በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል የሆነውን ማወቅና መፈጸም

ትክክል የሆነውን ማወቅና መፈጸም

የሕይወት ታሪክ

ትክክል የሆነውን ማወቅና መፈጸም

ሃደን ሳንደርሰን እንደተናገረው

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:17) እውነት ነው፣ ፈታኙ ሁኔታ ያለው የአንድን ነገር ትክክለኛነት በማወቁ ላይ ሳይሆን ያወቁትን በመተግበሩ ላይ ነው! ለ40 ዓመታት ያህል ሚስዮናዊ ሆኜ ያገለገልኩ ሲሆን አሁን 80 ዓመት አልፎኛል፤ ባሳለፍኩት ሕይወት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እውነተኛ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ። አምላክ ያዘዘውን መፈጸም ደስታ ያስገኛል። ይህ እውነት የሆነልኝ እንዴት እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።

በ1925፣ የሦስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ በከተማችን በኒውካስል፣ አውስትራሊያ በተደረገ ስብሰባ ላይ የቀረበ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር አደመጡ። “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ንግግር እናቴ እውነትን እንዳገኘች እርግጠኛ እንድትሆን ስላደረጋት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራ መገኘት ጀመረች። የአባቴ ፍላጎት ግን ወዲያውኑ ከሰመ። በመሆኑም በያዘችው አዲስ እምነት ምክንያት እናቴን ይቃወማትና በዚያው አቋሟ የምትጸና ከሆነ ጥሏት እንደሚሄድ በመናገር ያስፈራራት ጀመር። እናቴ አባቴን ትወደውና ቤተሰባችንም እንዳይፈርስ ትፈልግ ነበር። ይሁንና ከሁሉም በላይ ለአምላክ መታዘዝ እንዳለባት ታውቅ ስለነበር በእርሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ለማድረግ ወሰነች። (ማቴዎስ 10:34-39) አባቴም ጥሎን ሄደ፤ ከዚያ በኋላ አባቴን የማየው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር።

መለስ ብዬ ሳስበው፣ እናቴ ለአምላክ ያሳየችው ታማኝነት እጅግ ያስደንቀኛል። ያደረገችው ውሳኔ እኔም ሆንኩ ታላቅ እህቴ ቢዩላ መንፈሳዊ በረከቶችን እንድናጭድ ምክንያት ሆኗል። ከዚህም በላይ፣ ትክክል የሆነውን ካወቅን በኋላ ያንን ለመፈጸም ከልብ የመጣርን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ረድቶናል።

የእምነት ፈተናዎች

በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰባችንን ለመርዳት ብዙ ይጥሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሴት አያቴ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣች፤ እርሷም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበለች። አያቴና እናቴ በስብከቱ ሥራ የማይነጣጠሉ ጓደኛሞች የነበሩ ሲሆን ደርበብ ያሉና ተግባቢ መሆናቸው በብዙ ሰዎች ዘንድ አክብሮት አትርፎላቸዋል።

በዚህ ወቅት ትላልቆቹ ወንድሞች ለእኔ ልዩ ትኩረት ይሰጡና ያሠለጥኑኝ ነበር። ብዙም ሳልቆይ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለሰዎች አጠር ያለ ምሥክርነት ለመስጠት በመመሥከሪያ ካርድ እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ ተማርኩ። በተጨማሪም በቴፕ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻ አሰማ እንዲሁም ትላልቅ ማስታወቂያዎችን አንገቴ ላይ አንጠልጥዬ በከተማው አውራ ጎዳናዎች ላይ እሄድ ነበር። ዓይናፋር ስለነበርኩ ይህን ማድረግ ለእኔ ቀላል አልነበረም። ይሁንና ትክክል የሆነው ምን እንደሆነ ተረድቼ ስለነበረ ባወቅሁት መሠረት ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር።

ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ባንክ ቤት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ይህ ሥራ ደግሞ በመላው ኒው ሳውዝ ዌልስ የሚገኙትን በርካታ የባንክ ቅርንጫፎች እየተዘዋወሩ ማየት ይጠይቅ ነበር። በወቅቱ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በጣም አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ያገኘሁት ሥልጠና እምነቴ እንዳይጠፋ ረድቶኛል። እማማ የምትጽፍልኝ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች መንፈሳዊነቴን አጠንክረውልኛል።

ከዚህም በላይ ደብዳቤዎቹ በተገቢው ጊዜ አስፈላጊውን እርዳታ ለግሰውኛል። ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረ፤ እኔም በውትድርና እንዳገለግል መጥሪያ ደረሰኝ። የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አክራሪ ሃይማኖተኛና የአካባቢው ጦር አዛዥ ነበር። ክርስቲያን እንደ መሆኔ መጠን የገለልተኝነት አቋሜን በነገርኩት ጊዜ ሁለት አማራጮች ሰጠኝ፤ ወይ ሃይማኖቴን መተው አሊያም ባንኩን መልቀቅ ነበረብኝ! በአካባቢው ተቋቁሞ በነበረው የምልመላ ማዕከል ሪፖርት ለማድረግ ስሄድ ሁኔታው ይበልጥ ተባባሰ። ወደሚመዘግበው ሰው ስቃረብ በቦታው ተገኝቶ የነበረው የባንክ ቤቱ ኃላፊ ምን እንደማደርግ ለማየት በትኩረት ይጠባበቅ ጀመር። የምልመላው ቅጽ ላይ አልፈርምም ባልኩ ጊዜ ባለ ሥልጣናቱ በጣም ተበሳጩ። ሁኔታው የሚያስጨንቅ ቢሆንም ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ቆርጬ ነበር። በይሖዋ እርዳታ ተረጋግቼና ሳልፈራ መጽናት ቻልኩ። ቆየት ብሎም አንዳንድ ቅጥር ወሮበሎች እያፈላለጉኝ መሆኑን ስሰማ ወዲያውኑ ጓዜን ጠቅልዬ በባቡር ከከተማ ወጣሁ።

ወደ ኒውካስል ስመለስ የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልነበሩ ሌሎች ሰባት ወንድሞች ጋር ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ዳኛውም ከባድ የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ ለሦስት ወር እንድንታሰር ፈረዱብን። መታሰራችን ቢያሳዝነንም ትክክል የሆነውን ማድረጋችን ብዙ በረከቶችን አስገኝቶልናል። ከእስር ቤት ከተፈታን በኋላ አብሮኝ ታስሮ የነበረው ሂልተን ዊልኪንሰን በፎቶ ቤቱ ውስጥ አብሬው እንድሠራ ጠየቀኝ። በዚያም በእንግዳ መቀበያ ክፍል ትሠራ ከነበረችውና በኋላ ላይ ባለቤቴ ከሆነችው ከሜሎዲ ጋር ተዋወቅሁ። ከእስር ቤት ከወጣሁ ብዙም ሳይቆይ ለይሖዋ ራሴን መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ግብ አወጣን

ከጋብቻችን በኋላ እኔና ሜሎዲ ኒውካስል ውስጥ የራሳችንን ፎቶ ቤት ከፈትን። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በሥራ በጣም ከመወጠራችን የተነሳ ጤንነታችንም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና መጎዳት ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን በወቅቱ በአውስትራሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሲያገለግል የነበረውና አሁን የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ቴድ ጃራዝ ስለ መንፈሳዊ ግቦቻችን አወያየን። ከውይይቱ በኋላ ፎቶ ቤታችንን ለመሸጥና ሕይወታችንን ቀላል ለማድረግ ውሳኔ ላይ ደረስን። በ1954 አንድ አነስ ያለች ተጎታች ቤት ገዛንና በቪክቶሪያ ግዛት ወደምትገኘው ባለራት ከተማ ተዛውረን አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን በመሆን ማገልገል ጀመርን።

በባለራት ከሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ ጋር አብረን በሠራንባቸው ጊዜያት ይሖዋ ጥረታችንን ባርኮልናል። በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር ከ17 ወደ 70 ማደግ ችሎ ነበር። ከዚያም በደቡብ አውስትራሊያ ግዛት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ቀጣዮቹን ሦስት ዓመታት በአድሌድ ከተማ እንዲሁም በመሪ ወንዝ አቅራቢያ ባሉ ወይንና የብርቱካን ዝርያ የሆኑ ፍራፍሬዎች በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት አስደሳች ጊዜ አሳለፍን። ሕይወታችን በእጅጉ ተለውጦ ነበር! አፍቃሪ ከሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጎን ተሰልፈን ማገልገላችን እጅግ አስደሳች ነበር። በእርግጥም ትክክል እንደሆነ ያወቅነውን ነገር በመፈጸማችን በጣም ተክሰናል!

በሚስዮናዊነት ማገልገል ጀመርን

በ1958፣ በኒው ዮርክ ሲቲ በሚደረገው “መለኮታዊ ፈቃድ” የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ማሰባችንን ቀደም ብለን ለአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ አሳወቅን። እነርሱም በምላሹ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውና የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ የሆነውን የጊልያድ ትምህርት ቤት ማመልከቻ ቅጽ ላኩልን። በዚያን ጊዜ ዕድሜያችን በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ ስለነበር በጊልያድ ለመካፈል እንዳለፈብን ተሰምቶን ነበር። ያም ሆኖ የማመልከቻ ቅጹን ሞልተን ላክንና በ32ኛው የጊልያድ ክፍል እንድንካፈል ተጋበዝን። በሥልጠናው አጋማሽ ላይም ሕንድ መመደባችን ተነገረን። መጀመሪያ ላይ የፍርሃት ስሜት ቢያድርብንም ትክክል የሆነውን ለማድረግ ስለፈለግን የተሰጠንን ምድብ በደስታ ተቀበልን።

በ1959 አንድ ቀን ማለዳ ላይ፣ የተሳፈርንባት መርከብ ቦምቤ (የአሁኗ ሙምባይ) ደረሰች። ወደቡ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀን ሠራተኞች ዝርግትግት ብለው ተኝተዋል። ከመርከብ ስንወርድ እንግዳ የሆነ ጠረን አወደን። ረፈድ ሲል የነበረው ሙቀት የአየሩ ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል ጠቆመን። ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ሙቀት ፈጽሞ አይተን አናውቅም! ቀደም ሲል በባለራት አብረውን ሲያገለግሉ የነበሩ ሊንተንና ጄኒ ዶወር የተባሉ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ተቀበሉን። ከዚያም በከተማው መሐል ባለ አንድ ሕንጻ ላይ ወደሚገኘው የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ወሰዱን፤ በዚህ የተጣበበ የቤቴል ቤት ውስጥ የሚያገለግሉ ስድስት ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበሩ። ከ1926 ጀምሮ በሕንድ በሚስዮናዊነት ሲያገለግል የቆየው ወንድም ኤድዊን ስኪነር ወደ ምድባችን ከመሄዳችን በፊት ሁለት ትላልቅ የሸራ ሻንጣዎች እንድንገዛ መከረን። በሕንድ ባቡሮች ላይ እንዲህ ዓይነት ሻንጣዎች ተጭነው መመልከት የተለመደ ነው፤ እኛንም ቢሆን ቆየት ብሎ ባደረግናቸው የተለያዩ ጉዞዎች ላይ በእጅጉ ጠቅመውናል።

ለሁለት ቀናት ያህል በባቡር ከተጓዝን በኋላ በስተ ደቡብ በሚገኘው የማድራስ ግዛት ውስጥ ወዳለችው ቲራቸራፓሊ (የአሁኗ ታሚል ናዱ) ከተማ ደረስን፤ ይህ አዲሱ ምድባችን ነበር። በዚያም 250,000 በሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በማገልገል ላይ ከነበሩት ሦስት ሕንዳውያን ልዩ አቅኚዎች ጋር ተገናኘን። ሕዝቡ ከጥንታዊው የአኗኗር ዘይቤ ገና አልተላቀቀም ነበር። በአንድ ወቅት በኪሳችን የነበረን ገንዘብ 4 የአሜሪካ ዶላር የሚሞላ አልነበረም። ሆኖም ያለን ገንዘብ ቢያልቅም ይሖዋ አልተወንም። መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠና የነበረ አንድ ሰው ስብሰባዎችን ለማድረግ የሚያስችል ተስማሚ ቤት ለመከራየት የሚበቃ ገንዘብ አበደረን። በሌላ ጊዜ ደግሞ ቤት ውስጥ በቂ ምግብ አልነበረንም። ይሁንና አንድ ጎረቤታችን ቤት የተዘጋጀ የሕንዶች ምግብ ይዞልን መጣ። ምግቡን የወደድኩት ቢሆንም የተሠራበት ቅመም የሚያቃጥል ስለነበረ ስቅታ ያዘኝ!

በመስክ አገልግሎት መካፈል

በቲራቸራፓሊ ከሚኖሩት ሰዎች ውስጥ ጥቂቶች እንግሊዝኛ ቢናገሩም የብዙኃኑ መግባቢያ ግን ታሚል ነበር። በመሆኑም በዚህ ቋንቋ ለመስክ አገልግሎት የሚሆን ቀላል አቀራረብ ለመማር ብርቱ ጥረት ማድረግ ነበረብን። ቋንቋውን ለመማር ያደረግነው ጥረት በበርካታ ነዋሪዎች ዘንድ አክብሮትን አትርፎልናል።

ከቤት ወደ ቤት ማገልገል በጣም ያስደስተን ነበር። ሕንዶች በተፈጥሯቸው እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። በመሆኑም ብዙዎቹ ወደ ቤታቸው ገብተን ሻይ ቡና እንድንል ይጋብዙን ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የሙቀቱ መጠን ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ስለማይወርድ የሚቀርብልንን ግብዣ ካለ አንዳች ማመንታት አመስግነን እንቀበላለን። መልእክታችንን ከመናገራችን በፊት ስለግል ጉዳዮች መጨዋወት የጨዋነት ምልክት ተደርጎ ይታይ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የቤቱ ባለቤቶች እኔና ባለቤቴን እንደሚከተለው እያሉ ይጠይቁናል:- “አገራችሁ የት ነው? ልጆች አሏችሁ? ምነው አልወለዳችሁም?” በተለይ የልጅ ነገር ሲነሳ ብዙዎቹ ጥሩ ሐኪም ሊጠቁሙን እንደሚችሉ ይነግሩናል! ያም ቢሆን ግን እንዲህ ዓይነቱ ጭውውት ራሳችንን ለማስተዋወቅና የምናከናውነው መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች የማስተማሩ ሥራ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለመግለጽ በር ይከፍትልናል።

ከምንመሰክርላቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከክርስትና እምነት ፍጹም ልዩ የሆነው የሂንዱ እምነት ተከታዮች ነበሩ። ውስብስብ የሆነውን የሂንዱ ፍልስፍና እያነሳን ሙግት ከመግጠም ይልቅ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንሰብክላቸው ነበር፤ ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቶልናል። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በመኖሪያ ቤታችን በምናደርገው ስብሰባ ላይ 20 ያህል ሰዎች መገኘት ጀመሩ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ነለታምቢ የተባለ ሲቪል መሃንዲስ ይገኝበታል። ከጊዜ በኋላ እርሱና ወንድ ልጁ ቪጄዬለን 50 ያህል ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ረድተዋል። ከዚህም በላይ ቪጄዬለን በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የማገልገል መብት አግኝቶ ነበር።

ከቦታ ወደ ቦታ መጓዝ

በሕንድ የመጀመሪያው ቋሚ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ስጋበዝ በአገሪቱ መኖር ከጀመርን ገና ስድስት ወር አልሞላንም ነበር። ይህ ሥራ በመላው ሕንድ መዘዋወርንና ትላልቅ ስብሰባዎችን ማደራጀትን የሚጠይቅ ሲሆን በምንጎበኛቸው አካባቢዎች ዘጠኝ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ሥራው አድካሚ ነበር። በሦስት የብረት ሣጥኖችና ምንጊዜም በማይለዩን የሸራ ሻንጣዎቻችን ውስጥ ለስድስት ወራት የሚበቃንን ልብስና ቁሳቁስ ሸክፈን ከማድራስ ከተማ (ከአሁኗ ቼኒ) በባቡር ጉዞ እንጀምራለን። አውራጃው የሚሸፍነው ክልል ዙሪያ 6,500 ኪሎ ሜትር ስለነበረ ሳናቋርጥ ከቦታ ወደ ቦታ እንዘዋወር ነበር። በአንድ ወቅት፣ በደቡባዊው ግዛት በምትገኘው ባንጋሎር ከተማ ያደረግነውን ስብሰባ እሁድ ዕለት ካጠናቀቅን በኋላ በቀጣዩ ሳምንት በሚደረገው ሌላ ስብሰባ ላይ ለማገልገል በስተ ሰሜን በሂማልያ ተራራዎች ግርጌ ወደምትገኘው ዳርጂሊንግ አቀናን። ዳርጂሊንግ ለመድረስ አምስት ጊዜ ባቡሮችን መቀየርና ወደ 2,700 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት መጓዝ ነበረብን።

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል እንደጀመርን አካባቢ ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የተሰኘውን ተንቀሳቃሽ ፊልም ለሰዎች እናሳይ ነበር። ፊልሙ፣ ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች የሚያከናውኑት ሥራ ምን ያህል ስፋት እንዳለው እንዲረዱ ያስችላቸዋል። ብዙውን ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፊልሙን ለማየት ይገኙ ነበር። በአንድ ወቅት መንገድ ዳር ለተሰበሰቡ ሰዎች ፊልሙን ማሳየት ጀመርን። ፊልሙ በመታየት ላይ እያለ ሰማዩ እየጠቆረ ሄደና ብዙም ሳይቆይ ሊዘንብ ማስገምገም ጀመረ። ከዚህ ቀደም እንደዚሁ ተሰብስበው ሲያዩ የነበሩ ሰዎች ፊልሙ በመቋረጡ ሳቢያ ሁከት ፈጥረው ስለነበር ፊልሙን ከማቋረጥ ይልቅ ፈጠን ላደርገው ወሰንኩ። ደስ የሚለው ነገር ልክ ዝናቡ ማንጠባጠብ ሲጀምር ፊልሙ አለቀ።

ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት እኔና ሜሎዲ አብዛኛውን የሕንድ ክልል አዳርሰናል። እያንዳንዱ አካባቢ የራሱ የሆነ ምግብ፣ አለባበስ፣ ቋንቋ እንዲሁም መልክዓ ምድር ስላለው ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የመጓዝ ያህል ነበር። የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች በዓይነታቸው የተለያዩ መሆናቸው እንዴት ያስደስታል! ይህ ሁኔታ ሕንድ ባሏት የዱር እንስሳት ላይም ይንጸባረቃል። አንድ ጊዜ በኔፓሊዝ ጫካ እየተዝናናን ሳለ አንድ ትልቅ ነብር የማየት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። እጅግ አስደናቂ እንስሳ ነው። ይህ አጋጣሚ በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም በሚሰፍንበት በመጪው ገነት የመኖር ጉጉታችን ይበልጥ እንዲጨምር አድርጓል።

በድርጅታዊ አሠራር ረገድ ማስተካከያዎች ማድረግ

ቀደም ባሉት ዓመታት በሕንድ የነበሩት ወንድሞች የይሖዋ ድርጅት ሥራው እንዴት መደራጀት እንዳለበት የሚያወጣቸውን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል አስፈልጓቸው ነበር። አንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ወንዶቹ በአንድ ተርታ ሴቶቹ ደግሞ ለብቻቸው በሌላኛው ተርታ ይቀመጡ ነበር። ስብሰባዎች በሰዓቱ የሚጀመሩት አልፎ አልፎ ሲሆን በአንድ አካባቢ ደግሞ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ወደ ስብሰባ የሚመጡት ደወል ሲደወል ነበር። በሌላ አካባቢ ደግሞ አስፋፊዎቹ ፀሐይዋን በመመልከት ስብሰባው ይጀምራል ብለው ባሰቡበት ሰዓት አንድ በአንድ ይመጣሉ። ትላልቅ ስብሰባዎችም ሆኑ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ፕሮግራሞች በቋሚነት አይደረጉም ነበር። ወንድሞች ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ የነበሩ ቢሆኑም እንኳ ሥልጠና ያስፈልጋቸው ነበር።

በ1959 የይሖዋ ድርጅት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት አቋቋመ። ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ይህ የሥልጠና ፕሮግራም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ልዩ አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያንና የጉባኤ ሽማግሌዎች ያሉባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲወጡ አግዟቸዋል። በታኅሣሥ ወር 1961 ትምህርት ቤቱ በሕንድ ሲጀመር አስተማሪ ሆኜ አገልግያለሁ። ውሎ አድሮ የሥልጠናው ውጤት በአገሪቱ ባሉት ጉባኤዎች ላይ መታየቱ አልቀረም፤ ከፍተኛ እድገት መገኘትም ጀመረ። ወንድሞች ትክክለኛውን አሠራር ካወቁ በኋላ በአምላክ መንፈስ እርዳታ በተግባር ያውሉት ነበር።

ትላልቅ ስብሰባዎች ወንድሞች እንዲበረታቱና አንድነታቸው እንዲጠናከር እገዛ አድርገዋል። ከእነዚህ ስብሰባዎች መካከል በ1963 በኒው ዴልሂ የተደረገው “የዘላለም ወንጌል” የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ጉልህ ስፍራ ይይዛል። በመላው ሕንድ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ይህን ለማድረግ ሲሉ ያጠራቀሙትን ጥሪት በሙሉ አሟጠዋል። በስብሰባው ላይ 27 አገሮችን የወከሉ 583 ወንድሞች ተገኝተው ስለነበር የአገሬው ተወላጆች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ቁጥር ካላቸው የውጪ አገር ወንድሞች ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር።

በ1961 እኔና ሜሎዲ የቦምቤ ቤቴል ቤተሰብ አባላት እንድንሆን ተጋበዝን። ቆየት ብሎ በዚሁ ቤቴል የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ አገልግያለሁ። ከዚያም ሌሎች መብቶችን አገኘሁ። ለብዙ ዓመታት በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ በዞን የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ። ከእነዚህ አገሮች በብዙዎቹ ውስጥ የምሥክርነቱ ሥራ ታግዶ ስለነበር አስፋፊዎቹ “እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን” መሆን ነበረባቸው።—ማቴዎስ 10:16

የተገኘው እድገትና ያጋጠሙን ለውጦች

በ1959 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕንድ ስንመጣ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት አስፋፊዎች ቁጥር 1,514 ነበር። አሁን ይህ ቁጥር አድጎ ከ24,000 በላይ ሆኗል። ይህን ከፍተኛ ጭማሪ ለማስተናገድ ሲባል የቤቴል ቤተሰብ መኖሪያ ከአንድም ሁለት ጊዜ የተቀየረ ሲሆን በመጀመሪያ ቦምቤ ውስጥ በኋላ ላይ ደግሞ ቦምቤ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሌላ አዲስ ሕንጻ እንዲዛወር ተደርጓል። ከዚያም በመጋቢት 2002 የቤቴል ቤተሰብ በደቡብ ሕንድ፣ በባንጋሎር አቅራቢያ ወደተሠራ አዲስ መኖሪያ ተዛወረ። በአሁኑ ወቅት በዚህ ዘመናዊ ሕንጻ ውስጥ 240 ቤቴላውያን የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ 20 ቋንቋዎች በመተርጎሙ ሥራ ላይ ይካፈላሉ።

እኔና ሜሎዲ ወደ ባንጋሎር ለመዛወር ጎጉተን የነበረ ቢሆንም ያለብን የጤንነት ችግር በ1999 ወደ አውስትራሊያ እንድንመለስ አስገደደን። አሁን በሲድኒ ቤቴል በማገልገል ላይ እንገኛለን። ከሕንድ ብንወጣም በዚያ ላሉት ውድ ወዳጆቻችንና መንፈሳዊ ልጆቻችን ያለን ጥልቅ ፍቅር አልቀዘቀዘም። ደብዳቤዎቻቸው ሲደርሱን እጅግ እንደሰታለን!

እኔም ሆንኩ ሜሎዲ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍናቸውን ከ50 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብለን ስንመለከት ይሖዋ እጅግ እንደባረከን ይሰማናል። በአንድ ወቅት የሰዎችን ምስል በወረቀት ላይ እናትም ነበር፤ ይሁንና አምላክ መቼም የማይረሳቸው እንዲሆኑ ሰዎችን መርዳት ፍጹም የተሻለ ሥራ ነው። በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ለማስቀደም በመወሰናችን እንዴት ያሉ ግሩም ተሞክሮዎችን አግኝተናል! አዎን፣ አምላክ ትክክል ነው ያለውን መፈጸም ደስታ ያመጣል!

[በገጽ  15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒው ዴልሂ

ዳርጂሊንግ

ሕንድ

ቦምቤ (ሙምባይ)

ባንጋሎር

ማድራስ (ቼኒ)

ቲራቸራፓሊ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1942 ሃደን እና ሜሎዲ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሕንድ ቤቴል ቤተሰብ፣ 1975