብቻ ሲሆን ወደ እነዚህ ስብሰባዎች መጓዙም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ፣ አደገኛና አድካሚ ሊሆን ይችላል። በመንደሩ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት መሠረታዊ ትምህርት ብቻ ነው። ታዲያ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ከከተማ ወደ ገጠሩ አካባቢ ለመሄድ ያነሳሳቸው ምን ሊሆን ይችላል?
ሉዊስ የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “በቅርቡ በላፓዝ ከተማ ጥሩ ሥራ የመያዝ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ሆኖም ወላጆቼ ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ ከሁሉ የበለጠ መሆኑን ሁልጊዜ ይነግሩኝ ነበር። በዚህም ምክንያት በግንባታ ሞያ አጭር ሥልጠና ወሰድኩ። ለእረፍት ወደ ሩሬናባኪ በሄድኩበት ወቅት እዚያ የሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ጉጉት እንዳላቸው ተገነዘብኩ። እዚያ ያሉ ወንድሞች በጣም ጥቂት መሆናቸውን ስመለከት እነርሱን መርዳት እንዳለብኝ ተሰማኝ። በአሁኑ ጊዜ 12 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠና ሲሆን ከእነዚህም መካከል አራት ልጆች ያሏቸው ወጣት ባልና ሚስት ይገኛሉ። ባልየው ከልክ በላይ ይጠጣና ቁማር ይጫወት የነበረ ቢሆንም ሁሉንም እርግፍ አድርጎ በመተው ስለ ይሖዋ የሚማረውን ነገር ለጓደኞቹ መናገር ጀመረ። ለጥናቱ ሁልጊዜ ይዘጋጅ ነበር። ዛፍ ለመመንጠር ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት ወደ ጫካ ሲሄድ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ስለማይችል በጣም ያዝናል። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ስመለከት እዚህ ለመምጣት መሥዋዕት መክፈሌ የማያስቆጭ እንደሆነ ይሰማኛል።”
ሕዋና የተባለች ነጠላ ወላጅ እንዲህ ትላለች:- “በላፓዝ የቤት ሠራተኛ ሆኜ እሠራ ነበር። ልጄ ትንሽ እያለ በዚሁ ከተማ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ። በአንድ ወቅት ሩሬናባኪን ስጎበኝ ወደዚህ ብመጣ ምን ያህል ልሠራ እንደምችል ተገነዘብኩ። ወደዚህ ከመጣን በኋላም በቤት ሠራተኝነት ተቀጠርኩ። መጀመሪያ ላይ ሙቀቱም ሆነ ትናንሽ ነፍሳት አስቸግረውን የነበረ ቢሆንም እንኳ አሁን እዚህ ከመጣን ሰባት ዓመት ሆኖናል። በየሳምንቱ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ችያለሁ፤ በርካታ ጥናቶቼም ወደ ስብሰባ በመምጣት አድናቆታቸውን እያሳዩ ነው።” ሕዋና እና ልጇ ወደ ወንዞቹ መነሻ አካባቢ ለመሄድ በጀልባ ከተሳፈሩት መካከል ይገኛሉ። አንተም ከእኛ ጋር መምጣት ትችላለህ።
ወደ ወንዞቹ መነሻ ያደረግነው ጉዞ
በተራሮቹ መካከል ወዳለው ጠባብ ቦታ ስናመራ የጀልባው ሞተር በኃይል ይጮኽ ጀመር። በቀቀን የተባሉት ወፎች በመምጣታችን አለመደሰታቸውን ለመግለጽ ሲያንቋርሩ ነበር። ከተራሮቹ የሚወርደው በጭቃ የደፈረሰ ውኃ ወደ እኛ ሲመጣ የጀልባዋ ነጂ ማዕበሉን በዘዴ አለፈው። ረፋዱ አካባቢ አንዲት ትንሽ መንደር ስንደርስ ወረድን። እዚያም ከሩሬናባኪ ጉባኤ ሽማግሌ ጋር ከተገናኘን በኋላ የት መስበክ እንዳለብን አሳየን።
የመንደሩ ሰዎች በዛፍ ጥላ ሥር እንድናርፍ ወይም በቀርከሃ ተሠርተው ጣሪያቸው በዘንባባ ቅጠል ወደ ተሸፈኑ ቤቶች ውስጥ እንድንገባ በመጋበዝ በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉን። ብዙም ሳይቆይ አንድ ባልና ሚስት ከእንጨት በተሠራ መጭመቂያ የሸንኮራ አገዳ እየጨመቁ አገኘናቸው። ከሸንኮራ አገዳው የሚወጣው ጭማቂ ከመዳብ በተሠራ ጎድጓዳ ሳሕን ውስጥ ይጠራቀም ነበር። ከዚያም ጭማቂውን በማፍላት ሞላሰስ የሚባል ስኳር ለመስራት የሚያገለግል ጠቆር ያለ ንጥረ ነገር ካዘጋጁ በኋላ ከተማ ወስደው ይሸጡታል። እነዚህ ባልና ሚስት ቤታቸው እንድንገባ ከጋበዙን በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጥያቄዎች ጠየቁን።
