በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስን የሚያድስ ጤናማ መዝናኛ

መንፈስን የሚያድስ ጤናማ መዝናኛ

መንፈስን የሚያድስ ጤናማ መዝናኛ

“ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።”—1 ቆሮንቶስ 10:31

1, 2. አስደሳች መዝናኛዎች “የእግዚአብሔር ችሮታ” እንደሆኑ ተደርገው መታየት የሚችሉት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

 አስደሳች በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ የመካፈል ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። ደስተኛው አምላካችን ይሖዋ ተደስተን እንድንኖር ስለሚፈልግ ለዚህ የሚረዱንን ነገሮች አትረፍርፎ ሰጥቶናል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ 6:17) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ደስ ከመሰኘት . . . የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው” ሲል ጽፏል።—መክብብ 3:12, 13

2 አንድ ሰው በሥራው ውጤት የሚዝናናበት እንዲህ ዓይነት ጊዜ ማግኘቱ በእርግጥ ሰውነቱ እንዲታደስ ያስችለዋል፤ በተለይ የሚዝናናው ከቤተሰቡ ወይም ከወዳጆቹ ጋር ከሆነ ደስታው የተሟላ ይሆናል። እንዲህ ያለው ደስታ “የእግዚአብሔር ችሮታ” እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም ይህ ከአምላክ ያገኘነው የተትረፈረፈ ስጦታ መረን በለቀቁ መዝናኛዎች ላይ እንድንካፈል ሰበብ ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስካርን፣ ሆዳምነትንና የሥነ ምግባር ብልግናን ከማውገዙም በላይ እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ” በመግለጽ ያስጠነቅቃል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ምሳሌ 23:20, 21፤ 1 ጴጥሮስ 4:1-4

3. በመንፈሳዊ ተግተን እንድንኖርና ታላቁን የይሖዋ ቀን እንዳንዘነጋ የሚረዳን ምንድን ነው?

3 በዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ዘመን፣ ክርስቲያኖች የዓለምን ብልሹ አካሄድ እንዳይከተሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠንቅቀው መኖር ግድ ሆኖባቸዋል። (ዮሐንስ 17:15, 16) አስቀድሞ እንደተተነበየው በዛሬው ጊዜ ሰዎች በቅርቡ “ታላቅ መከራ” እንደሚመጣ ‘እስከማያውቁ’ ወይም እስከማያስተውሉ ድረስ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:4, 5፤ ማቴዎስ 24:21, 37-39) ኢየሱስ ተከታዮቹን “በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (ሉቃስ 21:34) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሰምተን እርምጃ ለመውሰድ ቆርጠናል። በዙሪያችን ካሉት አምላክ የለሽ ሰዎች በተቃራኒ በመንፈሳዊ ትጉ ሆነን ለመቀጠልና የይሖዋን ታላቅ ቀን ላለመዘንጋት እንጥራለን።—ሶፎንያስ 3:8፤ ሉቃስ 21:36

4. (ሀ) ተገቢ መዝናኛ ማግኘት አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ ምን በሥራ ልናውለው የሚገባ ምክር ይገኛል?

4 ዲያብሎስ የዓለምን ብልሹ ድርጊቶች ማራኪ አድርጎ ስለሚያቀርባቸውና በቀላሉ እንዲገኙ ስላደረጋቸው ከእነዚህ ነገሮች መራቅ ቀላል አይደለም። በተለይ መዝናናት በምንፈልግበት ጊዜ እንዲህ ማድረጉ በጣም ከባድ ነው። ዓለም የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ ነገሮች “ሥጋዊ ምኞት” ለመቀስቀስ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 2:11) ጎጂ መዝናኛዎች በሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች የሚቀርቡ ቢሆንም በጽሑፎች፣ በቲቪ፣ በኢንተርኔትና በቪዲዮ አማካኝነት ሰዎች ቤት ድረስ ሊገቡም ይችላሉ። ስለዚህ የአምላክ ቃል ለክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል:- “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።” (ኤፌሶን 5:15, 16) በጎጂ መዝናኛዎች ከመጠመድ፣ ጊዜያችንን ከማባከን እንዲሁም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ተበላሽቶ ወደ ጥፋት ከማምራት መዳን የምንችለው ይህን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ብቻ ነው!—ያዕቆብ 1:14, 15

5. ትልቅ እረፍት የምናገኘው ከምንድን ነው?

5 ክርስቲያኖች በሥራ የተጠመዱ በመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ መዝናናት እንደሚያስፈልጋቸው ሊሰማቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። እንዲያውም መክብብ 3:4 “ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መዝናናትን እንደ ጊዜ ማባከን አድርጎ አይገልጸውም። ይሁንና መዝናኛ እንድንታደስ የሚያደርገን እንጂ መንፈሳዊነታችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ወይም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን የሚያስተጓጉል መሆን የለበትም። የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ ትልቅ ደስታ የሚያስገኘው ለሌሎች መስጠት እንደሆነ ከሕይወት ተሞክሯቸው አይተዋል። በመሆኑም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ቅድሚያ ይሰጣሉ፤ እንዲሁም የኢየሱስን ልዝብ ቀንበር በመሸከም የሚገኘውን እውነተኛ ‘የነፍስ ዕረፍት’ ቀምሰዋል።—ማቴዎስ 11:29, 30፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35

ተገቢ መዝናኛ መምረጥ

6, 7. አንድ መዝናኛ ተገቢ ነው ወይም አይደለም ብለህ ለመወሰን የሚረዳህ ምንድን ነው?

6 አንድ መዝናኛ ለክርስቲያን የሚገባ እንደሆነ ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ ይሰጣሉ፤ የሽማግሌዎች እርዳታ የሚያስፈልግበት ጊዜም ሊኖር ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ዓይነት መጽሐፍ፣ ፊልም፣ ጨዋታ፣ ዳንስ ወይም ዘፈን ለክርስቲያን የሚገባ አይደለም ብሎ ሌላ ሰው እንዲነግረን አያስፈልግም። ጳውሎስ ‘የበሰሉ ሰዎች መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን እንዳስለመዱ’ ተናግሯል። (ዕብራውያን 5:14፤ 1 ቆሮንቶስ 14:20) መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ የሚሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ኅሊናህን የምታዳምጥ ከሆነ ትልቅ እገዛ ያደርግልሃል።—1 ጢሞቴዎስ 1:19

7 ኢየሱስ ‘ዛፍ በፍሬው እንደሚታወቅ’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:33) አንድ መዝናኛ በዓመጽ ድርጊት፣ በሥነ ምግባር ብልግና ወይም በመናፍስታዊ ሥራ የመማረክን ብልሹ ፍሬ የሚያፈራ ከሆነ ተቀባይነት ማግኘት አይገባውም። እንዲሁም የአንድን ሰው ሕይወት ወይም ጤንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ ኢኮኖሚን የሚያቃውስ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ አሊያም ደግሞ ሌሎችን የሚያደናቅፍ ከሆነ ተገቢ መዝናኛ አይደለም። ጳውሎስ የወንድማችንን ኅሊና ማቁሰል ኃጢአት እንደሆነ አስጠንቅቋል። እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቊሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።”—1 ቆሮንቶስ 8:12, 13

8. በኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችና በፊልሞች መዝናናት ምን አደጋ አለው?

8 ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችና ፊልሞች ገበያውን አጥለቅልቀውታል። አንዳንዶቹ ምንም ጉዳት የማያስከትል አስደሳችና አዝናኝ ነገር ያቀርቡ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት መዝናኛዎች በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ያሳያሉ። አንድ ኤሌክትሮኒክ ጨዋታ አካል በማጉደልና በመግደል አሊያም ደግሞ ጸያፍ የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸም ጭምር የሚካሄድ ከሆነ ጤናማ ነው ማለት አይቻልም! ይሖዋ “ዐመፃን የሚወዱትን” ይጠላል። (መዝሙር 11:5፤ ምሳሌ 3:31፤ ቈላስይስ 3:5, 6) እንዲሁም የምትጫወተው ጨዋታ በውስጥህ የስስትን ወይም የጠብ አጫሪነትን ባሕርይ እየፈጠረ፣ ስሜትህን እያደነደነ ወይም ጊዜህን እያባከነብህ ከሆነ ተከትሎ የሚመጣውን መንፈሳዊ ጉዳት በማሰብ በፍጥነት ማስተካከያ አድርግ።—ማቴዎስ 18:8, 9

የመዝናናት ፍላጎታችንን በሚያንጽ መንገድ ማርካት

9, 10. አስተዋይ ክርስቲያኖች የመዝናናት ፍላጎታቸውን ለማርካት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

9 አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች “ተገቢ የሆነው ምን ዓይነት መዝናኛ ነው? ዓለም የሚያቀርበው አብዛኛው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ ነው” ይሉ ይሆናል። ሆኖም አስደሳች መዝናኛ ሊገኝ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን፤ ለዚህ ግን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ላለው መዝናኛ፣ በተለይ በወላጆች በኩል አስቀድሞ ማሰብና እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። ብዙዎች ከቤተሰባቸውና ከጉባኤያቸው አባላት ጋር መዝናናት አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል። ቤተሰቦች ዘና ብለው እየተመገቡ ስለ ዕለቱ ገጠመኞቻቸው መጨዋወታቸው ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቶች ማድረጋቸው የሚያስደስትና የሚያንጽ ነው። ወጣ ብሎ መንሸራሸር፣ ተገቢ የሆኑ ጨዋታዎችን መጫወት ወይም የእግር ጉዞ ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ያሉት ጤናማ መዝናኛዎች አስደሳችና አርኪ ናቸው።

10 ሦስት ልጆች ያሳደጉ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ሚስቱ እንዲህ ብለዋል:- “ልጆቻችን ገና ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ለእረፍት ወዴት እንደምንሄድ በምንወስንበት ጊዜ በምርጫው ይካፈላሉ። እረፍቱን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ስንል አልፎ አልፎ እያንዳንዱ ልጅ ጥሩ ባሕርይ ያለውን ጓደኛውን እንዲጋብዝ እንፈቅድ ነበር። በልጆቻችን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ክስተቶች በቁም ነገር እንመለከታቸዋለን። አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻችንንና በጉባኤያችን የሚገኙ ጓደኞቻችንን ቤታችን እንጋብዝ ነበር። ከቤት ውጪ ምግብ በማብሰል እየተመገብን የተለያዩ ጨዋታዎችን እንጫወት ነበር። በመኪናና በእግር ተጉዘን ተራራ እንወጣ የነበረ ሲሆን እንዲህ ያሉትን አጋጣሚዎች ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ትምህርት ለማግኘት ተጠቅመንባቸዋል።”

11, 12. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ ለመዝናናት ስታቅዱ ሌሎችን ማካተት የምትችሉት እንዴት ነው? (ለ) በብዙዎች አእምሮ የማይረሳ ትዝታ ጥለው ያለፉት እንዴት ያሉ ግብዣዎች ናቸው?

11 በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ለመዝናናት እቅድ በምታወጡበት ጊዜ ሌሎችን ማካተት ትችላላችሁ? መበለቶች፣ ያላገቡ፣ አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸው ቤተሰቦችና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ሰዎች ማበረታቻ ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ሉቃስ 14:12-14) እንዲሁም ጥቂት አዳዲስ የጉባኤ አባላትን መጨመር ትችላላችሁ፤ በእርግጥ ሌሎችን ለመጥፎ ተጽዕኖ ላለማጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21) ከቤታቸው መውጣት የሚያስቸግራቸው አቅመ ደካሞች ካሉ ደግሞ ቤታቸው ምግብ ይዞ በመሄድ አብሮ ለመመገብ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል።—ዕብራውያን 13:1, 2

12 ብዙዎች ቀለል ያለ ግብዣ በተዘጋጀባቸው ቦታዎች ተገኝተው ሌሎች እንዴት ክርስቲያን እንደሆኑና ለአምላክ ታማኝ ሆነው እንዲጸኑ የረዳቸው ምን እንደሆነ መስማታቸው የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው አልፏል። ልጆችን ጨምሮ በግብዣው የተገኙት ሁሉ የሚካፈሉበት የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይም ማንሳት ይቻላል። እንዲህ ያሉት ውይይቶች ማንም ሰው ሳይሸማቀቅ ወይም የበታችነት ሳይሰማው እርስ በርስ ለመበረታታት ይጠቅማሉ።

13. ኢየሱስና ጳውሎስ ሌሎችን እንግድነት በመቀበልም ሆነ ጥሩ እንግዳ በመሆን ረገድ ምን ምሳሌ ትተዋል?

13 ኢየሱስ ሌሎችን እንግድነት በመቀበልም ሆነ ራሱ ጥሩ እንግዳ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። እንዲህ ያሉትን አጋጣሚዎች ሁሉ መንፈሳዊ በረከቶችን ለማካፈል ይጠቀምባቸው ነበር። (ሉቃስ 5:27-39፤ 10:42፤ 19:1-10፤ 24:28-32) የጥንት ደቀ መዛሙርቱም ምሳሌውን ተከትለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:46, 47) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር:- “እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ። ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።” (ሮሜ 1:11, 12) በተመሳሳይ እኛም አንድ ላይ የምንሰባሰብባቸው አጋጣሚዎች የምንበረታታባቸው መሆን ይገባቸዋል።—ሮሜ 12:13፤ 15:1, 2

ልናስብባቸውና ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች

14. ብዙ ሰዎች የሚገኙበት ግብዣ አለማዘጋጀት የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ብዙውን ጊዜ በርካታ ሰዎች የሚገኙበትን ግብዣ መቆጣጠር የሚከብድ በመሆኑ እንዲህ የመሰለውን ግብዣ አለማዘጋጀት ይመረጣል። ጥቂት ቤተሰቦች ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ጋር የማይጋጭ ጊዜ መርጠው ሽርሽር ሊሄዱ ወይም ከልክ ያለፈ የፉክክር መንፈስ የማይታይበት ጨዋታ ሊጫወቱ ይችላሉ። የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ አገልጋዮች ወይም ደግሞ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች በግብዣ ላይ በሚገኙበት ጊዜ በጎ ተጽዕኖ ማሳደርና ዝግጅቱ ይበልጥ መንፈስን የሚያድስ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ።

15. ግብዣ ማዘጋጀት ተገቢ ቁጥጥር ማድረግንም የሚጨምረው ለምንድን ነው?

15 ግብዣ የሚያዘጋጁ ሰዎች ዝግጅቱን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ መዘንጋት አይገባቸውም። እንግዶችን ማስተናገድ ቢያስደስትህም እንኳን በሆነ መንገድ ቸልተኛ በመሆንህ ምክንያት ቤትህ ውስጥ በተፈጠረ ነገር አንድ እንግዳ እንደተደናቀፈ ብትሰማ በጣም አታዝንም? በዘዳግም 22:8 ላይ የተገለጸውን መመሪያ ተመልከት። አዲስ ቤት የሚሠራ እስራኤላዊ፣ በአብዛኛው እንግዶች በሚስተናገዱበት ጣሪያ ወይም ሰገነት ዙሪያ መከታ ማበጀት ነበረበት። ለምን? ጥቅሱ “ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ” ይላል። አንተም በተመሳሳይ እንግዶችህን ምክንያታዊ ባልሆኑ ገደቦች ሳታስጨንቅ የምታደርገው ነገር ለአካላዊና ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው እንደምታስብ የሚያሳይ ሊሆን ይገባል።

16. ግብዣ በሚዘጋጅበት ጊዜ አልኮል መጠጥ የሚቀርብ ከሆነ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል?

16 ግብዣው ላይ አልኮል መጠጥ የሚኖር ከሆነ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በርካታ ክርስቲያኖች መጠጥ የሚያቀርቡት እንግዶቻቸው ምን እንደቀረበላቸው ወይም ምን ያህል እየጠጡ እንደሆነ ራሳቸው መቆጣጠር የሚችሉ ከሆነ ብቻ ነው። አንዳንድ ተጋባዦች እንዲሰናከሉ ወይም ከልክ በላይ ለመጠጣት እንዲፈተኑ የሚያደርግ ነገር ሊኖር አይገባም። (ኤፌሶን 5:18, 19) አንዳንዶቹ እንግዶች በተለያየ ምክንያት ከአልኮል መጠጥ ለመራቅ ወስነው ይሆናል። የበርካታ አገሮች ሕግ ከተወሰነ ዕድሜ በታች ያሉ ልጆች አልኮል መጠጣት እንደማይገባቸው ይደነግጋል፤ እንዲህ ያሉት ገደቦች ከልክ በላይ ጥብቅ ቢመስሉም እንኳ ክርስቲያኖች የቄሳርን ሕግ ይታዘዛሉ።—ሮሜ 13:5

17. (ሀ) በግብዣው ወቅት ሙዚቃ ካለ ጋባዡ ጥሩ ምርጫ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው? (ለ) ጭፈራ የሚኖር ከሆነ ልከኝነት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

17 ጋባዡ በወቅቱ የሚኖረው ሙዚቃ፣ ዳንስ ወይም ሌላ መዝናኛ ከክርስቲያናዊ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። የሰዎች የዘፈን ምርጫ የሚለያይ ከመሆኑም በላይ በርካታ የሙዚቃ ዓይነቶች አሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ዘፈኖች የዓመጸኝነት መንፈስን፣ የሥነ ምግባር ብልግናንና ወንጀልን የሚያበረታቱ ናቸው። ስለዚህ መራጭ መሆን ያስፈልጋል። አንድ ሙዚቃ ጥሩ ለመባል የግድ ረጋ ያለ መሆን አያስፈልገውም፤ ሆኖም ዘፈኑ የጾታ ስሜት የሚያነሳሳ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው፣ በጣም የሚጮህ ወይም ኃይለኛ ምት ያለው ሊሆን አይገባም። የሙዚቃውን ድምፅ በልክ የማድረግን አስፈላጊነት በሚገባ ያልተረዳ ሰው ሙዚቃ እንዲመርጥ ከመፍቀድ ተቆጠብ። የጾታ ፍላጎትን በሚያነሳሳ መንገድ ዳሌና ጡትን ማንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች አስነዋሪ ድርጊቶች የሚታዩበት ጭፈራ ለአንድ ክርስቲያን እንደማይገባ የተረጋገጠ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:8-10

18. ወላጆች ልጆቻቸው የሚያደርጉትን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ከአደጋ ሊጠብቋቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በተጠሩበት በማንኛውም ግብዣ ላይ ምን እንደሚደረግ ማጣራታቸውና አብዛኛውን ጊዜም አብረዋቸው መገኘታቸው የጥበብ እርምጃ ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጋባዦች ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ወይም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ባሕርይ እንዲያሳዩ በሚፈተኑበት ተቆጣጣሪ የሌለው ግብዣ ላይ እንዲገኙ ፈቅደዋል። (ኤፌሶን 6:1-4) ምንም እንኳን ወጣቶቹ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ቢሆኑና ድርጊታቸው ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ቢያሳይም ‘ከወጣትነት ክፉ ምኞት እንዲሸሹ’ መርዳት ያስፈልጋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

19. ‘አስቀድመን መፈለግ’ በሚገባን ነገር ላይ እንድናተኩር የሚረዳን የትኛው እውነታ ነው?

19 ጤናማ በሆነና መንፈስን በሚያድስ መዝናኛ አልፎ አልፎ መካፈል ሕይወትን ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ደስታ አልከለከለንም፤ ነገር ግን እነዚህ እንቅስቃሴዎች በራሳቸው ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ሀብት በሰማይ ለማከማቸት እንደማይረዱን አሳምረን እናውቃለን። (ማቴዎስ 6:19-21) ኢየሱስ በሕይወት ውስጥ አንገብጋቢ የሆነው ነገር ‘በቅድሚያ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቅ መፈለግ’ እንጂ ‘አሕዛብ የሚጨነቁላቸውን’ ነገሮች ማለትም ምግብና መጠጥ ወይም ልብስ ለማግኘት መሯሯጥ እንዳልሆነ ደቀ መዛሙርቱ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:31-34

20. ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከለጋሱ አምላክ ምን መልካም ነገሮች ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ?

20 አዎን፣ ‘ስንበላም ሆነ ስንጠጣ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስናደርግ’ መልካም ነገሮችን ሁሉ በልክ እንድንደሰትባቸው የሰጠንን ለጋስ አምላክ እያመሰገንን ‘ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር እናደርጋለን።’ (1 ቆሮንቶስ 10:31) በቅርቡ ይሖዋ ምድርን ገነት ካደረገ በኋላ፣ የጽድቅ መስፈርቶቹን ከሚፈጽሙ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሆነን በተትረፈረፉ ስጦታዎቹ በተሟላ ሁኔታ እየተደሰትን ለዘላለም እንኖራለን።—መዝሙር 145:16፤ ኢሳይያስ 25:6፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1

ታስታውሳለህ?

• በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ጤናማ መዝናኛ ማግኘት የሚያስቸግራቸው ለምንድን ነው?

• ክርስቲያን ቤተሰቦች ሊደሰቱባቸው የሚችሉት መዝናኛዎች የትኞቹ ናቸው?

• አንድ ሰው በጤናማ መዝናኛዎች ላይ በሚካፈልበት ጊዜ ስለ የትኞቹ ነገሮች ሊያስብና ሊጠነቀቅ ይገባል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መልካም ፍሬ የሚያፈራ መዝናኛ ምረጥ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች የሚርቁት ከምን ዓይነት መዝናኛ ነው?