በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ትምህርቶች በተግባር እየዋሉ ነው?

በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ትምህርቶች በተግባር እየዋሉ ነው?

በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ ትምህርቶች በተግባር እየዋሉ ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዛሬ ከኖሩት ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። እንዲያውም ብዙዎች ከሁሉም የሚበልጥ ታላቅ ሰው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሜልቪን ብራግ የተባሉ እንግሊዛዊ ጸሐፊ እንደተናገሩት ትምህርቶቹ ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት “እዚህ ግቡ በማይባሉ ጥሩና ደጋግ ሰዎች ሕይወት ላይ በእጅጉ ተጽእኖ ያደረጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ሰዎች መጠነ ሰፊ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንዲፈጽሙም አነሳስተዋል።”

ስለ ክርስትናስ ምን ለማለት ይቻላል?

ስለ ክርስትናስ ምን ለማለት ይቻላል? ክርስትና “የሰው ዘር በመንፈሳዊ ረገድ ከደረሰባቸው ከፍተኛ የእድገት ደረጃዎች መካከል አንዱ” እንደሆነ ተገልጿል። በስኮትላንድ የሚገኘው የግላስጎው ካሌዶኒያን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ ኬልሶ አንድ አስተያየት ሰንዝረው ነበር። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የክርስትና እምነት ባሳለፈው የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ በኪነ ጥበብ፣ በምህንድስና፣ በፍልስፍና፣ በሙዚቃና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ረገድ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።”

ሌሎች ብዙ ሰዎች ግን የተለየ አመላካከት አላቸው። የእነዚህ ሰዎች ቅሬታ በአንድ መዝገበ ቃላት መሠረት “ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በማመንና ትምህርቶቹን በመከተል ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት” የሚል ፍቺ ባለው በክርስትና እምነት ላይ አይደለም። (ኮሊንስ ኮቢውልድ) ከዚህ ይልቅ ክርስትናን እንወክላለን የሚሉ ተቋማትና ድርጅቶች በሚፈጽሙት ድርጊት ይንገሸገሻሉ።

ለምሳሌ የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒትሽ ክርስትናን “የሰው ዘር የማይፋቅ ግድፈት” ሲል ገልጾታል። አክሎም “ታላቅ ርግማን፣ ክፉኛ የተጣመመ፣ . . . ዓላማውን ለማሳካት ሲል ማንኛውንም ዓይነት መሰሪና ስውር የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን ከመጠቀም እንዲሁም የጭካኔ ድርጊቶችን ከመፈጸም የማይመለስ” ብሎታል። ኒትሽ የሰነዘረው አስተያየት የተጋነነ እንደሆነ ባይካድም ይበልጥ ምክንያታዊ የሆኑ አንዳንድ ታዛቢዎችም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ላለፉት መቶ ዘመናት ተለይተው የሚታወቁት የክርስቶስን ባሕርይ በማንጸባረቃቸው ሳይሆን “በሥነ ምግባር ዝቅጠታቸው፣ በሚፈጽሟቸው አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲሁም በአንደበታቸውም ሆነ በድርጊታቸው አምላክን በመስደባቸው” ስለሆነ ነው።

ክርስቶስ ከዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ጋር ነው?

ስለሆነም “ክርስቶስ ከዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ጋር ነው?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። አንዳንዶች ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” አብሯቸው እንደሚሆን ቃል መግባቱን በማስታወስ በፍጥነት “እንዴታ!” ብለው ይመልሱ ይሆናል። (ማቴዎስ 28:20) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እንደዚያ ብሎ ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የአንድ ሰው ጠባይ ምንም ይሁን ምን የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ስላለ ብቻ አብሮት እንደሚሆን መናገሩ ነበር?

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች አምላክ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ይሰማቸው እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። አምላክ እስራኤልን ለተለየ ዓላማ ስለመረጠ ምንም ነገር ብናደርግ ፈጽሞ አይተወንም ብለው ያስቡ ነበር። (ሚክያስ 3:11) ይሁንና ከጊዜ በኋላ ከአምላክ ሕግጋትም ይሁን ከአቋም ደረጃዎቹ ሙሉ በሙሉ ራቁ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!” በማለት ግልጹን ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:38) በዚያን ጊዜ የነበረው ሃይማኖታዊ ሥርዓት የአምላክን ሞገስ አጥቶ ነበር። አምላክ የተወው ከመሆኑም በላይ የሮም ሠራዊት የእምነቱ ማዕከል የነበረችውን ኢየሩሳሌምንም ሆነ ቤተ መቅደሷን በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንዲያጠፋቸው ፈቅዷል።

በክርስትናም ላይ ተመሳሳይ ነገር ይከሰት ይሆን? ኢየሱስ እስከ “ዓለም ፍጻሜ” ድረስ ከተከታዮቹ ጋር እንደሚሆን የገባውን ቃል ለመፈጸም ከእነርሱ ምን እንደሚጠብቅ እስቲ እንመርምር።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በምድር ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል