በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት እውነተኝነት ያረጋገጠ ጥንታዊ መረጃ

የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት እውነተኝነት ያረጋገጠ ጥንታዊ መረጃ

የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት እውነተኝነት ያረጋገጠ ጥንታዊ መረጃ

“እያንዳንዱ መስመር የተጻፈው በተለይ ጥንታዊውን የክርስትና ታሪክ የማወቅ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ጉጉት ለመቀስቀስ ታስቦ ይመስላል።” እንዲህ የሚል አስተያየት የተሰነዘረው አንድን ጥንታዊ ሰነድ በተመለከተ ነው። የትኛው ሰነድ እንደሆነ መገመት ትችላለህ?

ይህ ሰነድ ሙራቶሪያን ፍራግመንት በመባል ይታወቃል፤ ስለዚህ ሰነድ ሰምተህ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ያም ሆነ ይህ ‘ሙራቶሪያን ፍራግመንትን ይህን ያህል ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ ሰነድ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ዝርዝር የያዘ ተአማኒነት ያለው ጥንታዊ ጽሑፍ በመሆኑ ነው።

በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሆኑ ምንም አትጠራጠር ይሆናል። ሆኖም ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው መካተት ያለባቸው የትኞቹ መጻሕፍት ናቸው?’ የሚል ጥያቄ የተፈጠረባቸው አንዳንድ ሰዎች እንደነበሩ ብታውቅ ሳትገረም አትቀርም። ሙራቶሪያን ፍራግመንት በመንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ የሚታመኑትን ጽሑፎች ስም ይዘረዝራል። የትኞቹ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተት አለባቸው የሚለው ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ የታወቀ ነው። ታዲያ ይህ ሰነድ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት በተመለከተ ምን የሚገልጸው ነገር አለ? እስቲ በመጀመሪያ ስለ ሰነዱ ታሪክ ጥቂት እናንሳ።

እንዴት ተገኘ?

ሙራቶሪያን ፍራግመንት፣ እያንዳንዳቸው 27 በ17 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው 76 ገጾች ያሉት ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ አንድ ክፍል ነው። ይህን ሰነድ በሚላን፣ ጣሊያን በሚገኘው አምብሮሲያን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ያገኙት ሉዶቪኮ አንቶንዮ ሙራቶሪ (1672-1750) የተባሉ ታዋቂ ጣሊያናዊ የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። ሙራቶሪ፣ ሙራቶሪያን ፍራግመንት የተባለውን ግኝታቸውን በ1740 ያሳተሙ ሲሆን ሰነዱ ስያሜውን ያገኘውም ከእርሳቸው ስም በመነሳት ነው። ይህ የብራና ጽሑፍ በሰሜን ጣሊያን ባለው ፒያቼንዘ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ቦቢዮ የተባለ ጥንታዊ ገዳም በስምንተኛው መቶ ዘመን እንደተዘጋጀ ይገመታል። ከዚያም በ17ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ወደ አምብሮሲያን ቤተ መጻሕፍት ተወሰደ።

በዚህ ጥንታዊ ጽሑፍ ገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኘው ሙራቶሪያን ፍራግመንት 85 መስመር ጽሑፍ ይዟል። የተጻፈው በላቲን ቋንቋ ሲሆን ብዙም ጥንቁቅ ያልሆነ ጸሐፊ እንደገለበጠው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ነገር ግን በ11ኛውና በ12ኛው መቶ ዘመን ከተዘጋጁ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው አራት የብራና ጽሑፎች ጋር በማነጻጸር ገልባጩ የፈጸማቸውን ስህተቶች ማወቅ ተችሏል።

መቼ ተጻፈ?