ወንዙን ተከትለን በመጓዝ ከመንደር ወደ መንደር እየሄድን መስበካችንን ቀጠልን። ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ በሽታና ሞት እንደሚወገዱ እንደሚናገር ሲሰሙ በጣም ደስ አላቸው። (ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24) በአካባቢው የሕክምና ጣቢያ እንደልብ ስለማይገኝ ልጅ የሞተባቸው በርካታ ቤተሰቦች መሪር ሐዘን ደርሶባቸዋል። ገበሬዎችና ዓሣ አጥማጆች ሆነው የሚገፉት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ በጣም አድካሚ ከመሆኑም በላይ አስተማማኝነት የለውም። በመሆኑም አብዛኞቹ አምላክ ድህነትን የሚያስወግድ መንግሥት እንደሚያመጣ የሚናገረውን የመዝሙር 72ን ጥቅስ አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል። ራቅ ብለው በሚገኙ በእነዚህ ሥፍራዎች የሚኖሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት የሚያደርጉ ይመስልሃል? ይህ ጥያቄ በአማዞን አካባቢ፣ በመኪና የሦስት ሰዓት መንገድ ያህል ርቆ በሚገኘው በሳንታ ሮሳ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑትን ኤሪክንና ቪኪን አሳስቧቸው ነበር።
ፍላጎት ያሳዩት ሰዎች ይመጡ ይሆን?
ኤሪክና ቪኪ ከካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቦሊቪያ ከመጡ 12 ዓመት ሆኗቸዋል። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወደ ሳንታ ሮሳ እንዲሄዱ ሐሳብ አቅርቦላቸው ነበር። ቪኪ እንዲህ ትላለች:- “በከተማው ውስጥ ያሉት ሁለት የስልክ መስመሮች ብቻ ሲሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጽሞ ማግኘት አይቻልም። የዱር አራዊቶች በብዛት ስላሉ ራቅ ብለው ወደሚገኙ ቦታዎች በሞተር ብስክሌታችን ስንሄድ አርጃኖዎችን፣ ሰጎኖችንና ትላልቅ እባቦችን ማየታችን የተለመደ ነገር ነው። ከእንስሳቱ ይበልጥ ደስ የሚሉት ግን ሰዎቹ ናቸው። ቫካ የሚባልን አንድ ወጣት ከባለቤቱና ከአራት ትናንሽ ልጆቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናቸዋለን። ይህ ቤተሰብ የሚኖረው ከከተማው ውጭ 26 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው። አባትየው ከዚህ ቀደም ጠጪ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ተለውጧል። በየሳምንቱ መላ ቤተሰቡንና ታናሽ እህቱን ይዞ ወደ መንግሥት አዳራሹ ይመጣል። በብስክሌቱ ዕቃ መጫኛ ላይ ሚስቱንና ትንሿን ልጁን ያስቀምጣቸዋል። በሌላ ብስክሌት የዘጠኝ ዓመቱ ልጅ ታናሽ እህቱን ይዞ ሲሄድ፣ የስምንት ዓመቱ ልጅ ደግሞ የራሱን ብስክሌት ይነዳል። እዚያ ለመድረስ ሦስት ሰዓት ያህል ይፈጅባቸዋል።” የቤተሰቡ አባላት ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ሲሆን ከጉባኤው ጋር ለመሰብሰብ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሦስት ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን በሳንታ ሮሳ በሚገኘው አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ 25 ያህል ሆነው ይሰበሰባሉ። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ቢፈልጉም እንኳ ይሖዋን ለማገልገል እንዲችሉ ከባድ ችግሮችን መወጣት አስፈልጓቸዋል።
ጋብቻን ሕጋዊ ለማድረግ ያለው ፈታኝ ሁኔታ
ቦሊቪያ ከብራዚል ጋር በምትዋሰንበት ጠረፍ አካባቢ ራቅ ብላ በምትገኝ ከተማ የሚያገለግሉት ማሪና እና ኦስኒ የተባሉ ሚስዮናውያን እንደተናገሩት በአካባቢው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ሳይጋቡ ከተለያዩ ሰዎች ጋር አብረው ስለሚኖሩ ጋብቻን እንደ ቋሚ ትስስር አድርገው አይመለከቱትም። ኦስኒ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆነባቸው ይህ ነው። ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ለመሆን ሲፈልጉ የተወሳሰበና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ሂደት ይጠብቃቸዋል። አንዳንዶች በፊት አብረዋቸው ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች ጋር መለያየትና በሕጋዊ ሁኔታ ትዳር መመሥረት አስፈልጓቸዋል። ጋብቻን በሕግ ማስመዝገብ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርት መሆኑን በመገንዘብ አንዳንዶች ሕግ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስፈጸሚያ የሚሆናቸውን ብር ለማግኘት ብርቱ ጥረት አድርገዋል።”—ሮሜ 13:1, 2፤ ዕብራውያን 13:4
ማሪና የኖርቤርቶን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ዳቦ ጋጋሪ ከሆነች ሴት ጋር አብሮ መኖር ከመጀመሩ በፊት ከብዙ ሴቶች ጋር ይኖር ነበር። ኖርቤርቶ ይህችን ሴት በ35 ዓመት የሚበልጣት ሲሆን እንደ ልጁ አድርጎ የተቀበለው አንድ ወንድ ልጅ ነበራት። ልጁ እያደገ ሲሄድ ኖርቤርቶ ለልጁ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ፈለገ። ስለዚህ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ዳቦ ቤቱ መጥቶ ነጻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይፈልግ እንደሆነ ሲጠይቀው ምንም እንኳ ማንበብ የማይችልና ዕድሜው ከ70 ዓመት በላይ ቢሆንም ለማጥናት ተስማማ። ኖርቤርቶና አብራው የምትኖረው ሴት ይሖዋ የሚፈልግባቸው ምን እንደሆነ ሲማሩ በሕጋዊ መንገድ ተጋቡ፤ ከዚያም ተጠመቁ። ልጁም ልክ እንጀራ አባቱ እንደፈለገው ኃላፊነት የሚሰማው ክርስቲያን ወጣት ሆነ። ኖርቤርቶ ማንበብ የተማረ ከመሆኑም በላይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንግግር መስጠት ጀምሯል። ዕድሜው እየገፋ በመሄዱ አቅመ ደካማ ቢሆንም ምሥራቹን በመስበኩ ረገድ ግን ቀናተኛ ነው።”
ከይሖዋ መንፈስ ኃይል ማግኘት
ኢየሱስ ለጥንት ተከታዮቹ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ነግሯቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) የአምላክ መንፈስ ክርስቲያን ወንዶችንና ሴቶችን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እንዲሄዱ ሲያነሳሳቸው ማየቱ እንዴት ያበረታታል! ለምሳሌ፣ በ2004 በቦሊቪያ ወደ 30 የሚጠጉ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ራቅ ወዳሉ ሥፍራዎች በመሄድ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ለመሥራት ፈቃደኞች ሆነዋል። አቅኚዎች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ቤቴላውያን ወይም ሚስዮናውያን ሆነው ለማገልገል ወደ ቦሊቪያ የመጡትን 180 የሚያህሉ የውጭ አገር ወንድሞች ምሳሌነት ከልብ ያደንቃሉ። በቦሊቪያ የሚገኙት 17, 000 አስፋፊዎች 22, 000 የሚያህሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ።
እነዚህ ወንድሞች፣ በይሖዋ መንፈስ እንደሚመሩ ማወቃቸው ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። ለምሳሌ፣ ሮበርትና ካቲ የተባሉ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ሆነው በካሚሪ ከተማ እንዲያገለግሉ በተጠየቁ ጊዜ ፈቃደኞች ነበሩ። ራቅ ብላ ያለችው ካሚሪ በወንዝ አቅራቢያ ለምለም በሆኑት ኮረብታማ ቦታዎች ላይ ትገኛለች። ሮበርት እንዲህ ይላል:- “የመጣነው በትክክለኛው ጊዜ ይመስላል። በሁለት ዓመት ውስጥ 40 የሚያህሉ ሰዎች የምሥራቹ አስፋፊዎች ሆነዋል።”
ጠጪና ቁማርተኛ የነበረ ሰው ምሥራቹን ሰማ
መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ለውጥ ያደረጉትን ሰዎች ሲመለከቱ በርካታ የከተማው ሰዎች ይደነቃሉ። ለምሳሌ ከአራት ዓመት በፊት፣ ኤሪኤል የተባለ ጠጪ ሰው ብዙ በመጠጣቱ ምክንያት ታሞ ተኝቶ ነበር። በቁማርተኛነቱ የታወቀ ቢሆንም እንኳ ዕዳው እየጨመረ መምጣቱ፣ ጋብቻው ችግር ላይ መውደቁና ሴት ልጆቹ ችላ መባላቸው ያስጨንቀው ነበር። በዚህ ወቅት አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል አገኘው። ወንድም ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲያብራራለት ኤሪኤል በጥሞና ያዳምጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ኤሪኤል አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ስለ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት፣ ስለ ገነትና አምላክን ስለማምለክ ማንበብ ጀመረ። በኋላም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ።
