በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው መንገድ ላይ መጓዝ

ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው መንገድ ላይ መጓዝ

ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው መንገድ ላይ መጓዝ

“የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው።”​—⁠ምሳሌ 4:​18

1, 2. የአምላክ ሕዝቦች ከይሖዋ ተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃን በማግኘታቸው ምን አድርገዋል?

 ጎህ ሲቀድ የፀሐይ ውጋጋን በሌሊቱ ጨለማ ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ የብርሃን ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ የበለጠ ማን መግለጽ ይችላል? (መዝሙር 36:9) አምላክ ‘የንጋት ብርሃን የምድርን ዳርቻ ሲይዝ፣ ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ቅርጿ ይወጣል፤ ቅርጿ እንደ ልብስ ቅርጽ ጐልቶ ይታያል’ በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 38:12-14) የሸክላ ጭቃ በቅርጽ ማውጫ ማኅተም ሲደረግበት ለውጥ እንደሚታይበት ሁሉ የፀሐይዋ ብርሃን እየደመቀ ሲሄድ በምድር ላይ ያሉት ነገሮችም ይበልጥ ግልጽ ሆነው ይታያሉ።

2 ይሖዋ የመንፈሳዊ ብርሃንም ምንጭ ነው። (መዝሙር 43:3) ዓለም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም እውነተኛው አምላክ ለሕዝቦቹ ብርሃን መፈንጠቁን አላቋረጠም። ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ምሳሌ 4:​18) ከይሖዋ የሚመጣው እየደመቀ የሚሄድ ብርሃን የሕዝቦቹን መንገድ ማብራቱን ቀጥሏል። ይህ ብርሃን ከድርጅታዊ አሠራር፣ ከመሠረተ ትምህርትና ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

እየደመቀ የመጣው መንፈሳዊ ብርሃን ድርጅታዊ መሻሻል አስገኝቷል

3. በኢሳይያስ 60:​17 ላይ ምን ተስፋ ተሰጥቷል?

3 ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ” የሚል ትንቢት አስነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 60:17 የ1954 ትርጉም ) ተራ የሆነ ብረት ይበልጥ ጥራት ባለው የብረት ዓይነት መተካቱ ማሻሻያ መደረጉን እንደሚያሳይ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ወይም “በመጨረሻው ዘመን” በድርጅታዊ አሠራር ረገድ ማሻሻያዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1

4. በ1919 ምን ዝግጅት ተደረገ? ይህስ ጠቃሚ የነበረው እንዴት ነው?

4 በመጨረሻዎቹ ቀናት መባቻ አካባቢ፣ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይመረጡ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሽማግሌዎች እውነተኛ የወንጌላዊነት መንፈስ አልነበራቸውም። አንዳንዶች እነርሱ ራሳቸው በስብከቱ ሥራ አለመካፈላቸው ሳያንስ ሌሎችም እንዳይሰብኩ ለማዳከም ይጥሩ ነበር። ስለዚህ በ1919 በሁሉም ጉባኤዎች የአገልግሎት ዳይሬክተር የሚባል አዲስ የኃላፊነት ቦታ እንዲኖር ተደረገ። የአገልግሎት ዳይሬክተሩን የሚመርጠው ጉባኤው አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች ቅርንጫፍ ቢሮ ይህንን ወንድም ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይሾመዋል። የአገልግሎት ዳይሬክተሩ ካሉት ኃላፊነቶች መካከል የስብከቱን ሥራ ማደራጀት፣ የአገልግሎት ክልሎችን መስጠት እንዲሁም ወንድሞች በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ ማበረታታት ይገኙበታል። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩ ሥራ ትልቅ ለውጥ ይታይበት ጀመር።

5. በ1920ዎቹ ዓመታት ምን ማሻሻያ ተደረገ?

5 በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ በተካሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአውራጃ ስብሰባ ላይ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” የሚል ማበረታቻ መሰጠቱ ጉባኤዎች በሙሉ ይበልጥ ለሥራ እንዲነሳሱ አደረጋቸው። በ1927 የመስክ አገልግሎት በደንብ የተደራጀ ሲሆን እሁድ ቀን ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው የስብከት ሥራ በጣም ተስማሚ እንደሆነ ታመነበት። ይህ ቀን የተመረጠው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እሁድ ለአብዛኞቹ ሰዎች የእረፍት ቀን ስለሆነ ነው። ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ቤታቸው ሊገኙ በሚችሉበት ወቅት ይኸውም ቅዳሜና እሁድ ወይም ምሽት ላይ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለማገልገል ጥረት በማድረግ ተመሳሳይ መንፈስ ያንጸባርቃሉ።

6. በ1931 ምን የአቋም መግለጫ ወጣ? ይህስ የአምላክን መንግሥት በመስበኩ ሥራ ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል?

6 ሐምሌ 26, 1931 እሁድ ከሰዓት በኋላ በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጣውና በኋላም በዓለም ዙሪያ የተላለፈው የአቋም መግለጫ የአምላክን መንግሥት በመስበኩ ሥራ ላይ ትልቅ እመርታ አስገኝቷል። የአቋም መግለጫው በከፊል እንዲህ ይላል:- “እኛ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ስንሆን በስሙ እንድናከናውን የተሰጠን ሥራ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰበከውን መልእክት እንድናውጅ እንዲሁም ይሖዋ እውነተኛና ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ለሰዎች እንድናሳውቅ የተሰጠንን መመሪያ እንታዘዛለን፤ ስለዚህም ጌታ አምላክ ራሱ ያወጣውን የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በደስታ የምንቀበል ከመሆኑም በላይ በዚህ ስም ለመታወቅና ለመጠራት እንፈልጋለን።” (ኢሳይያስ 43:10) ይህ አዲስ ስያሜ በይሖዋ ስም የሚጠሩ ሁሉ ያለባቸውን ተቀዳሚ ኃላፊነት በግልጽ የሚያሳይ ነው! አዎን፣ ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ የሚካፈሉበት ሥራ ሰጥቷል። በጥቅሉ ሲታይ የተገኘው ምላሽ በጣም የሚያስደንቅ ነበር!

7. በ1932 ምን ለውጥ ተደረገ? ለምንስ?

7 በርካታ ሽማግሌዎች ትሑት በመሆን በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ጀመሩ። በአንዳንድ ቦታዎች ግን ጉባኤው የመረጣቸው ሽማግሌዎች እያንዳንዱ የጉባኤው አባል ለሕዝብ በሚሰጠው የምሥክርነት ሥራ መካፈል አለበት የሚለውን ሐሳብ አጥብቀው ተቃወሙ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ማሻሻያዎች ተደረጉ። በ1932 ጉባኤዎች፣ ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን መምረጥ እንዲያቆሙ በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት መመሪያ ተሰጣቸው። ከዚህ ይልቅ ለሕዝብ በመስበኩ ሥራ የሚካፈሉ መንፈሳዊ ወንዶችን ያቀፈ የአገልግሎት ኮሚቴ እንደሚመርጡ ተገለጸ። በዚህ መንገድ ጉባኤውን የመምራቱ ኃላፊነት በአገልግሎት በቅንዓት ለሚካፈሉ ወንድሞች ስለተሰጠ በሥራው ላይ እድገት መታየቱ ቀጠለ።

ብርሃኑ እየደመቀ ሲሄድ የተደረጉ ተጨማሪ ማሻሻያዎች

8. በ1938 ምን ማሻሻያ ተደረገ?

8 ብርሃኑ እያደር ‘እየጐላ መሄዱን’ ቀጠለ። በ1938 የምርጫ አሠራር ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ተደረገ። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አገልጋዮችን በሙሉ የሚሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሲሆን ሹመቱም ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወን ጀመረ። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም ) ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ማለት ይቻላል ለውጡን ወዲያው የተቀበሉት ሲሆን የስብከቱ ሥራም ፍሬ ማፍራቱን ቀጠለ።

9. በ1972 ምን ዝግጅት ተደረገ? ይህ ዝግጅት የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ከጥቅምት 1, 1972 ጀምሮ ደግሞ ጉባኤውን በበላይነት የሚመሩትን ወንድሞች በተመለከተ ሌላ ማስተካከያ ተደረገ። ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው ጉባኤዎች በአንድ የጉባኤ አገልጋይ (በዚያን ጊዜ ሽማግሌዎች የሚጠሩበት ስም ነው) ወይም የበላይ ተመልካች ሥር መሆናቸው ቀርቶ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሽማግሌዎች አካላት ተቋቋሙ። ይህ አዲስ ዝግጅት የጎለመሱ ወንድሞች በጉባኤው ውስጥ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7) በዚህም የተነሳ በርካታ ወንድሞች የጉባኤ ኃላፊነቶችን በመወጣት ረገድ ልምድ አግኝተዋል። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች ገና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለተቀበሉት እረኛ ሆነው በማገልገል ረገድ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል።

10. በ1976 የትኛው ዝግጅት ተግባራዊ ሆነ?

10 የበላይ አካሉ አባላት በስድስት ኮሚቴዎች የተደራጁ ሲሆን ከጥር 1, 1976 ጀምሮ እነዚህ ኮሚቴዎች የድርጅቱንና በዓለም ዙሪያ ያሉትን ጉባኤዎች እንቅስቃሴ በበላይነት መምራት ጀመሩ። ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙት ሥራዎች በሙሉ “በብዙ አማካሪዎች” የሚመሩ መሆኑ እንዴት ያለ በረከት ነው!​—⁠ምሳሌ 15:22፤ 24:6

11. በ1992 ምን ማሻሻያ ተደረገ? ለምንስ?

11 በ1992 ደግሞ እስራኤላውያንና ሌሎች ሰዎች ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ ከተከናወነው ነገር ጋር የሚመሳሰል ተጨማሪ ማሻሻያ ተደረገ። በዚያ ወቅት የቤተ መቅደሱን አገልግሎት የሚያከናውኑ በቂ ሌዋውያን አልነበሩም። በዚህም ምክንያት እስራኤላዊ ያልሆኑት ናታኒሞች ሌዋውያንን እንዲረዱ ተጨማሪ ሥራ ተሰጣቸው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ፣ ታማኝና ልባም ባሪያ በምድር ላይ ያለው ኃላፊነት እየጨመረ በመምጣቱ ለዚህ ሥራ እገዛ እንዲያደርጉ ሲባል በ1992 ‘ከሌሎች በጎች’ መካከል አንዳንዶቹ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ተሰጧቸው። እነዚህ ወንድሞች የበላይ አካሉን ኮሚቴዎች እንዲያግዙ ተሾሙ።​—⁠ዮሐንስ 10:​16 የ1954 ትርጉም 

12. ይሖዋ ሰላምን ገዢያችን አድርጎ የሾመው እንዴት ነው?

12 ይህ ሁሉ ማሻሻያ ምን ውጤት አስገኝቷል? ይሖዋ “ሰላምን ገዥሽ፣ ጽድቅንም አለቃሽ አደርጋለሁ” ብሎ ነበር። (ኢሳይያስ 60:17) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በመካከላቸው “ሰላም” አለ፤ እንዲሁም አምላክን እንዲያገለግሉ የሚገፋፋቸው ‘ጽድቅ አለቃ’ ሆኖላቸዋል። ስለ አምላክ መንግሥት የመስበኩንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለማከናወን በሚገባ ተደራጅተዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20

ይሖዋ በመሠረተ ትምህርት ረገድ ብርሃን ይፈነጥቃል

13. በ1920ዎቹ ዓመታት በመሠረተ ትምህርት ረገድ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ በመሠረተ ትምህርት ረገድም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሕዝቡ ብርሃን እየፈነጠቀ ነው። ራእይ 12:​1-9 ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ዘገባው ስለ ሦስት ምሳሌያዊ አካላት የሚናገር ሲሆን እነርሱም ነፍሰ ጡር የሆነችና በኋላም የወለደች “ሴት፣” “ዘንዶ፣” እና “ወንድ ልጅ” ተብለው ተገልጸዋል። እነዚህ አካላት ምን እንደሚያመለክቱ ታውቃለህ? መጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “የብሔሩ መወለድ” በሚል ርዕስ ውስጥ ማንነታቸው ተገልጾ ነበር። መጽሔቱ የአምላክ ሕዝቦች የመንግሥቱን መወለድ በተመለከተ ስለተነገሩት ትንቢቶች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደረገ ሲሆን ይህም ይሖዋንና ሰይጣንን የሚወክሉ ሁለት የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸውን እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። ከዚያም በ1927/28 የአምላክ ሕዝቦች፣ የገና በዓልንና ልደትን ማክበር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጭ ስለተገነዘቡ እነዚህን በዓላት ማክበር አቆሙ።

14. በ1930ዎቹ ዓመታት ከመሠረተ ትምህርት ጋር በተያያዘ ምን ማብራሪያ ተሰጠ?

14 በ1930ዎቹ ደግሞ በሦስት መሠረተ ትምህርቶች ላይ ተጨማሪ ብርሃን ፈነጠቀ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በራእይ 7:​9-17 ላይ የተጠቀሰው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው ከሚገዙት 144, 000 ሰዎች የተለየ እንደሆነ ካወቁ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-5) ይሁን እንጂ የዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ ማንነት ግልጽ አልነበረም። የንጋት ብርሃን እየጨመረ ሲሄድ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ቀለማቸውና ቅርጻቸው እንደሚለየው ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ የተባሉት “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉትና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች መሆናቸው በ1935 ታወቀ። በዚያው ዓመት ትንሽ ቆየት ብሎ በበርካታ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች የሆኑ ተማሪዎችን የሚነካ ማብራሪያ ተሰጠ። በዓለም ዙሪያ ብሔራዊ ስሜት ገንኖ በነበረበት በዚህ ወቅት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት ተራ ሥነ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ትርጉም እንዳለው ተገነዘቡ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ክርስቶስ ተሰቅሎ የሞተው ቀጥ ባለ እንጨት እንጂ በመስቀል ላይ እንዳልሆነ ሲብራራ በመሠረተ ትምህርት ረገድ ሌላ ማስተካከያ ተደረገ።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 10:39

15. ስለ ደም ቅድስና ትኩረት ተሰጥቶ የተብራራው መቼና እንዴት ነበር?

15 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጦርነቱ ለቆሰሉ ወታደሮች ደም መስጠት የተለመደ የሕክምና ዘዴ ሆኖ ነበር፤ በዚህ ወቅት የደምን ቅድስና በተመለከተ ተጨማሪ ብርሃን ፈነጠቀ። የሐምሌ 1, 1945 መጠበቂያ ግንብ “በአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ የይሖዋ አምላኪዎች በሙሉ ደምን ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱና በዚህ ዓቢይ ጉዳይ ረገድ ከአምላክ የጽድቅ ደንቦች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ” የሚያበረታታ ሐሳብ ይዞ ወጣ።

16. የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የወጣው መቼ ነበር? የዚህ ትርጉም ሁለት ጎላ ያሉ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

16 በ1946 በወቅቱ ያለውን እውቀት መሠረት ያደረገና ከሕዝበ ክርስትና ልማዶች ጋር በተያያዙ ትምህርቶች ያልተበከለ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት። በታኅሣሥ ወር 1947 ይህ የትርጉም ሥራ ተጀመረ። በ1950 የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በእንግሊዝኛ ተዘጋጀ። ከ1953 ጀምሮ ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የእንግሊዝኛ ትርጉም በአምስት ጥራዞች ተከፋፍሎ በተለያየ ጊዜ ወጣ። የትርጉም ሥራው ከተጀመረ ከ12 ዓመታት በኋላ የመጨረሻው ጥራዝ በ1960 ተጠናቀቀ። በ1961 ሙሉው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በአንድ ጥራዝ ሆኖ ታተመ። አሁን በብዙ ቋንቋዎች የሚገኘው ይህ ትርጉም አንዳንድ ጎላ ብለው የሚታዩ ገጽታዎች አሉት። በተገቢው ቦታ ሁሉ ላይ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም አስገብቷል። ከዚህም በላይ በእጅ የተጻፉትን የመጀመሪያ ጽሑፎች ቃል በቃል ለመተርጎም የተደረገው ጥረት መለኮታዊውን እውነት በመረዳት ረገድ ቀጣይ እድገት እንዲኖር አድርጓል።

17. በ1962 ምን ተጨማሪ ብርሃን ፈነጠቀ?

17 በሮሜ 13:​1 (የ1954 ትርጉም ) ላይ ‘በበላይ ያሉት ባለ ሥልጣኖች’ የተባሉት እነማን እንደሆኑና ክርስቲያኖች ለእነዚህ ባለ ሥልጣናት የሚገዙት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በ1962 ተብራራ። በሮሜ ምዕራፍ 13፣ በቲቶ 3:​1, 2 እንዲሁም በ1 ጴጥሮስ 2:​13, 17 ላይ የተደረገው ጥልቅ ምርምር ‘በበላይ ያሉት ባለ ሥልጣኖች’ የተባሉት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆኑ ሰብዓዊ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት መሆናቸው እንዲታወቅ አስችሏል።

18. በ1980ዎቹ ዓመታት የፈነጠቁት አንዳንድ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

18 ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም የጻድቃን ብርሃን እየጨመረ መብራቱን ቀጥሏል። በ1985 “ሕይወት” ለማግኘት ጻድቅ ተደርጎ መታየትና የአምላክ ወዳጅ ሆኖ እንደ ጻድቅ መቆጠር ምን ትርጉም እንዳላቸው ማስተዋል ተቻለ። (ሮሜ 5:18፤ ያዕቆብ 2:23) በ1987 ደግሞ የክርስቲያን ኢዮቤልዩ ትርጉም በስፋት ተብራራ።

19. በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይሖዋ ለሕዝቡ ተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?

19 በ1995 “በጎችን ከፍየሎች” የመለየቱ ሥራ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ተብራራ። በ1998 ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ የተመለከተው ራእይ በዝርዝር ተገለጸ። በ1999 ‘የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ የሚቆመው’ መቼና እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ተሰጠ። (ማቴዎስ 24:15, 16፤ 25:​32) በ2002 ደግሞ ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ ምን ትርጉም እንዳለው ተጨማሪ ማስተዋል ተገኘ።​—⁠ዮሐንስ 4:24

20. የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ማሻሻያ ያደረጉት በየትኛው ሌላ መስክ ነው?

20 በድርጅታዊ አሠራርና በመሠረተ ትምህርት ረገድ ከተደረገው ማሻሻያ በተጨማሪ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘም ማስተካከያዎች ተደርገዋል። ለአብነት ያህል፣ በ1973 ትንባሆ ማጨስ ‘ሥጋን እንደሚያረክስ’ ስለታወቀ እንደ ከባድ ኃጢአት እንደሚታይ ተገለጸ። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይህ ከሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ የሐምሌ 15, 1983 የመጠበቂያ ግንብ እትም በጦር መሣሪያ ስለመጠቀም ያለንን አቋም የሚያብራራ ሐሳብ ይዞ ወጣ። እነዚህ በጊዜያችን የፈነጠቀውን ብርሃን የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው።

ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው መንገድ ላይ መጓዛችሁን ቀጥሉ

21. ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው ጎዳና ላይ መመላለሳችንን ለመቀጠል የሚረዳን ምን ዓይነት አመለካከት መያዛችን ነው?

21 ለረጅም ጊዜ በእውነት ውስጥ የቆየ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ለውጥ ሲደረግ መቀበልና ከዚያ ጋር ተስማምቶ መመላለስ ከባድ ሊሆን ይችላል” ብሏል። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ ሆኖ ባገለገለባቸው 48 ዓመታት ውስጥ የተደረጉትን በርካታ ማሻሻያዎች እንዲቀበል የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ቁልፉ ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር ነው። ማሻሻያውን ለመቀበል አሻፈረኝ ካልኩኝ ድርጅቱ ወደፊት ሲሄድ እኔ ወደኋላ እቀራለሁ። አንዳንድ ለውጦችን ለመቀበል ከከበደኝ ጴጥሮስ ለኢየሱስ በተናገረው ‘ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ’ በሚለው ሐሳብ ላይ አሰላስላለሁ። ከዚያም ‘ወዴት መሄድ እችላለሁ? በጨለማ ወደተዋጠው ዓለም ልሄድ ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ይህ ከአምላክ ድርጅት ጋር ተጣብቄ እንድቀጥል ረድቶኛል።”​—⁠ዮሐንስ 6:68

22. በብርሃኑ መንገድ መመላለሳችን ምን ጥቅም አለው?

22 በዙሪያችን ያለው ዓለም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚገኝ ግልጽ ነው። ይሖዋ ለሕዝቡ ብርሃኑን መፈንጠቁን በቀጠለ መጠን በአገልጋዮቹና በዓለም መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ይሄዳል። ይህ ብርሃን የሚጠቅመን እንዴት ነው? በጨለማ በተዋጠ መንገድ ላይ የሚገኝ ጉድጓድ መብራት ስለበራበት ብቻ እንደማይወገድ ሁሉ ከአምላክ ቃል የሚገኘው ብርሃንም አደጋዎቹን አያስወግዳቸውም። ሆኖም መለኮታዊው ብርሃን ከእነዚህ ወጥመዶች በመራቅ እየደመቀ በሚሄደው የብርሃን መንገድ ላይ መመላለሳችንን እንድንቀጥል እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው “በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ” ሁሉ ለይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ትኩረት መስጠታችንን እንቀጥል።​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​19

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ ሕዝቦቹ የትኞቹን ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል?

• እየደመቀ የመጣው ብርሃን በመሠረተ ትምህርት ረገድ ምን ማሻሻያዎች አምጥቷል?

• አንተ በግልህ የትኞቹ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ተመልክተሃል? እነዚህን ማስተካከያዎች ለመቀበል የረዳህ ምንድን ነው?

• ብርሃኑ እየደመቀ በሚሄደው መንገድ ላይ መጓዝህን መቀጠል የምትፈልገው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክን ሥራ እንዲያከናውኑ አበረታቷቸዋል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1950 ወንድም ናታን ኖር “የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም” መውጣቱን ሲገልጽ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© 2003 BiblePlaces.com