በሙራቶሪያን ፍራግመንት ላይ የሚገኘው መግለጫ መጀመሪያ የተጻፈው መቼ እንደሆነ ትጠይቅ ይሆናል። ወደ ላቲን የተተረጎመው ሙራቶሪያን ፍራግመንት ከመዘጋጀቱ ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት የመጀመሪያው ጽሑፍ በግሪክኛ እንደተጻፈ ይታመናል። ዋነኛው ጽሑፍ መቼ እንደተዘጋጀ ለመገመት ፍንጭ የሚሰጥ ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል። ሙራቶሪያን ፍራግመንት፣ ሸፐርድ የሚል ርዕስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆነ መጽሐፍ ይጠቅስና ሄርመስ የሚባል ሰው “በጣም በቅርቡ፣ በእኛ ዘመን በሮም ከተማ ጻፈው” በማለት ይናገራል። ምሑራን ሸፐርድ የሚል ርዕስ ያለው የሄርመስ መጽሐፍ መደምደሚያ የተጻፈው ከ140 እስከ 155 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ሙራቶሪያን ፍራግመንት የተባለውን ላቲንኛ ትርጉም ለማዘጋጀት መሠረት የሆነው የመጀመሪያው ግሪክኛ ጽሑፍ፣ ከ170 እስከ 200 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባሉት ጊዜያት መካከል እንደተጻፈ የሚገመተው ለምን እንደሆነ መረዳት ትችላለህ።

ጽሑፉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሮምን ደጋግሞ መጥቀሱ የተዘጋጀው በዚሁ ከተማ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። የጸሐፊው ማንነት ግን አወዛጋቢ ሆኗል። ጸሐፊው የእስክንድርያው ክሌመንት ወይም የሰርዴሱ ሜለቶ አሊያም ደግሞ የኤፌሶኑ ፖሊክራተስ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በርካታ ምሑራን ግን በግሪክኛ ብዙ መጻሕፍት የደረሰውና ሙራቶሪያን ፍራግመንት እንደተዘጋጀ በሚታመንበት ጊዜ በሮም ይኖር የነበረው ሂፖሊተስ እንደጻፈው ይናገራሉ። የጸሐፊው ማንነት እምብዛም የማያሳስብህ ሊሆን ቢችልም ጽሑፉ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው ያደረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ትጓጓ ይሆናል።

የጽሑፉ ይዘት

ጽሑፉ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ዝርዝር ብቻ የያዘ አይደለም። መጽሐፎቹንና ጸሐፊዎቹን የሚመለከት ትንታኔም ይሰጣል። ሰነዱን ብታነበው የመጀመሪያዎቹ መስመሮች እንደሌሉ ማስተዋል ትችላለህ፤ መደምደሚያውም ላይ የጎደለ ነገር እንዳለ ያስታውቃል። ዝርዝሩ የሚጀምረው የሉቃስን ወንጌል በመጥቀስ ነው፤ አክሎም የዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጸሐፊ ሐኪም እንደነበር ይገልጻል። (ቈላስይስ 4:14) ጽሑፉ የሉቃስ መጽሐፍ ሦስተኛው ወንጌል እንደሆነ ይዘግባል፤ ስለዚህ በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ ዝርዝሩ ውስጥ የማይገኘው ክፍል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎችን የሚጠቅስ ሳይሆን እንደማይቀር ማስተዋል ትችላለህ። በዚህ የምትስማማ ከሆነ፣ ሙራቶሪያን ፍራግመንት የዮሐንስ ወንጌል አራተኛ መጽሐፍ እንደሆነ ስለሚገልጽ ግምትህን ያጠናክረዋል።

ሰነዱ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ሉቃስ ‘ለክቡር ቴዎፍሎስ’ እንደጻፈው ያረጋግጣል። (ሉቃስ 1:3፤ የሐዋርያት ሥራ 1:1) በመቀጠልም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች (ሁለት)፣ ለኤፌሶን ሰዎች፣ ለፊልጵስዩስ ሰዎች፣ ለቈላስይስ ሰዎች፣ ለገላትያ ሰዎች፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች (ሁለት)፣ ለሮሜ ሰዎች፣ ለፊልሞና፣ ለቲቶ እና ለጢሞቴዎስ (ሁለት) የላካቸውን መልእክቶች ይዘረዝራል። የይሁዳ መልእክትና ሁለቱ የዮሐንስ መልእክቶችም እንዲሁ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ ይገልጻል። የመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክት ደግሞ ራሱ ዮሐንስ ከጻፈው ወንጌል ጋር አብሮ ተጠቅሷል። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ የሚታመኑትን ጽሑፎች የሚዘረዝረው ይህ ሰነድ የሚደመደመው የአፖካሊፕስን ወይም የራእይን መጽሐፍ በመጥቀስ ነው።

ጽሑፉ የጴጥሮስ አፖካሊፕስ የሚባል መጽሐፍ መጥቀሱና ክርስቲያኖች ይህን መጽሐፍ ማንበብ እንደማይገባቸው አንዳንዶች የሚሰማቸው መሆኑን መግለጹ ትኩረት የሚስብ ነው። የሙራቶሪያን ፍራግመንት ጸሐፊ በእርሱ ዘመን በማስመሰል የተጻፉ የሐሰት ጽሑፎች በስፋት እየተሰራጩ እንደነበር አስጠንቅቋል። “ሐሞትንና ማርን መቀላቀል እንደማይገባ ሁሉ” እነዚህ የሐሰት ጽሑፎችም ተቀባይነት ማግኘት እንደሌለባቸው ሙራቶሪያን ፍራግመንት ያትታል። ሰነዱ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሊካተቱ የማይገባቸውን ሌሎች ጽሑፎችንም ይጠቅሳል። ይህም የሆነበት ምክንያት ሸፐርድ የሚል ርዕስ እንዳለው የሄርመስ መጽሐፍ ሁሉ እነዚህም ጽሑፎች ሐዋርያት ከኖሩበት ዘመን በኋላ ስለተጻፉ አሊያም ደግሞ መናፍቅነትን ስለሚደግፉ ነው።

ለዕብራውያን የተላከው መልእክት፣ ሁለቱ የጴጥሮስ መልእክቶችና የያዕቆብ መልእክት ሙራቶሪያን ፍራግመንት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው መጻሕፍት መካከል እንደማይገኙ ከላይ ከተጠቀሱት ሐሳቦች በመነሳት ሳትገነዘብ አልቀረህም። ዶክተር ጄፍሪ ማርክ ሃነማን ጽሑፉን ስለገለበጠው ሰው ሥራ ከገለጹ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “ሰነዱ አሁን የሌሉ ሌሎች መረጃዎችን ይዞ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ [ነው]፤ ከእነዚህም ውስጥ የያዕቆብና የዕብራውያን (እንዲሁም የ1ኛ ጴጥሮስ) መጻሕፍት ሳይገኙበት አይቀሩም።”​—ዘ ሙራቶሪያን ፍራግመንት ኤንድ ዘ ዲቨሎፕመንት ኦቭ ዘ ካነን

በአሁኑ ጊዜ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ መጻሕፍት፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ተደርገው ይታዩ እንደነበር ሙራቶሪያን ፍራግመንት ያረጋግጣል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆነው መካተት እንዳለባቸው የሚያረጋግጠው በአንድ ጥንታዊ ሰነድ ውስጥ ተዘርዝረው መገኘታቸው እንዳልሆነ እሙን ነው። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳየው የያዙት ሐሳብ ነው። ሁሉም መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ መሆኑን የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በላይ እርስ በርሳቸው ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሆኑ የሚታመኑት 66 መጻሕፍት እርስ በርስ የሚስማሙና የተሟሉ መሆናቸው ደግሞ አንድነት እንዳላቸውና ምንም እንደማይጎድላቸው ያሳያል። እንግዲያው እስከ ዘመናችን ተጠብቀው የቆዩትን እነዚህን መጻሕፍት ይሖዋ በመንፈሱ ያስጻፋቸው እውነተኛ ቃላት እንደሆኑ አድርገህ የምትቀበል ከሆነ ትጠቀማለህ።​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉዶቪኮ አንቶንዮ ሙራቶሪ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምብሮሲያን ቤተ መጻሕፍት

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙራቶሪያን ፍራግመንት

[ምንጭ]

Diritti Biblioteca Ambrosiana. Vietata la riproduzione. Aut. No. F 157 / 05

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Fragments: Diritti Biblioteca Ambrosiana. Vietata la riproduzione. Aut. No. F 157 / 05; Muratori, based on line art: © 2005 Brown Brothers