ሚስዮናውያኑ ወደ ካሚሪ ሲመጡ የኤሪኤል ባለቤት የሆነችው አርሚንዳ ለመጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም ፍላጎት ባይኖራትም ታጠና ነበር። አርሚንዳ “[ኤሪኤል] መጠጣቱን እንዲያቆም ምንም ነገር ለማድረግ እሞክራለሁ። ሆኖም የሚሳካልኝ አይመስለኝም፣ ተስፋ የሌለው ነገር ነው” በማለት ተናግራለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ እሷ ካሰበችው በላይ አስደሳች ሆነላት። በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠምቃ ለቤተሰቦቿ መመሥከር ጀመረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከዘመዶቿ መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ለይሖዋ ወሰኑ።
ኤሪኤል መጠጣቱን፣ ማጨሱንና ቁማር መጫወቱን ለመተው ከባድ ትግል ማድረግ ነበረበት። ጓደኞቹን በሙሉ በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንዲገኙ በጋበዘበት ወቅት ለውጥ ለማድረግ የሚያስችለው እርምጃ ወሰደ። “በዚያ ዕለት ካልመጡት ጋር ያለኝን ጓደኝነት አቆማለሁ፤ የመጡትን ግን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናቸዋለሁ” በማለት ወሰነ። በዚህ መንገድ ሦስት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረ። ኤሪኤል የጉባኤው አባል ከመሆኑ በፊትም እንኳ አንድ ዘመዱን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናው ነበር፤ ይህ ዘመዱ እድገት ያደረገ ሲሆን ኤሪኤል ከዚህ ሰው ጋር አብሮ ተጠመቀ። አርሚንዳ “የበፊቱ ኤሪኤል የሞተ ያህል ነው” በማለት ትናገራለች።
ሮበርት እንዲህ ይላል:- “እስከ ዛሬ ድረስ 24 የሚሆኑ የዚህ ቤተሰብ አባላት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር ይገኛሉ። አሥር የሚሆኑት የተጠመቁ ሲሆን ሌሎች ስምንት ደግሞ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነዋል። አንዳንዶች በእነርሱ ላይ የባሕርይ ለውጥ በማየታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል። በስብሰባ ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር ከ100 ወደ 190 ከፍ ብሏል። እኔና ካቲ 30 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራለን፤ ሁሉም ጥናቶቻችን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። እዚህ በመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን።”
ራቅ ብለው በሚገኙት የቦሊቪያ ከተሞች እየተከናወነ ያለው ስብከት በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ አስቀድሞ የተነገረው ዓለም አቀፋዊ የመሰብሰብ ሥራ ክፍል ነው። ጥቅሱ በጌታ ቀን ስለሚሰበሰቡትና ከታላቁ መከራ ስለሚተርፉት ሰዎች ይናገራል። (ራእይ 1:10፤ 7:9-14) በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የዚህን ዘመን ያህል በሚሊዮን የሚቆጠሩና ከተለያዩ ሕዝቦች የተውጣጡ ሰዎች እውነተኛውን አንድ አምላክ በማምለክ አንድነት ሲመሠርቱ ታይቶ አይታወቅም። አምላክ የሰጠው ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደሳች ማስረጃ ነው!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤቲ ጃክሰን
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፓምላ ሞዝሊ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልሲ ሜየንበርግ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሻርሎት ቶማሻፍስኪ (በስተ ቀኝ ዳር ላይ የቆመችው)
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤሪክና ቪኪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ክልል ለማገልገል ሄደዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቫካና ቤተሰቡ ወደ መንግሥት አዳራሹ ለመሄድ በየሳምንቱ ለሦስት ሰዓት በብስክሌት ይጓዛሉ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤኒ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ የአካባቢው ሰዎች ምሥራቹን በትኩረት ያዳምጣሉ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮበርትና ካቲ በካሚሪ ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግላሉ