በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች

ኡጋንዳ:- ሉሲ በአንድ ትልቅ የመድኃኒት ማከፋፈያ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራ የይሖዋ ምሥክር ናት። በአንድ ወቅት የመሥሪያ ቤታቸው ሒሳብ ሲመረመር በርከት ያለ ገንዘብ መጉደሉ ስለተደረሰበት እርሷና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቿ ገንዘቡን አለመውሰዳቸውን በመሐላ እንዲያረጋግጡ ተጠየቁ። ሉሲ ተራዋ ደርሶ እጅዋን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመጫን ንጹሕ ለመሆኗ እንድትምል ስትጠየቅ፣ እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ምሳሌ 15:3ን አወጣችና “የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ” የሚለውን ሐሳብ ድምጿን ከፍ አድርጋ አነበበች። ለጥቂት ጊዜ በክፍሉ ውስጥ ፍጹም ጸጥታ ከሰፈነ በኋላ ጥፋተኛዋ ሴት ወደ ተቆጣጣሪው በመሄድ ያደረገችውን ሁሉ ተናገረች። ተቆጣጣሪውም ለወደፊቱ ሁሉም “የሉሲን ጥቅስ” እንዳይረሱት መከራቸው። ብዙም ሳይቆይ ሉሲ የደሞዝ ጭማሪ ያገኘች ከመሆኗም በላይ የማከፋፈያውን ቁልፍ በኃላፊነት ተረከበች።

ቤኒን:- ዦዝዊ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚደርስበትን ተደጋጋሚ ፌዝ መቋቋም አስፈልጎት ነበር። በአንድ ወቅት ክፍል ውስጥ ሲመልስ በመሳሳቱ ምክንያት አንዳንድ የክፍል ጓደኞቹ “የይሖዋ ቄስ፣ አንተም ትሳሳታለህ?” ሲሉ አፌዙበት። ቀሪዎቹ ደግሞ “ቦርሳውን አንጠልጥሎ ሲንገላወድ ይውላል” በማለት አላገጡበት።

ዦዝዊ “ቅዳሜና እሁድ አገልግሎት ስወጣ በተለይ የክፍል ጓደኞቼን እንዳላገኛቸው እሰጋ ነበር” ሲል የተሰማውን በግልጽ ተናግሯል። ይሁንና ጉዳዩን አስመልክቶ ከጸለየ በኋላ ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሁኔታውን አጫወተው። ሽማግሌውም የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴውን ከፍ እንዲያደርግና ለክፍል ጓደኞቹም ቢሆን በድፍረት ጽሑፎችን በማበርከት ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ አበረታታው። ዦዝዊ ይህን ማድረጉ በሦስት አቅጣጫ ጥሩ ውጤት እንዳስገኘለት ይናገራል። እንዲህ ይላል:- “አሁን፣ አብዛኛውን ጊዜ ረዳት አቅኚ በመሆን አሳልፋለሁ፤ ሲያፌዙብኝ ከነበሩት የክፍል ጓደኞቼ መካከል ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ሆነዋል። ከዚህም በላይ የትምህርት ቤት ውጤቴ እጅግ ተሻሽሏል።”

ኢትዮጵያ:- ከዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በፊት አስናቀች መንጃ ፈቃድ አገኘችና የመንጃ ፈቃዱ ባለቤት ለሆነችው ኤልሳ የተባለች ሴት ለመመለስ ቀጠሮ ያዙ። ኤልሳ በአስናቀች ታማኝነት በጣም በመደነቋ ገንዘብ ልትሰጣት ፈለገች። አስናቀች ግን ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር አበረከተችላት። በቀጣዩ ቀን ኤልሳ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በዚህ ጊዜ፣ ይሖዋ የሚለው ስም ለእርሷ እንግዳ እንዳልሆነና ቄስ የሆኑት አባቷ ስለዚህ ስም ነግረዋት አንደነበር ገለጸች። መላው ቤተሰቧ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ይሁንና ቄስ የሆኑት አባቷ ነገሩን ሲሰሙ የይሖዋ ምሥክሮች የማይረቡ ናቸው በማለት እጅግ ተቆጡ። ኤልሳ ጥናቷን ለመቀጠል ቆርጣ ስለነበር ወደ አባቷ በመቅረብ የይሖዋ ምሥክሮች በፍጹም እርሳቸው እንዳሉት ዓይነት ሰዎች አለመሆናቸውን በትሕትና ትነግራቸዋለች። አባቷ ሁኔታው ስላሳሰባቸው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር እርሷ ሳታውቅ በመውሰድ ደግመው ደጋግመው አነበቡት፤ ያነበቡትም ነገር ልባቸውን ነካው። ከዚህ በኋላ መንገድ ላይ የሚያገኟቸውን ሰዎች እንደወትሯቸው በሥላሴ ስም መመረቃቸውን አቆሙ። ብዙም ሳይቆይ “ከሃዲ” ናቸው ይባሉ ጀመር፤ አንዳንዶችም ሊደበድቧቸው ፈለጉ። በዚህ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ እርሳቸውም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። አሁን ኤልሳና ሰባት የቤተሰቧ አባላት ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ባለቤቷና ልጅዋም ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ ናቸው።

ኮት ዲቩዋር:- አንደርሰን ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብብ ለሚያየው አንድ ባለሱቅ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ያበረክትለታል። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በተለይም “አምላክን የሚያስደስት የቤተሰብ ሕይወት” የሚለው ትምህርት የዚህን ሰው ትኩረት ሳበው። ሰውየው እንዲህ ብሏል:- “ሁለቱም የትዳር ጓደኞች በጋብቻ ውስጥ የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸው አላውቅም ነበር። አምሽቼ ስገባ እንኳ ባለቤቴ አንዲት ቃል እንድትናገረኝ አልፈልግም። ለመናገር ብትሞክር ግን፣ ‘ወንዱ እኮ እኔ ነኝ፣ ባሻኝ ሰዓት መውጣትና መግባት እችላለሁ፤ ሚስት እንደመሆንሽ መጠን ቤቱን መጠበቅ ያንቺ ፋንታ ነው’ እላት ነበር። አሁን ግን ከሥራ እንደወጣሁ ቤቴ እገባለሁ፤ እንዲሁም ባለቤቴን የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን አግዛታለሁ።

ኬንያ:- የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነ አንድ የሰባት ዓመት ልጅ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት መቃረቡን ይሰማል። ስለሆነም ከጉብኝቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ወደ ትምህርት ቤታቸው ርዕሰ መምህር በመሄድ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት እንደሚፈልግ ገልጾ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠየቀ። ርዕሰ መምህሩም ፈቀደለት። ይሁንና በሚቀጥለው ቀን ርዕሰ መምህሩ ልጁን ወደ ቤቱ በመላክ ወላጆቹንና ይመጣል የተባለውን እንግዳ ይዞ ወደ ትምህርት ቤት መምጣት እንዳለበት ይነግረዋል። በመሆኑም የልጁ አባትና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ተያይዘው ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ይህን ጊዜ ርዕሰ መምህሩ፣ እንግዳው በእርግጥም እንደመጣና ትምህርት ቤት ለመድረስም ቀጥ ያለውን አቀበት መውጣቱንና ከአንድ ሰዓት በላይ መጓዙን ሲመለከት በጣም ይደነግጣል። ይህ ሰው ጽሑፎችን የወሰደ ከመሆኑም በላይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተባባሪ ሆኗል።

ማላዊ:- አንድ ወንድም መስክ ላይ ሲያገለግል በብስክሌት የሚሄድ አንድ ሰው በተደጋጋሚ ያስቸግረው ነበር። ይህ ሰው ወንድምን ሲመሰክር ሲያገኘው ብስክሌቱን ያቆምና አተካራ ይፈጥራል። እንዲያውም የወንድምን መጽሐፍ ቅዱስ ለመንጠቅ የሞከረበት ጊዜም አለ። አንድ ቀን ይህ ሰው፣ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስጠናበት አካባቢ እያለፈ ሳለ ብስክሌቱን ለማስተካከል ሲሞክር እጁ በሽቦው መሃል በመግባቱ ጣቶቹ ክፉኛ ይጎዳሉ። ሰውየው በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው ከነበሩት ሰዎች መካከል ሊረዳው የሞከረው ያ ወንድም ብቻ ነበር። ወንድም ጣቶቹን አሰረለትና ወደ ሐኪም ቤት እንዲወሰድ አደረገ። ይኸው ወንድም ቆየት ብሎም ደህንነቱን ለመጠየቅ ወደ ቤቱ ሄደ። ሰውየው ቀደም ሲል ባደረጋቸው ነገሮች በማፈር እንዲህ ያደርግ የነበረው የሐሰት ወሬ በመስማቱ እንደሆነ ለወንድም ገለጸለት። ቀጥሎም “እውነተኛውን አንድ አምላክ የምታመልኩት እናንተ ናችሁ፣ ያንን ሁሉ መጥፎ ነገር አድርጌብህ እንደዚህ ያለ ደግነት ታሳየኛለህ ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅሁም” ሲል ተናገረ።

ካሜሩን:- አንዲት ወጣት እህት በጣም በተጨናነቀ የሐኪም ቤት ወረፋ መጠበቂያ ክፍል ተቀምጣ ሳለች አንድ በዕድሜ የገፉና በጠና የታመሙ ሰው ወደ ውስጥ ይገባሉ። መቀመጫው በሙሉ በሰዎች በመያዙ እኚህ ሰው መቆማቸው የግድ ነበር። እህት ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “አረጋዊው ስላሳዘኑኝ ወንበሬን ለቀቅሁላቸው። መቀመጫውን ለእርሳቸው መልቀቅ ማለት ወረፋዬንም መስጠት ማለት ስለነበር ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ማጉረምረም ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ አንዲት ሴት ወደ እኔ ቀረብ አለችና ሃይማኖቴ ምን እንደሆነ ጠየቀችኝ። እኔም የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ነገርኳት። እንዲህ ዓይነት የደግነት ድርጊት የሚፈጽሙ ወጣቶች እጅግ ጥቂት መሆናቸውን ከተናገረች በኋላ በጣም አመሰገነችኝ። እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ ለእርሷና በሥፍራው ለነበሩት ሌሎች ሰዎች መሰከርኩላቸው፤ የያዝኳቸውን ጥቂት ትራክቶችም አበረከትኩላቸው። ከዚያም ላቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ቻልኩ። ካነጋገርኳቸው ውስጥ አንዳንዶቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸውን አመለካከት የለወጡ ሲሆን ወንድሞች ቤታቸው ቢሄዱ ለመስማት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።”

ቶጎ:- ወንድሞች በገለልተኛ ክልል ውስጥ በማገልገል ላይ ሳሉ አንድ ወጣት እነርሱን በማግኘቱ እጅግ መደሰቱን ገለጸላቸው። ከዚያም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ እና “ሜክ ሹር ኦቭ ኦል ቲንግስ” የተባሉትን መጽሐፎች በእጁ የገለበጠባቸውን ሁለት ማስታወሻ ደብተሮች አሳያቸው። እነዚህን መጻሕፍት ያገኘው ቀደም ሲል ይኖርበት ከነበረ አንድ የኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ቄስ መኖሪያ ቤት አንደሆነም አጫወታቸው። ይህ ቄስ ሁለት የመጽሐፍ መደርደሪያዎች የነበሩት ሲሆን በአንደኛው ላይ የሚወዳቸውን መጻሕፍት በሌላኛው ደግሞ “ጥቅም የላቸውም” የሚላቸውን ያስቀምጣል። ወጣቱ እነዚህን መጻሕፍት ያገኘው ከሁለተኛው መደርደሪያ ላይ ነበር። ከአንዱ መጽሐፍ ላይ ጥቂት ገጾችን ካነበበ በኋላ መልዕክቱ ይማርከዋል። ሆኖም መጽሐፉን ለመውሰድም ይሁን የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ባለመቻሉ በእጁ መገልበጥ ይጀምራል። ስላነበባቸው ነገሮች ለሌሎች ሰዎች መናገር ሲጀምር እናቱና ቄሱ ተቃወሙት። ወንድሞች አንዳንድ ጽሑፎችን የሰጡት ሲሆን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግም እየረዱት ነው።

ደቡብ አፍሪካ:- ታንዲ የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር በትዳሯ ውስጥ ችግር የገጠማት ቤላ የምትባል የሥራ ባልደረባ ነበረቻት፤ አሠሪያቸው፣ ታንዲ ይህቺን ሴት እንድታነጋግራት ጠየቀቻት። ቤላ ፖሊስ የሆነው ባሏ ስለሚደበድባትና ስሜቷን የሚያቆስል ነገር ስለሚያደርግ ልትፈታው ወስና ነበር። ታንዲ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ሁለት ቅጂ ለቤላ ካበረከተችላት በኋላ አንዱን ቅጂ ለባለቤቷ እንድትሰጠው አበረታታቻት። ከሳምንት በኋላ ታንዲ ቤላን ስለ ሁኔታው ስትጠይቃት ባለቤቷ መጽሐፉን እያነበበው መሆኑንና ቤቷም ውስጥ ሰላም መስፈኑን አጫወተቻት። ከሦስት ወር በኋላ ቤላ በመጸለይዋና ለቤተሰብ ደስታ የተባለውን መጽሐፍ በማግኘቷ አምላክ ትዳሯን ከመፍረስ እንዳዳነላት ለታንዲ ገለጸችላት። የቤላ አሠሪ የሆነውን ስትሰማ 2,000 የሚያህሉት የኩባንያው ሠራተኞች በሙሉ የዚህን መጽሐፍ ቅጂ ማግኘት ቢችሉ ጥሩ አንደሆነ ገለጸች። እስከ አሁን ድረስ ታንዲ ለሥራ ባልደረቦቿ 96 መጻሕፍት አበርክታለች። መሥሪያ ቤቷም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ዓለም አቀፋዊ ሥራ ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ አድርጓል።