በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ጓደኞች እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ?

እውነተኛ ጓደኞች እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ?

እውነተኛ ጓደኞች እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ?

ብዙ ሰዎች ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሯቸው ይፈልጋሉ። ያጋጠሙንን ነገሮች የምናካፍላቸው እውነተኛ ወዳጆችን ማግኘት ሕይወታችንን ይበልጥ አስደሳች ያደርገዋል። ይሁንና እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ከዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት የተሳካ እንዲሆን ቁልፉ ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር ማሳየት መሆኑን ገልጿል። “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት አስተምሯል። (ሉቃስ 6:31) ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ በመባል የሚታወቀው ይህ አባባል ወዳጆች ማፍራት ከፈለግህ ራስ ወዳድ ከመሆን ይልቅ ለጋስ መሆን እንዳለብህ ይጠቁማል። በአጭር አነጋገር ጓደኛ ለማግኘት ከፈለግህ አንተ ራስህ ጓደኛ ሆነህ መገኘት ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

የምንቀርበውና የምንወደው ወዳጅ በአንድ ጀምበር ልናገኝ አንችልም። ጓደኝነት ከተራ ትውውቅ ያለፈ ጉዳይ ነው። ጓደኞችህ ውስጣዊ ስሜትህን የምታካፍላቸው ሰዎች ናቸው። የተቀራረበ ወዳጅነትን መመሥረትም ይሁን ጠብቆ ማቆየት ብርቱ ጥረት ይሻል። ብዙውን ጊዜ ጓደኝነት የባልንጀሮቻችንን ፍላጎት ከእኛ ጥቅም ማስቀደምን ይጠይቃል። ጓደኛሞች የሚጋሩት ደስታቸውን ብቻ ሳይሆን ሐዘናቸውንም ጭምር ነው።

በተለይም ችግር ለደረሰበት ሰው ስሜታዊና ተግባራዊ ድጋፍ በመስጠት እውነተኛ ጓደኛ መሆንህን ማሳየት ትችላለህ። ምሳሌ 17:17 “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። እውነት ነው፣ ጓደኝነት ከቤተሰብ ትስስር ይልቅ የሚጠነክርበት ጊዜ አለ። ምሳሌ 18:24 ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ወዳጅ የሚያበዛ ሰው ራሱን ለጥፋት ይዳርጋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።” እውነተኛ ጓደኝነት እንዴት መመሥረት እንደምትችል ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር በሚታወቁ ሕዝቦች መካከል ለመሆንስ ትሻለህ? (ዮሐንስ 13:35) ከሆነ፣ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ጓደኞችን እንዴት ማግኘት እንደምትችል ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው።